Monday, 17 July 2017 13:21

ኢትዮጵያና ያለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር  (IAAF) የሚያዘጋጀው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ዘንድሮ  ለ16ኛ ጊዜ  በእንግሊዟ ከተማ ለንደን ይካሄዳል፡፡ ሻምፒዮናው በዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ተሳትፎ እና የፉክክር ደረጃ ከታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ የላቀ ግምት እንደሚሰጠው ይታወቃል፡፡  ከወር በኋላ  በስትራትፎርድ ከተማ በሚገኘው እና 60ሺ ተመልካች በሚይዘው ኦሎምፒክ ስታድዬም ሻምፒዮናውን የምታስተናግደው የለንደን ከተማ አዘጋጅነቱ በአይኤኤኤፍ ምክር ቤት የተወሰነላት በ2011 እኤአ ላይ ከ6 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በመጀመርያ ለአዘጋጅነት ማመልከቻ  አስገብተው ለለንደን ተፎካካሪዎቿ የነበሩት ሌሎቹ ከተሞች የስፔኗ ባርሴሎና እና የኳታሯ ዶሃ ነበሩ። ባርሴሎና በመጀመርያ ዙር ከአዘጋጅነቱ ፉክክር ወጣችና እስከመጨረሻው ለንደንና ዶሃ ተፎካከሩ፡፡ በመጨረሻም በ15 ዓመታት ውስጥ ለአራት የተለያዩ ጊዜያት የመስተንግዶ ማመልከቻ ያስገባችው ለንደን ተመረጠች፡፡ በ2012 እኤአ ከተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ የምታስተናግደው ግዙፍ  የስፖርት መድረክ ይሆናል፡፡ በተለይ ዘንድሮ በተለያዩ የሽብር ጥቃቶች ስትታመስ የቆየችው  ለንደን ትልቁን የአትሌቲክስ መድረክ እንዴት  ታዘጋጀዋለች የሚለው ጉዳይ  ትኩረት ስቦ ቆይቷል። በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ የቀድሞ አትሌቶች የመጨረሻ ተሳትፏቸውን ማድረጋቸውም እንደልዩ ክስተት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ከእነሱም መካከል ዩሲያን ቦልት፤ ሞፋራህ፤ ዴቪድ ሩዲሻ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ ጥሩነሽ ዲባባ…. ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

አዘጋጅነቱ ወደ አፍሪካስ?
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው እ.ኤ.አ በ1983 በፊንላንዷ ከተማ  ሄልሲንኪ ነበር፡፡ ከዚያም በ1987 እኤአ ላይ ሁለተኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የጣሊያኗ ሮም እንዲሁም  በ1991  እኤአ ላይ ሶስተኛውን  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የጃፓኗ ቶኪዮ በአራት ዓመት ልዩነት  አዘጋጅተዋል፡፡ በ1993 እኤአ ላይ የጀርመኗ ስቱትጋርት ካስተናገደችው ከ4ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀምሮ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚስተናገድ ሆኗል፡፡ በ1995 እኤአ የስዊድኗ ጉተንበርግ፣ በ1997 እኤአ የግሪኳ አቴንስ፣ በ1999 እኤአ  የስፔኗ ሴቪላ፣ በ2001 እኤአ የካናዳዋ ኤድመንተን፣ በ2003 እኤአ የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ፣ በ2005 እኤአ የፊንላንዷ ሄልሂንኪ (ለሁለተኛ ጊዜ) በ2007 እኤአ የጃፓኗ ኦሳካ፣ በ2009 እኤአ የጀርመኗ በርሊን፣ በ2011 እኤአ  የደቡብ ኮሪያዋ ዴጉ፤  በ2013 እኤአ የሩሲያዋ ሞስኮና በ2015 እኤአ የቻይናዋ ቤጂንግ  ከ5ኛው እስከ 15ኛው ያለፉትን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በሁለት ዓመት ልዩነት በቅድም ተከተል አዘጋጅተዋል።
በ2017 እኤአ ላይ ለንደን 16ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ካስተናገደች በኋላ በቀጣይ ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን የሚያስተናግዱትን አገራት የአይኤኤኤፍ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ በ2019 እኤአ ላይ በካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም  የኳታሯ ከተማ ዶሃ እንዲሁም በ2021 እኤአ ደግሞ በሄይዋርድ ፊልድ ስታድየም የአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን 17ኛውና 18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል ያዘጋጃሉ፡፡ በ2023 እኤአ ላይ 19ኛውን እንዲሁም በ2025 እኤአ ላይ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እነማን እንደሚያዘጋጇቸው ግን አይታወቅም፡፡  ታላላቅ የዓለማችን አትሌቶች እንደማፍራቷ ጊዜው የአፍሪካ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ በርግጥ የአይኤኤኤፍ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው እንዳስታወቀው የአዘጋጅ አገር ምርጫ አስቀድሞ እንደነበረው ማመልከቻ አስገብቶ በመወዳደር የሚወሰን አይደለም፡፡ ማስተናገድ የሚፈልግ አዘጋጅ አገር ጋር የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ልዩ ምክርቤት በሚያደርገው ውይይት እና መግባባት አዘጋጅነቱ ይፈቀድለታል፡፡ በ2023 እኤአ ላይ የሚደረገውን 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዋና ከተማዋ ቡካሬስት ለማስተናገድ የምስራቅ አውሮፓዋ ሃንጋሪ ከፍተኛ ዘመቻ እያደረገች ነው፡፡ የሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት ወደ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መስተንግዶ ትኩረት ያደረገችው በ2024 እኤአ ላይ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የነበራት ፍላጎት ከተበላሸባት በኋላ ነው፡፡ የኦሎምፒክ መስተንግዶው ሊሳካ ያልቻለው ከ250ሺ በላይ ሃንጋሪያውያን ባሰባሰቡት የተቃውሞ ፊርማ ነበር፡፡ ሃንጋሪ በ2023 እኤአ ላይ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማስተናገድ ከቻለች ኦሎምፒክን በ2028 ወይንም በ2032 እኤአ ለማዘጋጀት አቅዳለች፡፡ የአፍሪካ አገራት  አንዳንድ ከተሞች በ2023 እኤአ ላይ ቢያንስ ሃንጋሪን በመፎካከር በ2025 ደግሞ በዋና ተፎካካሪነት እጩ ለመሆን ጥረት ካደረጉ ከሁለቱ አንዱን ሻምፒዮናዎች የማዘጋጀቱ እድል ይፈጠራል፡፡ በርግጥ ከሰሜን ሞሮኮ፤ ከደቡብ ደቡብ አፍሪካ፤ ከምእራብ ናይጄርያ ከምስራቅ ኢትዮጵያና ኬንያ በተናጠል ወይም በጋራ ለመስተንግዶው መፎካከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በ2007 እኤአ ላይ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ያስተናገደችው ኬንያ የዓለም ሀ 18 የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የማዘጋጀት እድል አግኝታለች፡፡ በሌላ በኩል የ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን የኡጋንዳዋ ካምፓላ ከተማ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡

በምንጊዜም የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ
ባለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 98 አገራት የሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን 2036 ሜዳልያዎች (670 የወርቅ ፤ 685 የብርና 681 የነሐስ) ለአሸናፊዎች ተበርክተዋል፡፡ ከ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት የምንግዜም የሜዳልያ ስብስብ ደረጃን በድምሩ 323 ሜዳልያዎች  (143 የወርቅ፤ 96 የብርና 84 የነሐስ) በመሰብሰብ አሜሪካ አንደኛነቷን አስጠብቃለች፡፡ ራሽያ 172 ሜዳልያዎች (55 የወርቅ ፤ 60 የብርና 57 የነሐስ)፤ ኬንያ 128 ሜዳልያዎች (50 የወርቅ፤ 43 የብርና 35 የነሐስ) ፤ ጀርመን 108 ሜዳልያዎች (33 የወርቅ፤ 35  የብርና 40 የነሐስ)፤ ጃማይካ 110 ሜዳልያዎች (31 የወርቅ፤ 44 የብርና 35 የነሐስ)፤ ታላቋ ብሪታኒያ 89 ሜዳልያዎች (25 የወርቅ፤ 30  የብርና 34 የነሐስ)፤ ሶቭዬት ህብረት 77 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 27 የብርና 28 የነሐስ) እንዲሁም ኢትዮጵያ 72 ሜዳልያዎች (25 የወርቅ፤ 22 የብርና 25 የነሐስ)  በማስመዝገብ እስከ 7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡

ሜዳልያዎችና የዓለም ደረጃ
ኢትዮጵያ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱት 15 የዓለም ሻምፒዮናዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪክ 72 ሜዳልያዎች (25 የወርቅ፤ 22 የብርና 25 የነሐስ) ሰብስባለች፡፡ ከ15ቱ የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ ሜዳልያ ሳታገኝ የቀረችው  2ኛው የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና በ1987 እኤአ በጣሊያን ሮም በተካሄደበት ወቅት ብቻ ነበር፡፡
በ1983 እኤአ  በ1ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ ላይ በ1 የብር ሜዳልያ - ደረጃ ከዓለም 15ኛ
በ1991 እኤአ በ3ኛው ስቱትጋርት፣ ጀርመን ላይ በ1 የብር ሜዳልያ - ደረጃ ከዓለም  21ኛ
    በ1993 እኤአ በ4ኛው ቶኪዮ ፣ ጃፓን በ1 የወርቅ፣ በ1 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም 12ኛ
በ1995 እኤአ በ5ኛው ጉተንበርግ ፣ ስዊድን ላይ በ1 የወርቅ እና በ1 የብር ሜዳልያ -ደረጃ ከዓለም 16ኛ
በ1997 እኤአ በ6ኛው አቴንስ ፣ግሪክ ላይ በ1 የወርቅ ሜዳልያ -ደረጃ ከዓለም  22ኛ
በ1999 እኤአ በ7ኛው ሲቪያ ስፔን ላይ በ2 የወርቅና 3 የነሐስ ሜዳልያ - ደረጃ ከዓለም  9ኛ
በ2001 እኤአ በ8ኛው ኤድመንትን፣ ካናዳ ላይ በ2 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም 7ኛ
በ2003 እኤአ በ9ኛው ሴንትዴኒስ ፣ፈረንሳይ ላይ በ3 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም 4ኛ
በ2005 እኤአ በ10ኛው ሄልሲንኪ ፣ ፊንላንድ ላይ በ3 የወርቅ፣ 4የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም  3ኛ
በ2007 እኤአ በ11ኛው ኦሳካ፣ ጃፓን ላይ በ3 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች -ደረጃ ከዓለም 4ኛ
በ2009 እኤአ በ12ኛው በርሊን ፣ ጀርመን ላይ በ2 የወርቅ፣ 2 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም  7ኛ
በ2011 እኤአ በ13ኛው ዴጉ ፣ ደቡብ ኮርያ ላይ በ1 የወርቅና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም 9ኛ
በ2013 እኤአ ላይ ሞስኮ፣ ራሽያ ላይ በ14ኛው  3 የወርቅ፤ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች - ደረጃ ከዓለም 6ኛ  
በ2015 እኤአ ላይ ቤጂንግ፣ ቻይና በ15ኛው 3 የወርቅ፤ 3 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች  - ደረጃ ከዓለም  5ኛ

25ቱ የወርቅ ሜዳልያዎች
ኢትዮጵያ ከ1983 እሰከ 2015 እኤአድረስ በተካሄዱት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 25 የወርቅ ሜዳልያዎች አስመዝግባለች፡፡እነዚህን  የዓለም ሻምፒዮና 25 የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት 13 የተለያዩ አትሌቶች  ሲሆኑ 13 በሴቶች እንዲሁም 12 በወንዶች የተገኙ ናቸው፡፡ 15 የወርቅ ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር (9 በወንዶች እና 6 በሴቶች)፤ 6 የወርቅ ሜዳልያዎች በ5ሺ ሜትር (5 በሴቶች  እና 1 በወንዶች)፤ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በማራቶን (1 በወንዶች እና 1 በሴቶች)፤ 1 የወርቅ ሜዳልያ በ1500 ሜትር (በሴቶች) እንዲሁም 1 የወርቅ ሜዳልያ በ800 ሜትር (በወንዶች) ናቸው፡፡ከዚህ በታች የቀረቡት በ15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ለኢትዮጵያ 25 የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰቡት የዓለም ሻምፒዮኖች ናቸው፡፡
★ ጥሩነሽ ዲባባ-  5 የወርቅ ሜዳልያዎች-በ10ሺ ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እንዲሁም በ2013 እኤአ ሞስኮ) በ5ሺ ሜትር 2 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 እኤአ ፓሪስ እና በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ)
★ ቀነኒሳ በቀለ -5 የወርቅ ሜዳልያዎች -በ10ሺ ሜትር4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 ፓሪስ፣ በ2005 ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እና በ2009 እኤአ በርሊን) በ5ሺ ሜትር 1 የወርቅ ሜዳልያ ( በ2009 እኤአ በርሊን) ሳላዲን
★ ኃይሌ ገብረስላሴ- 4 የወርቅ ሜዳልያዎች - በ10ሺ ሜትር 4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ1993 እኤአ ስቱትጋርት፤ በ1995 እኤአ ጉተንበርግ፤ በ1997እኤአ አቴንስ  እንዲሁም በ1999 እኤአ ሲቪያ)    
★ መሰረት ደፋር - 2 የወርቅ ሜዳልያዎች- በ5ሺ ሜትር (በ2007 እኤአ ሄልሲንኪ እና በ2013 እኤአ ሞስኮ)
★ ገዛሐኝ  አበራ -1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን(በ2001 እኤአ ኤደመንተን)
★ ማሬ ዲባባ -1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
★ ጌጤ ዋሚ -1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር(በ1999 እኤአ ሲቪያ)
★ ደራርቱ ቱሉ -1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር (በ2001 እኤአ ኤድመንተን)
★ ብርሃኔ አደሬ-1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2003 እኤአ ፓሪስ)
★ ኢብራሂም ጄይላን -1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2011 እኤአ ዴጉ)
★ አልማዝ አያና -1 የወርቅ ሜዳልያ - በ5ሺ ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
★ ገንዘቤ ዲባባ  - 1 የወርቅ ሜዳልያ- በ1500  ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
★ መሐመድ አማን - 1  የወርቅ ሜዳልያ- በ800 ሜትር (በ2013 እኤአ ሞስኮ)

Read 2151 times