Saturday, 22 July 2017 15:23

መረጃዎችን በቀላሉ በኢንተርኔት ለማስተላለፍ የሚያስችል አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ሥራ ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

  ደንበኞች የፅሁፍ፣ የድምፅና የምስል ፋይሎቻቸውን በቀላሉ፣ በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ በኢንተርኔት ለማስተላለፍ የሚችሉበትን አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ሥራ ጀመረ፡፡
“ዌብ ስፕሪክስ” የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ለሚሰጠው ለዚህ አገልግሎት አነስተኛ ክፍያ እንደሚያስከፍልም ተገልጿል፡፡ ቀደም ሲል የድረ ገፅ ተጠቃሚ ደንበኞች የHosting አገልግሎትን የሚያገኙት ባህር ማዶ ካሉ ተቋማት ሲሆን ክፍያ የሚፈፅሙትም በውጭ ምንዛሬ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ኩባንያው ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫና የጉብኝት ፕሮግራም ላይ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ብርሃኑ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ይሰጡ ከነበሩት አገልግሎቶች የተለዩና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡
በኩባንያው ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ኮንፈረንስ ኮሊንግ፣ ሚስድኮል ማርኬቲንግ፣ የድምፅ፣ የፅሁፍና የምስል መልዕክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማስተላለፍ ሥራና ድረ-ገፆችን በፍጥነት ለመክፈት የሚያስችል ሥራ እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡
አሁን የተጀመረው አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የሌሉ መሆናቸውንና ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ወደፊትም በአገሪቱ በሌሉ አዳዲስና ያልተለመዱ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡

Read 5471 times