Saturday, 22 July 2017 15:24

በኢትዮጵያ በቀን 10 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ አሁንም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን በአማካይ በቀን 10 ሰዎች በአደጋው ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተጠቆመ፡፡
“ጠጥቼ አላሽከረክርም” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ረቡዕ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ የታቀደውን የሙዚቃ ኮንሰርት አስመልክቶ በሸራተን አዲስ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ አብዛኛው የትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለው በምሽትና ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ሹፌሮች ነው፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ተሰማ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ እየደረሰ ላለው የትራፊክ አደጋ ዋንኛው መንስኤ አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ በከተማዋ ያለምንም ብቃትና የመንጃ ፍቃድ የሚያሽከረክሩ ሰዎች መበራከታቸውን ጠቁመው በያዝነው ዓመት ብቻ ከ1400 በላይ አሽከርካሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ፎርጅድ የመንጃ ፍቃድ ከተማዋን አጥለቅልቆታል ያሉት ኮማንደሩ፤ በዚህ ዓመት ከ200 የሚበልጡ ፎርጅድ መንጃ ፈቃዶች መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡
መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ያለ ብቃት ነው ያሉት ኮማንደሩ፤ “የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማትም የሚያሰለጥኑት ባረጁና በተበላሹ መኪኖች ሲሆን አሽከርካሪው ትምህርቱን ጨርሶ ሲወጣ ፈፅሞ ልምምድ አድርጎባቸው በማያውቃቸው ዘመናዊና አዳዲስ መኪኖችን ያሽከረክራል ይህ ደግሞ ለከፋ አደጋ ያጋልጠዋል” ብለዋል፡፡
ብቃት የሌላቸውና ከመንገድ መውጣት የሚገባቸው ተሽከርካሪዎች ከተማዋን ወረዋታል ያሉት ኮማንደር ግርማ፤ መኪኖቹ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በህዝብ ማመላለሻነት ነው፤ ይህም  የሚደርሰውን አደጋ የከፋ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አምና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 464 ሰዎች በመኪና አደጋ መሞታቸውንም ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡
“አብ ሐበን” የማስታወቂያ ድርጅትና “የዘሩት ፕሮሞሽን” በትብብር ያዘጋጁትና የፊታችን ረቡዕ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደውን የሙዚቃ ኮንሰርት አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስና የእስልምና ሃይማኖት ተወካይን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችና  የሹፌሮች ማህበር ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤን ለማስጨበጥ ያግዛል በሚል ዓላማ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚቀርበው “ጠጥቼ አላሽከረክርም” የሙዚቃ ኮንሰርት ያለክፍያ የሚገባበት ሲሆን ከአልኮል መጠጥ ነፃ የሆነ የሙዚቃ ፌስቲቫል እንደሆነም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይ የትራፊክ አደጋን አስከፊነት የሚያመለክት የአምስት ደቂቃ ዶክመንታሪ ፊልም እንደሚቀርብና የፕሮግራሙ ታዳሚዎችም “በእኔ ምክንያት አደጋ አይደርስም” በሚል ቃል የሚገቡበት የፊርማ ሥነ ስርዓት መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በተያያዘ ዜና በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ላይ የሚመክርና ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዙ ጭብጦች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የጥናት ወረቀቶች የሚቀርቡበት አገራዊ ኮንፍረስ አዲስ አበባ ውስጥ ሊካሄድ ነው፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሉሲ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ጋር በመተባበር ከነሐሴ 18 እስከ 19 በኢሲኤ በሚካሄደው አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ የትራፊክ አደጋን መቀነስ ያልተቻለበት ዋንኛ ምክንያት ምንድን ነው? የመስኩን ጠበብቶች የሚፈለገውን ያህል እየተጠቀምንባቸው ነው ወይ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግበትና ለፖሊሲ አውጪ አካላት ሊቀርብ የሚችል ሀሳብ የሚገኝበት እንደሚሆን አዘጋጆቹ ትናንት በሐርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ ኮንፍረንሱ በየዓመቱ የሚቀጥል እንደሆነና ከ5 ዓመት በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ኮንፍረንስ ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡


Read 6350 times