Saturday, 22 July 2017 15:26

የኦሮሚያ ከተሞች በንግድ አድማ ላይ ሰነበቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(32 votes)

‹‹በቀን ገቢ ገመታ ላይ የታየው ጉድለት መስተካከል አለበት›› - የክልሉ ፕሬዚዳንት

የቀን ገቢ ግመታን በመቃወም በአምቦና ወሊሶ ሰሞኑን የተጀመረው የንግድ ቤቶችን የመዝጋት አድማ ወደ በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የተዛመተ ሲሆን  በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡
መንግስት፤ “ችግሩን በመመካከር እፈታለሁ›› ብሏል - ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑን በመግለፅ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ በትላንትናው ዕለት ነዋሪዎችን በቀን ገቢ ግመታ ዙሪያ በወሊሶ ከተማ ማወያየታቸው ታውቋል፡፡
በወሊሶ በተደረገው የትናንትናው ስብሰባ ላይ የከተማው ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት፤ ‹‹የቀን ገቢ ገማቾች ግምቱን ሲሰሩ ያልተገባ ስህተት ሰርተዋል፣ የተጣለብን ግምት ከአቅማችን በላይ ነው፤ ግመታው ሆን ተብሎ መንግስትና ህዝብን ለማጋጨት ታስቦ የተሰራ ነው የሚመስለው›› ማለታቸውን የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
‹‹ወሊሶና የምዕራብ ሸዋ ከተሞች በልማት ወደ ኋላ ቀርተዋል፣ ሆስፒታል የለንም፣ ኢንዱስትሪ የለንም፣ ለወሊሶ ከተማ የሚመደበው በጀት በቂ አይደለም›› የሚሉ ቅሬታዎችንም መቅረባቸው ታውቋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ ራሱን ችሎ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማደግ አለበት፣ በጅምር የቀሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሊታሰብባቸው ይገባል እንዲሁም የከተማዋ ከንቲባ ተገቢውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም››  ጥያቄዎቹን ያዳመጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ በሰጡት ምላሽ  በቀን ገቢ ግመታ ላይ የታየው ጉድለት መስተካከል አለበት፤ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የእናንተ ነጋዴዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ የቀረቡትን ቅሬታዎች ተረጋግተን ማየት አለብን›› ብለዋል፡፡
 ለህዝቡ ቅሬታ በቂ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለዚህም የግብር መክፈያ ጊዜው እስከ ነሐሴ 15 እንዲራዘም መወሰኑን የኮሙኒኬሽን ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 10፣ የቀን ገቢ ገመታን በተመለከተ በአምቦ በተደረገው፤ ተቃውሞ ዋና መንገዶች ተዘግተው የነበረ ሲሆን ሁለት ተሽከርካሪዎችም መቃጠላቸውን የሚገልፁት ምንጮቻችን፤ ከሰኞ አስቀድሞ የግብር ግመታውን በመቃወም ለ3 ተከታታይ ቀናት የንግድ ማቆም አድማ እንደሚደረግ የሚያሳስብ በራሪ ወረቀት ተሰራጭቶ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በተከታታይ ቀናት አድማው ወደ ጊንጪና ወሊሶ የተዛመተ ሲሆን በእነዚህ ከተሞች እስከ ረቡዕ ድረስ ምንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳልነበርና የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጦ መሰንበቱ ታውቋል፡፡ ባንኮችና የመንግስት ተቋማት ግን መደበኛ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር ተብሏል፡፡
ረቡዕ በወሊሶና አምቦ የመንግስት አካላት ከነጋዴዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ሐሙስ በወሊሶ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ቢጀመርም በአምቦ ከተማ፣ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የኦሮሚያ ቢሮዎች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች በአምቦ መነሐሪያ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ታውቋል፡፡
የቀን ገቢ ገመታን በመቃወም ንግድቤቶች የመዝጋት አድማ ሲደረግ ከሰነበተባቸው የኦሮሚያ ከተሞች መካከል- ነቀምት መንዲ፣ ሜታ ሮቢ፣ ሆለታ፣ ወለንኮሚ፣ ጊንጪ፣ ነጆ፣ ቡራዩ፣ ላንጌና ደምቢዶሎ ይገኙበታል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የኮልፌ እፎይታ የገበያ ማዕከል ነጋዴዎችም ረቡዕ እለት ቅሬታቸውን በጋራ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ለአሜሪካን ድምፅ የገለፁ ሲሆን ሐሙስ እለት የንግድ ቤቶቻቸውን በመዝጋት አድማ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የንግድ ቤቶችን የመዝጋት አድማ በተደረገባቸው ከተሞች ከወትሮው በተለየ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥር በርክተው መታየታቸውንና ጠንካራ ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ የከፋ ግጭት አለመፈጠሩን ተናግረዋል፡፡


Read 8231 times