Saturday, 22 July 2017 15:30

የአፍታ ቆይታ - ከመድረክ አዲሱ ሊቀመንበር ጋር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ከተመሠረተ 10 አመት ሊሞላው ጥቂት የቀረው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ባለፈው ቅዳሜ፣ሐምሌ 8 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ አመራርነት እምብዛም ስማቸው የማይታወቀው የህክምና ስፔሻሊስቱን ዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶን በሊቀመንበርነት መርጧል፡፡ ሆኖም ግን ዶ/ር ሚሊዮን የመድረክ አንዱ አባል የሆነው የሲዳማ አንድነት ንቅናቄን (ሲአን) በሊቀመንበርነት ሲመሩ
የቆዩ ሲሆን የፖለቲካ ተሣትፎአቸውም ከተማሪነታቸው ዘመን እንደሚጀምር ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ ዶ/ር ሚሊዮን ማን ናቸው?
በአዲሱ አመራራቸው መድረክን የት ሊያደርሱት አቅደዋል?
ስለ ሃገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ያስባሉ? ስለ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎችስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡


መድረክ ከተመሰረተበት ጊዜ አንፃር “የተጠበቀውን ያህል ወደፊት አልተራመደም” ለሚሉ ተቺዎች ምላሽዎ ምንድን ነው?
መድረክ ብቻ ሳይሆን የትኞቹም  የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በዚህች ሃገር ላይ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን ትግል ከጀመሩ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዘመናዊ መልኩ ተደራጅቶ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለህግ የበላይነት ታግሎ ውጤት ለማምጣት ሁለት መቶ አመት ያስፈልጋል ይባላል። ብዙዎቹ ኃያል ሃገራት የዚህ ታሪክ አላቸው። ዛሬ ላይ እኩልነት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሠላም፣ ዲሞክራሲ በማስፈን ህዝባቸው የተሻለ ኑሮ እንዲመራ ያደረገ ስርአት የፈጠሩት በዚህ ሂደት ነው፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች ደግሞ ሠላም፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ የሚባሉትን በስም እንጂ  ህዝቡ አሁንም ድረስ የእነዚህን መሰረታዊ መብቶች እውን መሆን ናፋቂ ነው፡፡ የእኛም ሃገር እንዲሁ ነው፡፡ በኛ ሃገርም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ያለፈበት፣ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚል ግብግብ ተደርጓል፡፡ ግን አልሆነም፡፡ መድረክም እንግዲህ እንደ አንድ ድርጅት ትግል እያደረገ ነው፡፡ ትግል ብዙ ወጣ ውረድ ያለበት፣ እየወደቁ እየተነሱ የሚጓዙበት መንገድ ስለሆነ መድረክም እያለፈ ያለው በዚሁ መስመር ነው፡፡ በየጊዜው ድክመታችንን እያረምን ወደፊት እየተጓዝን ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ባስቀመጣቸው አግባቦች፣ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን መድረክ እየሠራ ነው፡፡ መድረክ የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላመጣም ለተባለውም ቢሆን፣ ዲሞክራሲ በአፍ እንጂ በተግባር በማይታይበት ሁኔታ ተግባራዊነቱን ለመፈተሽ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ ለወደፊትም ህዝቡን ቀጥተኛ ተሣታፊ የሚያደርግ ስራ መስራት እንደሚጠበቅብን ተገንዝበናል፡፡
በሌላ በኩል መድረክ  ውስጥ የተሰባሰቡ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ብሄር ተኮር ናቸው፤ ስብሰቡም አንድ ገዢ ርዕዮት አለም የለውም፤ የሚል ትችት ይሰነዘራል -----
አንዳንድ ወገኖች ባለማወቅ ወይም ሌላ ፍላጎት ኖሯቸው ካልሆነ በስተቀር በመድረክ አመለካከት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድ ላይ ሆነው የጋራ ችግሮቻቸውን መፍታት አለባቸው በሚል በጋራ የሚሰባሰቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህ ነው መልከ ብዙ ፓርቲዎች በስብስቡ የሚስተዋሉት፡፡ ለምሣሌ የመድረክ ትላልቆቹ የፖለቲካ ድርጅቶች አራት ናቸው። ግን ከነዚህ በተጨማሪ ግለሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በስብስቡ አሉ፡፡ እነዚህ አካላት በሙሉ በአንድ ወሣኝ ጉዳይ ላይ አይደራደሩም፤ እሱም ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ አይደራደሩም፡፡ የተሸራረፉ መብቶች በህግ የበላይነት በሂደት ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ የመድረክ ፍልስፍና የህግ የበላይነት ካለ አምባገነንነት አይኖርም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም መልኩ ቢለያይም በመድረክ ስር ተሠባስቦ ለህግ የበላይነትና ለዲሞክራሲ ይታገላል፡፡ የምናቀነቅነው ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰዎች በሃይማኖትና በጎሣ መከፋፈል የለባቸውም፡፡ የሰው ልጅ ማህበራዊ ፍጡር ነው፡፡
መድረክ የሚመራበት ርዕዮት አለም ምንድን ነው? የፓርቲዎቹ ርዕዮተ ዓለም የተለያየ ከሆነ እንዴት ጠንካራ ሊሆን ይችላል? ለምሳሌ ኢህአዴግ አራት ድርጅቶች ቢኖሩትም አብዮታዊ ዲሞክራሲን ያቀነቅናል--
እኛ ሊበራል ዲሞክራሲን በሀገሪቱ እውን ለማድረግ ነው የምንታገለው፡፡ መሬትም ሆነ ሌሎች ንብረቶች በግል መያዝ አለባቸው የሚለው መሰረታዊ አቅጣጫችን ነው፡፡ አስተሳሰባችን የሊበራል ዲሞክራሲ ነው፡፡
የመድረክ ስብስብን የበለጠ ለማጠናከር ምን እቅድ አላችሁ?
እኛ ከፓርቲዎች በመለስ የጥልቅ ሃሳብ ባለቤት የሆኑ ግለሰቦችንም ወደ ስብስባችን እናመጣለን፤ ከእነሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረግ በሀገራችን የወደፊት አቅጣጫ ላይ በቀጥታ የመወያየት፣ የመደማመጥ እቅድ አለን፡፡ በዋናነት ትኩረት የምናደርገው፣ የሀገሪቱ ችግሮች ላይ በመወያየት የመፍትሄ ሀሳቦች ማመንጨት ላይ ይሆናል። ምርጫውም ቢሆን ከቃል በላይ መሬት ላይ የወረደ እንዲሆን ከባለቤቱ ከህዝብ ጋር የመነጋገር እቅድ አለን፡፡ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች በመጠቀም ጭምር ስርአቶችን ማበጀት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን፡፡ በሀገሪቱ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን ማድረግ የሚያስችል ስራም ወሳኝ ነው። ያንን ለማድረግ ደግሞ ከምንም በላይ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ አብሮ መስራት የግድ ነው። መቻቻልን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን እውን ለማድረግ መድረክ ሁሉንም ወገኖች ባሳተፈ መልኩ ሰፋፊ እቅዶችን ይዞ ይሰራል፡፡
አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ የዲሞክራሲ ችግር እንዳለባቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ራሳቸውን አጋልጠው አሳይተዋል። ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ ክስና ፍረጃ፣ባስ ሲልም ወደ ዱላ ነው የሚገባው፡፡ የፓርቲ አመራር (ሥልጣን) በሃይል መንጠቅ ሁሉ እየታየ ነው፡፡ መድረክስ ከዚህ የጸዳ ሊሆን ይችላል?
እኛ ህዝቦችን አስተምረን፣ መንገድ አሳይተን፣ አዲስ ስርአት እንዲፈጠር ነው ጥረት የምናደርገው እንጂ እኛ መሪዎች አንሆንም፡፡ መሪውን የሚመርጠው ኋላ ላይ ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ ስለዚህ የስልጣን ሽኩቻ አይኖረንም፡፡ ሁሉም አካላት ወደ ስብስቡ መጥተው እንዲታገሉ ነው ፍላጎታችን። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡፡ ስልጣን በአጋጣሚ የያዘው መንግስት፣ዛሬ  የሚያስተዳድረው ሀብት የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የሚያስፈልገን ሁሉም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ከዚህ ሀብት የሚጠቀምበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። መድረክ ከማንም ኢትዮጵያዊ ቡድንና ወገን ጋር ጠላትነት የለውም፡፡
በቀጣይ ምርጫ ለመሳተፍ አቅዳችኋል? ምን  ውጤት ለማምጣት ነው ዝግጅት የምታደርጉት?
መቼም መቶ በመቶ አንድ አካል ምርጫን ያሸነፈበት የዓለም ታሪክ አለ ከተባለ፣በኛ ሀገር የተፈጠረው ብቻ ነው፡፡ የመጣንበት ሂደት ያደረሰንም ለዚህ ውጤት ነው፡፡ አሁንም በምርጫ ላይ የመድረክን ተሳትፎ የሚወስነው የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ነው፡፡ ቀሪውን ደግሞ ምርጫ ሲቃረብ ድርጅቱ የሚወስንበት ይሆናል፡፡ ምህዳሩ ካልሰፋ ዝም ብሎ አጨብጫቢ መሆን ነው። ያ ደግሞ ለሀገሪቱም ለህዝቡም አይጠቅምም። እንደ‘ኔ ከሆነ ሁሉም ቢማማር መልካም ነው፡፡ አንዱ የፖለቲካ ቡድን ከአንደኛው ቡድን በጎውን መማር አለበት፡፡ መከራከር፣ መደማመጥ፣ መወያየት ከማንም በላይ ለህዝባችን ይጠቅማል፡፡ ከምርጫ በፊት እነዚህ ሲደረጉ ነው፣ ፍትህና ርትዕ ያለበት ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው፡፡
ሀገራችን በድህነት ነው የምትታወቀው፡፡ ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት የፖለቲካ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአንድነት ማበር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢም ነው፡፡ መድረክ ይህን ዓይነት አቋም ካላቸው  ወገኖች  ጋር ለመስራትም ዝግጁ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ ስለመጣው የዘር ፖለቲካ ምን ይላሉ? መፍትሄውስ ምን ይመስልዎታል?
አሁን ላይ በጎሳና በሃይማኖት ብዙ ልዩነቶች ይራገባሉ፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ መድረክም በዋናነት ይሄን መሰረት አድርጎ ይሰራል፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማምጣቱ ሀገሪቱን በእድገት ወደፊት ለማስቀጠል ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጅ ሆኖ፣ አብሮ ተሳስቦ የኖረ ነው፡፡  ቋንቋውን፣ ባህሉን ለማሳደግ አብሮ ሲተጋ የኖረ  ህዝብ ነው፡፡ በሃይማኖትና በጎሳ ልዩነትን ሊያራግቡ የሚሞክሩ ግለሰቦች፣ የህዝቦችን አንድነት ስለሚያፋልሱ በጊዜ መታረም አለበት። ህዝብ አብሮ ኖሯል፤ ለወደፊትም ይኖራል፡፡ ግለሰቦች ግን ይሄን ሊያደፈርሱ ነው የሚጥሩት፡፡ ህዝብ ከህዝብ ጋር ምንም መሰረታዊ ቅራኔ የለውም፡፡ ችግሩ ያለው ከአፋኝና  ጨቋኝ ገዥዎች ነው፡፡ ገዥዎች፤ በህዝብ ላይ እንጂ ህዝብ በህዝብ ላይ ጦር የሰበቁበት ታሪክ የለንም፡፡
ለረጅም ጊዜያት በመድረክ አመራርነት የሚታወቁት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው፤ እርስዎ  በፖለቲካ ያለዎት ተሳትፎ እንዴት ነው?
በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የጀመርኩት በልጅነቴ ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ በ1966 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በወቅቱ ፖለቲካ ተሳትፌያለሁ። ተወልጄ ያደግሁት ቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር የሚባለው ይርጋለም ከተማ ነው፡፡ በበርካታ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ንቅናቄዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ በንጉሱ እና በደርግ ዘመንም እንዲሁ ለፍትህና ዲሞክራሲ የሚደረጉ ትግሎችን እደግፍና እሳተፍባቸውም ነበር፡፡ እኔ አሁንም የዲሞክራሲ ናፋቂ ነኝ፡፡ የሰዎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይረጋገጡ፤ እውን ይሁኑ የሚለው የአቋሜ መሰረት ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ አምጪ ነው፡፡ የህዝብን ለውጥ ሁሉ እደግፋለሁ፡፡ በመደበኛ ሙያዬ ደግሞ ሃኪም ነኝ፡፡ የኢፒዲሞሎጂ ስፔሻሊስት ሃኪም ነኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት የጤና ምርምሮችን በማድረግ በሰፊው እየሰራሁ ነው፡፡  



Read 1483 times