Saturday, 22 July 2017 15:28

የሀገራችን ትምህርት አብዮት ያስፈልገዋል!

Written by  ሳሙኤል ታደሰ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈዉ - በ2003 ዓ.ም አንድ በዩኤስኤድ በኩል በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ፣ በትምህርት ሚኒሰቴርና በ RTI –International ቅንጅት በ2ኛና 3ኛ ክፍሎች የንባብ ክህሎት ላይ የተጠና ሀገራዊ ጥናት ነበር፡፡ ይህ የዳሰሳ ጥናት (EGRA – Early Grade Reading Assessment) እንዳመለከተዉ፤ የኢትዮጵያ የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ ችሎታቸዉ በአስደንጋጭ ሁኔታ ዘቅጧል፤ ምንም እማያነቡ ልጆች በርካታዎቹ መሆናቸዉን አስታወቀ፤ ወይም አጋለጠ ቢባልም ይቻላል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ዉጤት ላይ ደነገጥን፤ አሳሰበን ምናምን እየተባ ለተጻፈ ዉይይት ተደረገ፤ በጣም ተፎከረ፡፡ ይሄን አስደንጋጭ ዉድቀት ለዉጦ የልጆቻችንን የንባብ ክህሎት ለማምጠቅ ትልቅ ፕሮጀክትም እየተተገበረ እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡ ያም አለፈ!
በቅርቡ ደግሞ የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከእንግሊዙ ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያደረገው ጥናት፤ “የተማሪዎች የዕውቀት ደረጃ በአለማቀፍ ደረጃ ከሰፈረው አማካይ ቫልዩ አንፃር 150 ዓመታት ወደ ኋላ መቅረቱን፤ ከኮሌጅ ተመርቀው 7ኛና 8ኛ ክፍሎችን ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑ መምህራን መካከል የ8ኛ ክፍል ፈተናንን በብቃት ማለፍ አለመቻላቸዉንና በኢትዮጵያ የሚገኙ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካና ሲንጋፖር በመሳሰሉ የአደጉ አገራት ከሚገኙት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል መሆኑን ”በግልጽ ቋንቋ ልክ ልካችንን ነግረዉናል፤ ለኛም የትምህርት ባለሙያዎች ለምንባለዉ ማለቴ ነዉ፡፡ ይሄና መሰል የጥናቱን ዉጤቶች በመመርኮዝ ተፃፈባቸዉ፤ ሰዎች ተነጋገሩባቸዉ፤ እኛም እያፈርን የእዉነታ ጉሸማዉን ተቀብለን ምንም እንዳልተፈጠረ ለሽ ማለታችንን እንቀጥላለን፡፡ ይሄም ያልፋል፡፡ ምናልባት ይህ ጥናትም እንደተለመደዉ፤ እንደ ትልቅ ፕሮጀክት ይወሰድ ይሆናል፡፡ ግን ትዉልድ አያድንም!
ትምህርት ሚኒስቴርም በተለይ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ከትምህርት አቅርቦት ወደ ትምህርት ጥራት በሚል መሪ ቃል- “እኔ እንኳን የትምህርት ጥራትና አቅርቦት ተራ በተራ የሚሰሩ ነገሮች ናቸዉ ብዬ አላምንም” - የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅን (GEQIP–General Education Quality Improvement Package) በመቅረጽ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በኣመታዊ የትምህርት ጉባኤዎች ብዙ ብዙ ነገሮች ይወራሉ ፤ የሚያማልሉ መግለጫዎች ይወጣሉ፡፡ የትምህርት ጥናቶች ይቀርባሉ፤ በየሩብ አመቱ በየዘርፉ የሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎች ታላላቅ ስብሰባ ያደርጋሉ። እሰየዉ! ግን ይህም ወደ ኋላ ከመሄዳችን አላዳነንም። ለምን ከእንደነዚህ አይነት ወሽመጥ ቆራጭ የጥናት ዉጤቶች መለየት አቃተን!? እየሰራን ነዉ እያልን! በርካታ ገንዘብ በየአመቱ “እያፈሰስን” ከአስር አመታት በኋላ ሌላ አሳፋሪ የጥናት ዉጤት መሰማት ነበረብን! በእነዚህ አመታት ከአንዱ ክቡር ሚኒስቴር ወደ ሌላዉ ክቡር ሚኒስትር በፍጥነት የተቀያየርንበት ዘመን ነዉ፤ ምናልባት አንዱ ሚኒስቴር ይገለጽለት ይሆናል ተብሎ ይሆን!!! ቁልፉ ገና የተገኘ አይመስልም “The Beautiful Ones are Not Yet Born’’ እንዳለ የጋናው ደራሲ Ayikwei Armah ሆኖ ይሆን!
እባካችሁ ቁልፉን ፍለጋ ላይ እናተኮር- ፖሊሲዉንም ቢሆን፤ የትግብራ ስርአቱንም ቢሆን፤ የመምህራን ምልምላ እና ስልጠናችንን ስርአታችንንም ቢሆን፤ የተጠያቂነት ደረጃዉንም ቢሆን፤ ሌላ ሌላዉንም ቢሆን በጋራ፤ በቅንነት፤ በድፍረትም ጭምር ፈታትሸን ቁልፉን አግኝተን፣ በየወቅቱ ብቅ እያለ አክርሮ እየጎሸመ ከሚሳለቅ የጥናት ዉጤት እንዉጣ፡፡ ክቡር ሚነሰትሮችን መቀያየሩ ቁልፉን አላስገኘምና፡፡
የትምህርት ጥራቱን መወዳደቅ የሚያሳዩ ምልክቶች ከገጠመኝነት አልፈዉ የዕለት ከዕለት ህይወታችን ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡  ወዳጆቼ ! ይሄን ነገር እነዳነሳዉ ያነሳሳኝ፤ ያለ መሻሻላችንን የሚያሳይ አሳዛኝ ትንሽ አጋጣሚ አጋጥሞኝ ነዉ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባችን፡፡ የአንዷ እህቴ ልጅ የመዋለ ህጻናቱን ጊዜ አጠናቆ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መሸጋገሩን አስመልክቶ ቡና እንድጠጣ ተጋብዣለሁ፡፡ አሁን አስኮ አካባቢ ነኝ - እህቴ ቤት፡፡ በደስታ መዓበል ዉስጥ ያለዉን የእህቴን ልጅ ስሜ፤ የማበረታቻ ስጦታዬን ከማበረታቻ ቃላቶቼ ጋር አዠጎድጉጄ ደስታዉን ጨምሬለት ቁጭ ከማለቴ የምረቃ መፅሄቱን እንዳየዉ ወርዉሮልኝ ወደ ጨዋታዉ ሮጠ፡፡ መፅሄቱን እያገላበጥኩ  ነዉ፤ ገረመኝ! አንድም ለመሃላዉ አማርኛ ወይም ሌላ የሀገር ዉስጥ ቋንቋ አልተካተተበትም፡፡ በሙሉ ከጫፍ እጫፍ እንግሊዘኛ ብቻ ነዉ፡፡ የህጻናቱ ስም እንኳ ሳይቀር። መገረሜን ያየች ከትንሽዋ ተጋባዧ እህቴ ጋር በመገረም፤ በማዘን ተወያየንብት፡፡ በመሃል ጋባዧ እህቴ ሌላ ነገር ጨመረችልን፡፡
ይሄዉ ት/ቤት የደስታ መገለጫ ካርድ ለእያንዳንዱ ተማሪዎቹ ሰጥቷል፤ መልካም ነገር ነዉ፡፡ ጋባዧ እህቴ እዚህ ካርድ ላይ የተፃፈዉን ለማስታወስ እንዲህ ሞከረች “እንኳን አደረሰክ”! ሳቅ … ኧረ ሌላም አለ ብላ እንዲህ ሙሉን አነበበችልኝ፤ እኔም አነበብኩት “እንኳን አደረሰክ፤ ዉጤታማና ስኬታማ የትምህርትና የዕዉቀት አመታት እንዲሆንልክ እንመኛልካለን” ይላል፡፡ ሌላ ሳቅ! ..እኔም አብሬ የማፈር ሳቄን ሳቅሁ፡፡  ጉድ! በል ያሰኛል፡፡ አልኩ በልቤ፤  ግን ዝም ማለት አቃተኝ፡፡
የትምህርት ጥራቱን መንቀዝ የሚያመላክቱ ነገሮች በገጠርም፤ በከተማም፤ ትናንትም፤ ዛሬም፤ በመንግስትም፤ በግልም፤ በርክተዋል። እንዲህ እንዲህ እያሉ እያሽመደመዱን ነዉ። እቤታችን ሰፈራችን፤ በየቀያችን፤ ጥናቶቹ እንደ ሚያመላከቱትም መሽመድምዱ በሀገርም ቀጥሏል፡፡ እኛ የትምህርት ባለሙያዎችም ነን የምንለዉ አላየንም፤ አልሰማንም፤ አንናገርም ብልን ይመስላልሻል ብለናል፡፡ ህሌናችን ሊወቅሰን ካልቻለ፡ ችግሩ ፈንድቶ እያንዳንዳችንን የሚጠይቅበት ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ሁላችንም ትምህርት የልማት መሰረት መሆኑን ስንት ጊዜ ደስኩረናል /ፅፈናል፤ ቁልፍ መሆኑን ተንትነን በየፅሁፎቻችን መግቢያ ላይ የሰነዶቻችን ማጣፈጫ አድረገናል፡፡ ግን ትምህርቱ እንዲህ እንዲህ ሲሆን የታለን!?
የሀገራችን ትምህርት አብዮት ያስፈልገዋል እላላሁ፤ ቁልፉን ለማፈላለግ፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቀራርቦ፡ ተደራጅቶ መነጋገር መፍትሄ መፈለግ፤ ትምህርት ሚኒስቴርንም ማገዝ... ቁልፉ ወደ ሚገኝበት አቅጣጫ መጓዝ ያስፈልጋል፤ ከመሽመድመድ የሚያወጣንን ቁልፍን ማግኝት ይገባናል፡፡
ሀገር ዓቀፍ የትምህርት ባለሙያዎች ማህበር ይህን አብዮት ለማቀጣጠል አስፈላጊ ነዉ፤ መቋቋም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ማህበር እዚህ አለን የሚልም ካለ ይህንን ኃላፊነት በሚወጣዉ ደረጃ መጠናከር ይገባዋል እላለሁ። እናናተስ! ምን ትላላችሁ? ሁላችንም ሄደን ሄደን ክክ ካለዉ ት/ቤት ጋር እንዳንቀላቀል እፈራለሁ። ወዳጆቼ፤ አንተ ምንአለብክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እያልኩ ያለሁት ስለትዉልድ መሽመድመድ ነዉ፤ ስለ ሀገር መዉደቅ፡፡ ከአንጀት እናስብበት!!!
ሰላም ሁኑ!
Read 932 times