Saturday, 22 July 2017 15:31

የ‘ምቀኛነት’ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

  “--የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ከሚነግሩን ይልቅ የቬንገር መነሳት አርሴናል ላይ ስለሚያመጣው ተጽእኖ አንድ ጥራዝ ሙሉ የሚነግሩን ተንታኞች በዙብና! (ለነገሩ አንዳንዴ በየቡድኑ ካሉ ኳስ አመራሮች ውስጥ በፍጹም ቅጣት ምትና በእጅ ውርወራመካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት የማይችሉ አሉ ብንባል አይገርመንም፡፡--”
                 
       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዚህ ሰሞን የሆነ ነው፡፡ ሰውየው ለሆነ ዝግጅት ትንሽዬ ያሪስ መኪና ይከራይና ቤቱ መግቢያ አካባቢ ያቆማታል፡፡
ቤቱ ደግሞ ከድሮው ሰፈሮች በአንዱ ነው፡፡ ምሳውን ጨርሶ ተመልሶ ሲወጣ የመኪናው አንድ ወገን በሆነ ነገር ተደጋግሞ ተፍቆ የመኪናው መልክ ብልሽት ብሏል፡፡ ለጊዜው በጣም ይበሽቃል አሉ፡፡ ሆኖም ትንሽ ቆይቶ ግን፣
“በገዛ እጄ ነው፣ እዚህ አምጥቼ ማቆም አልነበረብኝም፣” እያለ ራሱን ሲወቅስ ነበር አሉ ጓደኞቹ። ምክንያቱም አብዛኛው የዛ አካባቢ ሰው፣ እርስ በእርሱ በምቀኝነት የሚካሰስ አይነት ነበርና፡፡ እንደውም ሙሉ ልብስ ሲገዛ እንኳን ‘ኮቱን ለብቻው ከአሮጌ ሱሪ ጋር፣ ሱሪውን ለብቻው ከአሮጌው ኮት ጋር ማድረግ ነው’ እያሉ የሚቀላለዱት ነገር አላቸው።
ይቺን የምቀኝነት ነገር ደጋግመን አውርተንባታል። እንደምናያቸውና እንደምንሰማቸው ነገሮች ማውራታችን መቼም የሚቆም አይመስልም፡፡ ጥናት ምናምን ነገር ባይኖርም፣ ነገርዬው እየበሳበት ሰዉ እርስ በእርስ በሙሉ ዓይን እንዳይተያይ እያደረገው ይመስላል፡፡
ስሙኝማ… ስለ እኛ ምቀኝነት የሚወራውን …አንዳንዴ ‘ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሚያስወሩብን’ ምናምን ብለን እንዳናልፍ የሚያደርጉን ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይሄ ሁላችንንም አንድ ላይ መጨፍለቁ ቀሺም፣ ምናልባትም አስተያየቱ ራሱም ‘ምቀኝነት’ ሊመስል ቢችልም ነገሩ ግን በእርግጥም የሚያሳስብ ነው፡፡ ከትልቁ ነጭ ወረቀት ይልቅ ጎልታ የምትታየው መሀል ላይ ያለችው ትንሽዬ ጥቁር ነጥብ ነችና፡፡
ነገሮችን በአዎንታዊ የማየት ልምድ እየራቀን ነው። በር መቆለፍ ያበዛነው እኮ… አለ አይደል… የሳሎኑን ምንጣፍ፣ ሠላሳ ምናምን ኢንቹን ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን አይተው ‘እንዳይመቀኙን’ ነው። እንግዳ እንኳን ሲያንኳኳ በሯ ለአመል ነው የምትከፈተው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ከዚህ በፊት እንዳልነው የሰዎችን ስኬት የማጣጣል ነገር አለ፡፡ የመከራ ህይወት አሳልፎ ደህና ደረጃ ላይ ሲደርስ ‘ከታሪክ ማህደር’ አይነት እያመጡ ማሸማቀቅ አይነት ነገር አለ፡፡ እኛ እንዴት ዙፋን ላይ እንደነበርን፣ ያኛው ሰው ግን አይደለም ዙፋን አጠገብ ሊደርስ አሮጌ የሳጠራ ወንበር እንኳን እንዳልነበረው…አይነት ወሬ ይደረደራል፡፡
“እኛ ቤት የበግና የበሬ ቅልጥም ሰልችቶን ምግብ ለውጡልን እያልን ስንጣላ፣ እነሱ ቤት እኮ አምስት ቀን ያደረ ንፍሮ ነበር የሚበሉት፡፡ አሁን ነው እኮ ያለፈለት…ይሄኔ ዘርፎ ይሆናል እንጂ የትኛው ችሎታው ነው…” ምናምን አይነት ነገር ይደረደራል፡፡
ይሄ እንዲህ የተባለው ሰው “አለፈልኝ” ብሎ በመኪና ሰው ላይ ቆሻሻ ውሀ እየረጨ ይሄዳል? እንደውም፡፡ “አገኘሁ” ብሎ ቀድሞ ሰላም ይላቸው የነበሩትን ሰዎች እየገላመጠ ማለፍ ጀምሯል? በጭራሽ። እንደውም ትህትናው ጨምሮ ሰው በሁለት እጁ ነው የሚጨብጠው። ታዲያ ይሄ ሁሉ ውግዘት፣ ይሄ ሁሉ ናዳ ምን ባጠፋ፣ በምን ሀጢአቱ ነው! እናማ…ስኬት በራሱ እንደ ሀጢአት ሲታይ ልክ አይደለም፡፡
እናላችሁ… “ሀበሻ ምቀኛ ነው” አይነት ሰሊጡንም፣ ተልባውንም ቀላቅሎ መውቀጥ ልክ ባይሆንም… የሚያሳስቡን ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡  
እሷዬዋ ጥራ ግራ በኑሮዋ ትንሽ መሻሻል ስታሳይ ከምናሞግሳት፣ “ጎበዝ በርቺ፣ ለተሻለ ህይወትም ያብቃሽ!” ብለን ከምንመርቃት ይልቅ የህይወት ታሪኳን ራሳችን በፈለግነው መንገድ የምንጽፍላት እንበዛለን፡፡
“አናውቃትምና ነው…ለብሳ የዋለችውን ሻማ ቀሚስ ለብሳ የምታድር አልነበረች እንዴ! አሁን ባለታኮ ጫማ ሆነችና…”
“ይሄኔ ውሽሞቿ ገንዘብ እየሰጧት ይሆናል…”
“ኸረ እንደውም አገሯ ድረስ ሄዳ ያስተበተበችው ነገር እንኳን ሰው አገር ያሽመደምዳል አሉ!”
በፈርጅ፣ በፈርጁ ታሪክ ይደረደራል፡፡ ይሄ፣ ይሄ ሲታይ፣ ስሟን መሬት ለመሬት የምንጎትተው ሰዎች ስንበዛ… አለ አይደል… “እንደሚባለው የእውነት ግን ምቀኞች ነን እንዴ!”  ቢያስብል አይገርምም፡፡
አንድ ሰው ትናንት ከነበረበት ቦታ ተንቀሳቅሶ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ትናንት በሦስት ቀን አንድ ጊዜ መብላት ያቅተው የነበረ… ዛሬ በቀን አሥራ ሦስት ጊዜ የመብላት አቅም ቢኖረው ‘እሰየው’ ማለት እንጂ “አጅሬ ሜርኩሪ መሸጥ ጀምሮ ይሆናል…” አይነት ማጣጣል የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ ልንጎርሰው የነበረውን ከአፋችን አልነጠቀን!  
(በነገራችን ላይ ይሄን ሁሉ ስናወራ…አለ አይደል… ግራ በሚገባ ‘ቲራቲር’ በአንድ ጊዜ ከምድር ቤት ወደ አሥራ ምናምነኛ ፎቅ የምንወረወር እንዳለን ሳንረሳ ነው! በእርግጥም ሌሎች ሊጎርሱት የነበረውን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ነጥቀን፣ በራሳችን ጥረት ያለፈልን የምናስመስል እንዳለን አይካድም!)  
እናላችሁ…በምቀኝነት የተነሳ ሥራ መሥራት እንኳን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል “የችግራችን መሰረት ምንድነው?” ብሎ የሚያጠና፣ “እንዴት ነው ሥጋና ባዳን የሚያራርቁ አስተሳሰቦች እንደ ወረርሽኝ የተዛመቱት?” ብሎ የሚመረምር ባለሙያ አለመኖሩ የምርም ይቆጫል፡፡
ይልቁንም የበጎ ፈቃደኛ አዋቂዎች በዙና ነገሩ ሁሉ እቃ፣ እቃ ጨዋታ እየመሰለ ነው፡፡
ሁለት የታሪክ መጽሐፍ አንብቦ ሳይጨርስ ታሪክ እንደሌለን ሊያስረዳን የሚፈልግ የበጎ ፈቃድ ተንታኝ በዛብና! ምንም ስለማያውቀው ጉዳይ የመጨረሻውን ቃል አይነት ድምዳሜ የሚሰጠን የበጎ ፈቃድ ኤክስፐርት በዛብና፡፡
(የምር ግን…እውነተኛ እውቀት እንኳ እንዳናገኝ የማናየው፣ የማንዳስሰው ግንብ የተገነባብን አይመስላችሁም፡፡ መማሪያ መጽሐፍ ላይ ምን የሚያክለውን ተራራ፣ ከአንዱ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ መውሰድ አይነት ‘ስህተት’  ባለበት… እውነተኛ እውቀት ቢጠማን ምን ይገርማል!)
እናላችሁ…ከርሞ፣ ከርሞ ‘ጊዜ ሲያመች’ ብቅ ከሆነ፣ የቀበሮም ይሁን ከምን ጉድጓድ ብቅ እያሉ “ካላነቃኋችሁ ” የሚሉ በዙብና!
‘የቲማቲም መወደድ የእድገት ምልክት ነው’ የሚሉ፣ አትክልት ተራን ከቺቺንያ ለመለየት ጊዜ የሚወስድባቸው ተንታኞች በዙብና!
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ከሚነግሩን ይልቅ የቬንገር መነሳት አርሴናል ላይ ስለሚያመጣው ተጽእኖ  አንድ ጥራዝ ሙሉ የሚነግሩን ተንታኞች በዙብና! (ለነገሩ አንዳንዴ በየቡድኑ ካሉ ኳስ አመራሮች ውስጥ በፍጹም ቅጣት ምትና በእጅ ውርወራ መካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት የማይችሉ አሉ ብንባል አይገርመንም፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… ‘ሁሉም አገር ጠላት ያስፈልገዋል’ የሚባል ፖለቲካ ነገር አለ…አለበለዛ አገሮች ጦር ሀይላቸውን ማሳደግ አይችሉማ! ታዲያ ይሄ እኮ ለአገር ተባለ እንጂ ለእኛ አልተባለም፡፡ ለነገሩ ጥቅስ ኖረም፣ አልኖረ ራሳችን ጠላት ብለን የምንፈርጃቸው መአት አሉን፡፡
እኛን ትታ ወደዛኛው ቤት የሄደች ሚስት ጠላት ነች፡፡
ፈተና ላይ ‘ኤፍ’ ያስታቀፈን አስተማሪ ጠላት ነው፡፡
የዛኛው ፖለቲካ ቡድን አባል ‘አማራጭ ሀሳብ ያለው ሰው’ ሳይሆን ጠላት ነው፡፡
እንቅልፍ ለሚያስወስደው ንግግራችን ያላጨበጨበ ጠላት ነው፡፡
እናላችሁ…ምቀኝነት የሚባለው ነገር “አይ የሰው ነገር!” ብለን ብቻ ለማለፍ የሚያስቸግረን ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5941 times