Saturday, 22 July 2017 15:36

‹‹ዓላማ ካላችሁ የትም ትደርሳላችሁ፤ እኔን ተመልከቱ››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  • የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት እስከ 3 ሺህ ዓመት ይዘልቃል
                                        • ለሁሉም ቤተ-እስራኤላውያን እስራኤል አገራቸው፤ ቤታቸው ናት
        ተወልደው ያደጉት በደቡብ ጎንደር አምቦ በር በተባለች የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ በህጻንነታቸው እንደ ማንኛውም ገጠር ተወልዶ እንዳደገ ልጅ፤ ቤተሰቦቻቸውን እንጨት በመልቀም፣ ውሃ ከምንጭ በመቅዳትና በመላላክ እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ መብራት እንኳን በሌለበት የገጠር ቀበሌ ያደጉት የዛሬዋ እንግዳችን፤ በ16 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ እስራኤል በማቅናት ከአገራቸውና ቀዬአቸው ርቀው፣ በሂብሩ ቋንቋ ትምህርት በመጀመራቸው የገጠማቸውን ፈተና
አጫውተውናል፡፡ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ክብርት አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ፤ የዛሬ ሳምንት ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ፣ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡ ለተመራቂዎችም የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ በስፍራው የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በአምባሳደሯ
ትውልድና እድገት፣ በእስራኤል ቆይታቸው ስለተጋፈጧቸው ፈተናዎች፣ ለአምባሳደርነት እስከመድረስ ስላበቋቸው የጥንካሬ ምስጢሮች፣ ስለ ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት፣ በቤተ- እስራኤሎች የኑሮ ዘይቤና የመብት ጥሰቶች ዙሪያ (እጅግ በተጣበበ ሠዓታቸው) አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያን አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

      ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ዩኒቨርስቲ ተከፍቶ፣ እርስዎም የክብር እንግዳ ሆነው፣ ተማሪዎችን ሲያስመርቁ ምን ተሰማዎት?
እምም. . . በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እንዲያውም ልንገርሽ… ከተመራቂዎቹ በላይ እኔን ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም እኔ እዚህ በማድግበት ጊዜ ዩኒቨርስቲ ቀርቶ ብዙ የትምህርት ዕድል አልነበረም፡፡ ደስታዬን እጥፍ ያደረገው አንቺ እንዳልሽው እዚህ አካባቢ ተወልጄ አድጌ፣ በዚህ ሀገር ወግና ባህል ታንፄ፣ ከዚያም ወደ እስራኤል አገር ሔድኩኝ፡፡ በወቅቱ ት/ቤት ስገባ የመማሪያ ቋንቋው እንኳን እንግሊዝኛ አልነበረም፤ ሂብሩ ነበር፡፡ አንዳንዴ መምህራን ሲያስተምሩ  አይገባኝም ነበር፡፡ መጀመሪያ በአማርኛ ጽፌ፣ ከዚያ ወደ መኝታዬ እሔድና ያንን ጽሑፍ ወደ እንግሊዝኛ እቀይራለሁ፡፡ ከዚያ ነው በስንት ልፋት ወደ ሂብሩ የምቀይረው፡፡ እኔ በእንደዚያ ዓይነት አስቸጋሪና ፈታኝ ጊዜ ነበር ያለፍኩት፡፡ ያንን ችግር የተጋፈጥኩት መማር ስለነበረብኝ ነው፡፡  
ተምረው ትልቅ ደረጃ ለመድረስ የነበረውን ህልም ከየት ነው የታጠቁት?
እኛ ቤተሰቦቻችን ያሳደጉን “ጠንክራችሁ ከተማራችሁ ትልቅ ደረጃ ትደርሳላችሁ፤ ለአገራችሁም ኩራት ትሆናላችሁ” በሚል ምክር ነበር፡፡ ይህንን ተከትዬ አስቸጋሪ ፈተናዎችን አልፌ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ይህንን ስንቅ ያስታጠቁኝ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ ሌላውም ወጣት ምንም ፈተና ቢገጥመው፣ ዓላማ ካለው የፈለገበት መድረስ ይችላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዛሬ በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ይህቺን አገር የሚለውጡ ብዙ ራዕይ ያላቸው ተማሪዎች በአካባቢያቸው፤ በራሳቸው ቋንቋና በወገኖቻቸው ተምረው ተመርቀዋል፡፡ እኔም ተወልጄ ባደግሁበት አካባቢ፣ ያውም ዩኒቨርስቲ ተከፍቶ፣ እኔም እዚህ ደርሼ፣ በክብር እንግድነት ተጋብዤ ተማሪዎችን ስመርቅ፣ ከእነርሱ በላይ መደሰቴ ለዚህ ነው፡፡ አሁንም የምመክረው፣ ዓላማ ካላችሁ የትም ትደርሳላችሁ፤ እኔን ተመልከቱ የሚል ነው፡፡ በምረቃው ላይ ያስተላለፍኩትም መልዕክት ይሔው ነው፡፡
እንደሚያውቁት በተለይ በገጠሩ የአገራችን ክፍል፣ ሴት ልጅ ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን ትጋፈጣለች፤ ዛሬ እነዚህን ፈተናዎች አልፋ ከተመረቁት 2653 ተማሪዎች፣ አጠቃላይ ብልጫ ያመጣችውን  ወጣት የሸለሙት እርስዎ ነበሩ --
እጅግ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ይገርምሻል እኮ ስሟ እንደኔው በላይነሽ ነው፡፡ ይሔ የሚያሳየው የራሷን ጥረትና ትግል እንዲሁም የዓላማ ፅናት ነው። አየሽ እኔም የገጠሩን አስተዳደግ አልፌበታለሁ፤ አውቀዋለሁ፡፡ ፈተናዎችን ተጋፍጠው ለዚህ የሚበቁ ልጆችን ሳይ ልቤ ይነካል፡፡ ደስታዬ ከልክ ያልፋል፡፡ አየሽ ነገ ይህቺ ልጅ የአገር መሪ ልትሆን ትችላለች፡፡ ዛሬ ያገኘችው ክብር፣ አድናቆትና ምርቃት ለበለጠ ክብርና ኃላፊነት እየገፋፋት ይሔዳል፡፡ ለሌሎች አቻዎቿም ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ወደ ኋላም መሔድ አትፈልግም፡፡ ይህቺ ልጅ አገሪቷ በልጆቿ ተስፋ እንዳላት አመላካች ናት፡፡ ስላገኘኋት፤ ስላየኋት በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
እስቲ ስለ አስተዳደግዎ በጥቂቱ ያንገሩኝ ?
ከጎንደር 25 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በሚገኝ መንደር ነው የተወለድኩት፡፡ በጣም ጥሩ ጥሩና ጠንካራ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት። ትምህርትም የጀመርኩት እዚያው ሰፈር ውስጥ በነበረ ት/ቤት ነው፡፡ የእስራኤል ጂው (ቤተ እስራኤል) ከሆነ ቤተሰብ ነው የወጣሁት፡፡ አባቴ የታወቁ ትልቅ የሃይማኖት መሪ ነበሩ፤በተለይ አርብ አርብ መጽሐፍ ቅዱስ እየተነበበ፣ እንማራለን፡፡ በእኛ ሃይማኖት አርብ አርብ መሰብሰብ አለ፡፡ እራት የሚበላው በአንድ ላይ ነው፡፡ ከዚያ ለሕይወታችን የሚጠቅመንን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ አባታችን ያስተምሩን ነበር፡፡
ከያኔው የአባትዎ ትምህርት ይበልጥ ውስጥዎ የቀረውን ሊነግሩኝ ይችላሉ?
አንዳችን ሌሎችን እንደ ራሳችን ወድደን ስለመኖር፣ ተካፍለን ስለ መብላት፣ አካባቢያችንንና ሕዝቡን ስለ መውደድ፣ በአጠቃላይ ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር ስንማር ነው ያደግነው፡፡ መማር ብቻም ሳይሆን ቤተሰብም ይህንን በተግባር ሲያደርግ ዓይቼ ነው ያደግሁት፡፡ እንዲያውም አባቴ ‹‹የእኛ ቤት እንደ አብርሃም ቤት ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እነዚህ ትምህርቶችና ምክሮች አሁን ላለሁበት ደረጃ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የልጅነት ጊዜዬንም ከቤተሰቤ ጋር በደስታ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ይሔ ሁሉ አሁንም ትዝ ይለኛል፡፡
እስራኤል ምንድን ነው ያጠኑት?
በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በአፍሪካ ጥናቶች  ነው የመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪዬን የሰራሁት፤ በኋላ ፒኤችዲ ልሰራ ስል የሆኑ ሰዎች ‹‹ለምን አትሞክሪም፤ ዲፕሎማት መሆን ትችያለሽ›› የሚል ሃሳብ ሲያመጡ፣ ማስተርሴን እየሠራሁ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም፤ የሠዎቹ ሃሳብ ወደ ውስጤ ሰርፆ ነበር፡፡ ከዚያ ዲፕሎማት መሆን አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ዲፕሎማት ከሆንኩ በኋላ ግን ወደዚህ እመጣለሁ ብዬ ያሰብኩት አሁን በመጣሁበት ወቅት አልነበረም፡፡ ለምን ብዙ ልምዶችን መቅሰም እንዳለብኝ አምን ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ያው እንደሚታወቀው የዛሬ አምስት ዓመት አምባሳደር ሆኜ መጣሁ፤ ይሄው እየሠራሁ ነው፡፡
በአንድ ወቅት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበርና መልሶ መቀጠሉን ሠምቻለሁ፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያና እስራኤል በአሁኑ ወቅት ያላቸው ግንኙነት እጅግ በጣም በጣም የጠበቀ ነው። ግንኙነታቸው እስከ 3 ሺህ ዓመት ይዘልቃል፡፡ ከንጉሥ ሰሎሞንና ከንግሥት ሣባ ጊዜ ጀምሮ ማለት ነው፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም ጦርነት ስለነበረ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች፡፡ ግንኙነቱ እንደገና እ.ኤ.አ በ1989 ታደሰ። ግንኙነቱ ከታደሠ በኋላ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጥቶ፣ አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክቱ ነገሮችን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
የአገራቱ ግንኙነት ትልቅ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ከሚያመላክቱት አንዱ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ሲሆን ባለፈው ወርም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤልን መጎብኘታቸው የአገራቱን የጠበቀ ግንኙነት ያመለክታል፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽም፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከ3ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ አገራት ሕዝብ የተሳሰረ በመሆኑ፣ ይህን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሕዝብ ለሕዝብ፣ ዩኒቨርስቲ ለዩኒቨርስቲ፣ ሆስፒታል ለሆስፒታል ትስስር መፍጠር አለብን፡፡ እስራኤል ስፋቷና የሕዝቧ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም ትልቅ አገር ናት፡፡ በጠላት የተከበበች ብትሆንም በዕውቀት፣ በሥራና አገር በመውደድ የጠነከሩ ሕዝቦች ስላሏት አሁንም ትልቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ናት፡፡
ከዘመቻ ሠለሞን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ በርካታ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል መሔዳቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከአኗኗር፣ ከሠብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ የሚሰሙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ እስቲ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ?
የኢትዮጵያውያን ይሁዳዎች (ቤተ እስራኤላዊያን) በእስራኤል የሚኖሩት በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንድ ችግር ያለባቸውም አሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ሚድያው የሚያሳየውን ካጤንሽው ብዙ ጥሩ ነገር አያሳይም፡፡ አንድ ነገር ሲነሳ ነው ሔደው ያንን ብቻ ለመናገር የሚፈልጉት፡፡ እኛ አንደኛ የጀርባ ታሪካችንን (background) ማየት አለብን። አብዛኞቹ ቤተሰቦቻችን አርሰው፣ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ፣ እጅግ የምንኮራባቸው ገበሬዎች ናቸው፡፡ እዚያ አገር ስትሔጂ ቴክኖሎጂው፤ የባህሉ ጫና አለ፡፡ ያንን ሁሉ አልፈን፣ በዚህ አጭር ጊዜ ትልልቅ ቦታ የደረሱ ልጆችን ማየት መቻላችን፣ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ እርግጥ ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ነገሮች፤ ጫናዎች አንፃር አንዳንድ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ እነርሱን የማለፍ ብልሀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ሁሉም ቤተ-እስራኤላዊያን፣ እስራኤል አገራቸው፤ ቤታቸው ናት። ሁሉም መብት አላቸው፡፡ እንደውም ለኢትዮጵያ ቤተእስራኤላዊያን መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማስትሬት ወይም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን እስኪሰሩ  ድጋፍ አይለያቸውም። ቤት መግዛት ቢፈልጉ 80 በመቶውን ወጪ የሚሸፍነው የእስራኤል መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤሎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከራሺያ የመጣው ቤተ-እስራኤላዊ ተምሮ፣ ቴክኖሎጂውን አውቆ ነው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ የኖርነው ደግሞ የኖርንበት ሥርዓት ሌላ ነው፡፡ ስለዚህ መደገፍ አለብን፡፡ ያንን ለማስተካከል የእስራኤል መንግሥት እየሠራ ሲሆን  ሌሎች በዚሁ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ነገሮች በሒደት መቶ በመቶ ጥሩ ይሆናሉ፡፡

Read 905 times