Saturday, 22 July 2017 15:37

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ብቸኛዋ የዋንጫ ተሸላሚ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

      ‹‹የዛሬው ስኬቴ ከቤተሰቦቼ ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው››

    በላይነሽ አወቀ አባተ፤ ምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ በተባለ አካባቢ ደንጋባ በተባለች የገጠር ቀበሌ ነው የተወለደችው፡፡ እንደ ትልቋ አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ ሁሉ በልጅነቷ እንጨት በመልቀም፣ ውሃ በመቅዳትና በመላላክ፣ ቤተሰቦቿን ስታገለግል ቆይታ፣ እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ አካባቢዋ በሚገኝ ትምህርት ቤት ገብታ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በቅታለች፡፡ የዛሬ 3 ዓመት ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለችው በላይነሽ፤ የዛሬ ሳምንት እንደ ሌሎች ጓደኞቿ ትምህርቷን በኢኮኖሚክስ አጠናቅቃ ተመርቃለች፡፡ መመረቅ ብቻም ሳይሆን ከአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ማዕረግ ሰርተፍኬት፣ የወርቅ ሜዲሊያና የዋንጫ ብቸኛ ተሸላሚ በመሆን፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ከሆኑት አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲ እጅ ሽልማት ወስዳለች፡፡ በስፍራው የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከበላይነሽ አወቀ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡

        እስኪ ስለ አስተዳደግሽ አጫውቺን?
እኔ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ሸበል በረንታ በተባለ አካባቢ፣ ደንጋባ በተባለች ቦታ ነው የተወለድኩት። አስተዳደጌ እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ ቤተሰቤን በማገልገል ነው፡፡ ቤተሰቦቼ አርሶ አደሮች ናቸው። ባይማሩም የትምህርት ጥቅም የገባቸው ይመስለኛል። ስለዚህ እድሜዬ ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ልከውኝ፣ ተምሬ፣ ለዛሬው ቀን በቅቻለሁ፡፡
ጎበዝ ተማሪ መሆን የጀመርሽው መቼ ነው?
ከልጅነቴ ጀምሮ በትምህርቴ ጥሩ ውጤት እያመጣሁ ነው ያለፍኩት፡፡ ነገር ግን 7ኛና 8ኛ ክፍል ስደርስ ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ላይ መመሰጥና ሌላ ስራ ስታዘዝ እምቢ ማለት ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ የተነሳ አንዳንዴ ከቤተሰብ ጋር መጋጨት ሁሉ ጀምሬ ነበር፡፡ እነሱ እንደ በፊቱ አንዳንድ ነገር እንዳግዛቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ አንዳንዴ ተጭነውኝ ስራ ስታዘዝ፣ ከደብተሬ ጋር ተመልሼ የምገናኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አልቅሽ አልቅሽ ይለኛል፤ እበሳጫለሁ፡፡ በቃ ከደብተሬ ጋር ብቻ መሆን ነበር የሚያስደስተኝ፡፡
ተወልደሽ ያደግሽው በሰሜኑ የገጠር አካባቢ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የቤት ውስጥ ስራ ጫና እንዲሁም ባህል ተደማምሮ፣ ሴት ልጅ ወደ ትምህርት ቤት እንዳትሄድ፣ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። አንቺም ቤተሰቦችሽ እንዳልተማሩ ተናግረሻል፡፡ ታዲያ እንዴት ከነዚህ ተፅዕኖዎች አምልጠሸ ለዚህ በቃሽ?
በጣም የሚገርመኝና የሚያስደንቀኝ ነገር ቤተሰቦቼ በዚያን ሰዓት ምንም ያልተማሩ አርሶ አደሮች ቢሆኑም፣ ለትምህርት ልዩ ቦታና አክብሮት ነበራቸው፤ ይሄ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ከኔ በፊት የነበሩ ሴቶች ቢያንስ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ተድረው ከዚያ ተፋትተው ነው ት/ቤት የገቡት፡፡ እኔና ከኔ በታች ያሉ ልጆች ከሌሎች በተሻለ በነፃነት የመማር እድል አግኝተናል ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ እንግዲህ ጊዜውም እየተቀየረ፤ መንግስትም የገጠር ልጆች እንዲማሩ ጫና እያደረገ በመምጣቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህም ሆኖ ጉዳዩ ያልገባቸው ብዙ ቤተሰቦች አሉ፡፡ የእኔ ቤተሰቦች ጉዳዩ ገብቷቸው፣ እኔን ወደ ት/ቤት ልከውኛል፡፡ በፊት በፊት አልታዘዝም ብዬ ከደብተሬ ጋር ስጣበቅ በመጠኑም ቢሆን ቅር ይላቸው ነበር፤ በኋላ ላይ እንዲያውም ያበረታቱኝ ጀመር፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጃቸው ነኝ፤ ተምሬ ትልቅ ቦታ እንደምደርስ በኔ ተስፋ አላቸው። ለእኔ ደግሞ ይሄ ተስፋቸውና እምነታቸው ትልቅ ሀላፊነት እንዲሰማኝ ስላደረገኝ እየበረታሁ ነው የሄድኩት፡፡ የዛሬውም ውጤቴ ከዚህ የቤተሰቦቼ ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
በዚህ ዩኒቨርሲቲ የነበረሽ ቆይታ፣ ከጓደኞችሽ ጋር የነበረሽ ግንኙነትና የአጠናን ስልትሽ ምን ይመስል እንደ ነበር እስኪ ንገሪኝ?
እዚህ ግቢ ከገባሁ ጀምሮ ካስደሰቱኝ ነገሮች የግቢያችን ለመማር ምቹ መሆን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአካባቢዬ አብረውኝ የመጡ ተማሪዎች ስለነበሩ፣ አካባቢው እንግዳ እንዳይሆንብኝ ረድተውኛል፡፡ እነዚህ ልጆች በትውልድ መንደራችን አብረን አንድ ክፍል ውስጥ ስንማር አድገናል፡፡ አብረን ነው ስንጫወት ያደግነው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ስምንት እንሆናለን፡፡ ከእነሱ ጋር ስለሆንኩ ከቤተሰቤ ጋር የምኖር እንጂ ወደ ውጭ የወጣሁ እንደይመስለኝ አድርገውኛል፡፡ ይሄ አንደኛው ለውጤቴ ማማር አስተዋፅኦ ያደረገልኝ ነው፡፡ ከሌላ አካባቢ ከመጡት የግቢው ተማሪዎች ጋር በተወሰነ መጠንም ቢሆን የመግባባት አቅም አላጣሁም፡፡ ሰው ጥሩ ፍቅር ከሰጠኝ እኔም ሙሉ ልቤን ነው የምሰጠው፡፡ ከተማሪም ብቻ ሳይሆን ከመምህራን ጋርም ጥሩ መግባባትና ግንኙነት ነበረኝ፡፡ የአጠናን ስልቴን ጠይቀሽኝ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የማጠናው ከጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ በተለይ ከአንዱ ጓደኛዬ ጋር በጣም እናጠና ነበር፡፡ ብቻዬን ከሆንኩኝ ቶሎ የማንቀላፋት ባህሪ አለኝ፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን  በጥናት ሳሳልፍ ደስ ይለኛል፡፡ ወሬ ከሰማሁኝ ወሬኛም ጭምር ነኝ። ይህን ባህሪዬን ስለማውቅ አስቀድሜ ከወሬ እርቃለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ቀለል ያለና ብዙ ጫና የሌለበት የትምህርት ቆይታ አሳልፌያለሁ፡፡
ከትውልድ አካባቢሽ 8 ተማሪዎች በዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብረውሽ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ነግረሽኛል፡፡ ውጤታቸው እንዴት ነው?
ጓደኞቼና አብሮ አደጎቼ ምንም እንኳን ዛሬ ተሸላሚ ባይሆኑም አሪፍ ውጤት ያመጡ አሉ። መሰናዶ ትምህርት ቤት በነበርንበት ጊዜ የሶሻል ክላስ አንድ ብቻ ነበር፡፡ ከነዚህ ጓደኞቼ ጋር አብረን ነበር የተማርነው፡፡ አብረን እያጠናን እየተጋገዝን ነው ለዚህ የደረስነው፡፡ ስለዚህ አሁንም በትምህርት አቀባበላቸው፣ በአመለካከታቸው የላቀ አቅም ያላቸው ናቸው፤ ምንም እንኳን ዛሬ ባይሸለሙም ማለቴ ነው፡፡
በኢኮኖሚክስ ነው የተመረቅሽው፡፡ በቀጣይ ምን ልትሰሪ አቅደሻል?
የወደፊት አላማዬ ኢኮኖሚስት መሆን ነው። እዚህ ለመድረስ ተጨማሪ እውቀት ያስፈልገኛል። አሁን የያዝኩት እውቀት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብትከተል ውጤታማ ትሆናለች? አሁን እያራመደች ያለችውስ ፖሊሲ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ለማወቅ እንዳልኩሽ፣ ተጨማሪ እውቀት መገብየት አለብኝ። ይህን እውቀት በመምህርነት ተሰማርቼ፣ ሌሎችን እያስተማርኩ፣ እኔም ጎን ለጎን እየተማርኩኝ፣ የማሳደግ ዓላማ አለኝ፡፡
ዩኒቨርሲቲው እዚሁ መምህር አድርጌ ላስቀርሽ ቢልሽስ?
በደስታ ነዋ!
በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ብዙ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመምህራን የእውቀትና ክህሎት ማነስና ሌሎችም። እዚህ ስትማሪ ያጋጠመሽ ችግር አለ?
በዚህ ረገድ እኔ ብቻ ሳልሆን አብረውኝ የሚማሩት ሁሉ እድለኞች ነበርን ማለት ይቻላል። መምህሮቻችን በጣም ልዩዎች ነበሩ፡፡ እኔም ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት አንዳንድ ነገሮችን እሰማ ስለነበር ፈርቼ ነበር፡፡ እዚህ ያጋጠመኝ በተቃራኒው ነው፡፡ መምህሮቻችን ብዙ ሰዓት ተግተው የሚያስተምሩ፣ ከተማሪዎቻቸው ጋር ሲቆዩ የማይሰለቹና ለሙያቸው የሚተጉ ነበሩ፡፡ ይሄ ደግሞ እኛን እድለኛ ያደርገናል፡፡
ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች አሉሽ?
ከእኔ በታች ያሉት ወንድሞቼ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ በተለይ የእኔ ተከታይ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነው፡፡ አሁን 8ኛ ክፍል ደርሷል፡፡ እውነት ለመናገር፤ ጉብዝናው ከኔ ከመብለጡ የተነሳ፣ አንዳንዴ እሱን ሳይ እኔ ባለኝ እውቀት አፍራለሁ። የሆነ ነገር ስንጠያየቅ አንዳንዴ ያስደነግጠኛል። በፊት ትንሽ እያለ እኔ የማደርገውን ይከተላል፤ ሳጠና ያጠናል፤ አሁን ግን  ጎበዝ ነው፡፡ ይህ ወንድሜ ከኔ የሚጠብቀው ውጤት ነበር፤ ያንን በማሳካት ለታናናሾቼ አርአያ ለመሆን ጉዞ ጀምሬያለሁ። አርአያነቴን በማስቀጠል ታናናሾቼ ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ የምችለውን አደርጋለሁ፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታሽ ለሴት ልጅ አስቸጋሪ ናቸው የምትያቸው ነገሮች ገጥመውሻል?
እንግዲህ ለሴት ልጆች በተለይ እንደ ፈተና የማየው፣ ከአካባቢያቸው… ከወላጆቻቸው ርቀው ሲሄዱና ቦታው እንግዳ ሲሆንባቸው ትንሽ  ይቸግራቸዋል፡፡ ይሄ ግን ብዙ አይቆይም፤ ይላመዳሉ። ሌላ የጎላ ፈተና አላስተዋልኩም፤ አንድ ሴት በርትታ ከተማረች፣ በራስ መተማመንና ስነ-ስርዓት ካላት፣ ያለ ምንም ችግር ትምህርቷን ተከታትላ ለውጤት ትበቃለች፡፡ ይሄ ወንድ ተማሪዎችንም ያጠቃልላል፡፡

Read 2183 times