Saturday, 22 July 2017 15:39

የታክስ ጉዳይ፣ የኑሮ ጉዳይ ነው! “የፖርቲ ብሽሽቅ” አናስመስለው!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(8 votes)

   የኑሮ ጉዳይ፣ ከሁሉም ነገር ይቀድማል! ከአገርም ጭምር!
የሁለት መቶ ሺ ብር ሽያጭ የሚያከናውን ሱቅ፣ አንድ ሚሊዮን ብር ተብሎ ከተገመተበት፣ የ45 ሺ ብር ተጨማሪ የታክስ ክፍያዎችን ያስከትልበታል፤ ከነቤተሰቡ ኑሮውን ይደረምስበታል።
የሰዎችን የግል ኑሮ፣ ከሁሉም የላቀ ክቡር ጉዳይ መሆኑን ላለመቀበል የሚያንገራግር ወይም የሚያናንቅ አገርና ሕዝብ፣... አንድ ደረጃ ከፍ ቢል፣ እጥፍ ቁልቁል መውረድ አይቀርለትም።
ለኑሮ ጉዳይ ቅድሚያ ካልሰጠን፣ ‘ታክስ’ን ካስቀደምን፣... በግል ኢንቨስትመንት የስራ እድል የማስፋፋት ጉዳይ፣ “ዋና የፖለቲካ ጉዳያችን” እንዲሆን ካላደረግን፣... አያልፍልንም።   
አነስተኛ የቢዝነስ ድርጅቶች ላይ የተጣለው የታክስ ክፍያ ከባድ እንዳልሆነ ለማስረዳት መግለጫ የሰጡ የመንግስት ሃላፊ እንዲህ አሉ፡... “1ሚሊዬን ብር ገቢ ያለው ነጋዴ፣ 18ሺ ብር ታክስ መክፈል አይችልም ማለት ምን ማለት ነው?”...  
(‘ይሄኮ፣... ያን ያህልም ማብራሪያ አያስፈልገውም’ ለማለት የፈለጉ ይመስላል ከአነጋገራቸው)።
እንዲህ አይነቱ መግለጫና ዲስኩር የሚቀርበው፣ በፓርቲዎች የብሽሽቅ መድረክ ላይ ቢሆን ኖሮ፣... በሙያተኛ ሃላፊዎች ሳይሆን የቃላት ጨዋታ ብቻ በሚታያቸው የፓርቲ ተከራካሪዎች ቢሆን ኖሮ፣... በዚያ ላይ ጉዳዩ ከሰዎች ኑሮ ጋር የማይገናኝ ቢሆን ኖሮ፣... አስተዋይነትንና አዋቂነትን ባይላበስም፣  እንደ ‘ብልጣብልጥነት’ ሊቆጠር ይችል ነበር።
ነገር ግን፣ ጉዳዩ በብዙ ሺ ሰዎችና በቤተሰባቸው ኑሮ ላይ፣ ውሳኔና ፍርድ የማስተላለፍ ጉዳይ ነው። ‘ለፓርቲ ብሽሽቅ’ በሚሽቀዳደሙ ሌጣ ፖለቲከኞች ሳይሆን፣ የታክስ ስሌቱን ከሚመሩ ሃላፊዎችና ባለሙያ ሰዎች አንደበት፣ እንዲህ አይነት መግለጫ እየተደጋገመ በቴሌቪዥን ሲሰራጭ፣ ከማሳዘንም አልፎ፣ ተስፋ ያስቆርጣል።
የታክስ ሃላፊዎች መግለጫ ለመስጠት የዘመቱት፣ “የግንዛቤ ጉድለት አለ... የግንዛቤ ችግር አለ... የውዝግቡ ዋና መነሻ የግንዛቤ እጥረት ነው” በሚል ምክንያት ነው። የውሸት መረጃዎችን አርመው፣ የተሳሳቱ ሃሳቦችን አስተካክለው፣ እውነተኛና ትክክለኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሆኑ ነው።
በዓመት የ1 ሚሊዮን ብር ገቢ ማለት፣ በአማካይ በቀን በ5 ብር ሂሳብ፣ ከ600 ሲኒ በላይ ቡና መሸጥ እንደ ማለት ነው (ስድስት መቶ ስኒ ቡና፣... በየቀኑ፣ ሳምንቱን ሙሉ፣ ክረምት ከበጋ!)። ወይም በየእለቱ፣ 700 እንጀራ እየጋገሩ መሸጥ። አራት ወይም አምስት የፀጉር ማስተካከያ ወንበሮች ያሉት ፀጉር ቤት፤ ወይም “በቀን ሃምሳ መጻሕፍት ትሸጣለህ” የተባለ ሱቅ፣ በዓመት “የሚሊዮን ብር ሽያጭ” ይገመትበታል።።
አነስተኛ ምግብ ቤት ውስጥ፣ በቁርስ ሰአት፣ በምሳ ሰዓት፣ ምግብ ለመብላትና ሻይ ለመጠጣት የሚመጡ፣ ከጠዋት እስከ ቀትር ሃምሳ ደንበኞችን፣ ከዚያም በኋላም ሃምሳ ደንበኞችን ማስተናገድ እንደ ማለትም ነው - በአማካይ እያንዳንዱ ደንበኛ ሠላሳ ብር ቢከፍል እንደማለት ነው - (በእርግጥ፣ ደንበኞች ቀኑን ሙሉ በየተራ አይመጡም። ስለዚህ፣ በቁርስ ሰዓት ሃምሳ ደንበኞችን፣ በምሳ ሰዓት ደግሞ ሃምሳ ደንበኞችን እንደማስተናገድ ማለት ነው። አነሰ ቢባል፣ ሠላሳ ወንበሮችን የሚይዝ አዳራሽ ሊያስፈልግ ነው። ባለሰፊ አዳራሽ ‘አነስተኛ’ ምግብ ቤት!)።
እነዚህን የመሳሰሉ ስራዎች ላይ፤ “በዓመት የሚሊዮን ብር ሽያጭ” የግምት ውሳኔ ሲተላለፍ፣ ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ፣ የብዙዎቹ ታክስ ከፋዮች ቅሬታና የታክስ ሃላፊዎች ተደጋጋሚ ምላሽም ምን እንደሚመስል ለማየት እንሞክር።
የታክስ ከፋዮች ዋና ቅሬታ፣ ሚስጥር አይደለም። በአብዛኞቹ ቅሬታ ግልፅ ነው። “በአንድ ቀን ውስጥ 50 መጻሕፍት ሸጬ አላውቅም”፣ “በቀን 600 ሲኒ ቡና እንዴት እሸጣለሁ?”፣... “እያንዳንዱ ፀጉር አስተካካይ፣ ዓመቱን ሙሉ፣ ከንጋት እስከ ምሽት፣ ያለ እረፍት ቢሰራ እንኳ፣ እንዴት ሃያ፣ ከዚያም አልፎ ሠላሳ ደንበኞችን በየእለቱ ማግኘትና ማስተናገድ ይችላል?”... በአጠቃላይ፣... “የተገመተብን ሂሳብ፣... በጣም በጣም የተጋነነ ነው”... የሚል ነው ቅሬታቸው። በሌላ አነጋገር፣ “በዓመት ውስጥ፣ የሚሊዮን ብር ገቢ የሚለው ግምት፣ አጠገቤም አይደርስም” ይላሉ።
ያው፣ የዓመት የሽያጭ ገቢ ግምት የተሳሳተ፣ የተጋነነ፣ ወይም ሁለት እጥፍ፣ አራት እጥፍ ያህልና ከዚያም በላይ፣ ከእውነታው ጋር በጣም ከተራራቀ፣... በዚያው መጠን፣ የታክስ ስሌቶች፣... (ማለትም፣ የዓመት የሽያጭ ተርንኦቨር ታክስ እና የትርፍ ግብር ውሳኔዎች)፣... በእጅጉ የተሳሳቱና የተጋነኑ ይሆናሉ - ከሰዎች የመክፈል አቅም በላይ በእጥፍ ድርብ እያለፉ፣ ከእውነተኛው የሰዎች ኑሮም እየራቁ፣ ሰማይ ለመንካት የሚንደረደሩ!።
የብዙ ግብር ከፋዮች፣ ዋናው ቅሬታና ችግር ይሄው ነው። አይደለም እንዴ? ከላይ እንደገለፅኩት፤ ሚስጥር አይደለም። ቅሬታቸው ግልፅ ነው። ታዲያ፣ በዚህ “የግምት” ዱብዳ ግራ ለተጋቡና ለተጨነቁ ግብር ከፋዮች፣ “የግንዛቤ ማስጨበጫ ምላሽ”፣ ምን ፋይዳ፣ ምን ትርጉም አለው? ምንም!
ከሽያጭና ከኪራይ፣ በዓመት 200ሺ ብር ገቢ የሚያገኝ ቪዲዮ ቤት፣... (ብዙ ወጪዎች እንዳሉበት ሳንዘነጋ)፣ 12 ሺ ብር የታክስ ክፍያዎች ይጠየቃል። የዓመት ሚሊዮን ብር ገቢ ታገኛለህ ተብሎ በተጋነነ ግምት ከተወሰነበት ግን፣... ከዚህኛው ሐምሌ እስከ መጪው ሐምሌ፣ የታክስ ክፍያዎቹ 100 ሺ ብር ይሆናሉ።... ይሄ፣ እውነተኛ መፍትሔ የሚያሻው ከባድ የኑሮ ጉዳይ እንጂ፣ ‘በግንዛቤ ማስጨበጫ’ የሚፈወስ ኩርፊያ አይደለም።      
እናም፣ የታክስ ጉዳይ ሃላፊዎች፣ ከእለት ተእለት የስራ ሃላፊነታቸው ተፈጥሮውና ባሕሪ የተነሳ፣ በሰዎች ኑሮና ሕይወት ላይ ውሳኔ እያስተላለፉ መሆናቸውን ከምር ተገንዝበው፤ ትክክለኛ የማስተካከያ መፍትሄ ለመስጠት ከምር መቁረጥ አለባቸው። ይሄ፣ ከቃላት ጨዋታ ያላለፈ ወገኛ የፓርቲዎች ክርክርና ብሽሽቅ አይደለም። ይሄ፣... የምር የኑሮ ጉዳይ ነው።

የኑሮ ጉዳይ፣ ከሁሉም ነገር ይቀድማል! ከአገርም ጭምር!
የኑሮ ጉዳይ፣... ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የለውም።
የበታች እንጂ የበላይ የለውም - የኑሮ ጉዳይ።
የአገር ጉዳይ፣ የልማት ጉዳይ... ሁሉም ጉዳዮች በሙሉ፣ ከኑሮ ጉዳይ አይበልጡም። እንዲያውም፣ ለጥሩ ኑሮ ሲባል ነው፣ አገርን ጥሩ ማድረግ የሚያስፈልገው። “አገር”፣ “ልማት” የሚሉ ቃላት፣ በጭራሽ የጥፋት ሰብብ ሊሆኑ አይገባቸውም። በማንኛውም ሰበብ፣ የሰዎችን ኑሮ አላግባብ መጉዳት፣ መሸርሸር አልያም መናድ፣... ለዚያውም “በግምታዊ አሰራር”፣... በፍፁም በቸልታ ሊታይ አይገባም። የታክስ ሰራተኞች፣ ሃላፊዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በዚህ ሃሳብ እንደሚስማሙ ነው ተስፋ የማደርገው።
የሰዎችን ኑሮ ማበላሸት፤... እንደዘበት፣ የሃምሳ ሺ ቤተሰቦችን ሕይወት ማናጋት፤... እንደተራ ነገር፣ የመቶ ሺ ቤተሰቦችን ኑሮ ማመሳቀል እፈልጋለሁ የሚል የታክስ ሰራተኛም ሆነ ሃላፊ፣ ባለስልጣንም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖራል ብዬ አላስብም።
በሰዎች ኑሮ ላይ፣ እንደቀልድ መጫወት የማይፈልግ ሰው ደግሞ፣ እያንዳንዷ “የገቢ ግምት”፣... “በሰዎች ኑሮ ላይ የተላለፈች ፍርድ እና ውሳኔ” መሆኗን የመገንዘብ ሃላፊነት አለበት። ከዚህ እውነታ ለመሸሽ፣ ከዚህ ሃላፊነት ለማምለጥ መሞከር፣ ከንቱ ነው። “ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎች መኖራቸው...” በሚል አባባል የሚጀምሩ የጅምላ ንግግሮች፣... የተለመዱ የማምለጫ ፈሊጦች ናቸው። ግን፣ አጥፊ ድርጊት ማመካኛ ከመሆን ያለፈ ትርጉም የላቸውም። “ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች መኖራቸው...” በሚል ንግግር አመካኝቶ፤ ሰዎች ላይ በግምትና በዘፈቀደ እየፈረደ እስር ቤት ለማስገባት የምንወስን አውሬ ዳኛ ሆንን እንደማለት ይሆናልና - ለሰው ሕይወትና ኑሮ ምንም ክብር የሌለው ዳኛ።
 “ግብር መክፈል ግዴታ ነው”፤ “ያለ ግብር መንግስት መቆም አይችልም፤ ስርዓትና ሕግ አይኖርም”፣ እና... እነዚህን የመሳሰሉ ንግግሮችና ምላሾችም ማመካኛ ሊሆኑ አይገባም - የሰዎችን ኑሮ በዘፈቀደ ለማፍረስ ወይም ‘በግምት’ ለመደረማመስ የሚፈቅድ ምንም አይነት ሰበብና ማመካኛ ሊኖር አይገባም። ስለዚህ፣ እንዲህ አይነት ምላሾችና ማሳበቢያዎች መቅረት አለባቸው። የአቤቱታዎቹን ክብደት በመገንዘብ፣ በጥንቃቄ አጠቃላይና ዝርዝር ምርመራ ለማካሄድ መትጋት እንጂ፣ ማምለጫ ክርክሮችን በማቅረብ ምላሽ ለመስጠት መሞከር የለባቸውም።
ጭራሽ የሃላፊዎች ምላሽ፣ ከማምለጫ ክርክርነትም የባሰ ሲሆን ደግሞ አስቡት።

ማምለጥ ብቻ ሳይሆን ማላገጥም ይቅር - በኑሮ ጉዳይ ላይ!
“1 ሚሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ይቅርና፣ ሩቡን ያህል የሽያጭ ገቢ የለኝም” የሚል ጭንቀትና እሮሮ ሲበረከት፤ በደፈናው “ነጋዴ ድሮም ማማረር ይወዳል” ብሎ ለማለፍ መሞከር፣ በቀሽም ማመካኛ ከሃላፊነት ለማምለጥ እንደመሞከር ነው። እሮሮው፣ ትክክለኛ ቢሆንስ? ኑሮውን የሚያፈርስ የተጋነነ የግምት ውሳኔ ተፈርዶበት ከሆነስ? “ነጋዴ፣ ድሮም ማማረር ልማዱ ነው”... በሚል ጭፍን ግምታዊ ስሜት፣ ፍርድ እናፀናበታለን?
የሁለት መቶ ሺ ብር ሽያጭ የሚያከናውን ሱቅ፣ አንድ ሚሊዮን ብር ተብሎ ከተገመተበትኮ፣ የ45 ሺ ብር ተጨማሪ የታክስ ክፍያዎችን ያስከትልበታል። እናም፣ በጭንቀት እሪ ቢል አይገርምም። (ለንፅፅር የቀረቡትን የታክስ ክፍያ ሰንጠረዦች መመልከት ይቻላል።)
ከሃላፊዎች በኩል የቀረቡ ምላሾችስ?
“1 ሚሊዬን ብር ገቢ ያለው ነጋዴ፣ 18ሺ ብር ታክስ መክፈል አይችልም ማለት ምን ማለት ነው!” የሚል የሃላፊዎች ምላሽ፣ በተደጋጋሚ በቲቪ ሲሰራጭ ሰንብቷል።
እንዲህ አይነት ምላሽ ምን ማለት ነው? ይሄ፣ “ግንዛቤ ማስጨበጫ ምላሽ” ሳይሆን፣ “ማላገጫ” ነው የሚመስለው።
የኤሌክትሪክ መስመር ለማግኘት የተመዘገበ ነዋሪ፣ በእንግልት መጉላላቱ አንሶ፣ በአመቱ መጨረሻ 18ሺ ብር ሂሳብ ሲመጣበት ምን ያህል እንደሚደነግጥ አስቡት። ግራ ተጋብቶም፣ “መስመር ከተዘረጋ’ኮ ሦስት ወር ብቻ ነው፤ ለዚያውም ለሁለት አምፖል...” እያለ፣ የቤቱን አምፖል እየቆጠረ ያማርራል።
“አመቱን ሙሉ ስትጠቀም ከርመህ፣ ይሄኔ ደርዘን ማሽኖችን ተክለህ፣ ኤሌክትሪክ ስትፈጅ ቆይተህ፣... 18ሺ ብር በዛብኝ ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ግምታዊ ምላሽ ብንሰጠውና ፍርድ ብናፀናበት .. እንደ ማለት ነው።
ግን ከዚህም ይብሳል።

የ18 ሺ ብር ተረት
የሽያጭ ገቢ ግምት ላይ የሚፈጠረውን ትልቁንና ዋናውን ችግር እንርሳው እንበል።
ለመሆኑ፣ ከታክስ ሃላፊዎች በተደጋጋሚ እንደምንሰማው፣ የሚሊዮን ብር የዓመት ሽያጭ የሚያገኝ ነጋዴ፣ የታክስ ክፍያው 18 ሺ ብር ነው? አይደለም።
ለጊዜው፣ ሌላኛውን የታክስ አይነት ትተን፣ የትርፍ ግብርን (የገቢ ታክስን) ብቻ እንይ። በፀጉር ቤት እና በልብስ ስፌት ስራ የተሰማሩ ሰዎች፣ 18ሺ ብር የትርፍ ግብር ቢከፍሉ እንኳ፣.... እንጀራ ጋግረው የሚነግዱ ወይም በጀበና ቡና አፍልተው የሚሸጡ ከሆነ ግን፣ 34ሺ ብር የገቢ ግብር (የትርፍ ታክስ) እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።
የዱቄት ንግድ ወይም የአጣና ሽያጭ ላይ የተሰማራ ሰው ደግሞ፣ የገቢ ግብር ክፍያው 38ሺ ብር ይሆናል።

“የዓመት የሽያጭ ገቢ 1 ሚሊዮን ብር ነው” ተብሎ የተገመተባቸው
(የቀን ገቢ ግምት ከ2700 ብር እስከ 3300 ብር ገደማ)
የቢዝነስ አይነት    የገቢ ግብር (የትርፍ ታክስ)
ጥጥ እና ተዛማጅ ንግድ    41 ሺ ብር
የጫማ ስራ እና እድሳት    45 ሺ ብር
አሸዋ፣ ካባ ድንጋይ፣ ብሎኬት ስራ    45 ሺ ብር
የቆዳ ስራ፣ ሽያጭ፣ ስፌት    55 ሺ ብር
የህክምና አገልግሎቶች    55 ሺ ብር
ሻማ ሰርቶ መሸጥ    66 ሺ ብር
ቁርስ ቤት፣ ምግብ ቤት    70 ሺ ብር
ስፖርት ቤቶች    70 ሺ ብር
ፎቶ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች    73  ሺ ብር
ሲኒማ ቤቶች    76 ሺ ብር
ትምህርት ቤቶች    80 ሺ ብር
ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ ቤት    80 ሺ ብር
መዋዕለ ሕፃናት    87 ሺ ብር
የመኪና ኪራይ    87 ሺ ብር


ምናለፋችሁ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ከተዘረዘሩት 99 የቢዝነስ አይነቶች መካከል፣ የአብዛኞቹን ብትመለከቱ... ማለትም 63ቱ የቢዝነስ አይነቶች ላይ፣ የትርፍ ታክስ ክፍያው፣ ከ18ሺ ብር በላይ ነው።  
በትምህርት ቤት ወይም በመዋዕለ ሕፃናት፣ ወይም... በቁርስ ቤትና በምግብ ቤት፣ በአሸዋ አቅርቦትም ሆነ በብሎኬት ስራ፣ በጫማ ስራም ሆነ በጫማ እድሳት... እንጀራ ጋጋሪ አልያም የጀበና ቡና ቸርቻሪ... በዓመት፣ የሚሊዮን ብር ሽያጭ ከተገመተባቸው፤ የትርፍ ግብር ክፍያቸው፣ ከ18ሺ ብር በእጅጉ ይበልጣል - ከ34ሺ እስከ 87 ሺ ብር ይጠየቃሉ።
የመንግስት የታክስ ሃላፊዎችና ተቆጣጣሪዎች፣ ‘ግንዛቤ ለማስጨበጥ’ በቴሌቪዥን ያቀረቡልንን መግለጫና ማብራሪያ ሰምታችሁ ከሆነ ግን፣ ትልቁ የታክስ ክፍያ 18ሺ ብር የሚያስመስል ነው። (“ሚሊዮን ብር ገቢ ያለው ነጋዴ፣ 18ሺ ብር ታክስ መክፈል አይችልም ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል የሃላፊዎች ምላሽ፣ በተደጋጋሚ በቲቪ ሲሰራጭ መሰንበቱን አትርሱ።) ታዲያ፣ እንዲህ አይነት የሃላፊዎች ማብራሪያ፣ ግንዛቤን ከመስጠት ይልቅ፣ ግንዛቤን የሚነሳ አይሆንም?
ይህም ብቻ አይደለም።

ከገቢ ግብር በተጨማሪ፣... ሌላ ታክስ የለም እንዴ?
“የሽያጭ ገቢ ግምት”፣... በአንዳች ምክንያት ከተሳሳተ አልያም ከተዛባ፣... ከተጋነነ ወይም ከነጭራሹ ምድርን እየለቀቀ ከጣሪያ በላይ ከሸመጠጠ፣... መዘዙ እጥፍ ድርብ ነው።
በአንድ በኩል፣ የትርፍ ገቢ ግብር ክፍያው፣... ፈር የለቀቀ ይሆናል።
የ500 ሺ ብር ሽያጭ ብቻ የሚያከናውን ቁርስ ቤት፣ “ሽያጭህ፣ሚሊዮን ብር ይደርሳል” ተብሎ ከተገመተበት፣... በቃ አለቀለት ማለት ይቻላል። ከተገቢው የገቢ ግብር በላይ፣ 40ሺ ተጨማሪ ግብር ይጫንበታል። ሸክሙ፣ ይሄ ብቻ አይደለም።
ከእያንዳንዱ ሽያጭ፣ ሁለት በመቶ ‘ተርንኦቨር’ ታክስ መክፈል ይጠበቅበታል። ለ500 ሺ ብር ሽያጭ፣... የተርንኦቨር ታክስ ክፍያው 10ሺ ብር ነው። በተሳሳተ ወይም በተጋነነ የግምት ስራ፣ “ሽያጭህ፣ ሚሊዮን ብር ይደርሳል” ተብሎ ከተወሰነበት ግን፣ 20ሺ ብር የተርንኦቨር ታክስ እንዲከፍል ይገደዳል።
ማንኛውም አይነት የቢዝነስ ስራ፣ ፀጉር ቤትም ሆነ፣
1. “የዓመት የሽያጭ ገቢ 1 ሚሊዮን ብር ነው” ተብሎ ሲገመት
የቢዝነስና የስራ አይነት    የገቢ ታክስ    ተርንኦቨር ታክስ    የታክስ ድምር
ፀጉር ቤት፣ ልብስ ስፌት፣ የእህል ንግድ    18,000    20,000    38,000
እንጀራ ጋግሮ ወይም የጀበና ቡና አፍልቶ መሸጥ    34,000    20,000    54,000
የዱቄት ንግድ፣ የአጣና ሽያጭ    38,000    20,000    58,000
ጥጥ እና ተዛማጅ ንግድ    41,000    20,000    61,000
የጫማ ስራ እና እድሳት    45,000    20,000    65,000
የአሸዋና የካባ ድንጋይ፣ የብሎኬት ስራ    45,000    20,000    65,000
የቆዳ ስራ፣ ሽያጭ፣ ስፌት    55,000    20,000    75,000
የህክምና አገልግሎቶች    55,000    20,000    75,000
ሻማ ሰርቶ መሸጥ    66,000    20,000    86,000
ቁርስ ቤት፣ ምግብ ቤት    70,000    20,000    90,000
ስፖርት ቤቶች    70,000    20,000    90,000
ፎቶ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች    73 ,000    20,000    93,000
ሲኒማ ቤቶች    76,000    20,000    96,000
ትምህርት ቤቶች    80,000    20,000    100,000
ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ ቤት    80,000    20,000    100,000
መዋዕለ ሕፃናት    87,000    20,000    107,000
የመኪና ኪራይ    87,000    20,000    107,000

 2. “የዓመት የሽያጭ ገቢ 500,000 ነው” ተብሎ ሲገመት
የቢዝነስ አይነት     የገቢ ታክስ    ተርንኦበር ታክስ    የታክስ ድምር
ፀጉር ቤት፣ ልብስ ስፌት፣ የእህል ንግድ    6,000    10,000    .16,000
እንጀራ ጋግሮ ወይም የጀበና ቡና አፍልቶ መሸጥ    12,000    10,000    22,000
የዱቄት ንግድ፣ የአጣና ሽያጭ    13,000    10,000    23,000
ጥጥ እና ተዛማጅ ንግድ    14,000    10,000    24,000
የጫማ ስራ እና እድሳት    16,000    10,000    26,000
የአሸዋና የካባ ድንጋይ፣ የብሎኬት ስራ    16,000    10,000    26,000
የቆዳ ስራ፣ ሽያጭ፣ ስፌት    19,000    10,000    29,000
የህክምና አገልግሎቶች    19,000    10,000    29,000
ሻማ ሰርቶ መሸጥ    24,000    10,000    34,000
ቁርስ ቤት፣ ምግብ ቤት    26,000    10,000    36,000
ስፖርት ቤቶች    26,000    10,000    36,000
ፎቶ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች    27,000    10,000    37,000
ሲኒማ ቤቶች    29,000    10,000    39,000
ትምህርት ቤቶች    31,000    10,000    41,000
ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ ቤት    31,000    10,000    41,000
መዋዕለ ሕፃናት    34,000    10,000    44,000
የመኪና ኪራይ    34,000    10,000    44,000

3. “የዓመት የሽያጭ ገቢ 200,000 ነው” ተብሎ ሲገመት
የቢዝነስና የስራ አይነት    የገቢ ታክስ    ተርንኦቨር ታክስ    የታክስ ድምር
ፀጉር ቤት፣ ልብስ ስፌት፣ የእህል ንግድ    1,290    4,000    5,290
እንጀራ ጋግሮ ወይም የጀበና ቡና አፍልቶ መሸጥ    2,790    4,000    6,790
የዱቄት ንግድ፣ የአጣና ሽያጭ    3,090    4,000    7,090
ጥጥ እና ተዛማጅ ንግድ    3,390    4,000    7,390
የጫማ ስራ እና እድሳት    3,690    4,000    7,690
የአሸዋና የካባ ድንጋይ፣ የብሎኬት ስራ    3,690    4,000    7,690
የቆዳ ስራ፣ ሽያጭ፣ ስፌት    4,770    4,000    8,770
የህክምና አገልግሎቶች    4,770    4,000    8,770
ሻማ ሰርቶ መሸጥ    5,970    4,000    9,970
ቁርስ ቤት፣ ምግብ ቤት    6,370    4,000    10,370
ስፖርት ቤቶች    6,370    4,000    10,370
ፎቶ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች    6,770    4,000    10,770
ሲኒማ ቤቶች    7,170    4,000    11,170
ትምህርት ቤቶች    7,570    4,000    11,570
ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ ቤት    7,570    4,000    11,570
መዋዕለ ሕፃናት    8,370    4,000    12,370
የመኪና ኪራይ    8,370    4,000    12,370

4. “የዓመት የሽያጭ ገቢ 100,000 ነው” ተብሎ ሲገመት
የቢዝነስና የስራ አይነት    የገቢ ታክስ    ተርንኦቨር ታክስ    የታክስ ድምር
ፀጉር ቤት፣ ልብስ ስፌት፣ የእህል ንግድ    280    2,000    2,280
እንጀራ ጋግሮ ወይም የጀበና ቡና አፍልቶ መሸጥ    780    2,000    2,780
የዱቄት ንግድ፣ የአጣና ሽያጭ    880    2,000    2,880
ጥጥ እና ተዛማጅ ንግድ    980    2,000    2,980
የጫማ ስራ እና እድሳት    1,080    2,000    3,080
የአሸዋና የካባ ድንጋይ፣ የብሎኬት ስራ    1,080    2,000    3,080
የቆዳ ስራ፣ ሽያጭ፣ ስፌት    1,440    2,000    3,440
የህክምና አገልግሎቶች    1,440    2,000    3,440
ሻማ ሰርቶ መሸጥ    1,890    2,000    3,890
ቁርስ ቤት፣ ምግብ ቤት    2,040    2,000    4,040
ስፖርት ቤቶች    2,040    2,000    4,040
ፎቶ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች    2,190    2,000    4,190
ሲኒማ ቤቶች    2,340    2,000    4,340
ትምህርት ቤቶች    2,490    2,000    4,490
ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ ቤት    2,490    2,000    4,490
መዋዕለ ሕፃናት    2,790    2,000    4,790
የመኪና ኪራይ    2,790    2,000    4,790

Read 3461 times