Print this page
Saturday, 22 July 2017 15:40

ጥሪዎች ለበቆጂ ሯጮች ትንሳዔ - 1

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    • የበቆጂ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት 10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፈዋል፡፡ 15 የዓለም አትሌቲክስ ሪከርዶች አስመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ከ34 በላይ        የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡
    • ጥሪዎች ለበቆጂ ሯጮች ትንሳዔ ከጋዜጠኛ፤ ከከንቲባ ፤ ከእውቅ አሰልጣኞች…
    • በመላው ኢትዮጵያ ትልልቅ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡ በቆጂ ግን የረባ ስታድዬምና የመሮጫ ትራክ የላትም፡፡ ለምን ?
    • አትሌቲክስ ኢንቨስትመንት ነበር… ግን የታላላቅ አትሌቶች መቆጠብ፤ የበቆጂ የተሰጥኦ አካባቢነት መዘንጋት

     ባለፉት 25 ዓመታት በታላላቅ የዓለማችን የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ለኢትዮጵያ የላቁ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ቆይተዋል፡፡  ትውልዳቸው በአርሲ  አሰላ፣ በቆጂና ሌሎች የገጠር ከተሞች ናቸው፡፡ በረጅም ርቀት  10ሺ  እና 5ሺ ሜትር፤ በመካከለኛ ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ዓለምን ተቆጣጥረዋል፡፡ በማራቶንና በጎዳና ላይ ሩጫዎች በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶችም የገነኑ  ናቸው፡፡
አንድ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ የሯጮች ከተማ በሚል በሰራው የፎቶ ቡክሌት የበቆጂ ጉብኝቱን አስመልክቶ  ‹‹…. የዓለማችንንን ምርጥ ማራቶን ሯጮች የልደት ምስክር ወረቀቶች ቢመረመሩ በቆጂ ተደጋግማ ትጠቀሳለች…›› በሚል መፃፉን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በ10ሺ ሜትር የአፍሪካን ፈር ቀዳጅ ድል ያስመዘገበችው ደራርቱ ቱሉ፤ በዓለም አትሌቲክስ የረጅም ርቀት ንጉስ ለመባል የበቃው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ10ሺሜ፤ በ5ሺ ሜትር የማይሰበር ክብረወሰን የያዘው ቀነኒሳ በቀለ፤ በኦሎምፒክ ማራቶን ልዕልቷን ወደ አገራቸው የመለሱት ገዛሀኝ አበራና ፋጡማ ሮባ እንዲሁም ቲኪ ገላና፤ ፤ የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ የተባለች ባለከፍተኛ ውጤት ባለቤት ጥሩነሽ እና የዘመኑ ምርጥ ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያዊ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፤ ፈጣኑ የኢትዮጵያ አትሌት መሃመድ አማን  ሌሎችም ከአርሲዎቹ የገጠር ከተሞች ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ በኦሎምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ፣ በአፍሪካ ሻምፒዮና፤ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች ከ67 በላይ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ ሰብስበዋል፡፡  
ከአዲስ አበባ በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው በቆጂ በተለይ የምትነሳ ናት፡፡ ደራርቱ ቱሉ በጣዕሜ ፤ ፋጡማ ሮባ በመራሮ፣  ጥሩነሽ ዲባባ በጨፋ፣ ቀነኒሳ በቀለና፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቲኪ ገላናና፣ እልፍነሽ ዓለሙ በሌሙ፣ የተወለዱባቸው የገጠር መንደሮች ናቸው፡፡ የበቆጂን ዙርያዋና ከበዋታል።  የበቆጂ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት 10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፈዋል፡፡  15 የዓለም አትሌቲክስ ሪከርዶች አስመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ከ34 በላይ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡
 በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ የቱርክ ጋዜጠኛ እንደጻፈው በቆጂ እንደ  አገር በመቆጠር በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ምን ያህል የገዘፈች መሆኗን በንፅፅር መመልከት ይቻላል፡፡  ባለፉት 25 ዓመታት በኦሎምፒክ መድረክ ከ60ሺ ነዋሪዎች ከሚገኙባት በቆጂ የወጡ አትሌቶች የሰበሰቧቸው ሜዳልያዎች  1.2 ቢሊዮን ህዝብ ያላት ህንድ በሁሉም ስፖርቶች በኦሎምፒክ ከሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች የሚበልጥ፤ 247 ሚሊዮን ህዝብ ካላት ኢንዶኔዥያ በእጥፍ የሚልቅ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለናሙና ያህል ብቻ የዲባባ እህትማማቾች በኦሎምፒክ መድረክ ያገኟቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 22 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሶሪያ እና 28 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሳውዲ አረቢያ በድምር ከሰበሰቡት የሚበልጥም ነው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክ እና በዓለም አገር አቋራጭ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ የሰበሰበችው የወርቅ ሜዳልያ ብዛት 179 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ፓኪስታን እንኳን አላስመዘገበችውም፡፡
በዚህ ከፍተኛ ስኬት የኢትዮጵያ ክብር በዓለም አትሌቲክስ በወርቃማ ቀለም እንዲሰፍር ሆኗል፡፡ በቆጂን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ የሯጮች ምድርም  አድርጓታል።
የአትሌቶቹ ውጤታማነት ላይ በየጊዜው በአትሌቲክስ ባለሙያዎች ምርምሮች እየተደረጉባት ይገኛል፡፡  በመላው ዓለም በሚሰራጩ ትልልቅ ሚዲያዎች  በተደጋጋሚ የምትጠቀስ ከተማ መሆኗም ቀጥሏል፡፡ በየጊዜው ልዩ ዘጋቢ ፊልሞች ተሰርተውላታል፡፡  በተለያዩ ጊዜያት ስለሚወጡባት ታላላቅ አትሌቶቿ፤ ስለመልክዓምድሯ፤ ስለአየር ንብረቷ፤ ስለ አትሌቶች አኗናር፤ ስልጠና እና የእለት ተዕለት ህይወት በስፋት እየተወሳ ነው፡፡  
ጥሪ ከጋዜጠኛው
በ1ኛው «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» የጎዳና ሩጫ መነሻነት… በቆጂን በአትሌቲክስ ለማልማት
የታላላቅ  አትሌቶች መገኛ በሆነችው በቆጂ ከተማ  ለመጀመሪያ ጊዜ  የ5ነ ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» በሚል መርህ ከወር በፊት ተዘጋጅቶ ነበር። ከበቆጂ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ  በተካሄደው ውድድር ከአምስት ሺ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ የከተማዋ የሩጫ ባህል ሆኖ የ5ኪ ሜትር ውድድሩ በአትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን ተሳታፊው ህዝብም  ችግኝ ይዞ በመሮጥ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው ጭላሎ ሚዲያ ፕሮሞሽን በተባለ ድርጅት የተዘጋጀ ነው፡፣፡ ጭላሎ በበቆጂ ገዝፎ የሚታይ ልዩ ግርማ ሞገስ ያለው ተራራ ነው፡፡ የድርጅቱ ባለቤት   ጋዜጠኛ እና ገጣሚ አንዱዓለም ጌታቸው ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው በቆጂ ላይ ነው፡፡ ስለበቆጂ ልጆች አስተዳደግ እና የሩጫ ባህል ለስፖርት አድማስ ሲገልፅ‹‹ እንደማንኛውም የከተማዋ ተወላጅ ልጅነቴን ያሳለፍኩት በእረኝነት ነው ፡፡ ቤተሰብ  ሲልክህ ሮጥ ብለህ  ይባላል፡፡ ወደ ተላክበት የምትሮጠው ብዙ ርቀት ነው። ሽርካ የተባለች የገጠር ከተማ ወደ የሚኖሩ አያቶቼ ቤት ስላክ አስታውሳለሁ፡፡ 3 ሰዓታት ይወስድብኛል፡፡ አብዛኛውን እየሮጥኩ ነበር የምሸፍነው፡፡ ስለዚህ ሩጫ የልጅነት ህይወታችን አካል ነው፡፡ የከተማዋ ባህል ሆኖ አድገንበታል፡፡ …የሁሉ መነሻ  ከ25 ዓመታት በፊት የደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ፈርቀዳጅ ድል ማስመዝገቧ ነበር። ያኔ በቆጂ የነበረ ትውልድ በሙሉ ሯጭ መሆንን ተመኘ፡፡›› ብሏል።
አንዱዓለም እነ ቀነኒሳ፤ የዲባባ እህትማቾችና ሌሎችም ምርጥ አትሌቶች በተማሩበት ትምህርት ቤት ስለነበረው የሩጫ ትጋት እና ፍቅር ትውስታ አለው፡፡ በተለይ በእረፍት ሰዓት በተማሪዎች መካከል ይደረጉ የነበሩ ውድድሮች ናቸው። በቆጂ ዛሬም ድረስ ሩጫን  ባህሏ ያደረገች  ልዩ ከተማ ናት። በትምህርት ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ በከተማዋ ዙርያ ገብ በሚገኙ ጫካዎች፤ የተንጣለሉ መስኮች እና ጋራዎች ልምምድ እና ስልጠና የተለመዱ ትእይንቶች ናቸው፡፡
ጋዜጠኛ አንዷለም ምንም እንኳን ገና በታዳጊነቱ የሩጫ ህልም ቢኖረውም ብዙ አልገፋበትም፡፡ በከተማዋ ሚኒ ሚዲያዎች ግን ስለ በቆጂ ታላላቅ አትሌቶች ገድል በመዘገብ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ አድልቶ ነበር፡፡ በከተማዋ ከአትሌቲክስ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለማከናወን ሲተጋ  ቆይቷል፡፡ ‹‹ በቆጂ የስሟን ያህል ትኩረት አላገኘችም፡፡ በስፖርት መሰረተ ልማቶች እጅግ ኋላ ቀር ናት፡፡ ስለዚህም ይቆጨኛል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በገነነ የሯጮች ምድር  ሁለገብ ስታድዬም፤ የማሰልጠኛ ማዕከልና የመሮጫ ትራክ አለመኖሩ ተገቢ አይደለም፡፡ የዛሬ አስር ዓመት  የኢትዮጵያ አትሌቶች ሙዚዬም በከተማዋ ሊገነባ መሰረት ተጥሎ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ይህን ለመቀየር ነው የበኩሌን ጥረት ማድረግ የጀመርኩት፡፡›› በማለት የተነሳበትን ዓላማ ለስፖርት አድማስ አስረድቷል፡፡
ስለዚህም አንዷለም ጌታቸው ለከተማዋ ባደረበት ቁጭት የጎዳና ላይ ሩጫውን ለማዘጋጀት እንዲወስን አድርጎታል፡፡ ጭላሎ ሚዲያ የተባለ ድርጅቱን ካቋቋመ በኋላ በመጀመርያ ለ2009 የገና በዓል የአትሌቶች መንደር በሚል ልዩ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡ በቆጂ ማናት የሚለውን ጥያቄ መልስ ለመስጠት በተዘጋጀው በዚህ ልዩ ስነስርዓት እንደመዝናኛ የሙዚቃ ከንሰርት ከማዘጋጀቱም በላይ እነ ኃይሌ፤ ገዛሐኝ አበራ እና ሌሎች ትልልቅ አትሌቶች በክብር እንግድነት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ከዚህ ተመክሮው በኋላ እንዷለም የመጀመርያውን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በከተማዋ ሊያስተናግድ ችሏል። የአትሌቶች መገኛ የሆነች ታሪካዊ ከተማ እንዴት ስፖርተኛ ህዝቧን የሚያሳትፍ ውድድር አይኖራትም በሚል ቁጭት በቀረፀው ፕሮጀክት ነው፡፡«አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» በሚል መርህ በስኬት የተካሄደውን የጎዳና ላይ ሩጫ በየዓመቱ ለመቀጠል እንደሚፈልግ ያሳወቀው አንዷለም፤ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ታላላቅ አትሌቶች የተገኙባት በቆጂ ከተማ ተጎጂ መሆኗን ለዓለም ለማሳወቅ የሚያስችል ፈርቀዳጅ ሃሳብ በመሆኑ ውጤታማነቱን ያመለክታል ብሏል፡፡
አትሌቲክስ ስታድዬም በሚል ስያሜ ያልተሟላ መሰረተ ልማት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ትራክ የሌለው አጥር የለሌለው የበቆጂ ስታድዬም፡፡ በሌላ በኩል የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልም በተሟላ ግንባታና መሰረተ ልማት የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በትኩረት ተገንብተው የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸው ከባድ ቁጭት የሚፈጥርብኝ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የውጤት መውረድ እና የላቀ ብቃት ያላቸው አትሌቶች በተተኪነት የማፍራት እድል የተበላሸው ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ይመስለኛል፡፡›› በማለት አንዷለም ጌታቸው ለበቆጂ ከተማ የሚሰማውን ቁጭት ይገልፀዋል። በርግጥ የበቆጂ አትሌቶች ከስታድዬሙ እና ከማሰልጠኛ ማዕከሉ ይልቅ በተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሮችን መስራት ይመርጣሉ ግን የስፖርት መነሰረተ ልማቶች መገንባት አለባቸው፡፡

ጥሪ ከከንቲባው
ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ  አትሌቶችን ለማፍራት
 የበቆጂ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ተስፋዬ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት  1ኛው «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» የጎዳና ላይ ሩጫው የበቆጂን 80 ዓመት ከመዘከሩም በላይ ከውድድሩ ጎን ትልልቅ አጀንዳዎች በማንገብ በመከናወኑ አስደስቶናል ይላሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚደረግ ዘመቻን ለማፋፋም፤ በአትሌቲክስ እየተንሰራፋ የመጣውን የዶፒንግ ችግር ተመለከተ የግንዛቤ እና የማስተማርያ መድረክ ለመፍጠር እንዲሁም ዜግነታቸውን የሚቀይሩ አትሌቶች እየበዙ መምጣታቸውን ተቃውሞ ለውጥ ለመፍጠር የሚደረጉ  ጥረቶችን ያስተዋወቅንበት መድረክ ስለሆነ በማለትም ማስረጃቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በቆጂ የማትነጥፍ የአትሌቲክስ ስኬት ምንጭ ሆና እንድትቀጥልና ተከታዮችን ለማፍራት ታላላቅ አትሌቶች ያላቸው ምሳሌነት አስተዋፅኦ ቢኖረውም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡›› የሚሉት ከንቲባው ‹‹አትሌቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል ሰርተዋል ብሎ የከተማው መስተዳድርም ሆነ ህዝቡ አያምንም፡፡ ከተማዋ ጥሩ ስታድዬም፤ የልምምድ ማዕከል እንኳን የላትም፤ ይህ ደግሞ መቀየር አለበት ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በከተማው መስተዳድር፤ በወጣቶችና ስፖርት፤ በአትሌቲክስ ፌደሬሽንነና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የተከናወኑ ጅምር ተግባራት መኖራቸውን አያይዘው የጠቀሱት ከንቲባው በቆጂ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ስታድዬም እንዲሁም የልምምድ እና ማሰልጠኛ ማዕከል መገንባት ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡
‹‹ታላላቆቹ አትሌቶች በስፖርቱ ካገኙት ክብር እና አንፃር እንዲሁም በኢኮኖሚ ካላቸው አቅም ጋር ተያይዞ በቆጂ ላይ ብዙ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህን አስመልክቶ በየጊዜው ውይይት እያደረግን ቆይተናል፡፡ የአትሌቶችን ተግባራዊ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በከተማው አስተዳደር በኩል ለአትሌቶቹ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ሰርተናል፡፡ በአሰላ ከተማ የንግድ ማዕከል፤ ሆቴል የሰሩ አሉ፡፡ የከተማው መስተዳድር ከዚህ በፊት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ይሆናል በሚል መሬቶችን ለአትሌቶች ሰጥቶ ነበር፡፡ ታላላቆቹ አትሌቶች በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የምንሰራቸው የግንባታ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ግዜ ስጡን ብለው ስለነበር እንጅ። አትሌቶች ለእኛ አምባሳደሮቻችን ምልክቶቻችን ናቸው። የከተማው መስተዳድር አብሯቸው ለመስራት ይፈልጋል። እነሱም ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን፡፡›› ብለዋል የበቆጂ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ተስፋዬ፡፡
የከተማው መስተዳድር በተለያዩ ክለቦች፤ በግብረሰናይ ተቋማት የተያዙ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች እንደሚከታተል የከተማው ከንቲባ ተናግረው፤  የኦሮምያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሚያንቀሳቅሰው የበቆጂ ማሰልጠኛ ማዕከልም በመንግስት በጀት ተገንብቶ ከተለያዩ ስፍራዎች ተሰጥኦ ያላቸውን አትሌቶች በመመልመል በቂ ስልጠና በመስጠት እየሰራ መሆኑን፤ የብዙ ቀደምት አትሌቶች ዛሬም ቢሆን ዋና መገኛዎች ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው በዚያም ሰፊ ተግባር ለማከናወን እንቅስቃሴ አለ የሚሉት ከንቲባው በአጠቃላይ ግን በተሟላ ጥራት እና ብቃት እየሰራን ስላልሆንን ይህን በከፍተኛ ንቅናቄ ለመቀየር ትኩረት አድርገናል ብለዋል፡፡
ይቀጥላል

-------------------------------------------------
                          
                         የአፍሪካ ዋንጫን በቻይና ወይም በአሜሪካ የማዘጋጀት ሃሳብ ቀርቧል

      የ2023 የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድርን በቻይና፣ በአሜሪካ ወይም በኳታር ለማዘጋጀት እና ከአህጉሪቱ ውጭ የሚገኙ 3 አገራት ብሄራዊ ቡድኖችን በውድድሩ ለማሳተፍ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ በአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ስብሰባ ላይ መቅረቡ ተዘግቧል፡፡
ካፍ የአፍሪካ የአግር ኳስ ዋንጫን የገንዘብ አቅም ለማጠናከርና ውድድሩን የበለጠ ሳቢነት ያለው ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ባለፈው ማክሰኞ እና ረቡዕ በሞሮኮ ባካሄደው ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ ምክረ ሃሳብ፣ የ2023ን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያዘጋጁ ቻይናን፣ አሜሪካን ወይም ኳታርን የመጋበዝ አማራጭን ያቀረበ ነው፡፡ የገንዘብ አቅምን ማጠናከርንና የአፍሪካ ዋንጫን አለማቀፋዊ ማድረግን ግቡ ያደረገ ነው የተባለው ምክረ ሃሳቡ፣ በመገናኛ ብዙሃን በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ በበርካታ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡
ሃሳቡ በካፍ ተቀባይነት የማግኘቱ ዕድል ጠባብ መሆኑን የዘገበው ጋና ሶከር ኔት ድረገጽ፣ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ተራውን ለጊኒ ቀደም ብሎ መስጠቱንም አስታውሷል፡፡

Read 3066 times Last modified on Saturday, 22 July 2017 15:47
Administrator

Latest from Administrator