Saturday, 22 July 2017 15:42

ባለፈው አመት 12.9 ሚ. የአለማችን ህጻናት ምንም አይነት ክትባት አላገኙም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚገኙ 12.9 ሚሊዮን ህጻናት ምንም አይነት የክትባት አገልግሎት አለማግኘታቸውንና ይህም ክትባት ያላገኙ ህጻናትን ለከፉ በሽታዎች ያጋልጣል ተብሎ እንደሚሰጋ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣውና የ194 የአለማችን አገራትን የክትባት ሽፋን ደረጃ በሚያሳየው ሪፖርት እንዳለው በአመቱ ከአለማችን 10 ህጻናት አንዱ ምንም አይነት ክትባት ያላገኘ ሲሆን፣ በ8 የአለማችን አገራት ከሚገኙ ህጻናት በ2016 አመት የክትባት አገልግሎት ያገኙት ከግማሽ በታች ናቸው፡፡
አነስተኛ የህጻናት ክትባት አገልግሎት ካለባቸው የአለማችን አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የክትባት አገልግሎት መስፋፋት ለመቻሉ ፖሊዮን የመሳሰሉ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰቱ ሰበብ ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
ተጨማሪ 6.6 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናትም ዲቲፒ የተባለውን የክትባት አይነት ለመጀመሪያ ዙር ከወሰዱ በኋላ፣ ቀሪ ሁለት ዙር ክትባቶችን ሳያገኙ መቅረታቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ክትባት በአለማችን ተቅማጥንና ቲታነስን ጨምሮ በተለያዩ የበሽታ አይነቶች ሳቢያ በየአመቱ ሊከሰቱ ይችሉ የነበሩ 3 ሚሊዮን ያህል የህጻናት ሞቶች እንዳይከሰቱ እያደረገ ይገኛል ያለው ሪፖርቱ፣ ባለፉት 10 አመታት በአገራት መካከል ያለው የክትባት ሽፋን ልዩነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ በአለማቀፍ ደረጃ የተሟላ የጤና አገልግሎት አቅርቦትን ለማሟላት የተያዘውን የዘላቂ ልማት ዕቅድ ግብ ለማሳካት፣ በየአመቱ 371 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ መመደብ እንደሚያስፈልግ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
መንግስታት፣ ለጋሾችና በጎ አድራጊዎች በየአመቱ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ መድበው ከሰሩ እስከ 2030 ድረስ 97 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን በበሽታ ለህልፈተ ህይወት ከመዳረግ ሊያድኑ እንደሚችሉ የጠቆመው ድርጅቱ፣ ለአብዛኞቹ አገራት ይህን ያህል ገንዘብ መመደብ አዳጋች በመሆኑ ለጋሾች ድጋፋቸውን መስጠት እንደሚኖርባቸውም አመልክቷል፡፡

Read 1240 times