Saturday, 22 July 2017 15:46

ኢራናዊቷ የዘመናችን የሂሳብ ሊቅ በ40 አመቷ አረፈች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከዘመናችን የአለም ታላላቅ የሂሳብ ሊቃውንት አንዷ እንደሆነች የሚነገርላት እና የሂሳብ የኖቤል ሽልማት ተብሎ የሚታወቀውን የፊልድስ ሜዳል ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ የአለማችን ሴት የሆነቺው ኢራናዊቷ መሪየም ሚርዛካኒ በጡት ካንሰር ህመም በ40 አመቷ ማረፏ ተዘግቧል፡፡ ላለፉት ለአራት አመታት ያህል በጡት ካንሰር ስትሰቃይና ህክምናዋን ስትከታተል የቆየቺው ኢራናዊቷ የስታንፎርድ የሂሳብ ፕሮፌሰር መሪየም ሚርዛካኒ ባለፈው ቅዳሜ ለህልፈተ ህይወት መዳረጓን ሜይል ኤንድ ግሎብ ዘግቧል፡፡ መሪየም ሚርዛካኒ ኮምፕሌክስ ጂኦሜትሪ እና ዳይናሚክ ሲስተምስ በተባሉ ዘርፎች ባፈለቀቻቸው እጅግ ገራሚ ግኝቶቿ የሂሳብ የኖቤል ሽልማት ተብሎ የሚታወቀውንና በመስኩ የላቀ አስተወጽኦ ላበረከቱ ላላላቅ ተመራማሪዎችና መምህራን የሚሰጠውን የፊልድስ ሜዳል ሽልማት እ.ኤ.አ በ2014 ማግኘቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ መምህርት ሆና ስታገለግል መቆየቷንም አመልክቷል፡፡
በቴህራን በሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርሲቲ እና በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የተከታተለቺው መሪየም፣ የኢራን አለማቀፍ የሂሳብ ኦሎምፒያድ ሽልማት አሸናፊ ከመሆኗ በተጨማሪ የተለያዩ በርካታ አለማቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቷንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1938 times