Saturday, 22 July 2017 15:48

የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው መንገድ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

   ያ ስልጣኔ ቀድሞ የማለደ፤
የማይነቅዝ ግዙፍ ግብሩ፣ አዲስ ብርሃን የቀደደ
ያ-ባየር በረሀ የምታየውን ተዓምር፤
ባልተደነሰ ቴክኖሎጂ፤ የማይጠፋ ቅርስ ያኖረ፤
ያ የለሊበላን መቅደስ ፈልፋይ፤ የአክሱምን ሀውልት ጠራቢ፤
የጣናን ደብሮች ደባሪ፣ የፋሲልን ግንብ ገንቢ፡፡
 ያ ስልጣኔን ቀድም የማለደ፤
እውን አንተን ወለደ!?
የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ›› በዚህ ስሜት የተቃኘ፤ የኋሊት ያለውን ብርሃን፤ በጭጋጋማው ሕይወት ውስጥ ሆኖ ወደ ነገ የሚናፍቅ፤ ሀገራዊ ቅንዐት ያነገበ መጽሐፍ ነው። መንገድ አሣሽ፣ ህልም አርጋዥ፤ ጨለምተኝነትን፣ ዳተኝነትን የሚወቅስ ነው፡፡ በ188 ገፆች የተጠረዘ.፤ አልፎ አልፎ ሥዕላዊ መግጫዎች ያሉት፡፡
ፕሮፌሰሩ፤ ”ሀሳቡ ቢኖረኝም፤ ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርፅን ለማሳመር ባለሞያ ያስፈልገኛል፡፡” ብለው ስላመኑ፣ አንዱ ዓለም አባተን (የአፀደ ልጅ) አሰናጅ አድርገውታል፡፡ በእኔ አተያይ፤ ለሰዎች ሞያና ክህሎት ዋጋ ሰጥቶ፣ ”እገሌ ነው ያሰናዳልኝ” ማለትም ሰውየው እንደፃፉት የሚያስቡ ለመሆናቸው እማኝ ነው፡፡ ሰዎችን አሰርተው፣ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ የራሳቸውን ስም ያስጻፉ ሰዎችን አሥታውሳለሁ፡፡ ቅንነት ከዚህ ይጀምራል፡፡
የመጽሐፉ ዋና ጉዳይ ‹‹ጥራት ምርታማነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡… ይሁን እንጂ ይህ- ርዕሰ ጉዳይ በእኛ አዕምሮ ውስጥ ፈጥኖ ብቅ እንደሚለው ቀላል ያለ ሳይሆን ጥልቅና ሰፊ ፍልስፍና እንደሆነ ይነግሩናል-  ፕሮፌሰሩ፡፡ ጉዳዩም እንደ ሀገር ሊያለማንም ሊጎዳንም የሚችል ነው፡፡ እስቲ በጥቂቱ እንይ፡- ‹‹ስለ ጥራትና ምርታማነት ስንነጋገር፤ ስለምንምገበው ምግብና ስለምንጠጣው ውሃ፤ ስለምንለብሰው ልብስና ስለምንኖርበት ቤት ጭምር ማለታችን ነው፡፡ ስለምንሄድባቸው መንገዶችና ስለምናከናውናቸው ጉዳዮች ጭምር ማለታችን ነው፡፡ ስለምንናገረውና ስለምንሰማው ነገር፤ ስለምናስበውና ሀሣቡን ስለምንረዳበት ደረጃ ጭምር ማለታችን ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ፣ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍልና የትኛውንም ርዕስ ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ ከላይ የተንደረደርኩበት የዶክተር በድሉ ዋቅጅራን ግጥም ቅንዐት በበጎ መንገድ ቋጥረውታል፡፡ ቁጭት ውስጣቸው አለ፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ያወረሱን ክብር ወድቆ፣ ወደ ሀፍረትና ውርደት ተቀይሯል፣ ብለው ያዝናሉ፡፡ ገና ወደ መግቢያው ገፅ 4 ላይ፤ ከሃያ ዓመታት በፊት ዚምባብዌ ለስብሰባ ሄደው ሳለ ከኢትዮጵያ መምጣታቸውን ያወቁ ተሰብሳቢዎች ሁሉ በመደነቅ፣ “ከኢትዮጵያ አንተን የሚያህል ሰው ይመጣል ብለን አላሰብንም ነበር” ብላቸዋል፡፡ እንዲያውም አንዱ የግራ እጁን ትንሽ ጣት እያሣየ፣ ”ይቺን የሚያክል ሚጢጢ እንጂ እንደ አንተ ጎላ ያለ ሰው ይመጣል ብለን አላሰብንም›› እንዳሉዋቸው ይተርካሉ፡፡ ይህ የሆነው በረሀብ ምክንያት ነው፡፡ በዳቦ ልመና መታወቃችን የዚህ ሥልጣኔ አባቶች የወለዱን አያስመስለንም፤ይህ ብቻ አይደለም፤ የልመና መንፈስ ተጠናውቶናል  የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ ፊደል ቆጥሯል የተባለው እንኳ ‹‹ተደራጅተን አንድ ነገር እንሥራ!›› ሲባል፣ “ማን ይረዳናል?” ብሎ ፊቱን ወደ ረጂዎች  ያዞራል፤ በማለት ይቆጫሉ፡፡
ስለ ሰብአዊና ዴሞክራሲ መብቶች መከበር ያነሣሉ፡፡ ላደጉት ሀገራት የእነዚህ መብቶች መከበር ምን ያህል መሠረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምናልባትም ጀፈርሰን፤ “I have Sworn up on the altar of God eternal hostility against every form of tyranny over the mind of man!››  ያለው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ቁርጠኝነት እርሱ ውስጥ ባይኖር፤ ጓደኞቹ ባይጋሩት፤ አሜሪካ ይሄኔ ባለችበት ትረግጥ ነበር፡፡ ቁርጠኛ አመራርና፤ ቀና ልብ ላለው ወሳኝ ነው፤
ደራሲው፤ መነጋገርና መደራደር መማርን በተመለከተ ያስቀመጡት  ሀሳብ አለ፡፡ ያ የሚጀምረው ታዲያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ልጅ ቤተሰቦቹን አምሥት ነገር ቢጠይቅ፤ ወላጆች በዚያ ጉዳይ ላይ በመነጋገር፤ ሦስት አራት እያሉ የመነጋገርና የመደራደርን ሥርዐት ያዳብራሉ ባይ ናቸው፡፡ ይህ ድንቅ ሀሳብ ይመሥለኛል፡፡ አሁን የምንናፍቃቸው ነገሮች ሁሉ በአንድ ምሽት ከሰማይ ዱብ አይሉም፡፡ የነገይቱ ሀገር የምትሠራው ዛሬ በየድንኳናችን ባሉት ልጆቻችን ውስጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲም የሚያድገው፤ ከሥር ሲጀምር ነው፡፡… በሀሳብ ከመሞገት ይልቅ ስድብና ጠመንጃ የሚያሥነሳንም ያለመስልጠን ነው፡፡
ስለ ብልፅግና የሚመኙት ፕሮፌሰሩ፤ ዕድገትና ብልፅግና ሦስት እግር አለው ብለው ያምናሉ፡፡ መንግሥት፣ የግል ባለሀብቱና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፡፡ እነዚህ ሦስቱ ካልተመጋገቡ የትም አንደርስም ባይ ናቸው፡፡
በጥራት ውስጥ ብዙ መለኪያዎች እንዳሉ መጽሐፉ በዝርዝር በዐቢይና ንዑስ ርዕስ እየከፈለ ያስቀምጣል፡፡ ለምሳሌ ምድብ ሦስት ብለው፣ ‹‹አቅርቦት›› በሚል ንዑስ ርዕስ ባስቀመጡት ሥር፣ የመሰጠኝና የገረመኝ ሀሳብ አለ፡፡ አቅርቦት ሲባል በቁጥርና በአይነት እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ይላሉ ስለ አቅርቦት ገጠመኛቸው፡-
አንድ የውጭ ባለሀብት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ አንዱን ድርጅት የቆዳ ጃኬት ለመግዛት እንደሚፈልጉ ያሳውቁታል፡፡ ገዢውና አቅራቢውም በሚገባ ከተነጋገሩ በኋላ፣ገዢው  የቆዳውን ጥራት፤ የጃኬቱን የአሰፋፍ ሁኔታ ---- ሌሎች ጉዳዮች አይተው በጣም ስለወደዱት ድርጅቱን በዓመት ሰባ አምስት ሺህ ጃኬት እንዲያቀርብላቸው ይጠይቁታል፡፡ ይሁን እንጂ  አቅራቢው ድርጅት ይህንን ያህል ብዛት ያለው ጃኬት ማሟላት አይችልም ነበር፡፡ የተጠየቀውን ያህል ለማቅረብ ባለመቻሉም ስምምነቱ ፈረሰ፡፡ ይህ የአቅርቦት ችግር ይባላል፡፡ ታዲያ ለዚህ የፍላጎት መጠን መሟላት የምርቱ የፊትና የኋላ ቅብብሎሽ እንዲሁም በጋራ መሥራት (Clustering) መፍትሔ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ከታች ከገበሬው እስከ አምራቹና ሸማቹ የተሰናሰለ ቅንጅት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
የሲንጋፖሩን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኩዋን ዩ ጠቅሰው፤ “ምርታማነትን ለማሳደግ እያንዳንዱ ግለሰብ ለሚገኘው የሥራ ውጤት ወሳኝ ሚናና አስተዋፅኦ እንዳለው አውቆ ለራሱ ክብር እየሰጠ፤ ከሥራ ባልደረቦቹና አለቆቹ ጋር በሕብረት ለአንድ ዓላማ ለመሥራት አእምሮውን ሲቀይርና ሲያስተካክል ነው” ለሚለው ሀሳብ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡  
መጽሐፉ ውስጥ “የተመረጡ አብነቶች” በሚል ርዕስ ሥር፣ የእስያዊቷ ሲንጋፖርና የአፍሪካዊቷን ቦትሰዋና በማነፃፀር ያሰፈሩት ሀሳብ በእጅጉ መሣጭ፣ ጠቃሚ ነው፡፡ እውነትነቱ፤ በጊዜ፣ በቦታና፣ በተሞክሮ የተረጋገጠ ስለሆነ ወደ ሰዎች ልብ መግባቱና ማሣመኑ አያጠራጥርም፡፡ ከተሞክሯቸው መውሰድ የሚገባንን ወስደን፣ መጣል የሚገባንን እንጥላለን፡፡
ስለ ሲንጋፖር ሲነግሩን፤ ከአዲስ አበባ ብዙ የማትሰፋ፤ በምስራቅ እስያ የምትገኝና አምሥት ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ናት፡፡ ሰባ አራት በመቶ የሚሆኑት ሕዝቦቿ ከቻይና፤ አስራ ሦስት ከመቶ የሚሆኑት ከማሌዥያ፤ አሥራ ሦስት በመቶ የሚሆኑት የህንድ ዝርያ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህቺ ሀገር በ1965 እ.ኤ.አ ከማሌዥያ ስትለይ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 533 ዶላር ነበር፤ በ1981 የነፍስ ወከፍ ገቢ 11 ሺህ ዶላር ደረሰ፡፡ በ2001  አድጎ 37100 ዶላር ሆነ፡፡ ይህ የነፍስ ወከፍ ገቢ መሻሻል ደግሞ በእያንዳንዱ ሰው የመኖር ዕድሜ ላይ ለውጥ አመጣ፡፡ ቀድሞ 73 ዓመት የነበረው አማካይ የአንድ ሰው ዕድሜ ጣሪያ ወደ 78 ዓመት ከፍ አለ። ስለ ለውጡ እንዲህ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤ “በቅርብ ጊዜ ሲንጋፖር የደረሰችበትን ለውጥ ብንመለከት ደግሞ በ2009/10 የዓለም የመወዳደሪያ ልኬት (Global Competitiveness index) ባወጣቸው 12 የመወዳደሪያ መስፈርቶች ስሌት፤ ሲንጋፖር ከ133 ሀገሮች ውስጥ ከስዊዘርላንድና ከአሜሪካ በመከተል 3ኛ ለመሆን ችላለች፡፡ በሀገራችን ላይ በዚህ የውድድርና የምዘና ሥርዓት ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ133 ሀገራት ውስጥ 116ኛ ነበረች፡፡
ከዚያ ቀጥሎ ባለው የውድድር ዘመን ደግሞ ከቀድሞው በላቀ ሁኔታ እንደተገኘች ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። በ2010 ዓ.ም በተደረገው ውድድር፡- ስዊዘርላንድ 1ኛ፣ ስዊድን 2ኛ ስትሆን ሲንጋፖር 4ኛ የወጣችውን አሜሪካንን ቀድማ 3ኛ ሆናለች። ይህ የሥራ፣ የታታሪነትና የአንድነት ውጤት ነው። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በቅርብ ዓመታት ተቀይጠው በአንድነት ተዓምር ሲሰሩ፣ የሺህ ዓመታት አብሮ የመኖርና የባህል ዝንቅ ያለን እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እየተባላን፣ ድህነት ሲበላን እያየን ነው፡፡ እራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡
ለሲንጋፖር ዕድገት ገፊ ምክንያት ያሏቸው ደንበኛው የመጠየቁ ጉይ ነው፡፡ ደንበኛ ሁሌ ይጠየቃል፤ በዚህም ደንበኛው ገበያውን ይመራዋል። ሁለተኛው ገፊ ምክንያት ውድድር ነው፡፡ ውድድር ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ፣ ከፍ ባለ ጥራትና መልካም አገልግሎት፣ በፍጥነት በማቅረብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሦስተኛው ገፊ ምክንያት ለውጥ ነው። የለውጥ ባህሪ ፈጣንና ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ የሚተነበይና የሚገመት ሊሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ደንበኛ፣ ውድድርና ለውጥ የተባሉ ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች፣ ጥራትና ምርታማነትን ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰሩ ገፅ 79 ላይ የጠቀሷት ነገር ክፉኛ የምትከነክንና የምታብሰለስል ናት፡፡ ስለ ሲንጋፖር ዕድገት ከተረኩ በኋላ እንዲህ ይላሉ፡- “… በተሳሳተ ጎዳ ላይ የተጀመረ ጉዞ ፍፃሜው ከስህተት አረንቋ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ስለዚህ ‹ሰባቴ ለካ፣ አንዴ ቁረጥ› እንደሚባለው፣ ጉዞ ከመጀመር በፊት ቢያንስ መድረሻን አሻግሮና በደምሳሳውም ቢሆን ማየት ያስፈልጋል፡፡” ይህ ነገር እኛን በቀጥታ የሚመለከተን ይመስላል፡፡ አሁን ባለው አካሄዳችን ላይ ልናቃናቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች አሉና!
በመጽሐፉ ውስጥ አፍሪካዊቷ ቦትስዋናም፤ የሲንጋፖር አይነት ጅማሬና ህልም ነበራት፡፡ ቦትስዋና ከሲንጋፖር ይልቅ የአልማዝ ክምችት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን የተፈጥሮ ሀብቱን አላቂነት በመረዳት፣ ከዚህ ማዕድን ውጭ በሆኑ ምርቶች ላይ በጥራትና ምርታነት ላይ መስራት እንደሚገባት ወስና ነበር፡፡ ለዚህ ውሳኔዋም ትምህርት ለመቅሰም ከሲንጋፖር ጋር ሰንሰለት አበጀች፡፡ ይህን ያደረገችውም የህዝቧን የስራ ባህል በተሻለ ሁኔታ ለማሻሻልና ለመቃኘት ነበር፡፡ የቦትስዋና አንዱና ዋናው ችግር የስራ ሰዓት ያለማክበር ነበር፡፡ እናም የሀገሪቱ መንግስት “Botswana National Productivity Center” አቋቋመ፡፡ በዚህም ዓላማ በመታገዝ የጥራትን ፍልስፍና በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽና ወደ ተግባር እንዲለወጥ ለማድረግ ተንቀሳቀሰች፡፡
በየሴክተሩ ውስጥ ጥራት ሲኖር ምርታማነት ከፍ እንደሚልና የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬታማ እንደሚሆን በማሰብ ጉዞው ተጀመረ፡፡ ከጉዞው በፊትም ሕዝቡ የንቅናቄው አካል እንዲሆን የማሳወቅ ሥራ ተሰራ። የቦትስዋና መንግሥት የምርታማነት ማዕከል፣ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ሲሆን መንግሥቱ ደግሞ አምስት አምዶች ነበሩት፡፡ እነዚህም፡-
ዴሞክራሲ
ልማት
ክብር
ሥነ ምግባር
አቅርቦት
የምርታማነት ማዕከሉ እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር ነበረው፡፡ ይህም ቡድን ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንዲሰራ የታለመ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል፣ ለዘመናት የቆየውና ሥር የሰደደው ሰዓት ያለ ማክበር ጉዳይ በቀላሉ ሊላቀቃቸው አልቻለም። ለአንድ ደንበኛው ወይም ወዳጁ ቀጠሮ የያዘ ሰው፤ አንድ ሰዓት አርፍዶ ከተገኘ ፈጣን ነው እስኪባል ዘለቀ፡፡ ስንፍና አለ። ፕሮፌሰሩ ለዚህ ዋቢ አድርገው የጠቀሱት አንድ የታክሲ ሾፌር ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ጋቦሮኒ ሄደው ሳለ የተዘጋጀላቸው ታክሲ፤ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ዘግይቶ ነበር የመጣው - ለዚያውም ተደውሎለት፤ “መጣሁ” ካለ በኋላ፡፡ በታክሲው ሾፌር ጉዳይ የሚደንቀው ማርፈዱ ብቻ አልነበረም። ይልቅስ አንዳችም ጥፋት የሰራ መስሎ ያለመታየቱ ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ ዋነኛ የሚያተኩሩበት ለውጥ አለ - “የልቡና ውቅር ለውጥ!” (Paradigm shift) በርሳቸው አባባል፤ ይህ የልቡና ውቅር ማለት፣ የአንድ ሰው የአስተሳሰቡ ሚዛንና የግንዛቤው ልክ ማለት ነው፡፡ ለዚህም የሰጡት ምሳሌ ለልባችን ቅርብ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ይላሉ “አንድ ሰው ቢያንሸራትተውና ቢወድቅ አንዱ “ዘራፍ” ሲል፣ ሌላኛዋ “እናቴ ድረሽ” ልትል ትችላለች፡፡ ይህ ነው የልቡና ውቅር! … የታነፀበት፣ የተሰራበት የማህበረሰብ መልኮች ማለታቸው ይመስለኛል፡፡
ስለ ጥራት ሲያነሱ ብዙ ጊዜ በሀገራችን ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ፕሬስ የአይኤስኦ የጥራት ተሸላሚ እያሉ የሚያስነግሩትን ማስታወቂያ ጉዳይ ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ ይህ የምስክር ወረቀት የልቀት አይደለም። ይልቅስ አንድ የቢራ ፋብሪካ መጀመሪያ ያመረታት ጠርሙስ ቢራና አንድ ሺህኛዋ ጠርሙስ ቢራ አንድ ዓይነት ጠርሙሶች፣ አንድ ዓይነተ የቢራ የልኬት መጠን፣ አንድ ዓይነት ጣዕም አላቸው ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉ፤ በብዙ ማስረጃና ምሳሌ፣ ሀገራዊ ሥነ - ልቡናና ባህልን እያዛመደ፣ አንዳች ቁጭትና የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጅማሬው ላይ ያለው ጭርታና አጋዥ ሪፈረንሶች ያለመኖር አንባቢን ወደ ኋላ የሚገፋ ይመስለኛል፡፡ ወደ መሀል ሲመጣ ነው እንደ ቀትር ፀሐይ እየጨመረ የሚሄደው፡፡
የኢንዱስትሪያል መሀንዲስ የሆኑት ፕሮፌሰሩ፤ ቀናነትና የሀገር ፍቅርም ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላው ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ወይ ተስፋ ቆርጠዋል፤ አሊያም ቸል ብለዋል፡፡  ትንሽ ቢስተካከሉ ጥሩ ነበር የምለው፤ አንዳንድ ቦታ ያሉትን የስም ብዜቶች ነው፤ ለምሳሌ ገፅ 7 “እጸዋቶች” የሚለው “እፀዋት” ቢሆን፣ ገፅ 112 ላይ ያለው መዋዕለ ህፃናት “ሙአለ ህፃናት” በሚል ቢተካ ደግ ነበር፡፡ ስብዕና የሚሉትም “ሰብ” በሚለው - “ሰብዕና” ቢባሉ ትክክለኛ ትርጉማቸውን ያገኛሉ፤ በተረፈ የሀሳብ አፈሳሰሱ፣ የአጻጻፍ ለዛውም ጥሩ ነው፡፡
ነገሮች ከላይ ጀምረው መሬት በመውረድ አሁን ያለንበትን የሥነ ምግባር መውደቅ በምሳሌ መቆንጠጣቸው ደስ ይላል፡፡ ችግሮቻችንን እንድናውቅና አውቀን መንገዳችንን እንድናቀና ይረዳናል፡፡ እንዲህ ለሀገር የሚቆረቆሩ፣ ህመምዋ  የሚያማቸው ምሁራን ቢበዙና ቢያካፍሉን፣ ከችግሮቻችን ጥቂቱን እንኳን ቢሆን እንቀርፋለን ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 1337 times