Saturday, 29 July 2017 11:30

የአዲስ አድማስ ማሳሰቢያ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

    ያለወትሮአችን ማሳሰቢያ ለመፃፍ የተገደድነው አንዲት ስማችን የተጠቀሰባት ሃሰተኛ (‹ፎርጂድ› የበለጠ ይገልፀዋል) ደብዳቤ ሰሞኑን ዝግጅት ክፍላችን በመድረሷ ነው፡፡ ደብዳቤዋ የታለመችው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ነው፡፡ ‹‹ስፖንሰር አድርጉን›› ትላለች፡፡ መታለም ብቻ ሳይሆን ለፋብሪካውም ደርሳለች፡፡ ‹‹አፍሪካ ፖስት ሚዲያ ሴንተር›› በሚል ማህተም የተከተበችው ይህች ‹‹ጉደኛ›› ደብዳቤ፤ በአጭሩ ‹‹አዲስ አድማስ ጋዜጣ የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ከአፍሪካ ፖስት ሚዲያ ሴንተር ጋር በመተባበር፣ በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ በታላቅ ድምቀት ይከበራል›› በሚል መግቢያ ትጀምራለች፡፡ (ልብ በሉ! ‹‹አዲስ አድማስ›› 15ኛ ዓመቱን የዛሬ ሁለት ዓመት በብሔራዊ ቴአትር ‹‹በታላቅ ድምቀት›› አክብሯል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ የ15ኛ ዓመት በዓላችንን እንዳከበርን ያላወቁት ወይም ያልሰሙት እነዚህ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቀ ‹‹ ቁጭ በሉዎች››፤ (‹‹ሿሿ›› ነው የሚሏቸው?!) ዝግጅቱን በርካታ ድርጅቶች ስፖንሰር እንዳደረጉ ይጠቅሱና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራም በዓይነትም በገንዘብም ስፖንሰር እንዲያደርጋቸው ይጠይቃሉ፡፡ (የአዲስ አድማስን 15ኛ ዓመት በዓል ማለት ነው፡፡) በርግጥ የቢራውም ሆነ የገንዘቡ መጠን አልተጠቀሰም በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ቢራ ፋብሪካው ስፖንሰር ሲያደርግ የሚያገኘውን ጥቅማ ጥቅም ይገልፃሉ- ‹‹ድርጅታችሁን በሚታተመው ተከታታይ ሳምታዊ የጋዜጣ ዕትም ላይ በብዙ ብር ከፍለው ስፖንሰር ካደረጉን ድርጅቶች እኩል የምናስተዋውቅ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን” በማለት፡፡
በነገራችሁ ላይ በዚህ የጋዜጣችንን ስም ለማጭበርበርያነት ጠቅሰው በፃፉት ደብዳቤ ላይ እውነተኛ ወይም ትክክለኛ የሚመስል ነገር አለ ከተባለ፣ ፅሁፉ የሰፈረበት ነጭ ወረቀት ብቻ ነው፡፡ በደብዳቤው ላይ የሰፈሩት ሁለት ስልክ ቁጥሮች ጨርሶ አይሰሩም። ‹‹አፍሪካ ፖስት ሚዲያ ሴንተር›› የሚባል ድርጅት በተጨባጭ መኖሩን ለማረጋገጥም አልቻልንም (ሊኖር እንደማይችል ገምቱ!)፡፡
በመጨረሻም፤ ለውድ የአዲስ አድማስ ቤተሰቦች፣ አንባቢያን፣ ድርጅቶች፣ የመንግስት ተቋማትና ሌሎችም ልንገልፅ የምንወደው፣ የአዲስ አድማስ ህጋዊ ማህተም፣ ሎጎ፣ በቂ አድራሻዎች … ወዘተ በቅጡ ሳትመለከቱ (ሳታጣሩ) ለደብዳቤዎች ጥያቄ ምላሽ እንዳትሰጡ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኞችም ሆኑ ተወካዮች የድርጅቱ መታወቂያ እንዳላቸው እግረመንገዳችንን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡ ራሳችንን እንጠብቅ!!

Read 6517 times