Sunday, 30 July 2017 00:00

“ሰማያዊ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ፣ሰላማዊ ሰልፍ እጠራለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

አዋጁ ለተጨማሪ ጊዜያት እንዳይራዘም ፓርቲው ጠይቋል

ከታወጀ 10 ወር ገደማ ያስቆጠረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከ5 ቀን በኋላ ይነሳ ይቀጥል የሚታወቅ ሲሆን  ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ፣ ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ሰሞኑን ባወጣው ወቅታዊ የአቋም መግለጫው፤አስር ወራትን ያስቆጠረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማብቂያው ጊዜ ከ5 ቀን በኋላ፣ መሆኑን በመጠቆም፣ አዋጁ ለተጨማሪ ጊዜያት እንዳይራዘም መንግስትን ጠይቋል፡፡
አዋጁ ተጥሎ በቆየባቸው ጊዜያት፤ “የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የጣሰ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ያጠበበ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል ያደረገና የህዝብን ማህበራዊ መስተጋብሮች የገታ ነበር” ያለው ሰማያዊ፤ “መንግስት ሀገሪቱን አረጋግቻለሁ ስላለ አዋጁን ማራዘም አያስፈልግም፤ ሊነሳ ይገባዋል” ብሏል፡፡
በቅርቡ በሚኒስትሮች ም/ቤት ተወስኖ፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቀረበው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ህዝብ ሳይመክርበት መውጣቱን ፓርቲው ተችቷል፡፡ የግብር አጣጣል ስርዓቱም የዜጎችን ገቢ ያገናዘበ እንዲሆን የጠየቀው ፓርቲው፤ በአጠቃላይ ህዝቡ በአግባቡ ሳይመክርባቸው እየወጡ ያሉ አዋጆች፣ በዜጎች ላይ መደናገጥ እየፈጠሩ በመሆኑ ሊታረሙ  ይገባል ሲል አሳስቧል።
“ሰማያዊ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊነሳ ይችላል በሚል መተማመን፣ ሐምሌ 30፣ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የመብራት ሃይል አዳራሽ፣ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲሁም ነሐሴ 7፣ መነሻውን ሚኒልክ አደባባይ፣መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገ፣ ሰላማዊ ሠልፍ ለመጥራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የስብሰባውም ሆነ የሰልፉ አጀንዳዎች፣ በዋናነት እየወጡ ባሉ አዋጆች ላይ እንደሚያተኩር ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ አካሉ፤ሰልፉም ሆነ ስብሰባው የታቀደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሣ ይችላል በሚል ግምት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡




Read 5161 times