Sunday, 30 July 2017 00:00

የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮችና ቤተ እስራኤላውያን የትውልደ - ኢትዮጵያዊ መብት እንዲያገኙ ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በመላው ዓለም ከ1 ሚሊዮን በላይ ራስ ተፈሪያውያን አሉ
· አስተዋፅኦ ያበረከቱ የውጭ ሀገር ዜጎችም የመብቱ ተጠቃሚ ናቸው
    ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የውጭ ሀገር ዜጎች፤ ቤተ እስራኤላውያንና የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች፤ የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ እንዲያገኙ ተወሰነ፡፡
እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ እንዲያገኙ መወሰኑ፣ ከዚህ ቀደም ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚመልስና ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ በህግ ያለውን መብቶች የሚያጎናፅፏቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም አስታውቀዋል፡፡
መመሪያው የወጣው ከዚህ ቀደም ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመሆን መመሪያውን ማውጣታቸው ታውቋል፡፡
በዚህ መመሪያ የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ የሚሰጣቸው የውጭ ሀገር ዜጎች እንደእነ ሪቻርድ ፓንክረስት ቤተሰቦች፣ ታዋቂው የስነ ጥበብና የሚዲያ ሰው ፕ/ር አብይ ፎርድ እና ሌሎች በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን አቶ መለስ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡
እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች የትውልደ ኢትዮጵያዊነት መታወቂያ እንዲሰጣቸው መደረጉ የኢትዮጵያን ገፅታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመገንባት ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና የሚሰጥና ከኢትዮጵያ ጋር በፈጠሩት ቁርኝት፣ ለሀገሪቱ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ተወልደው ከቆዩ በኋላ ወደ እስራኤል የተመለሱ ከ150 ሺህ በላይ ቤተ እስራኤላውያንም በእስራኤልና በኢትዮጵያ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ በመሆናቸው፣ የትውልደ - ኢትዮጵያዊነት መታወቂያውን እንዲገኙ ተደርጓል፡፡
ለረጅም ዘመናት የትውልደ ኢትዮጵያዊነቱ ክብር እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ የነበሩት የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች፣ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በየአደባባዩ ሲገልፁ የነበሩና በመላው ዓለም ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቁ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡
አስቀድሞም ራሳቸውን የኢትዮጵያ አካል አድርገው የሚቆጥሩት ራስ ተፊሪያውያን፤ በመላው ዓለም ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዮን እንደሚልቅ የሚጠቁሙ መረጃዎች የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች ጃማይካውያን ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የአውሮፓና አፍሪካ እንዲሁም የካሪቢያን ሀገራት ዜጎች እንደሆኑም ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ሃገር ዜጎች የትውልድ ኢትዮጵያዊነት መታወቂያ በመያዛቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባትና ለሃገሪቱ ለመቆየት ከእንግዲህ የመግቢያ ቪዛና የመኖሪያ ፍቃድ አይጠየቁም፤ ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያ የተጎናፀፈው መብት ሁሉ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
ኢንቨስትመትን ላይ ለመሠማራት ሲፈልጉም እንደ ሃገር ውስጥ ባለሃብት ተቆጥረው እንዲስተናገዱ ይደረጋል፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ለመጠቀም በውጭ ሃገር ዜጎች ላይ የተጣሉ ገደቦች አይመለከታቸውም ተብሏል፡፡
ይህ ሁሉ መብት ቢሰጣቸውም የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም በአገር መከላከያ፣ የአገር ደህንነትና የውጭ ጉዳይ መሠል የፖለቲካ፣ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በመደበኛነት ተቀጥረው መስራት እንደማይችሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡  ለእነዚህ ዜጎች ይህ እድል መከፈቱ ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ፍቅር የበለጠ የሚያሣድግና በሃገሪቱ ገፅታ ግንባታ ላይ በጎ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያበረታታ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፡፡
በተለይ ለራስ ተፈሪያውያን የተሠጠው እድል የባህል አምባሣደር ሆነው እንዲያገለግሉ ከማስቻሉም ባለፈ የፓን አፍሪካዊ አስተሳሰብን ያጠናክራል ተብሏል፡፡


Read 5892 times