Sunday, 30 July 2017 00:00

ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በአምባሳደርነት ተሾሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(33 votes)

· የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የአ.አ.ዩ ፕሬዚዳንት፣ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ይገኙበታል ----
· በቻይና፣ በአሜሪካ፣በአውሮፓ ፓርላማ --ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሊተኩ ይችላሉ

ከ97 ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን፣ በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት ፕ/ር መርጋ በቃናን ጨምሮ፣የታወቁ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ሰሞኑን በአምባሳደርነት የተሾሙ ሲሆን ለየትኞቹ አገራት እንደተሾሙና ማንን እንደሚተኩ የታወቀ ነገር የለም፡፡  
ባለፈው ረቡዕ  11 የሚደርሱ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች የሙሉ አምባሳደርነት ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን የቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ እውነቱ ብላታ፣  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት  በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡
የፌደራልና  አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ፣ የመልካም አስተዳደርና ክላስተር አስተባባሪ የነበሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም፣ የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱለማን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፣ አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ አምባሳደር ተበጀ በርሄ፣ አቶ መታሰቢያ ታደሰ፣ አቶ ሙሉጌታ ዘውዴና ወ/ሮ ሉሊት ዘውዴ ደግሞ፤በፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ በሙሉ አምባሳደርነት ማዕረግ ተሹመዋል፡፡
የአምባሳደርነት ሹመቱ በሥራ ላይ ያሉ ሚኒስትሮችንና በከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናትን ማካተቱ የተለየ ምክንያት ይኖረው እንደሆነው ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ “የተለየ ነገር የለውም፤የተለመደ የሥራ የቦታ ልውውጥ አድርጎ መወሰድ ይገባል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፤በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ በአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ በርካታ አምባሳደሮች የሥራ ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ቃል አቀባዩ፤ “የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ አምባሳደሮች ማንነት የሚታወቀው ጊዜው ሲደርስ ነው” በማለት ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡   




Read 9409 times