Sunday, 30 July 2017 00:00

የሙስና ተጠርጣሪ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች፣ መንግስትን ከ1.15 ቢ.ብር በላይ አሳጥተዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(53 votes)

• የተያዙት ተጠርጣሪዎች ቁጥር 39 ደርሷል
• የአ.አ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በርካታ የስኳር
• ኮርሬሽን ሃላፊዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል
• መንግስት ተጨማሪ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ማደን መቀጠሉን አስታውቋል

መንግስትንና አገርን ከ1.15 ቢሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ሰሞኑን  ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ከተጠርጣሪዎቹ  መካከል ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ቁጥር 39 ደርሷል ተብሏል፡፡
በዋናነት የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችንና ነጋዴዎችን በሙስና ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባለፈው ማክሰኞ ያስታወቀው መንግሥት፤ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን የማደን ስራ  መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡  
ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች  መካከል የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ኢ/ር ፍቃደ ኃይሌን ጨምሮ፣ ኢንጂነር ዋሲሁን ሽፈራው፣ ኢንጂነር አህመድ ቡሴር፣ የትህዳር ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሚናሽ ሌቪ የሚገኙበት ሲሆን ከፖሊስ የክስ መዝገብ መረዳት እንደተቻለው፤በዋናነት የተጠረጠሩበትም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሃ ልማት ድረስ ያለውን መንገድ ሲሰሩ መመሪያና ህግን ባልተከተለ ውል፣ ከትህዳር ኮንስትራክሽን ጋር በመመሳጠር፣ 198 ሚ. 872 ሺ 730 ብር ከ11 ሳንቲም መንግስትን አሳጥተዋል በሚል ነው፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፡- አቶ አብዶ መሃመድ፣ አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ገላሶ ቡሬ፣ አቶ የኔነህ አሰፋ፣ አቶ አሰፋ ባራኪ፣ አቶ ገብረ አናኒያ ፃዲቅና አቶ በቀለ ባልቻ ሲሆኑ የተጠረጠሩበትም፣ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ሆነው፣ በኮምቦልቻ፣ ሃረርና ጅግጅጋ እንዲሁም ጋምቤላ ጎሬ በተሰሩ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ባልተገባ የዲዛይን ጥናቶችና የግንባታ ኮንትራት ውል፣ ፕሮጀክቱን በማዘግየት፣ 646 ሚ. 980 ሺ 626 ብር ከ61 ሳንቲም ጉዳት አደርሰዋል በሚል ነው፡፡
ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከስኳር ፋብሪካዎች ጋር በተገናኘ የኮርፖሬሽኑን ሁለት የሥራ ሃላፊዎች ጨምሮ የመተሃራ፣ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 እና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች የተለያዩ የሥራ ሃላፊዎች ተጠርጣሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ የፋብሪካው የአገዳ ተከላ፣ ም/ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጠቅላላ ሂሳብ ያዥ አቶ ቢልልኝ ጣሠው፣ ከአንድ ስሙ ካልተጠቀሰ ኩባንያ ጋር በመመሳጠር፣ 31 ሚ. 379 ሺ 985 ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረዋል፡፡
በሌላ መዝገብ፤ እነዚሁ የሥራ ኃላፊዎች፣ አቶ የማነ ግርማይ ለተባሉና በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር ውለው ፍ/ቤት ለቀረቡት ግለሰብ፣ ያለ አግባብ 20 ሚ. ብር ክፍያ እንዲፈፀም በማድረግ ተጠርጥረዋል። በሌላ ሶስተኛ መዝገብ.፤አቶ አበበ ተስፋዬ፣ ከአቶ የማነ ግርማይና አቶ ኤፍሬም አለማየሁ ጋር ያለ ጨረታ የስራ ውል በመስጠት፣ ከ216 ሚ. ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል፡፡
ከመተሃራ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ፣ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣ ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ፣ አቶ አየለው ከበደ በፋብሪካው የግዥ ቡድን መሪ ሆነው ሲሰሩ፣ 13 ሚ. 104 ሺህ ብር ለአቅራቢዎች ያለ አግባብ በመክፈል፣ እንዲሁም የፋይናንስ ኃላፊው አቶ በለጠ ዘለለው፣ ለመሳሪያ እድሳት በሚል 1 ሚ. 164 ሺ ብር ክፍያ ያለ አግባብ በመፈፀም መጠርጠራቸውን ከፖሊስ መዝገብ መረዳት ተችሏል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ፋብሪካ፣ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መልካሙ፣ የቻይናው “ጄጄ አይኢሲ” ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጂ ዩአን፣ ወ/ሮ ሳሌም ከበደ፣ አቶ ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔርና አቶ ፍሬው ብርሃኔ ያለ አግባብ ውል በመስጠት፣ 184 ሚ. 408 ሺህ ብር ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸው ታውቋል፡፡  ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕሮጀክት ም/ስራ አሥኪያጅ አቶ ሙሳ መሃመድን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሰሩት አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ አቶ ታምራት አማረ፣ አቶ ሰም ጎበና፣ አቶ አክሎግ ደምሴ፣ አቶ ጌታቸው ነገራ እንዲሁም የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ ያልሆኑት ዶ/ር ወርቁ አለሙ፣ አቶ ዮናስ መርአዊና አቶ ታጠቅ ደባልቄ፣ ህጋዊ የጨረታ አካሄድን ሳይከተሉ በመስራት፣ መንግስትን 2.2 ሚ.  ዶላር በማሳጣት ተጠርጥረዋል፡፡
በአጠቃላይ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከ1.15ቢሊዮን ብር በላይ መንግስትን በማሳጣታቸው፣ በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ለፍ/ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ፤አሰባስቤ ያልጨረስኩት ሰነድና ማስረጃ አለ፤ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ ማስረጃዎችን ሊያሸሹ ይችላሉ ሲል፣ የ14 ቀን የምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆ  ፍ/ቤቱ  ዋስትናውን ሳይፈቅድ፣የፖሊስን ጥያቄ በመቀበል፣ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    


Read 10110 times