Print this page
Saturday, 29 July 2017 11:40

ታሪክ፣ የታሪክ ሽሚያ፣ ብሄርተኝነትና የዘመኑ ፖለቲካ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክና የታሪክ ሽሚያ እንዲሁም አዲስ አበባን ማዕከል አድርገው በሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ ለታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ቴዎድሮስ
ኃ/ማርያም የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በኢ-ሜይል ላቀረበላቸው ጥያቄ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እነሆ፡-

• በሀገራችን የምናየው ታሪክን የፖለቲካ ደንገጡር ለማድረግ የሚካሄድ ፍልሚያ ነው
• በ1960ዎቹ የተቀሰቀሰው የዘመናዊነት መንፈስ፣ የማይጠገን የታሪክ ውልቃት አስከትሏል
• ብሄርተኝነት ዘመን አመጣሽና ግለኛ ፖለቲካ ነው፤ገና አልበሰለም ፣ ግልብ ነው
• ዛሬም ድረስ ታሪክን ከመንግሥት ጥላ ሙሉ በሙሉ ማላቀቅ አልተቻለም

  በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀደምት የምድሪቱ ህዝቦች ተብለው በታሪክ የሚጠቀሱት የትኞቹ ናቸው? አሰፋፈራቸውስ ምን ይመስል ነበር?
በመጀመሪያ ይህ ማን ቀደመ፣ ማን ተከተለ የሚለው ጥያቄ በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል። ታሪካዊ መቼት ካላስያዝነው በስተቀር ባላገሩንና ሰፋሪውን ለመለየት አንችልም፡፡ ኢትዮጵያ ኦና ምድር ሆና ለመጀመሪያ ጊዜ የሰፈረባት ህዝብ ወይም ህዝቦች ማንነትን ማወቅ አይቻልም፡፡
ታሪክ በተለያየ መልክ ቅንጣት መረጃዎች መተው ከጀመረበት ዘመን፣ ከሁለትና ሶስት ሺህ ዓመታት ወዲህ እንኳን ዛሬ ኢትዮጵያ በምንላት መልክአ ምድር የሰፈሩ ህዝቦች እገሌና እገሌ ነበሩ ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ህዝብ ሃውልት አይደለም፡፡ በታሪክ ሂደት ይስፋፋል፣ ይከፋፈላል፣ ይቀየጣል፡፡ አልፎ ተርፎም አሰፋፈሩን፣ ማንነቱን (እምነቱን፣ ስሙን፣ ባህሉን፣ ወዘተ) ይለውጣል፡፡ ስለዚህም ታሪካችንን ዛሬ በምናውቃቸው ህዝቦች ዓይን ብቻ የምንመለከት ከሆነ እጅግ ርቀን አንሄድም፡፡
ለምሳሌ በዘመነ አክሱም እስከ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ፣ የአዱሊስ የድንጋይ ፅሁፍ ድረስ በግዛተ መንግሥቱ ሥር ስለነበሩት ህዝቦች ታሪካዊ መረጃ የለንም፡፡ ጥቂት ተጨማሪ ፍንጭ የምናገኘው  ከአንድ ምዕተ ዓመት ገደማ በኋላ ሲሆን፤ በነዚህ ፅሁፎች ውስጥ በኋለኛው ዘመን ለይተን የምናውቃቸው አገው፣ ባሪያ፣ ቤጃ ከሚሉት በስተቀር ሌሎችን አናገኝም፡፡ ስለ ጥንታዊት ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው፣ አክሱማውያን ቢያንስ ከዘመነ ኤዛና አንስቶ ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ብለው መጥራታቸውንና፤ በኋላም እነዚህ ህዝቦች በባዕዳን ‹‹ሀበሾች›› ተብለው መጠራት መጀመራቸውን ነው። ጥቂት ብርሃን የምናገኘው ከዘመነ ዛጉዌ  ጀምሮ ሲሆን፤ ከዚህ ወቅት ጀምሮ አንዳንድ ህዝቦችን ለምሳሌ ትግሬዎችን፣ አማሮችን፣ ጉራጌዎችን፣ ጋፋቶችን፣ አርጎቤዎችን፣ አደሬዎችን፣ አዳሎችን፣ ሲዳማዎችን፣ ሀድያዎችን፣ ወዘተ በሀገሪቱ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ መስማት እንጀምራለን፡፡ የነዚህም ህዝቦች አሰፋፈር በትክክል ከዚህ እስከዚህ ነበር ብለን ለመናገር አንችልም፡፡
የመካከለኛው ኢትዮጵያ ታሪክ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ህዝቦች በአካባቢዎቹ ይኖሩ ነበር? ቀደምት ሊባሉ የሚችሉ ህዝቦችስ የትኞቹ ናቸው? ዛሬ አዲስ አበባ ብለን የምንጠራው አካባቢ የየትኞቹ ህዝቦች ታሪክ ነው የነበረው? በተለይ ከሸዋ ነገስታት በፊት የነበሩ ታሪኮች ምን ይመስላሉ? ከ4ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ የሚጠቀሱ ታሪካዊ ማስረጃዎች ሲቀርቡ ይታያል… ይሄን እርሶ እንዴት ይመለከቱታል?
ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ታደሰ  ታምራት እንደጻፉት፣ በተለይ ከሰለሞናዊው አልጋ መመለስ በኋላ ዜና መዋዕላቸው ለትውልድ የተረፈልን ነገሥታት፡- አምደ ፅዮን (1314 – 44 እ.ኤ.አ)፣ ይሰሃቅ (1414 – 30)፣ ዘርዓ ያዕቆብ (1434 – 68)፣ ከነሱም በኋላ እስከ ዘመነ ጎንደር ድረስ በየገድሉ፣ በየመዛግብቱ ስማቸው የተዘረዘረው በርካታ ህዝቦች አብዛኞቹ በአግባቡ አልተጠኑም፣ ማንነታቸውም በትክክል አይታወቅም፡፡ በየመፃህፍቱና ሰነዶች የተጠቀሱት ስሞች ዛሬ በምንረዳው መልኩ የብሄረሰቦች መለያ አልነበሩም። በመካከለኛው ዘመን የተንሰራፋው የመሬት ከበርቴ ስርዓት አስተዳደራዊ መዋቅር ከዘውግ ይልቅ ታሪክና መልክአ ምድር በረዥም ሂደት የፈጠራቸውን አውራጃዊ ግዛቶች የተመረኮዘ ነበር፡፡ ስለዚህም አማራ የሚለው ግዛት በመካከለኛው ዘመን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከጎንደር እስከ ጎባና ጅማ፣ እዚህም እዚያም ሰፍረው የነበሩትን አማርኛ ተናጋሪዎች አያመለክትም፡፡ ሌሎችንም እንደዚያው፡፡
ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የጠቀስናቸው ማህበረሰቦች ከሞላ ጎደል በዛሬው አካባቢያቸው ሰፍረው የምናገኘው በመካከለኛው የታሪክ ዘመን ነው፡፡ እዚህ ላይ በታሪክ ማስረጃዎች የምንመረኮዝ ከሆነ፣ ነባሩን የኢትዮጵያን ህዝባዊ ታሪክ መልክ በከፍተኛ ሁኔታ የለወጠው፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአካባቢው የነበረው የህዝቦች እንቅስቃሴ ነው። የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የአፋርና የኦሮሞ ህዝቦችን በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይ ዛሬ በታሪክ ሽሚያ የተነሳ አከራካሪ ጉዳይ የሆነው፣ በዚህ ዘመን የተደረገው የኦሮሞ ህዝቦች መስፋፋት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለኔ እንደሚገባኝ ኦሮሞዎች እንዲያው ዱብዳ የመጡ ናቸው ማለት አይደለም። በደቡባዊውና መካከለኛው የሀገሪቱ ክልል እንደ ማህበረሰቦች እዚህም እዚያም አልነበሩም ማለት አይመስለኝም፡፡ 16ኛው ክፍለ ዘመን ወሳኝ ቁምነገሩ ኦሮሞዎች ሃይል አግኝተው፣ ከፍተኛ የግዛት ማስፋፋት በማድረግ እስከ ሰሜናዊው ኢትዮጵያ ድረስ የዘለቁበት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ዘመን ኦሮሞዎች በአንድ በኩል ከማዕከላዊው መንግሥት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች የአካባቢ መንግሥታትና ህዝቦች ጋር እየተጋፉ፣ ግዛታቸውን ማፅናታቸው አከራካሪ አይመስለኝም፡፡
የፊውዳል ኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ግዛቶች ዞሮ ዞሮ ዋዣቂና በሃይል ሚዛን ላይ የተመሰረቱ ስለነበር፣ አንዱ ወገን ሃይል ሲሰማው ሌላውን መግፋቱና ማስገበሩ የተለመደ ነበር፡፡ ስለዚህም ማንም ቢሆን በየትኛውም ዘመን በባዶ ወና ምድር መጥቶ ሰፈረ ለማለት አይቻልም፡፡ በዚህ የመገፋፋትና መቀማማት ሰንሰለት ውስጥ የአንድ ግዛት ባለቤት ወይም ባላገር አሁን ያለው ነው ወይስ ከአሁኑ በፊት የነበረው፣ ወይስ ከዚያ በፊት? ቁምነገሩ ግን ማናቸውም ይዞታ ዘላቂነት የሚኖረው በጥሬ ጉልበት ብቻ ሳይሆን በረዥም ዘመናት ድርድር፣ በሰፊ መስጠትና መቀበል በሚገነባ ፈርጀ ብዙ መተሳሰሪያ ነው፡፡ ዛሬ በዝርዝር የምናውቃቸው ህዝቦች በየአካባቢያቸው ሰፍረው የቆዩት በዚህ በዚህ መልኩ ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ማህበረሰቦች በሰፊው የኢትዮጵያ ክፍል በየግንባሩ ካጋጠሟቸው ነባር ህዝቦች ጋር የወል መተሳሰሪያ ፈጥረዋል፡፡ ከነዚህ ህዝቦች የተለያዩ ሃይማኖቶችን ተቀብለዋል፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ ቅርፆችን ወስደዋል፣ የተለያዩ የኑሮ ዘይቤዎችን መስርተዋል፡፡ እነሱም በፊናቸው ለየማህበረሰቡ ከባህላቸው፣ ከቋንቋቸው፣ ከእምነታቸው፣ ወዘተ አበርክተዋል፡፡
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና መናገሻ ከመሆኗና ከሆነች በኋላ ያለው  ታሪኳ ምን ይመስላል?
ዛሬ አዲስ አበባ ብለን በምንጠራው አካባቢም ልክ ከላይ በገለፅነው የታሪክ ፍሰት የተለያዩ ህዝቦች ተፈራርቀውበታል፡፡ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ሃይል ሲያገኝ እየተስፋፋና በደረሰባቸው ቦታዎች ያሉ ግዛቶችንና ህዝቦችን እያስገበረ፣ ሲዳከም ደግሞ ወደ መሃል ሀገር እየተሰበሰበ ቆይቷል፡፡ ከግራኝ ወረራ በኋላ መንግሥቱ በመዳከሙና በዚህም የተነሳ በየፊናው ያሉ ባላባቶችና ማህበረሰቦች ጉልበት ስለተሰማቸው መልሶ እንደቀድሞው ሊቆጣጠራቸው አልቻለም፡፡
የሸዋ መሣፍንትም በዚህ ወቅት ሃይል አግኝተው ነው መጠናከርና በፊናቸው ግዛታቸውን ማስፋፋት የጀመሩት፡፡ በተለይ ሸዋ የተለያዩ ማህበረሰቦች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ወዘተ መደባለቂያ ድንበር ስለነበረ፣ በመካከለኛው ዘመን እያደር የተስፋፋው የሸዋ ሥርወ መንግሥት፤ ይህንኑ ህብረ ባህላዊ መቀያየጥ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ የሸዋ ነገሥታት መሰረተ አማሮች ቢሆኑም፣ መንግሥታቸውን ያቆሙት በአማራ ስም አልነበረም፡፡ የወረ ሴህ ወይም የጁ ሥርወ መንግሥት መሰረተ ኦሮሞ ቢሆኑም መንግሥታቸው የፀናው በኦሮሞ ስም አልነበረም፡፡ ምከንያቱም አማራም ኦሮሞም የሚባሉ ብሄረሰቦች ገና አልተፈጠሩም ነበርና፡፡
አዲስ አበባም የተፈጠረችው በመንግሥቱ መቀመጫ ከተማነት እንጂ በአንዱ ወይም ሌላው ብሄረሰብ ወይም ነገድ ማዕከልነት አልነበረም። በአካባቢው በወቅቱ የነበሩ ህዝቦችም ሆነ ማህበረሰቦች ፈቃዳቸውን ተጠይቀው አይደለም። በዛሬ አመለካከት ዴሞክራሲያዊ አይደለም ልንል እንችላለን፡፡ ይህ ግን ላም ባልነበረችበት ኩበት ፍለጋ ከመሆን አያልፍም፡፡ ስለዚህ የታሪክ ማስረጃዎችን ጠቅሶ፣ በዚህ ዘመን እዚህ ቦታ ነበርኩ ማለት ከብዙ አንፃር  አያስኬድም፡፡ ለምሳሌ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ጅማዎች አማሮች መሆናቸውንና፣ ለዚህም ለገ አማራና ቱሉ አማራ የሚሉ ቅሪት ስሞችን መጥቀሳቸው፣ ታሪክን ወደ ኋላ የሚመልስበት መንገድ የለም፡፡ በዚሁ መልክ አንዳንድ ዘመነኛ የብሄረሰብ ጠበቆች፣ በተለይም ጥቂት የኦሮሞ ‹‹ምሁራን››፣ በዚህ ዘመን፣ በዚህ መፅሃፍ ስማችን ተጠቅሷል፣ ወይም ‹‹ስማችን ያልተጠቀሰው ሆን ተብሎ በተደረገብን ሴራ ነው›› በማለት የሚያስተጋቡት ከድር የቀጠነ ክርክር፣ መጥፎ ታሪክና ቀሽም ፖለቲካ ነው፡፡
ታሪክን የምር ዋቢ እናድርግ ከተባለ፣ በዛሬው የህዝብ አሰፋፈር ላይ የሚጎለጉለው መዘዝ መፍቻ አይኖረውም፡፡ በዚህ ላይ በታሪክ ማስረጃ ሞግቶና ረትቶ ሀገር ያስመለሰም የሚያስመልስም አይኖርም። ይህ ማለት ደግሞ ዛሬ በሰፊው ያንሰራራው፣ በየቦታው አንዱን ወራሪ አንዱን ተወራሪ፣ አንዱን ባላገር አንዱን መጤ ማድረግ፣ መሬቴን ተቀማሁ ከግዛቴ ውጡልኝ የሚባለው የታሪክ ሳይሆን የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡ የዘረኝነት ቃና ያለው ብሄርተኝነት በነገሰበት ሀገር የሚቀርብ የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታው በድርድር፣ በአብሮነትና በአርቆ ተመልካችነት ሳይሆን፤ በስሜት፣ በማናለብኝነትና በጉልበት ነው፡፡
 ብሄርተኝነት ዘመን አመጣሽና ግለኛ ፖለቲካ ነው፡፡ ዘመን አመጣሽ በመሆኑ ገና አልበሰለም፣ ግልብ ነው፡፡ ስለዚህም ሰፊውን፣ ውስብስቡንና እድሜ ጠገቡን ታሪክ የሚረዳበት አቅም የለውም። በግለኝነቱም የተነሳ ታሪክን ለዛሬ ጥቅሙ በመቆንጸል፣ በማጣመምና በመፈብረክ ራሱን እየሸነገለ ይኖራል፡፡ በመጀመሪያ በታሪክ ያልነበሩ ብሄረሰቦችን ከፈጠረ በኋላ፣ ለነዚህ ፍጡራኖቼ ከኔ በላይ ማን አለ ይላል፡፡  በጠማማና ሃሳዊ ርዕዮት፣ ታሪክን የኋሊት ለመጎተት ደፋ ቀና ይላል፡፡ ዛሬ በሀገራችን የምናየውም ታሪክን የፖለቲካ ደንገጡር ለማድረግ የሚካሄድ ፍልሚያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የህዝቦች ታሪክ ሣይሆን የነገስታቱ የጦርነትና የአስተዳደር ጉዳይ ብቻ መዘገቡ ዛሬ ለምንገኝበት የታሪክ ሽሚያ አጋልጦናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ እንደ ታሪክ ተመራማሪነትዎ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
ይህን ጉዳይ በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል። አንደኛው ታሪክ ስንል ቀደምቱን በተለይም በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ከጥንት የነበረውን ባህላዊ የታሪክ አዘጋገብ የሚመለከት ነው፡፡ ይህ አፃፃፍ በኃይማኖታዊ አመለካከት የተቃኘ፣ በኃይማኖት ሊቃውንት የሚደረስ ሲሆን፣ ብሄረ ኢትዮጵያን ሁለት ዋና መገለጫዎች ተደርገው ከሚቆጠሩት ከእምነቷና ከመንግሥቷ አኳያ የሚተነትን ነበር፡፡ አላማውም የመንግሥቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ ስለ ህዝብም ለህዝብም ታልሞ አልተፃፈም፡፡ ገና ‹‹ህዝብ›› የሚባለው ፈርጅ ራሱን ችሎ አልተወለደም፡፡ ስለዚህም ረዥሙ ሥነ ታሪካዊ ቅርስ በዘይቤውም፣ በይዘቱም፣ በአድማሱም ሆነ በዓላማው ውሱን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ብርቅ ነገር አልነበረም፡፡ የዓለም የሥነ ታሪክ እድገት ያለፈው በዚሁ መንገድ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘመናዊ ወይም ‹‹ሳይንሳዊ›› ሥነ ታሪክ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ሲወለድ እንኳን ለረዥም ዘመናት ትኩረቱ መንግሥትን ያማከለና ብሄርተኛ ባህሪ ያለው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ታሪክ ዘይቤውንና ትኩረቱን ከየዘመኑ ጋር እያጣጣመ የሚሄድ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ ከመንግሥት ጥላ ሙሉ በሙሉ ማላቀቅ አልተቻለም፡፡
ቁምነገሩ ያለው ሀገሪቱ ወደ ዘመናዊነት ያደረገችው ሽግግር መጨንገፉ ላይ ነው፡፡ ይህ ከላይ የገለፅነው ታሪካዊ ሥነፅሁፍ እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቢዘልቅም ፣ በተለይ የዘመናዊነቱ አራማጅ ተደርጎ በአስኳላ ትምህርት የተፈጠረው ዘመነኛ ትውልድ፣ በ1960ዎቹ ያስነሳው ፍጹም በባእድ አምልኮ ላይ የተመሰረተ አብዮታዊ አመፅ፣ ብሄራዊ ታሪክና ባህልን እንደ አሮጌ ቁርበት አሽቀንጥሮ እንዲጥል አደረገው፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው የዘመናዊነት መንፈስ፣ ሚዛኑን ስቶና መሰረቱን ለቅቆ መባዘኑ የማይጠገን የታሪክ ውልቃት አስከትሏል፡፡ የኋላ ታሪካችን በወጉ ሳይጠናና ሳይመረመር፣ ለዘመናችንም አዳዲስ ጥያቄዎችና ችግሮች የሚኖረው አስተዋፅኦ እድል ሳያገኝ መክኖ ቀርቷል፡፡
ሁለተኛው ታሪክ ስንል፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አቆጥቁጦ፣ በ1950ዎቹ ተቋማዊ መሰረት ያገኘውን ዘመናዊ ሥነ ታሪክ የሚመለከተው ሲሆን፣ ከላይ በገለፅነው ምክንያት የተነሳ ከፅንሱ የማንነት ብዥታ ያደናበረው ነበር፡፡ በዚህ ላይ ገና ከአፍላነቱ የተነሳው የአብዮት ማዕበል ከናካቴው የተቀናቃኝ ሃይሎች ኢላማ አደረገው፡፡ በሚያስደምም ሁኔታ የታሪክ መንፈሱን ያጣ ትውልድ፣ ለግማሽ ምዕት ገደማ የታሪክ ጥናትን ህልውና ክፉኛ ሲፈታተነው ከረመ፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ተቋማት የተስፋፋው ሥነ ታሪክ ሞያዊ ሚዛኑን ለመጠበቅና ብሄራዊ ታሪካችንን በዘመናዊ ዘዴና እይታ ለመመርመርና ለመዘገብ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ ትኩረቱ መንግሥትና ፖለቲካ ብቻ አልነበረም፡፡ በተለይ ድህረ አብዮት ሰፊው ህዝብ የሚባለው ፈርጅ በገሃድ የተወለደበትና ማዕረግ ያገኘበት ዘመን ስለነበር የህዝቦችን ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ወዘተርፈ ታሪክ በሰፊው አጥንቷል ፅፏል። በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ‹‹ህዝብ›› በብሄር ፖለቲከኞች እንደገና ወደ ‹‹ህዝቦች›› አልፎም ወደ ‹‹ብሄር ብሄረሰቦች›› ከመተንተኑ ሂደት ጋር ትኩረቱን እያስተካከለ፣ ከሰሜናዊው ወደ ደቡባዊው፣ ከማዕከሉ ወደ ጠረፉ አድማሱን እያስፋፋ፣ የሀገሪቱን ታሪክ ጊዜና አቅም በፈቀደ የተሟላ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ለራስ መቁረስ ሳይሆን፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች (ባእዳኑንም ጨምሮ) የሰሩትን ድንቅ ሞያዊ ሥራ ወደፊት ለታሪክ ቀና አመለካከት ያለው ትውልድ መዝኖ ሊፈርደው የሚችለው ነው፡፡
ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክ ያለመጠናት ብቻ አይደለም የታሪክ ሽሚያን ያስነሳው፡፡ ሥነ ታሪክ አቅምና ነፃነት በማጣቱና፣ የተጠናው እንኳን በወጉ ለባለታሪኩ ሳይደርስ አቧራ ለብሶ መቅረቱ ነው፡፡ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተና በሞያዊ ሥነምግባር የታረቀ ምሁራዊ ታሪክ የቀጨጨው፣  ህዝባዊ ታሪክ ያለቅጥ የብሄረሰብ ፖለቲከኞችና የአገም ጠቀም ደራሲያን መፈንጫ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡





Read 5358 times