Sunday, 30 July 2017 00:00

አወዛጋቢው የቀን ቁርጥ ገቢ - አስተያየቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  (መንግስት - ታክስ - የግል ዘርፉ)

       አነስተኛ ነጋዴዎች በቀን የሚያገኙትን ገቢ በግምት በማስቀመጥ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑን ተከትሎ በርካቶች ጉዳዩን መነጋገሪያ አድርገውታል፡
፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችም በጉዩ ላይ የራሳቸውን ምልከታ እያስቀመጡ ሲሆን አዲስ አድማስ ጋዜጣም እነዚህን ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ
አነጋግራለች፡፡ የባለሙያዎቹንና ፖለቲከኞችን አስተያየትና ሀሳብ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

                “የግብር ጥናቱ፣ እንደገና በባለሙያዎች መከናወን አለበት”
                           አቶ አበባው መሐሪ (የኢኮኖሚ ባለሙያና ፖለቲከኛ)

     በዓለም የፖለቲካ ስርአት ውስጥ ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ መንግስት ደግሞ ያንን ሰብስቦ ለተገቢው አላማ ማዋል አለበት፡፡ አሁን በእኛ ሀገር ችግር እየፈጠረ ያለው መንግስት ከዜጎች ታክስ ሰብስቦ የሚሰጠው አገልግሎት በቂ አለመሆኑ ነው፡፡ በውሃ፣ በመብራት በቴሌኮሚኒኬሽን መሰረተ ልማቶች ካየን፣ አገልግሎቱ የተሟላ ካለመሆኑም በላይ አማራሪ ነው፡፡
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በግምት ላይ ተመስርቶ የተጣለው የቀን ቁርጥ ገቢ ደግሞ በህብረተሰቡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ላይ የበለጠ ችግር የሚፈጥር ነው። በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ይሄ ከባድ ጫና የሚፈጥር ነው፤ በአቅምም ሆነ በሥነ ልቦና፡፡ መንግስት ህዝቡን ሊያምን ይገባል፡፡ መተማመን በመፍጠር፣ ታክስ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው ሀገሩ እንድታድግና እንድትለማ ይፈልጋል። ታክስ ደግሞ ለዚህ ጠቃሚ ነው፡፡ አብዛኛው ህዝብም በዚህ እምነት አለው። ነገር ግን በአለመተማመን መንፈስ፣ ዝም ብሎ በጫና፣ ግብር ለማስከፈል መሞከሩ አይበጅም፡፡ መንግስት ይሄን ጉዳይ በድጋሚ ሊያየው ይገባል፡፡
ነጋዴው አሁን በዚህ መጠን መማረሩ፣ ለሀገሪቱ ቀጣይ እድገትም አይበጅም፡፡ ይሄ በአንክሮ ሊጤን ይገባዋል። መንግስት በነጋዴው ላይ፣ ነጋዴው በመንግስት ላይ እምነት የሚገነባበት ሰፊ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ነጋዴው የሚከፍለው ታክስ፤ ለሀገሬ ልማት እየዋለ ነው የሚለውን በአረጋጋጭ ማሳያዎች ማግኘት አለበት፡፡ መንግስት ከህዝቡ የሚቀበለው ገንዘብ፣ በሙሰኞች አለመበላቱንና በቀጥታ የሀገር ግንባታ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለበት። ህዝቡ በሚከፍለው ታክስ፤ ሙሰኞች የማይከብሩበት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሊኖር ይገባል። በሌላ በኩል፤ መንግስት ራሱ ህብረተሰቡን ሊያምን ይገባል፡፡
በጫና የሚሆን ነገር የለም፡፡ እነዚህ ነገሮች እስካልተሻሻሉ ድረስ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ታክሱን አስመልክቶ የተፈጠረው አድማ አደገኛ ነው፡፡ መፍትሄ በአፋጣኝ መሰጠት አለበት፡፡ ህብረተሰቡ የማይማረርበት ሁኔታ መፍጠር ብልህነት ነው፡፡ የግብር ጥናቱ፣እንደገና  በባለሙያዎች መከናወን አለበት፡፡ መፍትሄው ይኸው ነው፡፡

------------------------------

                         “እኔ ያልኩህን ብቻ ተቀበል የሚባልበት ዘመን ላይ አይደለንም”

      ሀገራችን የቫት ሲስተም ውስጥ ከገባች ገና ሁለት አስርት አመታት ነው የተቆጠሩት፡፡ በወቅቱ የገቢ ሰብሳቢው አካል፣ ስለ ቫት ግንዛቤ ለመስጠት አንድ መፅሄት ያሳትም ነበር፡፡ እዚያ ላይ በርካታ ግንዛቤ የሚሰጡ ጉዳዮች በተከታታይ ይታተሙ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ የንግድ ም/ቤት ተጠሪ ስለነበርኩ በጉዳዩ ላይ ቃለ መጠይቅ አድርገውልኝ ነበር፡፡ የቫት ስርአት ጥሩ ስርአት ነው፤ ነገር ግን መጀመሪያ ለህብረተሰቡ ትምህርት መሰጠት አለበት ብዬ ነበር፡፡ እንደውም “ከትምህርቱ በትሩ እንዳይቀድም ተጠንቀቁ!፤ መጀመሪያ ማስተማር አለባችሁ” ብዬአለሁ፡፡  ከሰሞኑ በታክስ እወጃው ላይ ያጋጠመው ችግርም ግንዛቤ ያለመስጠት ችግር ነው፡፡ ግንዛቤ ለመስጠት ደግሞ ሥርአቱ በራሱ መስተካከል አለበት፡፡ አሁን ያለው የገቢ ስርአት ለውይይት አይመችም፡፡ ምናልባት ፓርላማ ተወያይቶበታል ሊባል ይችላል፡፡ ይሄ መልስ አይሆንም፡፡ ዋናው ታክሱ በቀጥታ የሚነካው አካል ነው ተሳታፊ መሆን ያለበት፡፡
በአሳዛኝ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማየው፣ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እስከተናገረ ድረስ፣ የተናገረው ቃል መፈፀም አለበት የሚል ጭፍን አካሄድ አለ፡፡ ለምሳሌ ባንኮች አካባቢ፣ እኔ ብሔራዊ ባንክ ጥናት አድርጌያለሁ፣”በዚህ አቅጣጫ ስሩ” ነው የሚለው እንጂ “ኑ በዚህ ጉዳይ እንወያይ” አይልም። ይሄ ሊሆን አይገባውም፡፡ ሁላችንም አንዲት ሀገር ነው ያለችን፡፡ ታክስ ከፋዩ የሀገሩ ባለቤትም ነው፡፡ እርግጥ ነው ማጭበርበር፣ ማሸሽ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ካገኘ ችግር አይኖርም፡፡ በታክስ አሰባሰብ ግንዛቤ መስጠት ማለት፣ ለአፈፃፀሙ ግማሽ መንገድ መሄድ ማለት ነው፡፡ ስልጣኑ ላይ ያለው አካል፣ “እኔ ካልኩ መፈፀም አለበት” ማለቱን ትቶ፣ በሰከነ መልኩ ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
አሁን ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ግንዛቤ ለመስጠት ሲሞከር እየተስተዋለ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ መደረግ የነበረበት ግዳጁን ወደ ነጋዴው ሳያወርዱ በፊት ነው፡፡ መቼም አሁን ያለንበት ስርአት፣ ወታደራዊ ስርአት አይደለም፡፡ ይሄን እንዴት ለህዝቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይከብዳል? እኔ እንደሚገባኝ፣ አብዛኛው ህዝብ መጀመሪያውኑ እንዲወያይ ቢደረግ፣ አሁን የተፈጠረው ግርግርና ትርምስ ላይፈጠር ይችል ነበር። እንደ መሳፍንቱ ዘመን፣ ሳያስገነዝቡ፣ ዝም ብሎ አዋጅ አውጥቶ፣”እኔ ያልኩህን ተቀበል” የሚባልበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡ በነገስታቱ ዘመን እንኳ ለምሳሌ፡- አፄ ምኒልክ ግብር ሲጨምሩ፣ መጀመሪያ፣ ህዝቡን ይሄን ያህል ትከፍላለህ ተብሏል እያሉ ያስወራሉ፡፡ ከዚያ ህዝቡ የሚሰጠውን ግብረ መልስ፣ ህዝቡ ምን አለ? ሲሉ ይጠይቃሉ። “ኧረ እንዳው በጣም ነው ህዝቡ የተቆጣው” ከተባሉ፣ መጠኗን ቀነስ አድርገው እንደገና እንዲወራ ያስደርጋሉ፡፡ አሁንም ህዝቡ ከተቃወመ፣ እንደገና ማሻሻያ ያደርጋሉ፡፡ ህዝቡ መቃወሙን ሲያቆም፣ ታክሱን በአዋጅ አስነግረው ያፀናሉ፡፡ ይሄ ነበር ህዝቡን የማማከር ጥበባቸው፡፡
እኛ ጋ ግን አሁን “ህዝቡን አማክረናል” ሲሉ አንደኛ ህዝቡን አያገኙትም፡፡ የንግድ ም/ቤቱም፣ ለንግዱ ህብረተሰብና ለመንግስት መገናኛ ድልድይ ይሆናል የሚለውን ጨርሶ ማድረግ አልቻለም። መንግስት፤ አዲስ ዘዴ ፈጥሮ ህዝቡን ማስተማር አለበት፡፡

-------------------------------

                             “ታክስ ለመሰብሰብ አሰራርን ማዘመን ያስፈልጋል”
                                ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)

      የዓለም ታላላቅ ሀገራት ኢኮኖሚ በእግሩ የቆመው በታክስ አሰባሰብ ስርአታቸው ነው፡፡ ጣሊያንና ግሪክ አጠቃላይ ኢኮኖሚያቸው ቀውስ ውስጥ የገባው ታክስ መሰብሰብ ስላቃታቸው ነው፡፡ በተለይ ግሪክ ግማሹ ህዝብ ታክስ የማይከፍልበት፣ ታክስ በተጨመረ ቁጥርም፣ በምርጫ መንግስት እየተቀየረ መቀመጥ የሚፈልግ ህዝብ በመሆኑ፣ አሁን ኢኮኖሚያቸው እየወደቀ ለአለማቀፍ እርዳታ ተጋልጠዋል፡፡ በአይኤምኤፍ፣ በዓለም ባንክ እና በተለያዩ ድርጅቶች እየተደጎሙ ነው የሚኖሩት። ሀገራችንም ለዚህ ችግር እንዳትጋለጥ፣ የታክስ መሰረቱን አመቻችቶ፣ ህዝቡ ታክስ እንዲከፍል መደረጉ አግባብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ታክስ ለመሰብሰብ መጀመሪያ አሰራርን በሚገባ ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ነጋዴዎች ምሬት ውስጥ እየገቡ ያለው ጥራት ባለው ባለሙያ ባለመሰራቱ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ አንዳንድ ሰውም ታክስ ያለመክፈል ጥረት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ግን ግብር ሰብሳቢው አካል መጠንቀቅ ያለበት፣ እንደዚህ ዓይነት ግምት ሲቀመጥና ነጋዴው ሱቁን በመዝጋት አድማ እስከማድረግ ሲደርስ ነው፡፡ ይሄን ነገር መንግስት በጥንቃቄ ነው መያዝ ያለበት። ግብር አሰባሰቡን ፍትሃዊ አለማድረግም ሌላ ችግር ይፈጥራል፡፡ የሚጣለው ግብር በባለሙያዎች በጥንቃቄ የተጠና መሆን አለበት፡፡ በርካታ ያደጉ ሀገሮች፣ ይህን መሰሉን ጥናት ለማድረግና አሰራሩን ለመዘርጋት በርካታ መዋዕለ ንዋይ ነው የሚያወጡት፡፡
በሌላ በኩል፤ በታክስ እንዲሁም በገበያ ዋጋ ጉዳይ መንግስትን የሚያማክር ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይህ መሰሉ ተቋም ቢቋቋም፣ ጥናቶችን በማድረግ ለመንግስት አጋዥ ይሆናል፡፡ አንድ ተቋም ብቻ ግብር እየጣለ፣ ራሱ እየሰበሰበ፣ ራሱ እርምጃ እንዲወስድ ማድረግ መልካም አይሆንም። ይሄ፤ ህዝብ አቤት የሚልበትን አሳጥቶ፣ አመፅን እንደ መፍትሄ እንዲወስድ ስለሚገፋፋ ሊታሰብበት ይገባል። አሁን ያለውን የግብር አሰባሰብ ችግር ለማቅለል፣ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል። በአለም ባንክም ሆነ በአይኤምኤፍ፣ ብዙ ጊዜ “የታክስ መረጃችሁን አሻሽሉ” የሚሉ ምክሮች ይለገሳሉ፡፡
ስለዚህ  ከፍተኛ ወጪ መድቦ የታክስ ስርአቱን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፋችንም  መስተካከል አለበት፡፡ የፋይናንስ ስርአቱን “ሊበራላይዝ” እስካላደረግን ድረስ፣ ታክሱን መሰብሰብ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ይሄን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡
የፋይናንስ ስርአቱን ነፃ ማድረግ (ሊበራላይዜሽን) ሲባል፣ አንዱ መንገድ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ መፍቀድ  ነው፡፡ ይሄ የውጭ ምንዛሬ ችግርንም ይፈታል፡፡
ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎችም ሀገራት አሁን የውጭ ምንዛሬ ችግር የሌለባቸው፣ የውጭ ሀገር ባንኮች በየሀገራቱ ስላሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፋይናንስ ስርአቱን ለማስተካከል አንዱ መፍትሄ፣ የውጭ ባንኮችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ሊካሄዱ ይገባል፡፡

-----------------------------

                  “ኢኮኖሚው የንግዱን ማህበረሰብ ማዕከል አላደረገም”
                      ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢኮኖሚ ባለሙያና ፖለቲከኛ)

       የአገሪቱ የኢኮኖሚ ስርአት መሽመድመዱ ነው የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ፡፡ መንግስት የሚከተለው የኢኮኖሚ ስርአት ወጥ ባለመሆኑ የንግዱ ህብረተሰብ ወጥ በሆነ መርህና ደረጃ እንዳይሰራ አድርጎታል፡፡ ይሄ መተማመንንም አሳጥቷል፡፡ ኢኮኖሚው የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ፣ የሸቀጦች ዋጋ አንዴ በተሰቀለበት አይቀርም  ነበር፡፡
የተስተካከለ ኢኮኖሚ ባላቸው በርካታ ሀገራት፣ የሸቀጦች ዋጋ ከፍ እና ዝቅ የተለመደ ነው። በኛ ሀገር ግን የሸቀጦች ዋጋ በወጣበት ቀርቶ፣ እየጨመረ ነው የሚሄደው። አንዴ የወጣ ዋጋ  ወደ ኋላ የማይመለስበት ምክንያት ደግሞ የኢኮኖሚ ስርአቱ አቅርቦትንና ፍላጎትን ሚዛናዊ አድርጎ የማይሄድ በመሆኑ ነው፡፡ የዋጋ መሰቀልን ማውረድ  የሚቻለው  አቅርቦትን በመጨመር ነው፡፡  
በአጠቃላይ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የዚህ ወጥነት የጎደለው ኢኮኖሚ ስርአት ተሳታፊ በመሆኑ ነው፣ የግብር ጉዳይ ላይም ችግር የተፈጠረው። ኢኮኖሚው የንግዱን ህብረተሰብ ማዕከል አላደረገም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች፣ በሰፊው በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተጠንተው መፈተሸ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል፤ ግብር ገማቾች፤ የሰለጠኑ ባለሙያዎች  መሆን አለባቸው፡፡ ህብረተሠቡ የሚያነሣው አንዱ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ እርግጥ ነው አገሪቱ ባለሙያ አላጣችም፤ ግን የአሠራር ስርአት ችግር አለ፡፡ የአሠራር ስርአት ችግር ደግሞ ባለሙያን እንዲሁ የሚያባክን እንጂ ክህሎቱን አውጥቶ እንዲጠቀምበት አያደርግም፡፡ መንግስት ይሄን ማጤን አለበት፡፡
በንግዱ ማህበረሰብ በኩል ደግሞ ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ግዴታ ለህብረተሰቡ  በሚገባ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው በቀጥታ ወደ ህብረተሰቡ ማውረድ ነው፡፡ ይሄ አካሄድ የትም አያደርስም፡፡ የሰሞኑን አይነት ችግር ነው የሚፈጥረው፡፡ አሁን አብዛኛውም እሮሮ እየተሰማ ያለው ከዝቀተኛው የነጋዴ መደብ ነው፡፡ ለዚህ የነጋዴ መደብ መጀመሪያ ሊደረግለት የሚገባው ደግሞ፣ አቅም ያለው ግብር ከፋይ ሆኖ የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ሃብቱ እየካበተ ሲሄድ፣ ራሱ ወደ ታክስ ስርአቱ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል፤ የታክስ ስሌት መደረግ ያለበት እንዳሁኑ 6 ዓመት ቆይቶ አይደለም፤ በየአመቱ ነው መደረግ ያለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቁ የሆነ ተቋምና የሠው ሃይል ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የአሁኑ አገማመት ከባለሙያ ይልቅ ወደ ፖለቲካ ውሳኔ የሚያመዝን ነው የሚመስለው፡፡ ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ የሚወሰኑ ውሳኔዎች  ህብረተሰቡን አሣማኝ መሆን አለባቸው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ህዝቡ ወደ ኩርፊያ ነው የሚሄደው፡፡ ገማቾች ማኑዋል ይዘው ነው የሚሰሩት፡፡ ይሄ ማኑዋል ፖለቲካዊ ቅርፅ ያለው እንዲመስል ተደርጎ፣ በህብረተሰቡ ግንዛቤ መወሰዱ ነው አደገኛው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በድጋሚ  ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መታየት ቢችል መልካም ነው፡፡ በቀጥታ ወደ ማስከፈል መግባት ስህተት ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ ግብር ህብረተሰቡ አምኖበት ካልከፈለ፣ ከፍተኛ የካፒታል በጀት ክፍተት ነው የሚፈጠረው። ይሄ እንዳይሆን መንግስት ወደ ራሱ ተመልሶ ማየት አለበት፡፡ ይሄ ካልተደረገ ቅራኔ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህቺ ሃገር መረጋጋት አለባት፤ እንድትረጋጋ ደግሞ መንግስት ብልህ መሆን አለበት፡፡ ሃገሪቱ የምሁራን ችግር የለባትም፤ የተቋም ችግርም የለባትም፤ ትልቁ ችግሯ፤ የአሠራርና የአፈፃፀም ህግን ተከትሎ ያለ መስራት ነው፡፡

---------------------

                          “ፍትሃዊነተ ከሌለ ብሶት ይወለዳል”
                           ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የኢኮኖሚ ባለሙያና ፖለቲከኛ)

      በተለይ በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ በተመን መልክ የተወሰነው ግብር ትክክል አይደለም። ነጋዴው መክፈል ያለበት ባገኘው ገቢ ልክ ነው። የኛ ሀገር የንግድ ሁኔታ ደግሞ መጠናት አለበት። ይሄ ጥናት በሌለበት፣ አንድን ነጋዴ፣”በቀን ይሄን ያህል ታገኛለህ” ብሎ መደምደም፣ በየትኛውም መርህ አይደገፍም፡፡ አሁን አብዛኛው አቤቱታ እየቀረበ ያለው በአነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎችን የበለጠ ማበረታታትና ወደ ከፍታ ማጋገር ሲገባ፣ ገና በእንጭጩ ማስደንገጡ አይደገፍም፡፡ በሌሎች ሀገራት የሚደረገው፣ ቅድሚያ እነዚህን ማበረታታት ነው፡፡ ጥብቅ ቁጥጥርና ፈር ማስያዝ የሚገባው፣ በከፍተኛ ደረጃ ባሉ ነጋዴዎች ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ነጋዴዎች ምን ያህሉ በትክክል የሀገር ግብር ይከፍላሉ? ከመንግስት ጋር በመመሳጠር፣ በሙስና የተጨማለቁ አይደሉም ወይ? መቼም በየጊዜው ነጋዴዎችና ባለስልጣናት በሙስና ተጠርጥረው፣ ታሰሩ ሲባል እየሰማን ነው፡፡ የዚህ ችግር ስፋት ምን ያህል ነው የሚለው ግን በተጨባጭ ጥናት ሲቀርብ አናይም! እስካሁን ባለው ሁኔታ፣ የመንግስት አካላት ትኩረት እያደረጉ ያሉት፣ ትንንሾቹ ነጋዴዎች ላይ ነው። ይሄ ነው የህዝብ ብሶት የሚወልደው፡፡ ፍትሃዊነት ከሌለ ብሶት ይወለዳል። ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ፣ ትንንሽ ነጋዴዎችን ከማበረታታት ይል በግብር ማስጨነቁ ተገቢ አይደለም፡፡ ትልልቆቹ፣ በሙስና ተጨማልቀዋል የሚባሉት ናቸው መፈተሸ ያለባቸው፡፡
ሌላው ለእነዚህ ነጋዴዎች፣ እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ፣ የይግባኝ ስርአት መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡ በጎን ግን ወደ ፍ/ቤት ይግባኝ ለመጠየቅም፣ የተጣለውን ግብር 75 በመቶ መክፈል አለባቸው ፤ ይላል ህጉ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ይሄን ያህል መክፈል ከቻለ፣ ምን ይግባኝ ያስፈልገዋል? ይሄ ስርአትና አሠራር በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ መንግስት  የእነዚህን ዜጎች ድምፅ በጥንቃቄ መስማት አለበት፡፡ ህዝቡ ከዓምና  ጀምሮ በርካታ ብሶቶችን እያሰማ ነው። ነጋዴው ከዚህ ቀደም እንደዚህ ሲበሳጭና ሲያድም አላስተዋልንም፤ አሁን ለምን እንዲህ አደረገ? መንግስት እነዚህን ሁሉ መጠየቅና እውነተኛ መፍትሄ ማበጀት አለበት፡፡ ሰው መቼም ብሶት የሚያሰማው ከአቅሙ በላይ ሲሆን ነው፡፡ “ከአቅሜ በላይ ነው” እያለ፤”አይ በአቅምህ ነው” ማለት ምንድነው ትርጉሙ፡፡ በአጠቃላይ የግብር አጣጣሉ፣ አቅምን ያገናዘበ፣ በምሁራን ጥናት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡

-----------------------

                             “99.2% ለሚሆኑ ቅሬታዎች እልባት ሰጥተናል”

                           አቶ አትክልት ገ/እግዚአብሔር (የአ.አ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ፅ/ቤት ሥራ አስኪያጅ)

     አማካይ የቀን ገቢ ግምቱን፣ ከሚያዚያ 17 ጀምረን፣ ለ1 ወር በተከታታይ ነው የሰበሰብነው። በተሰበሰበሰው መረጃ ላይ ነጋዴዎቹ ቅሬታ ካላቸው፣ የቅሬታ ማዳመጫ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠን እየተመለከትን ነው የምንገኘው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን ቅሬታ፣ እስከ ሐምሌ 30 ሙሉ በሙሉ እንፈታለን ብለን ባቀድነው መሰረት፣ 99.2 በመቶ ለሚሆኑ ቅሬታዎች እልባት ሰጥተናል፡፡ ቅሬታዎችን የሚመለከትም ሁለት እርከን ነው ያደረግነው፤ የደረጃ “ለ” እና “ሀ” የራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦላቸዋል። በዚያ መሰረት የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡
መጀመሪያ ግምቱን የሚሰሩ አራት ባለሙያዎች ናቸው በአንድነት የሚመደቡት፡፡ ሁለቱ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ አንድ ከንግድ ሚኒስቴር፣ አንድ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ነበር ተውጣጥተው ግመታውን ያከናወኑት፡፡ ከነዚህ ያለፈ ችግር ካለም ለማጥራት፣ የኢንስፔክሽን ቡድን አቋቁመን ነበር የተንቀሳቀስነው፡፡ ይሄ መጀመሪያውኑ አሰራሩ ቅሬታ እንዳይፈጥር በመጨነቅ፣ የዘረጋነው አሰራር ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ካለፈና ግመታው የተሳሳተ ከሆነ ደግሞ አሁን በዘረጋነው የቅሬታ አሠማም ሂደት ይስተናገዳል፡፡  በዚህ አልረካሁም የሚል ካለ ደግሞ እስከ ፍርድ ቤት መሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበትን ሰፊ አሠራር ነው የዘረጋነው፡፡ ይህ በሆነበትና በህግ በሚተዳደር ሃገር፣ ሱቅ በመዝጋት የሚፈታ ችግር የለም፡፡ የታክስ አስተዳደሩ በአሠራር ስርአት ነው የሚመራው፡፡ ግብር ከፋዩ በዚህ አሠራር መብቱን መጠቀምና ቅሬታውን ማሠማት ይችላል፡፡
ግንዛቤ በመፍጠር በኩል በእርግጥም ክፍተት እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ አሁንም ግንዛቤ በሰፊው እየተሰጠ ነው፤ ለወደፊትም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ይዘጋጃሉ፡፡ በተለይ በቀጣይ አመት ከነጋዴው ጋር በሰፊው የምንገናኝበት መድረኮች ለመፍጠር አቅደናል፡፡

Read 3657 times