Monday, 31 July 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

 አንድ ሊቅ ቁጭ ብሎ እያሰበ ሳለ፣ አንድ ሰው መጣ፡፡ “ጤና ይስጥልኝ” በማለት ሰላምታ ካቀረበለት በኋላ፡- “ሀሳብ አለህ መሰለኝ?” አለው፡፡
ሊቁም “ሀሳብ? ሃሳብማ አለኝ” ሲል መለሰለት፡፡
“ምን ዓይነት?”
“ጥቁርና ነጭ”
ሰውየውም፤ “የሚጠቅመኝ ነጩ ነው፤ እሱን ነው የምፈልገው” አለው፡፡
ሊቁም የሚፈልገውን አዘጋጅቶ ሰጠው፡፡ ሰውየው ቤቱ እንደደረሰ ዕቃውን ቢከፍተው ነገሩ የለም፡፡
“ወዴት ገባ?” እያለ … እያሰበ ወደ ጠቢቡ ዘንድ ተመለሰና “ኧረ አጣሁት” ቢለው፤ “እስኪ ይኼኛውን ደግሞ ሞክር” በማለት ሌላኛውን ቀየረለት፡፡
ሰውየው፤ “እኔ የምፈልገው ነጩን ነው፤ ይኸ ምን ይጠቅመኛል” በማለት እየተነጫነጨ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ እንደደረሰም ቢከፍተው አላገኘውም። ግራ ገባው፡፡ እንደገና ወደ ጠቢቡ ተመለሰና፤ “ኧረ ጉድ ነው፣ ይኼኛውንም አላገኘሁትም” አለው፡፡
ጠቢቡም፤ “እንግዲህ ሁለቱንም አንድ ላይ ውሰድና ሞክራቸው” ብሎ እንደተለመደው አዘጋጅቶ ሰጠው፡፡ ሰውየው ፈጠን ፈጠን እያለ ከቤቱ ደረሰ። የያዘውን ዕቃ ከፍቶ ሲመለከት፣ ጥቁርና ነጭ ጎን ለጎን ቁጭ ብለው ይቁለጨለጫሉ፡፡ ሰውየው ገባው፤ ለየብቻቸው ሲሆኑ ሊታዩት ያልቻለው ለካስ ያንደኛው አለመኖር ሌላኛውን እንዳይታይ ስላደረገ ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ የምትፈልገውን ለማግኘት፣ የማትፈልገውን አብረህ ልትቀበል ትችላለህ፡፡ አንዳንዴ ለምትፈልገው ነገር ስትል መክፈል ያለብህ ነገር ይኖራል፡፡ ዋናው የአንተ ጥንቃቄና አያያዝ ነው። ፅጌረዳዋን ለመውሰድ እሾሁን መጥላት የለብህም፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ ዓለማችን ሥጋት ላይ ናት፡፡ አያድርስ ነው እንጂ የኑክሊየር ጦርነት ቢነሳ፣ ስልጣኔአችን እንዴት ሊናድ እንደሚችል ገምት፡፡ ሰው በገዛ ሃሳቡና ፈጠራው ሊጠፋና ሊያጠፋ ይችላል፡፡ በልጅነቴ ያየሁት አንድ ፊልም እስከ አሁን ድረስ ትንሽ ትንሽ ትዝ ይለኛል፡፡ ሰውየው አእምሮው ውስጥ ሰው የሚመስል ጭራቅ (Predator) ፈጠረ፡፡ ሀሳቡን እውን ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ለ “ፕሮጀክቱ” ያስፈልጉኛል ያላቸውን አካላት ከአንድ የመካነ መቃብር ቦታ ከዘበኛው ላይ እየገዛ ሰበሰበ፡፡ የሰበሰበውን እንደ ሀሳቡ እያስተካከለ፣ ገጣጥሞ ጨረሰና አንድ ነገር ብቻ ቀረው፡፡ ጭንቅላት። ሀሳቡ ውስጥ ያለውን ጭንቅላት የሚመስል አንድ ቦታ እንደተመለከተ አስታወሰ፡፡ ፈልጎ ማግኘት ግን አልቻለም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ሌላ ቦታ ለመፈለግ ተነሳ፡፡ ከቀብር ስፍራው በመውጣት ላይ እንዳለ ድንገት ትዝ አለው፡፡ ወደ ኋላ ተመለሰ፡፡ መሳርያውን አውጥቶ፣ ዘበኛውን ገደለና አንገቱን ቆርጦ ወሰደ፡፡
በመጨረሻም ‹ፕሮጀክቱን› አጠናቆ እንደጨረሰ ጭራቁ ተነቃነቀ፡፡ ሰውየውም በስራው እየተደነቀ፣ ምን ዓይነት ትዕዛዝ እንደሚሰጠውና እንደሚጠቀምበት ሲያስብ፣ ጭራቁ ዘሎ ጉብ አለበት፡፡ ገነጣጥሎ ሲያጣጥመው አፍታም አልወሰደበት፡፡ የገዛ ሃሳቡ፣ የገዛ ስራው መልሶ ሰውየውን በላው፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ ሀሳብህን ወደ ድርጊት ከመቀየርህ በፊት መርምረው፡፡ “ያልተፈተነ ሀሳብ ቅዠትን ይወልዳል፡፡ ያኔ ባላጋራህን ሩቅ አትፈልገው፤ እዚሁ አንተውጋ ነው ያለው፤ እንዲያውም አንተው ራስህ ነህ” ይላሉ አዋቂዎች፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጠላታቸው የገዛ ሃሳባቸው መሆኑን ሳይረዱ ሌላ ቦታ እየመሰላቸው ለጦርነት ሲዘጋጁ ጦርነቱ ሳይጀመር ያበቃል፡፡ አየህ ወዳጄ፣ ጠላቴ ነው የምትለው ሰው በአካል ካለ ስታየው ትሸሸዋለህ፡፡ ከፈለግህ ደግሞ ጠብቀህ ወይያለበት ሄደህ ትገጥመዋለህ፡፡ ታሸንፈዋለህ ወይ ትሸነፋለህ። ጉዳዩ እዛ ላይ ያበቃል፡፡ ያ ካልሆነ ሰግሞ ከሰህ ወይ ተከሰህ በህግ ትዳኛለህ፡፡ አእምሮህ ውስጥ የፈጠርከውን ባላጋራ ግን ምን ታረገዋለህ? የምትበላውን ሲበላብህ አታየውም፡፡ ስትራመድ ወይ ስትሰራ ያደናቅፍሃል … አታየውም፡፡ አንተ ተጋድመህ እሱ እንቅልፍህን ይለጥጥልሃል … አታየውም፡፡ ከፈለገ ሚስትህን ይዳራብሃል … አታየውም፡፡ ኑሮህን እየኖረብህ አንተ በስጋት ታልቃለህ፡፡ ስትሞትም አይሞትም፡፡ መጀመሪያም አልነበረማ!!
በነገራችን ላይ አጉል ሃሳብ፣ አጉል ጥርጣሬ ስልህ፣ ተገቢ ያልሆነውን ማለቴ እንጂ መጠርጠር ያለብህ ጉዳዮችማ ብዙ፣ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› ነው ወዳጄ፡፡ ‹‹መስቀል ከሰማይ ወረዳ›› ሲሉህ ካልጠረጠርክ ምኑን አንተ ሆንክ? አራት ኪሎ ሰማይ ላይ ማርያም ታየች ሲሉህ ካልጠረጠርክ ምኑን አንተ ሆንክ? “የዓለም መጨረሻ በዚህ ቀን፤ በዚህ ወር፣ በዚህ ዘመን ነው›› ሲሉህ ካልጠረጠርክ ምኑን አንተ ሆንክ? አልማዝን አይቼ አልማዝን ሳያት የሚለው ወይም የአበበች ደራራ በናዝሬት አድርገህ ግባ አዲስ አበባ የሚለው ወይም የእንትናና የእንትና ዘፈን እንዲህ ማለት ነው እኮ ብለው ሲተረጉሙልህ፣ ካልጠረጠርክ ምኑን አንተ ሆንክ? የወዳጅህ ስም ሲጠፋ ነግ በኔ ብለህ ካልጠረጠርክ፣ ምኑን አንተ ሆንክ? እኔ ባንተ ቦታ ብሆን፣ ይህንን የፃፈልኝን ሰው ራሱ ልጠረጥረው እችላለሁ፡፡ ‹‹ጠርጥር ከቅቤም አይጠፋም ስንጥር›› መባሉ ያለ ነገር አይደለማ!
ወዳጄ ሆይ፤ ምኑን አንተ ሆንክ? ስልህ፣ አንተ የራስህ ሃሳብ ያለህ ሙሉ ሰው ነህ፣ የነፍስህ ብርሃን ማብሪያና ማጥፊያ አንተው ራስህ ነህ ማለቴ ነው። ሀሳብ በየጊዜው እየተሰራ ሲጫንብህ፤ እንደ ሮቦት እንዲቆጣጠሩህ አትፍቀድ፡፡ ሄንሪ ሚለር እየደጋገመ፤ ‹‹I don’t want a master in human form ›› …(የራሴ ጌታ ራሴ ነኝ፤ የኔው ቢጤ ሰው ጌታዬ እንዲሆን አልፈልግም ማለቱም አይደል?)
ብዙውን ጊዜ አጓጉል ሃሳቦች የሚመጡት ‹‹እኛ እናውቅልሃለን›› ከሚሉ ግን እንደ አዲስ አበባ ጠንቋዮች ስለ ራሳቸው ከማያውቁ አስመሳዮች (ሂፖክራቶች) በመሆኑ ማናቸውም ጉዳዮችህ ላይ ደግመህ ደጋግመህ እንድታስብ አሳታውስሃለሁ… አንተ “አንተ” ነህ፡፡
ኤሪክ ፎሮፎርም ‹‹Man for Himself›› በሚል መጽሐፉ ውስጥ ከአንድ ሌላ ሰው የወሰደውን ‹ግጥም› እንዲህ ይጠቅሰዋል፡-
… I see I am I is only mine
And belongs to me
And to nobody else,
To no other man
Not to an angle nor to God
Except in as much as
I am one with him
ሃሳቡ ባጭሩ እንዲህ ይመስለኛል፡-
እኔን ‹እኔ› የሚያረገኝ፣
አለመስማማቴ ኮ ነው፣
የሚያስማማ ነገር ከሌለኝ
ከማንም ይሁን ማን
ከራሱም ቢሆን ከ‘ግዜር
ጨርሶ ካልመሰለNE በቀር፡፡
እናም ወዳጄ; ሀሳብ የስልጣኔአችን መሠረት እንደሆነ ሁሉ; አጉል ሃሳብና አጉል ጥርጣሬ ደግሞ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ጨምሮ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ እየሆኑ የምናያቸው ጥፋቶችና ክፍቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
የዓለም ህዝብ እያንዳንዱne ቀን በጥርጣሬ እንደሚኖር ለማወቅ ከሚዲያው የበለጠ ምስክር የለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነው ዋነኛው ነገር ሃሳብን በቅጡ አለመመርመር ይመስለኛል፡፡ ይህም ራስን ካለመሆንና በሌሎች ሰዎች ቅዥቶች መታለል (Persuaded) ጋር በቀጥታም፤ በዘወርዋራም የተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ ወዳጄ፤ ሰው ማለት ሀሳቡ ነውና አስብበት፡፡ ዴስካርተስ፤ ‹‹እኔነቴን (መኖሬን) የማውቀው ሰለማስብ ነው›› ያለው ቅኑንና ትክክለኛውን ብቻ ባይሆን Right or Wrong የሚል ይጨምርበት ነበር፡፡
ሠላም!!

Read 2100 times