Print this page
Saturday, 29 July 2017 12:07

ሉካንዳና ‘የቱሪዝም መዳረሻ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

    እንዴት ከረማችሁሳ!
ስሙኝማ ዓመቷ ሽው አለች አይደል! ገራሚ ዓመት ነው…እንዲሁ እንዳንጫነጨን ገብቶ አብሶብን ሊሄድ ነው፡፡
ዓመት ሁለት ዓመት ሲሄድ እያያችሁ
ጊዜው ገሠገሠ ለምን ትላላችሁ
በዘመነ ግሥገሣ ዕድሜያችን ተማርኮ
ያለፍነው እኛ ነን  ጊዜ አይደለም እኮ
ብለዋል ከበደ ሚካኤል፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “በደህና አውለህ፣ በደህና አሳደረኝ” ማለትን የመሰለ ነገር የለም እኮ! ሁላችንም የውስጥ ብሽቀታችንን በሆነ ባልሆነው፣ ምንም ባላደረገን ላይ የመወጣት ነገር አላኗኑር እያለን ነው፡፡
በቀደም እለት አንድ ወዳጃችን ከሆኑ ጓደኞቹ ጋር በስንት ጊዜያቸው ከከተማችን በአንዱ ቁርጥ ቤት ይገባሉ፡፡ ገና እንደተቀመጡ ዘወር፣ ዘወር እያሉ ሰዉን እያዩ ሲጨዋወቱ ማዶ የተቀመጠ ሰው ከመሀል አንዱን…
“ምን አፍጠህ ታየኛለህ!” ብሎ ይጮህበታል፡፡ የተጮኸበት ጓደኛቸው ይደነግጥና “እኔን ነው!” ይላል። “እኔን ነው!” አባባሉ የጠብ ሳይሆን የመገረም ነበር፡፡ ያኛው ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ
“አዎ፣ አንተን!” ብሎ የስድብ መአት ያዘንብበታል፡፡ ክፍሏ ትታመሳለች፡፡ ሁለቱም ያዙኝ ልቀቁኝ ሲባባሉ፣ የ‘ቁርጥ ሥጋ ማህበረሰቡ’ እንደምንም ይገላግላቸዋል፡፡
እንኳን እዚህ የሚያዳርስ ግጭት ሊኖር ቀደም ሲል ተያይተው የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ጠብ ፈላጊው፤ ሰው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከሠራተኞቹም ከሌሎችም ጋር ኃይለ ቃል ሲለዋወጥ ነበር አሉ፡፡ እኔ የምለው… ብስጭታችንን ሁሉ ምንም ያላደረገው ሰው ላይ ለመወጣት መሞከር  ከየት አገር የኮረጅነው ተሞክሮ ነው? ለዚህ ነው “በደህና አውለህ በደህና አሳደረኝ፣” ማለትን የመሰለ ነገር የለም የምንለው፡፡
እናላችሁ…ሰውየው ከተራ ስድቡ አልፎ አካባቢያዊ የሆኑ ቃላትን ጣል ሲያደርግ ነበር አሉ፡፡ እኔ የምለው…‘ከዚህ ነህ፣’ ‘ከዛ ነህ፣’ ሳንባባል ምግብ እንኳን መብላት ሊያቅተን ነው!
“የት ነው የተወለድከው?”
“የት ነው የተወለድከው!”
“አዎ ቀላል ጥያቄ ነው፣ የት ነው የተወለድከው?”
“የተወለድኩት…የተወለድኩት…”
“የተወለድክበትን የምትናገረው ገና አስበህ ነው…”
“አዎ…ለአንተ የሚመችህን ቦታ እየመረጥኩ ነው…”
“ምን ለማለት ነው…”
“አንተ የተወለድክበት አካባቢ ከሆነ ጭቅጭቁን
ትተወኛለሀ!”
እናማ ምግብ እንኳን ስንበላ የየት አካባቢ ሰው እንደሆንን ማወቅ ለሚፈልጉ “የአንተን ንገረኝና በልክህ እሰፋዋለሁ” ምናምን ማለቱ ሳይሻል አይቀርም። ቢያንስ፣ ቢያንስ ምግባችንን በሰላም በልተን እንወጣለን፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የጥሬ ሥጋ ነገር ሲነሳ፣ ሀሳብ አለን…እንግዲህ ቱሪስት የሚመጣው ለየት ያለ ነገር ፍለጋም አይደል! የልዩ፣ ልዩ የዶሮ ማነቂያ የቱሪስት መዳረሻ የማይሆኑትሳ! አንድም ሌላ ቦታ ያጣናትን ‘ፎሪን ከረንሲ’ ምናምን በዚህ እናገኝ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጭኑ ሀበሻ ጥሬ ሥጋውን እንዴት እንደሚጨረግደው ቢያዩ አሪፍ ነው። ልክ ነዋ… ሀገራት ‘አንተ፣ አንቺ’ እያሉ በሚፎካከሩበት ዘመን፣ ምድረ የለየለት ጠላት ወይም ጠላት ሊሆን ያሰበ ሁሉ…አለ አይደል… “ምንም ያላደረጋቸው በሬ ላይ እንደዚህ የሆኑ እኛን ምን ሊያደርጉን ይችላሉ!” ብሎ አርፎ ይቀመጣላ!
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደ ጥሬ ሥጋ አበላላችን እኮ ከበሬውና ከሰባት ቤቱ ጋር ትውልዶች የተሻገረ ቂም ያለን ነው የምንመስለው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…በእርሻ ቦታ ላይ እንደገረፍነው፣ ግጦሽ ላይ እንደገረፍነው፣ ወደ ገበያ ስንነዳው እንደገርፍነው፣ ወደ ቄራ ስንጭነው እንደገረፍነው…እንደገና ሥጋውን ስንበላ እንደጨረገድነው! የበሬ የሙት መንፈስ የለውም ያለው ማነው! ሊኖረው ይችላላ! ብቻ አንድ ቀን እንደ ሀምሌት መንፈስ… አለ አይደል… የ‘ዳለቻ’ው መንፈስ  መጥቶ… “በህይወት እንደዛ ስታንገላቱኝ ኖራችሁ ምናለ ሞቼ እንኳን ባርፍበት!” ያለ እንደሁ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁሉም በሩን በሚከረችምበት ዘመን “ኸረ የሰው ያለህ!” ብሎ መጣራት እንኳን ያስቸግራል፡፡  (በነገራችን ላይ፣ ስንት “ምናለ ሞቼ እንኳን ባርፍበት!” የሚሉ የአገር ልጆች ይኖሩ ይሆን!)
እናላችሁ… በፊት እኮ በየመሥሪያ ቤቱ የጥሬ ሥጋ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ቅዳሜ፣ ቅዳሜ ሉካንዳዎቹ ጢም ይሉ የነበረው ዝም ብሎ አልነበረም፡፡ አሁን፣ አሁን ‘የቁርጥ ሥጋ ቡድን’ ነገር ታሪክ እየሆነ ነው፡፡ ለነገሩ አይገርምም፡፡ ልክ ነዋ…ቁርጥ ቲሚቲም የቅልውጥ ምግብ በሆነበት፣ ቁርጥ ሥጋ ከማግኘት የማርስን ደርሶ መልስ ትኬት ከእንትን የሬድዮ ሾው ማግኘት ይቀላል፡፡
ሀሳብ አለን… እንግዲህ ጊዜውን ተከትሎ መሄድ ያስፈልግ የለ… ማህበራዊው ኑሮ እንዳይናጋ የሹሮ ቡድኖች የማይመሰረቱሳ!  የሥጋና የሹሮ ዋጋ እንደሁ “የሳንቲም ልዩነት ብቻ ነው…” ሊባል በደረሰበት፣ ሹሮ ራሷ ለይቶላት ቪአይፒ ከመሆኗ በፊት ብናውቅበት አሪፍ ነው፡፡ (ወዳጄ፣ “ሹሮ ሁለት መቶ ሀምሳ ብር”  ያልከኝ የተፈጨ ኩንታሉን ማለትህ ነበር እንዴ! ምግብ ቤቶችም ሹሮ እያስፈጩ መሸጥ ጀመሩ ማለት ነው!)
በነገራችን ላይ፣ ጥሬ ሥጋ የ‘ወንድነት መለኪያ’ ነበር አሉ፡፡ (ጊዜ እንዲህ ‘ሊለውጠን!’ ቂ…ቂ…ቂ…) እኛ እኮ “ጥሬ ሥጋና በርበሬ አይስማማኝም” ስንል… ‘ድሮስ አልጫ!’ የሚሉን ለጨዋታ ይመስለን ነበር፡፡ አያውቁትም እንጂ ቢያውቁት ኖሮ…
የለመደው መሸሽ የለመደው
በመጫኛም ቢያስሩት ሄደ እየጎመደው
ይለን ነበር፡፡ መሸሹ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ እስካለው ድረስ አይደለም በመጫኛ በካቦ ቢያስሩንም እየጎመድነው መሄዳችን አይቀርም፡፡
ስሙኝማ…ጥሬ ሥጋ በጠፋበት … “ሻሽ የመሰለ ቀይ ጥሬ ሥጋ አማረኝ!” የምትል ነፍስ ጡር ሚስት ያለው  አባወራ የምር ያሳዝናል፡፡ ጥሬ ሥጋ ከምትጠይቀው… “የሞንጎሊያ ምንቸት አብሽ አምሮኛል፣” ብላ ብትጠይቅ ማሟላት ይቀል ይሆናል! ግን መጀመሪያ የዓለም ካርታ አምጥቶ “ሞንጎሊያ ያለችበትን አሳዪኝና ነገ ጠዋት በመጀመሪያው አውቶብስ እሄዳለሁ” ማለት ነው፡፡
የምር ግን…አለ አይደል…ከጥሬ ሥጋ ጋር የተበላሸውን ግንኙነታችንን ከማደሳችን በፊት መካከለኛ ገቢ የሚባለውን ፌርማታ አልፈነው ልንሄድ እንችላለን፡፡ ከእሱ ነገር ጋር ቀጠሮ ከያዝን ስንት ጊዜ ሆነን አይደል፡፡ ችግሩ እኛ ተጠጋን ስንል ‘መካከለኛ ገቢ’ የሚባለው መስመር እየሸሸ መሄዱ፡፡
በነገራችን ላይ ያልተዘመረለት ምግብ ቢኖር ፍርፍር ነው፡፡ የምር…ፍርፍር ባይኖር ኖሮ፣ ራሱ ጥብቅና ምን ይሆን እንደነበር ማሰብ አይቻልም፡፡  ቂ…ቂ…ቂ…. አንድ ኪሎ ስጋ አሁን በልተዋት ትንሽ ቆይታ ልትጠፋ ትችላለች፡፡ አንድ ሳህን ፍርፍር ግን እግዚአብሔርን ካልፈሩ መብላት ተጀምሮ ‘ቱ ቢ ኮንቲኒዩድ’ ብሎ ለተከታዩ ቀን እንድትቆይ ማድረግም ይቻላል፡፡ እስከዛ ድረስ አይርብማ!
እና…ሉካንዳ ቤቶች በቱሪስት መዳረሻነት ይመዝገቡልንማ! እኛ ቢያቅተንም… አለ አይደል… እነሱ ከእለታት አንድ ቀን… “ጥሬ ሥጋ የመብላት ተሞክሮ የቀሰምነው ከሀበሻ ልጆች ነው” ብለው ‘ያስጨበጭቡልን’ ይሆናል፤ ጤፍን “ፈረንጅ ወደዳት” ብለን እኛ ‘እንዳጨበጨብነው’ ማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3687 times