Saturday, 29 July 2017 12:11

የሦስተኛው “ንባብ ለህይወት” ትሩፋቶች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   · ለ5 ቀናት የሚዘልቀው አውደርዕይ ትላንት ተከፍቷል፡፡
               · ኬኔዲ ላይብረሪ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በኢንተርኔት ሊያቀርብ ነው
               · 28 መፅሐፍት በ5ቱ ቀናት ውስጥ ይመረቃሉ
                  
       አገራችን ውስጥ ብዙ ሊሰራበት የሚገባውን የንባብ ባህል ለማዳበር አልሞ ከሶስት ዓመት በፊት የተቋቋመው “ንባብ ለህይወት”፤ ትላንት ከ5፡30 ሰዓት ጀምሮ በኤግዚቢሽን ማዕከል 3ኛው ዙር በድምቀት ተከፍቷል፡፡ እስከ ማክሰኞ አመሻሽ ክፍት ሆኖ በሚቆየው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ከሁለት መቶ በላይ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት ሲሆን በተለይ ከዚህ ቀደም ተሳትፈው የማያውቁት እንደ ቡክ ወርልድ፣ ቡክ ኮርነር፣ ቡክ ላይት፣ ቡክ ላክ ፐብሊሸርስ፣ ዩኒቨርሳልና  ሌሎችም ትልልቅ ድርጅቶች መሳተፋቸውን  የንባብ ለህይወት መስራችና ዋና አዘጋጅ፣ አቶ ቢኒያም ከበደ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ እንደ ትልቅ የምስራች የሚቆጠር ዜና አለ” ያሉት አቶ ቢኒያም፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ኬኔዲ ላይብረሪ ባልተለመደ ሁኔታ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በኢንተርኔት ማቅረብ መጀመሩን ይፋ የሚያደርገው በዚሁ አውደርዕይ ላይ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ሁለት ዓመታት ትልቅ በጀት በመመደብ፣ ዳታ ቤዝ በማዘጋጀት ሸልፍ ላይ ያለምንም ጥቅም አቧራ ሲጠጡ የነበሩትን የጥናትና ምርምር ውጤቶች፣ ለማንኛውም ተጠቃሚ ስራ ላይ እንዲውሉ ኦን ላይን ለማቅረብ መዘጋጀቱን አቶ ቢኒያም አድንቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር፣ እና ቡክ ኤይድ ኢንተርናሽናል ከንባብ ለህይወት ጋር በመተባበር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢ-ቡኮችን ለተጠቃሚ የሚያቀርቡ ሲሆን በኤግዚቢሽን ማዕከል በርካታ ኮምፒዩተሮች ለተጠቃሚ ዝግጁ መሆናቸውንና በተለይ የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እነዚህን ኢ-ቡኮች ለማጣቀሻነት እንዲጠቀሙ በነፃ መቅረቡ፣ ንባብ ለህይወት የተቋቋመበትን አላማ ከዓመት ዓመት እያሳካ መሆኑን እንደሚያመላክት የገለፁት አቶ ቢኒያም፤ በመጀመሪያው በመቶ ሺህ፣ በሁለተኛው 500 ሺህ እያለ ዘንድሮ የኢ-ቡኮቹ መጠን ከሚሊዮን በላይ መድረሱ፣ የንባብ ለህይወት ስኬት አንዱ መገለጫ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
አምስት ቀናት በሚዘልቀው ንባብ ለህይወት አውደርዕይ ላይ በግጥም በልብ ወለድ፣ በታሪክና በምርምር ዙሪያ የተፃፉ 28 መፅሐፎች ለምርቃት የሚበቁ ሲሆን እስከ ዛሬ ከሚመረቁት ቁጥራቸው እየላቀ መምጣቱንና በቀጣዩ ዓመት ከዚህ በላይ መፅሐፍት ይመረቃሉ ብለው እንደሚያምኑም አቶ ቢኒያም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  
‹‹የዘንድሮውን ንባብ ለህይወት ለየት ከሚያደርጉት መካከል የእምነት ተቋማት እንደየአስተምህሮታቸው መፅሀፍትን ይዘው ተሳታፊ መሆናቸው ንባብ ለህይወት በየዘርፉ እያደገና ልዩነት እያመጣ መሆኑን ያመላክታል›› ብለዋል፡፡
የህፃናት ጉዳይ በንባብ ለህይወት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የሚያስረዱት አዘጋጁ፤ ዘንድሮ ኤዞፕ፣ ሚዳቆ አሳታሚዎች፣ ጦቢያ መፃኅፍት፣ የኢትዮጵያ ልጆች መፃኅፍትና ማርታ ዳዲ በርካታ የህፃናት መፃህፍትን ይዘው እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡ መፃህፍት ሻጮች መፅሀፍት ላይ  የተደረጉትን ቅናሾች በግልፅ በሚታይ ቦታ የሚለጥፉ በመሆኑ፣ ጎብኚዎች የትኛውን መፅሀፍ በየትኛው ዋጋ እንደሚገዙ ግልፅ ይሆንላቸዋል፤ ከመደናገርና ከአላስፈላጊ ወጭም ይድናሉ ተብሏል፡፡
በዚህ የመፅሀፍት ኤግዚቢሽንና የንባብ አውደ ርዕይ ላይ በየቀኑ ተጋባዥ እንግዶች እየመጡ፣ በንባብ ባህል ላይ ለታዳሚው ንግግርና ምክክር ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን ከተጋባዦቹ መካከል የፍልስፍና ሊቁ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ የታሪክ ባለሙያው አበባው አያሌው፣ የሥነ ልሳንና መምህሩ አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ ዶ/ር ዘላለም ጌታቸውና አቶ መኮንን ፀጋዬ እንደሚገኙበትና እነዚህ ተጋባዦች ለአዋቂዎች የሚሆኑ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርቡም ተጠቁሟል፡፡
የልጆችን ጉዳይ በተመለከተ ህፃናት የንባብ ክህሎትን እንዴት ያዳብሩ በሚለው ዙሪያ ከወላጆች ጋር ውይይት የሚደረግ ሲሆን የትነበርሽ ንጉሴ፣ ሀረገወይን አሰፋ፣ እንዳለ ጌታ ከበደ፣ መቅደስ አለም እና ህብስት አሰፋ (ኪኪ) የተመረጡ ታሪኮችን በየቀኑ ከ4-6 ሰዓት እንደሚያነቡም ተገልጿል፡፡ ዘንድሮም እንደተለመደው የወርቅ ብዕር ተሸላሚ ይኖራል ያሉት አቶ ቢኒያም እንደሚታወሰው በ2007 በመጀመሪያው ንባብ ለህይወት የወርቅ ብዕር ተሸላሚ የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ  ሲሆኑ በሁለተኛው ማለትም ባለፈው ዓመት ደግሞ ታዋቂው የረጅም ልቦለድ ደራሲ አዳም ረታ የወርቅ ብዕር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ ማን ይሆን  የሚለው ይፋ ባይሆንም በአውደ ርዕዩ የመዝጊያ ምሽት ማክሰኞ ማታ ይታወቃል፤ የዘንድሮ ተሸላሚ ያልተዘመረላቸው ነገር ግን ለስነ-ፅሁፉ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ በተለይ አንዱ መፅሀፋቸው በ8 ቋንቋዎች የተተረጉሙላቸው አንጋፋ ፀሀፊ እንዲሆኑ ጠቆም አደርገዋል፡፡
ይህንን አውደ ርዕይ ከመቶ ሺህ ሰው በላይ ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አዘጋጆቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ብራና፣ ቦሌ፣ ሜጋ፣ ብርሀንና ሰላምና ሌሎችም ትልልቅ ማተሚያ ቤቶች ተሳታፊ ሲሆኑ ሚዲያዎችም የየራሳቸውን ስራዎች ይዘው እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም የንባብ ለህይወት ዋና አዘጋጅ አቶ ቢኒያም ከበደ ደራሲያን ማህበርን፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮን ትምህርት ሚኒስቴርን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ላደረጉላቸው ድጋፍና ሙያዊ እገዛ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ለንባብ ፍቅር ያለው በሙሉ በአምስቱ ቀናት በነፃ በመታደም መፅሀፍትን በቅናሽ እንዲገዙ፣ በሚቀርቡ ፕሮግራሞች እውቀት እንዲሸምቱና የልጆችን የንባብ ክህሎት እንዲያሳድጉ ግብዣ አቅርበዋል፡፡

Read 613 times