Sunday, 30 July 2017 00:00

የተዘነጋው ወልደ ሕይወት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(4 votes)

 “-- ወልደ ህይወት “ሌባና ቀማኛ” የሚለው ፊውዳላዊውን የገባር ሥርዓት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የልሒቃን ታሪክ ውስጥ የገባሩን ሥርዓት
ለመጀመሪያ ጊዜ የተቸው ወልደ ህይወት ነው - በ17ኛው ክ/ዘመን፡፡ ከወልደ ህይወት 200 ዓመታት በኋላ የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ሰፋፊ
የመሬት ይዞታዎችን ለጭሰኞች በማከፋፈል የገባሩን ህዝብ ሸክም ለማቃለል ሙከራ አድርገው ነበር፡፡--”
               
     የኢትዮጵያ ፍልስፍና በኢትዮጵያ የሥነ ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ይሄንን ዘውግ የመሰረቱት ፈላስፎቻችን ደግሞ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ናቸው፡፡ ብዙ የሀገራችን አንባብያን የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሲባል ወዲያው ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ዘርዓያዕቆብ ብቻ ነው፡፡ አስተማሪን ከተማሪው መነጠል አይቻልምና እኔም በዚች ፅሁፌ የዘርዓያዕቆብ ብቸኛ ተማሪ ስለነበረው ስለ ወልደ ሕይወት አንዳንድ ነገሮች ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
ወልደ ሕይወት ከዘርዓያዕቆብ ጋር ከ1626 - 1685 ዓ.ም ድረስ ለ59 ዓመታት በእንፍራንዝ፣ ደቡብ ጎንደር አንድ ላይ የኖረ ሲሆን፣ ፍልስፍናንና የሃይማኖት ትምህርትንም ከዘርዓያዕቆብ ተምሯል፡፡ በነገራችን ላይ በጥንቱ የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የቅኔ ወንበር፣ የዜማ (የድጓ) ወንበር፣ የትርጓሜ ወንበር ... እየተባለ በቤተ ክርስትያን ሊቃውንት የሚመሩ ትምህርት ቤቶችን መክፈት በጣም የተለመደ ነው፤ አሁንም ድረስ፡፡ ፍልስፍናንና ሃይማኖትን በማጣመር ለመጀመሪያ ጊዜ ወንበር የዘረጋው ግን ዘርዓያዕቆብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወልደ ሕይወት ከሌሎች የሀገራችን ሊቃውንቶች ለየት ያለ ሐሳብ ይዞ የመጣው፡፡
የወልደ ህይወት ፍልስፍና የዘርዓያዕቆብ ቅጥያ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከዘርዓያዕቆብ ወደ ወልደ ህይወት የተደረገው ሽግግር ዕድገትም ምልሰትም አለው፡፡
“ሽግግሩ ዕድገት አለው” የምንለው ከስፋት እና ከአቀራረብ (Scope and method) — ከሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ብዛት፣ ስፋትና የማስተማር ስነ ዘዴ አንፃር ሲሆን፤ “ሽግግሩ ምልሰት አለው” የምንለው ደግሞ ከይዘትና ከአዲስነት (Content and originality) — ከርዕሰ ጉዳዮቹ ጥንካሬና ከአዲስነት አንፃር ነው፡፡ እስቲ ሁለቱን በየተራ እንመልከታቸው፡፡
ከይዘትና ከአዲስነት አንፃር
ከይዘትና ከአዲስነት አንፃር ከዘርዓያዕቆብ ወደ ወልደ ህይወት የቀጠለው ፍልስፍና “ምልሰት” አለው — ቀንሷል፡፡ አብዛኛዎቹ ወልደ ህይወት ያነሳቸው ሐሳቦች አስቀድሞ በዘርዓያዕቆብ የተነሱ ናቸው፡፡ በርግጥ ዘርዓያዕቆብ ያላነሳቸው ሆኖም ግን በወልደ ህይወት ብቻ የተነሱ ሐሳቦችም አሉ። ለምሳሌ፡- ስለ ህፃናት አስተዳደግ፣ ስለ አለባበስ፣ ስለ ፍቺ፣ ስለ ስልጣንና የመንግስት ሹመት፣ ስለ መላዕክት እንዲሁም ስለ ሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ፅፏል፡፡
ወልደ ህይወት ስለ ስልጣንና የመንግስት ሹመት ማንሳቱ በዘርዓያዕቆብ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፍልስፍና ገና የመጀመሪያው ትውልድ ላይ አድማሱን እያሰፋ ከሃይማኖታዊና ከማህበራዊ ትችቶች ወደ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የመስፋት አዝማሚያ መጀመሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ምንም እንኳ ከላይ “የወልደ ህይወት ብቻ” ተብለው የቀረቡ ሐሳቦችን ዘርዓያዕቆብ ባያነሳቸውም፣ አብዛኛዎቹ ግን በሃይማኖታዊ ትምህርት አማካኝነት ህብረተሰቡ ውስጥ ሲነገሩ የነበሩ በመሆናቸው ሐሳቦቹን የወልደ ህይወት አዲስ (original) ሐሳብ አድርገን መውሰድ አንችልም፡፡
በርግጥ የወልደ ህይወትን አቀራረብ ለየት የሚያደርገው በመፅሐፍ ቅዱስ የሚታወቁ ሐሳቦችን ሲፅፋቸው የአብዛኛዎቹን ማሳመኛቸውን ከእምነት ወደ አመክንዮ እየቀየረ መሆኑ ነው፡፡ ይሄም ተግባሩ የሚያስደንቀው ነው፤ እንደ ኦገስቲንና አኳይነስ ትንታኔዎችን የሰሩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡
የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና አስፈሪ ያደረገው ማህበረሰቡ የቆመባቸውን መሰረታዊ ሃሳቦችን፣ ልማዶችንና እምነቶችን ስለሚነቀንቅ ነው። በዚህ ረገድ ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብን ሐሳቦች ደገማቸው እንጂ ህብረተሰቡን የሚነቀንቅ አዲስ ትችት አላመጣም፡፡
እንዲያውም የወልደ ህይወት አብዛኛዎቹ ሐሳቦች ወደ ማህበራዊ ምክር ያመዝናሉ፡፡ ከዚህ ግምገማ አንፃር ከአስተማሪው ጋር ስናነፃፅረው፣ ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ከማህበራዊ ትችት ወደ  ማህበራዊ ምክር አውርዶታል ማለት እንችላለን፡፡
ሌላው፣ ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብን ሐሳብ እንዳለ ከመቀበል ውጭ አስተማሪውን ለመተቸት አለመድፈሩ እንደ ድክመት ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ከአንድ ሐሳብ በስተቀር ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብ ቅጣይ ነው፤ ይሄም ሐሳብ የሴቶች ጉዳይ ነው፡፡
ዘርዓያዕቆብ በሐተታው ምዕራፍ 12 ላይ “ባልና ሚስት በጋብቻ እኩል ናቸው፤” ሲል፤
ወልደ ህይወት ግን “ሴቶች በተፈጥሮ ደካማ ሲሆኑ በማሰብ ችሎታቸውም ከወንዶች ያንሳሉ፤” ይላል (ምዕራፍ 26)፡፡
በፍልስፍና ውስጥ ተማሪው አስተማሪውን መተቸት በጣም የተለመደና የሐሳብ ዕድገትንም የሚያመላክት ነው፡፡ ተማሪ አስተማሪውን ለምን መተቸት እንዳለበት ደግሞ “መርሁ”ን አርስቶትል ነግሮናል፤ እንዲህ በማለት፣
ፕሌቶ የተከበረ ነው፤ እውነት ግን የበለጠ የተከበረች ናት!!
Plato is dear; but, Truth is the dearest!!
አርስቶትል የፕሌቶ ተማሪ ነው፤ ሆኖም ግን ፕሌቶን በመተቸት አርስቶትልን የሚያህል የለም። ተማሪ አስተማሪውን የሚተቸው ከክብር ማጣት የተነሳ ሳይሆን ስለ እውነት ሲባል ነው — ለእውነት በመወገን!!
በዘርዓያዕቆብና በወልደ ህይወት መካከል እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ያልታየው፣ ከይዘትና ከጥልቀት አንፃር ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ስላላሳደገው ነው፡፡ እንዲያውም ወልደ ህይወት የሐተታው የመጨረሻዎቹ ምዕራፍ አካባቢ ፈላስፋነቱን ይረሳና ፍፁም የእምነት ሰው እየሆነ ይሄዳል፡፡
ከስፋትና ከአቀራረብ አንፃር
ከርዕሰ ጉዳዮች ስፋትና ብዛት አንፃር ወልደ ህይወት የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ይበልጥ አስፋፍቶታል፡፡ የሐተታዎቻቸውን የምዕራፍ ብዛት ብንመለከት እንኳን የወልደ ህይወት መፅሐፍ ከዘርዓያዕቆብ በ20 ምዕራፎች ይበልጣል፤ የዘርዓያዕቆብ ሐተታ 15 ምዕራፎች ሲኖሩት፣ የወልደ ህይወት ሐተታ ግን 35 ምዕራፎች አሉት።  በምዕራፎቹ ብዛት ልክም ወልደ ህይወት የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሰፊና ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስለ ጤና እንክብካቤ፣ ስለ ስራና ተግባረዕድ (የእጅ ሙያ)፣ ስለ ጋብቻና ምንኩስና፣ ስለ አመጋገብና ፆም፣ ስለ በይነ ዲሲፕሊን ትምህርቶች አስፈላጊነት (ከአንድ ቀኖናዊ ትምህርት መውጣት እንዳለብን) እንዲሁም እምነትን፣ አፈታሪክንና ልማድን ስለ መፈተሽ ዘርዓያዕቆብ አስቀድሞ የፃፈባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ቢሆኑም ወልደ ህይወት ግን ይበልጥ አስፋፍቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ፍልስፍና በማጥናት በጣም የሚታወቀው ካናዳዊው ፕ/ር ክላውድ ሰምነር፣ በወልደ ህይወት በ2 ነገሮቹ አብዝቶ ይመሰጣል፤ የመጀመሪያው በማስተማር ስነ ዘዴው ነው፡፡ ምንም እንኳ ወልደ ህይወት በአመዛኙ የራሱን አዲስ ሐሳብ ይዞ ባይመጣም የማስተማር ስነ ዘዴው ግን ምርጥ ነው፡፡ ክላውድ ሰምነርም ይሄንን ይመሰክራል፡፡ እንዲህ በማለት፡-
ምንም እንኳ የወልደ ህይወት ሐሳቦች በመሰረቱ ከዘርዓያዕቆብ የወሰዳቸው ቢሆንም ሐሳቦቹን ለሰው በማስረዳት ረገድ ግን ወልደ ህይወት በጣም የተዋጣለት ነው፡፡ በተለይ ምክሮችንና ተግሳፆችን በምሳሌና በወግ እያጀበ የሚያቀርብበት መንገድ ሲበዛ መሳጭ ነው፤ የማህበረሰቡን ስነልቦናም በደንብ ያገናዘበ ነው፡፡ ባጠቃላይ ወልደ ህይወት ምርጥ መምህር ነው፡፡
ሁለተኛው፣ ወልደ ህይወት ስራና የእጅ ሙያ ላይ ባለው ፅኑ አቋም ነው፡፡ የመሬት ከበርቴው የጭሰኛውን ጉልበት በሚበዘብዝባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፣ የእጅ ሙያ መሰደቢያ በሆነባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፣ የጉልበት ስራ ለመኳንንት ልጆች አይገባም በሚባልባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ ላይ ወልደ ህይወት ስለ እጅ ሙያ የፃፈው ነገር አጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በሐተታው ምዕራፍ 18 ላይ ወልደ ህይወት እንዲህ ይላል፡-
የእጅ ስራን መስራት ውደድ፤ ከአኗኗርህ ጋር ይስማማልና፡፡ የእጅ ስራ መስራት አትፈር፡፡ ያለ እጅ ስራ የተፈጠረ ሰው ሁሉ ይጠፋል፤ አኗኗሩም ሁሉ ይፈርሳል፡፡ “የእጅ ስራን መስራት ግን ለድሆችና ለገበሬዎች፣ ለአንጥረኞችና ለግንበኞች፣ ለገባርም ልጆች የተገባ ሲሆን፤ ለታላቆችና ለከበርቴ ልጆች ግን አይገባቸውም” አትበል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በፍላጎቱ እኩል ነው፡፡ እንደዚህ የሚል ህሊና ከትዕቢተኛ ልብ የሚመነጭ ነውና፡፡ መስራት እየተቻለው የሌላውን ድካም የሚበላ ግን ሌባና ቀማኛ ነው፡፡ አንተ ግን ከትንሽነትህ ጀምረህ የእጅ ስራን መስራት ልመድ፡፡
ክላውድ ሰምነር ይሄንን የወልደ ህይወት ሐሳብ “በፊውዳላዊት ኢትዮጵያ የስራ ባህል ላይ የተሰነዘረ አብዮታዊ ሐሳብ” ይለዋል፡፡ ሰው ሥራ እየጠላ “ወታደር” በሚሆንባት ሀገር ላይ ወልደ ህይወት ስለ ሥራ የፃፈው ነገር እውነትም አብዮታዊ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ወልደ ህይወት “ሌባና ቀማኛ” የሚለው ፊውዳላዊውን የገባር ሥርዓት ነው። በኢትዮጵያ የልሒቃን ታሪክ ውስጥ የገባሩን ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቸው ወልደ ህይወት ነው - በ17ኛው ክ/ዘ፡፡ ከወልደ ህይወት 200 ዓመታት በኋላ የመጡት አፄ ቴዎድሮስ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን ለጭሰኞች በማከፋፈል የገባሩን ህዝብ ሸክም ለማቃለል ሙከራ አድርገው ነበር።
ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የገባሩን ህዝብ ህመም ሲፅፉለት የነበሩት በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ እነ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ በጅሮንድ ተ/ሐዋርያት ተ/ማርያም እና ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ናቸው። ይሄም ከወልደ ህይወት 260 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። ወልደ ሕይወት አስቀድሞ 17ኛው ክ/ዘ ላይ የነቀፈው አስከፊው የገባሩ ሥርዓት ግን የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የመወሰን ኃይል እንደነበረው የታየው ሀገሪቱን ውጥንቅጥ ውስጥ በከተታትና እስከ አሁንም ድረስ ልትሻገረው ያልቻለችው አበሳ ውስጥ በከተታት የ1966ቱ “የመሬት ላራሹ“ አብዮት ነው፡፡
ወልደ ህይወት በሐተታው ምዕራፍ 20 ላይ ስለ አመጋገብ የፃፈውም ነገር እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በየቴሌቪዥን ጣቢያው የምግብ አዘገጃጀት ፕሮግራሞችን መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ወልደ ህይወት ከዛሬ 350 ዓመት በፊት የምግብ ዝግጅት እንደ አንድ ሙያ መታየት እንዳለበትና ምግባችንንም በዕውቀት እያዘጋጀን በትኩስነቱ እንድንመገብ መክሮናል፡፡ ከአመጋገብ ጋር በተገናኘ አብዛኛው ህዝባችን አሁንም ድረስ የዕውቀት ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ወልደ ህይወት ግን በ17ኛው ክ/ዘ በተመጣጠነ ምግብ አካሉና መንፈሱ የዳበረ ዜጋ መፍጠር እንዳለብን መክሮናል፡፡
ክላውድ ሰምነር ባያነሳውም ወልደ ህይወት በሐተታው ምዕራፍ 24 ላይ ስለ ሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ተጨንቆ የፃፈው ነገርም እጅግ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ወልደ ህይወት እንዲህ ይላል፡-
የሩካቤን ጣዕም ከሚስትህ ጋር ተካፈለው እንጂ ለብቻህ አትሻው፡፡ ከአንተ እርካታ ኋላ ቀርታ ጣዕሙ እንደይጎድልባት፣ እርሷም በአንተ እስክትደሰት ጠብቃት እንጂ እግዚአብሔር የሰጣትን ፈንታዋን ከልክለህ በችኮላ አታድርገው፡፡ ይህንንም ፍቅር ካላደረክላት ታዝንብሃለች፣ ትንቅሃለች፡፡ ጋብቻህም ለእግዚአብሔር በረከት የተዘጋጀ አይሆንም፡፡
በትዳር ውስጥ ሳይቀር ስለ ወሲብ ማውራት ነውር በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ጭራሽ ስለ ሴቷ የወሲብ እርካታ ተጨንቆ መፃፍ እጅግ በጣም አስገራሚ ነው። አሁን ባለንበት ዘመን እንኳ ወንዱ የራሱን ወሲባዊ እርካታ እንጂ ስለ ሴቷ ስሜት ብዙም አይጨነቅም፡፡ ይሄም ነገር በተለይ በትዳር ውስጥ ቤተሰብ እስከመበተን የሚያደርስ አደጋ ቢኖረውም በህብረተሰቡ ውስጥ ግን በግልፅ አይወራም፡፡ ወልደ ህይወት ይሄንን የየጓዳችንን ገመና ነው ወደ አደባባይ አውጥቶ እንወያይበት ያለው። ዘርዓያዕቆብ ስለ ሴቶች መብት የተከራከረ ቢሆንም የስሜቷን ነገር ግን ረስቶት ነበረ፤ ይሄንን ክፍተት ያሟላውና የሴቶችን ጥያቄ ምልዑ ያደረገው ወልደ ህይወት ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው፤ የ”ፍልስፍና ፩ እና ፪” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 9151 times