Saturday, 29 July 2017 12:34

ኢራንና ሩስያ በማዕቀብ ጉዳይ አሜሪካን አስጠንቅቀዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አሜሪካ በኢራንና በሩስያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን ለመጣል እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት፣ የሁለቱ አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ማዕቀብ የምትጥይብን ከሆነ ምላሻችን የከፋ ነው ሲሉ አሜሪካን አስጠንቅቀዋል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ ከቴህራን እንደዘገበው፣ የአሜሪካ ኮንግረስ በኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም ላይ በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ ለመጣል የታሰበውን ህግ የሚያጸድቀው ከሆነ፣ አገራቸው የከፋ ምላሽ እንደምትሰጥ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ ባለፈው ረቡዕ አስጠንቅቀዋል፡፡
ኢራን በባለስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሟ ላይ በሚሳተፉ ግለሰቦችና ከእነሱ ጋር የንግድ ግንኙነት ባለው ማንኛውም አካል ላይ የከፋ ቅጣትና ማዕቀብ ለመጣል በእንቅስቃሴ ላይ የምትገኘው አሜሪካ ያሰበቺውን የምታደርግ ከሆነ፣ አገራቸው ጥቅሟን ለማስከበር ስትል አፋጣኝ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቀዋል፡፡ አሜሪካ በኢራን ላይ ለመጣል ባሰበቺው አዲሱ ማዕቀብ፣ በአገሪቱ የጦር ሃይል ላይ የሽብርተኝነት ማዕቀቦችን እስከመጣል እና የጦር መሳሪያ እገዳ እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል መነገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፣ አሜሪካ ልትጥልባት ያሰበቺው አዲስ ማዕቀብ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ባለፈው ረቡዕ ማስጠንቀቋን ሮይተርስ ዘግቧል። የሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ራብኮቭ፣ አሜሪካ በሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል እያደረገቺው የምትገኘው እንቅስቃሴ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚቻልበትን ዕድል የሚያጨልምና ግንኙነቱን ወደባሰ መሻከር የሚያመራ እንደሆነ ባለፈው ረቡዕ ከኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የማዕቀብ ዕቅድ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሩስያ መንግስት ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር፣ በፕሬዚዳንት ፑቲን በሚሰጥ ውሳኔ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑንም የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ፣ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ያሻሽሉታል የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም፣ ሩስያ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች በሚል የተፈጠረው አተካሮ ተስፋውን እንዳጨለመው ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 3687 times