Monday, 31 July 2017 00:00

ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ ግዙፉን የጦር ሰፈር አስመረቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

         43 የመንግስት ተቃዋሚ ግብጻውያን በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

       የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ በአገሪቱ የድንበር ከተሞች የሚገኙ ተቋማትንና ፕሮጀክቶችን ከጥቃት ለመከላከል ታስቦ የተገነባውንና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ በግዙፍነቱ ቀዳሚው እንደሆነ የተነገረለትን አዲስ የጦር ሰፈር መርቀው መክፈታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የተለያዩ የአረብ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተመርቆ የተከፈተው ይህ የጦር ሰፈር፣ ከአሌክሳንድሪያ በስተምዕራብ በማርሳ ማትሮ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ኖጊብ ስም መሰየሙም ተነግሯል፡፡
የግብጽ መንግስት ታጣቂዎች ወደ ግዛቱ ሰርገው እንዳይገቡ ለመከላከል ሲል አገሪቱን ከሊቢያ ጋር በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ ባራኒ የተባለ የጦር ሰፈር ማቋቋሙን በቅርቡ ማስታወቁንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በአገሪቱ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት መንግስትን ተቃውመዋል ባላቸው 43 ዜጎች ላይ ባለፈው ማክሰኞ የዕድሜ ልክ እስራት ቅጣት ማስተላለፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በ2011 መጨረሻ መንግስትን ተቃውመው በመዲናይቱ ካይሮ አደባባይ በመውጣት ብጥብጥ ፈጥረዋል፣ አመጽ ቀስቅሰዋል፣ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል የተከሰሱት ግለሰቦቹ፣ በወቅቱ በተፈጸመው ግጭት 17 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንዲዳረጉና 2 ሺህ ያህል ሌሎች ግብጻውያን እንዲቆስሉ ሰበብ ሆነዋል መባሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በዕድሜ ልክ እስራት ከመቅጣቱ ባለፈም፣ በወቅቱ በህዝብ ተቋማት ላይ ለፈጸሙት የዝርፊያ ወንጀል በድምሩ ከ948 ሺህ ዶላር በላይ እንዲከፍሉ የገንዘብ ቅጣት እንደጣለባቸውም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ 9 ግብጻውያን በአስር አመት እስራት፣ አንድ ግለሰብ ደግሞ በአምስት አመት እስራት መቀጣቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል።

Read 2193 times