Monday, 31 July 2017 00:00

ትራምፕ ሙሉ ደመወዛቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር ለገሱ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    ደመወዝ የሚቀበሉት ህግ አስገድዷቸው ነው

       የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ 100 ሺህ ዶላር የሚሆነውን የ2017 የሁለተኛው ሩብ አመት ደመወዛቸውን፣ አሜሪካውያን ተማሪዎች ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለመርዳት፣ለአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር በስጦታ መልክ መለገሳቸው ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ በዋይት ሃውስ የፕሬስ ጸሃፊ ሳራ ሳንደርስ በኩል ለትምህርት ሚኒስቴር በስጦታ የለገሱት ገንዘብ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና በመሳሰሉት የትምህርት መስኮች ዝንባሌ ያላቸው የአገሪቱ ህጻናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለማገዝ እንደሚውል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የትምህርት ጸሃፊዋ ቤትሲ ዴቮስ ስጦታውን ከተቀበሉ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ልገሳው ትራምፕ ሁሉም የአገሪቱ ህጻናት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻልና የትምህርት ስርዓቱን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም ያሳዩበት ነው ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ትራምፕ ባለፈው ሩብ አመት በተመሳሳይ ሁኔታ ደመወዛቸውን በመለገስ ሁለት ፕሮጀክቶችን መደገፋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ቀዳማዊት እመቤት ኢቫንካ ትራምፕም አሜሪካውያን ልጃገረድ ተማሪዎች፣ የንባብ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩና ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የተለየ ትኩረት እንዲሰጡ በሚያግዙ ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ አመልክቷል፡፡
የናጠጡት ባለጸጋ ዶናልድ ትራምፕ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት፣ ካሸነፉ ደመወዛቸውን ጨርሶ እንደማይወስዱ ቃል መግባታቸውን  ያስታወሰው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን የአገሪቱ ህግ፣ ፕሬዚዳንቶች ደመወዛቸውን እንዲወስዱ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ቃላቸውን ሙሉ በሙሉ ማክበር አልቻሉም ብሏል፡፡ ይኼን ተከትሎም፣ ሙሉ ደመወዛቸውን እየተቀበሉ  ለበጎ ምግባር ለመለገስ መወሰናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 3206 times