Sunday, 30 July 2017 00:00

ውሻውን በፕሬዚዳንቱ የሰየመው ናይጀሪያዊ ከክስ ነጻ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ውሻውን በናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ስም በመሰየሙ ባለፈው አመት የታሰረውና ሰላም የሚያደፈርስ ተግባር ፈጽሟል በሚል ክስ የተመሰረተበትን ናይጀሪያዊው ጆአኪም ኢሮኮን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፣ ግለሰቡን ከጥፋተኝነት ነጻ የሚያደርግ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ፤ ግለሰቡ የአገሪቱን ሰላም የሚያደፈርስ ተግባር ስለመፈጸሙ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም በማለት ባለፈው ረቡዕ ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጠውን ውሳኔ እንዳስተላለፉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ግለሰቡ ውሻውን በፕሬዚዳንቱ ስም መሰየሙን ለፖሊስ የጠቆመውና ያሳሰረው አንድ ጎረቤቱ የሆነ ሰው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ እስራቱ  በመላ አገሪቱ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበርም ዘገባው አውስቷል፡፡
በአነስተኛ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ህይወቱን የሚገፋው የ41 አመቱ ተከሳሽ፣ በውሻው ግራና ቀኝ ጎን ላይ ቡሃሪ የሚል ጽሁፍ በመለጠፍ፣ የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች በሚበዙበት አካባቢ ሲንቀሳቀስ ታይቷል፤ ይህም ድርጊት ጸብ አጫሪና ሰላምን የሚያደፈርስ ነው በማለት ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ እንደመሰረተበትም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ፣ ግለሰቡ በሰጠው መግለጫ፣ “የምወደውን ውሻዬን በማደንቀው ጀግናዬ በፕሬዚዳንት ቡሃሪ ስም መሰየሜ ከመልካም ስሜት የመነጨ ነው፤ መታሰሬ አግባብ እንዳልነበር አውቃለሁ፣ ድርጊቱን በመቃወም ከጎኔ የቆማችሁትን ሁሉ አመሰግናለሁ” ማለቱንም ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 2308 times