Saturday, 29 July 2017 12:43

ኢትዮጵያ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    • የምታሰልፈው ቡድን በወጣትና አዳዲስ አትሌቶች የተሞላ ነው ፡፡
                   • የዓለም ሚዲያዎች ከኬንያ ዝቅ ያለ ግምት ሰጥተዋታል፡፡፡፡
                   • ፌደሬሽኑ የሜዳልያ እቅዱን መግለፅ አልቻለም፡፡
                   • 2 የወርቅ 4 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ፡፡ የትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያ


       16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን  ከተማ ከሐምሌ 28 ቀን እስከ ነሐሴ 8 ቀን  የሚካሄድ ሲሆን ለኢትዮጵያ የዓለም ሚዲያዎች ከኬንያ ዝቅያለ ግምት ሰጥተዋታል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን እንዳስታወቀው በ16ኛው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለአሸናፊ አትሌቶች ብቻ ሳይሆን ለአሰልጣኞች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሜዳልያ ተዘጋጅቷል፡፡ ሻምፒዮን አትሌቶች ለአሰልጣኞቻቸው የሜዳልያ ሽልማት ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከ200 አገራት የተውጣጡ አትሌቶች በ48 የውድድር መደቦች ለሚካፈሉበት ሻምፒዮና 800 ሺ የስታድየም መግቢያ ትኬቶች እንደሚሸጡ ተጠብቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን ሰሞኑን ያስታወቀ ሲሆን፤ በምርጫው በርካታ ወጣት እና አዳዲስ አትሌቶች መያዛቸውና አዋጋቢ አጀንዳዎች በስፋት አለመነሳታቸው የሚጠቀስ ነው፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ቡድን ዝርዝር ይፋ በተደረገበት መግለጫ ላይ ያልተጠበቀ ዜና የሆነው በማራቶን እንደሚሳተፍ ከ1 ወር በፊት ተገልፆ የነበረው  የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ቀነኒሳ በቀለ በሕመም ከቡድኑ ራሱን ማግለሉ  ነው፡፡ በሌላ በኩል በመግለጫው ማግስት ጣሳ ባዮ የተባለ አትሌት ለምን አልተመረጥኩም በሚል አሰልጣኙን ደብድቦ ለሁለት ዓመት የታገደበት ክስተት ነበር፡፡ በተለይ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ አለመሳተፍ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ነው። በዚሁ ዙርያ   ፌደሬሽኑ በሰጠው አስተያየት ለዓለም ሻምፒዮና ብቁ በሆነበት አቋም ላይ ስለማይገኝ ከቡድኑ መገለሉ ተገቢ ነው ብሏል። ቀነኒሳ በ2017 ላይ በበርሊን ኦሎምፒክ ሲያሸንፍ 2፡03፡03 በሆነ ጊዜ የምንግዜም ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት እና የኢትዮጵያን ሪከርድ እንዳስመዘገበ የሚታወስ ሲሆን በዱባይ ማራቶን አቋርጦ ከወጣ በኋላ በለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ይፋ ባደረገው ዝርዝር መሰረት የኢትዮጵያ ቡድን ጥንካሬ የሚታየው በማራቶን ሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ላይ ነው፡፡ ካለፉት የዓለም ሻምፒዮኖች የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ቡድን የተለየ ያደረገው  ባዓለም ሚዲያዎች ስለ አትሌቶች ዝግጅት፤ የሚዳሊያ ተፎካካሪነት ዙሪያ ከኬንያ ያነሰ ሽፋን በማግኘቱ ነው፡፡ በሴቶች ምድብ  የዓለም ሻምፒዮና ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚሰለፉት  ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና ለወርቅ ሜዳልያዎች ባገኙት ግምት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ገንዘቤ እና አልማዝ በአለም ሻምፒዮናው በሁለት የውድድር መደቦች የሚሮጡ ሲሆን ለድርብ ድል የሚጠበቁ ይሆናል፡፡  ከ2 ዓመት በፊት ቤጂንግ ባስተናገደችው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በ1500 ሜትር ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፈችው ገንዘቤ ዲባባ በ5000 ሜትርም የምትሳተፍ ይሆናል። የወቅቱ የዓለም ኮከብ ሴት አትሌት ፤ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ የያዘችውና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነችው አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር የምትገባ ሲሆን በ5000 ሜትር በተጨማሪ የምትሳተፈው ከ2 ዓመት በፊት ያስመዘገበችውን የዓለም ሻምፒዮንነት ለማስጠበቅ ይሆናል፡፡ በ5000 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና መገናኘታቸው ለርቀቱ የዓለም ክብረወሰን መሰበር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እየተገለፀ ነው።
በቀድሞ አትሌቶች የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የዓለም ሻምፒዮናውን ቡድን በይፋ ባስታወቀበት መግለጫ ላይ ስንት ሜዳልያዎችን ለማግኘት እንዳቀደ ቢጠየቅም ይህን ያህል ብሎ አለመግለፁ ያልተለመደ ነው፡፡ ይሁንና ‹‹ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ›› የተባለ ታዋቂ የአትሌቲክስ ዘጋቢ በድረገፁ ከወር በፊት ለዓለም ሻምፒዮናው የአትሌቲክስ ውድድሮች የሜዳልያ ትንበያዎችን  አሰራጭቶ ነበር። በሰንጠረዥ በቀረበው ትንበያ ላይ ብሄራዊ ቡድንን ወክለው በሚመረጡ አትሌቶች ላይ በሰራቸው ግምታዊ የስም ዝርዝሮች መጠነኛ መፋለስ ቢኖርበትም  ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ኢትዮጵያ በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጠቃላይ 2 የወርቅ፤ 4 የብር እና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ልታገኝ እንደምትችል ገምቷል። በወንዶች 3 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በሴቶች ደግሞ 2 የወርቅ፣ 1 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን በማለት ነው። በወንዶች 5ሺ ሜትር ሙክታር ኢድሪስ የብር እንዲሁም ዮሚፍ ቀጀልቻ የነሐስ፤ በ10ሺ ሜትር አባዲ ሃዲስ የብር እንዲሁም በማራቶን ተስፋዬ አበራ እና ታምራት ቶላ የብርና ነሐስ ሜዳልያ እንደሚያገኙ በትንበያው አስፍሮ በሴቶች ደግሞ  ሁለቱን የወርቅ ሜዳልያዎች አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን ጥሩነሽ ዲባባ እንደሚያስገኟቸው በመገመት በ5ሺ ሜትር አልማዝ የብር እንዲሁም ሰንበሬ የነሐስ፤ በማራቶን ገለቴ ቡርቃ የነሐስ ሜዳልያ ሊወስዱ እንደሚችሉ ጠቁሟል። ምንም እንኳን ይህ ግምት ጥሩነሽ በማራቶን ሳይሆን በ10ሺ መወዳደደሯ እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ ከእነራሹ በብሄራዊ ቡድን ባለመካተቷ የተፋለሰ ቢሆንም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ የተተነበየላት 6 የወርቅ 5 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ናቸው፡፡
ኬንያ  ለዓለም ሻምፒዮናው አዳዲሶች በብዛት የሚገኙበትን የ49 አትሌቶች ቡድንን ይፋ ያደረገች ሲሆን በአጭር ርቀት፤ በጦር ውርወራ በሱሉስ ዝላይ እና በርምጃ ውድድር ከኢትዮጵያ የተለየ ተሳትፎ ይኖራታል። የኬንያን ቡድን በ800 ሜትር የዓለምን ሪከርድ ያስመዘገበው የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩድሻ እንደሚመራው ሲታወቅ ከተሳታፊ አትሌቶች ተቀማጭነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉም ይገኙበታል። ኬንያ ከኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ የምትሳተፍባቸው የአጭር ርቀት ውድድሮች በሴቶች 400 ሜትር፤ በወንዶች 400 ሜትር፣ 400 ሜትር መሰናክል እና በ200 ሜትር የሚደረጉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱት 15 የዓለም ሻምፒዮናዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪክ 72 ሜዳልያዎች (25 የወርቅ፤ 22 የብርና 25 የነሐስ) ሰብስባለች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በቻይና ቤጂንግ ተደርጎ በነበረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በሦስት ወርቅ፣ በሦስት ብርና በሁለት የነሐስ በድምሩ በስምንት ሜዳሊያ ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቶች የተያዙ የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች
ብርሃኔ አደሬ በ10 ሺ ሜትር 30፡10.18 (2003 እ.ኤ.አ)
ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺ ሜትር 26፡46.31 (2009 እ.ኤ.አ)
አልማዝ አያና በ5 ሺ ሜትር 14፡26.83 (2015 እ.ኤ.አ)
ከአንድ በላይ የዓለም ሻምፒዮና ሜዳሊያ ያላቸው የኢትዮጵያ አትሌቶች
በወንዶች
ኃይሌ ገ/ሥላሴ 4 ወርቅ፤ 2 ብር፤ 1 ነሐስ =
7 ሜዳሊያዎች
ቀነኒሳ በቀለ 5 ወርቅ፤ 1 ነሐስ  = 6 ሜዳሊያዎች
ስለሺ ስህን 3 ብር፤ 1 ነሐስ =  4 ሜዳሊያዎች
ኢብራሒም ጄይላን 1 ወርቅ፤ 1 ብር =
2 ሜዳሊያዎች
ፊጣ ባይሳ 1 ብር፤ 1 ነሐስ = 2 ሜዳሊያዎች
አሰፋ መዝገቡ 1 ብር፤ 1 ነሐስ = 2 ሜዳሊያዎች
ሐጎስ ገብረህይወት 2 ነሐስ= 2 ሜዳሊያዎች
በሴቶች
ጥሩነሽ ዲባባ 5 ወርቅ = 5 ሜዳሊያዎች
መሰረት ደፋር 2 ወርቅ፤ 1 ብር፤ 2 ነሐስ =
5 ሜዳሊያዎች
ብርሃኔ አደሬ 1 ወርቅ፤ 2 ብር = 3 ሜዳሊያዎች
ደራርቱ ቱሉ 1 ወርቅ፤ 1 ብር = 2 ሜዳሊያዎች
ጌጤ ዋሚ 1 ወርቅ፤ 1 ነሐስ = 2 ሜዳሊያዎች
እጅጋየሁ ዲባባ 2 ነሐስ = 2 ሜዳሊያዎች
አየለች ወርቁ 2 ነሐስ = 2 ሜዳሊያዎች
ብዙ የዓለም ሻምፒዮና የተሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች
በወንዶች
ኃይሌ ገ/ሥላሴ 6 (1993/95/97/99/2001/03 እ.ኤ.አ)
ፊጣ ባይሳ 5 (1991/93/95/97/99 እ.ኤ.አ)
ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም
5 (2003/05/07/09/11 እ.ኤ.አ)
ቀነኒሳ በቀለ 5 (2003/05/07/09/11 እ.ኤ.አ)
በሴቶች
ብርሃኔ አደሬ
7 (1993/95/97/99/2001/03/05እ.ኤ.አ)
ደራርቱ ቱሉ
6 (1991/95/97//2001/03/05እ.ኤ.አ)
መሰረት ደፋር
6 (2003/05/07/09/11/13እ.ኤ.አ)
ጥሩነሽ ዲባባ (2005/07/09/11/13/17 እ.ኤ.አ)

Read 1912 times