Sunday, 06 August 2017 00:00

የአዲስ ፓርቲ አመሰራረትን የሚያከብድ ማሻሻያ ለማድረግ ተስማምተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ኢህአዴግ 15 አንቀፆች እንዲሻሻሉ ጠይቋል
ፓርቲዎች ንግድ እንዲያከናውኑ ሀሳብ ቀርቧል

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ሰሞኑን ለ2 ቀናት በዝግ ባደረጉት ድርድር የፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅን በርካታ አንቀፆች በስምምነት ማሻሻላቸውን የሂደቱ ተሳታፊ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ፓርቲዎችን ለመመዝገብ በ2000 ዓ.ም የወጣው አዋጅ 573/2000 ላይ ኢህአዴግ 15 አንቀፆች እንዲሻሻሉለት ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን ተቃዋሚዎችም የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦች ማቅረባቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ባለፈው ማክሰኞና ሐሙስ እለት ባደረጉት ድርድር፣ ከፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ 63 አንቀፆች ውስጥ 31 ያህሉ ላይ ተደራድረው በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በዚህ የአዋጁ ክፍል እንዲሻሻሉ ሀሳብ ከቀረበባቸው ዋነኛ ጉዳዮች አዳዲስ ፓርቲዎች ለመመስረት የሚያስፈልጋቸው የድጋፍ ድምፅ መጠን ሲሆን ቀድሞ በነበረው አዋጅ አንድ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 1500 ሰዎች ፊርማና ድምፅ፣ እንዲሁም ክልላዊ ፓርቲ ከሆነ የ700 ሰዎች የድጋፍ ድምፅ ማሰባሰብ በቂ ነበር፡፡
ኢህአዴግ የአዲስ ፓርቲ የመመስረቻ የድጋፍ ድምፁ 3 ሺህ እንዲሆን ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን መኢአድና ኢዴፓ ያሉበት 4 ፓርቲዎች ደግሞ 2500 ይሁንልን ብለው ነበር፡፡ 5 ሺህ እንዲሆንም ሀሳብ ያቀረቡ ነበሩ ተብሏል፡፡
ከቀረቡት አማራጮች ኢህአዴግ ያቀረበው 3 ሺህ የሚለው ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል - ምንጮቻችን፡፡ የክልል ፓርቲዎች የመመስረቻ ድምፅ ቀድሞ 1500 እንዲሆን ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡
የፓርቲዎች ፅ/ቤት በተመለከተም ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ቢያንስ በመላ ሀገሪቱ 25 በመቶ ጽ/ቤቶች ቅድሚያ እንዲኖራቸውና ጽ/ቤት የሚያዘጉ የመንግስት አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡
ሁለት ዜግነት ያላቸው (ትውልደ ኢትዮጵያውያን) በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንዲሳተፉ የሚል የማሻሻያ ሃሳብ በመድረኩ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ህገ መንግስቱ አይፈቅድም በሚል ሀሳቡ በአብዛኞቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት አላገኘም። በዚሁ የድርድር አጀንዳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግድ እንዲያከናውኑ ይፈቅድላቸው የሚል ሀሳብ ተነስቶም አብዛኞች ተቃሚዎችን ጨምሮ ኢህአዴግም ሃሳቡን ተቃውሞታል፡፡
እስካሁን ያለው የድርድሩ ሁኔታ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው? በሚል ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ “ድርድሩ እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው፤ የከፈልንለትን ዋጋ የሚያሳጣ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ 

Read 2853 times