Sunday, 06 August 2017 00:00

በኮሬና በጉጂ መካከል በተፈጠረ ግጭት 13 ሰዎች ሞተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በድንበር ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች ተበራክተዋል፣ አሳሳቢ ሆነዋል

ከሰሞኑ በጎጂ ኦሮሞ እና በኮሬ ብሔረሰቦች መካል በድንበር ምክንያት የተፈጠረ ግጭት የ13 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ያስታወቀው የመድረክ አባል ድርጅት የሆነውና በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው ኢኮዴፓ በየጊዜው በክልሎች ድንበር የሚፈጠሩ ግጭቶች እየተበራከቱና የሰው ህይወት እየቀጠፉ መምጣታቸው በእጅጉ አሳስቦኛል ብሏል።
የኢትዮጵ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በተናጠል በሰጠው መግለጫ ከሐምሌ 16 እስከ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለተከታታይ ስድስት ቀናት በዘለቀ በመሳሪያ የታገዘ የከፋ ግጭት በደቡብ ክልል የኮሬ ብሔረሰብ እና በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ኦሮሞ መካከል ተከስቶ የ13 ሰዎች ህይወት ከመጥፋቱ ባሻገር ከ40 በላይ ሰዎች የመቁሰል ከ700 በላይ መኖሪያ ቤቶችና ከ400 በላይ የእህል ክምሮች መቃጠላቸውን ፓርላማው አስታውቋል፡፡
ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተዘራና በማሳ ላይ የነበረ የበቆሎ ምርት እንደወደመና እንደተዘረፈ እንዲሁም ከ40 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ፓርቲው ጨምሮ ገልጿል፡፡
የግጭቱ መነሻም የኮሬ ብሄረሰብ በሚኖርበት የአማሮ ወረዳ እና የጉጂ ኦሮሞ በሚኖርበት የገላና - አባያና የቤሌ ሆራ ወረዳዎች አዋሳኝ ድንበሮችን እንደ አዲስ ለመለየትና ለማካለል የተደረገ እንቅስቃሴ ተከትሎ መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው ለዚህም የአካባቢው ባለስልጣናት ተጠያቂ ናቸው ብሏል፡፡
የተጠቀሰው ግጭት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑንና ወደተለያዩ ቀበሌዎች እየተዛመተና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ያስገነዘበው ኢሲዴፓ ለግጭቱ ምክንያት የሆነው የድንበር ማካለል በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣ በግጭቱ የተሳተፉና የቀሰቀሱ ኃላፊዎች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፡፡
ድንበርን አስመልክቶ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የተፈጠረው ግጭት በርካቶች ለሞት እና ለጉዳት የዳረገ ሲሆን በቅርቡም በአማራ ክልል እና አፋር አዋሳኞች የተከሰተ ተመሳሳይ ግጭት ለበርካቶች ሞትና ጉዳት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡
እነዚህ ድንበርን አስታከው የሚፈጠሩና የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች በእጅጉ አሳስቦኛል ያለው ፓርቲው በበኩሉ የግጭቶቹ መነሻዎች ህገ መንግስታዊ ጥሰቶች እንደሆኑ በማመላከት መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እርምት እንዲያደርግባቸው ጠይቋል፡፡

Read 3302 times