Sunday, 06 August 2017 00:00

የንግድ ባንክ 6ኛው ‹‹የይቆጥቡ ይሸለሙ›› አሸናፊዎች ዕጣ ወጣ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(27 votes)

· የንግድ ባንክ ተቀማጭ ሀብት 364 ቢሊዮን ብር ደረሰ
· የኤቲኤም አገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል ስምምነት ተፈራርሟል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቁጠባ ባህልን ለማዳበርና የባንኩን ሀብት ለማሳደግ አቅዶ የጀመረው የ‹‹ይቆጥቡ ይሸለሙ›› 6ኛ ዙር እጣ አሸናፊዎች ወጣ፡፡ በትላንትናው ዕለት በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በወጣው እጣ፣ ለ1ኛ እጣ ሶስት የመኖሪያ ቤቶች፣ ለሁለተኛ እጣ 15 አገር ውስጥ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች፣ ለ3ኛ እጣ 15 ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ለ4ኛ እጣ 15 ጀነሬተሮች፣ለ5ኛ እጣ 15 ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችና ለ6ኛ ዕጣ 1ሺህ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች ባለዕድለኞች መውጣታቸው ተገልጿል፡፡
ባንኩ የትኩረት አቅጣጫውን ለባንኩ ሀብት ማሰባሰብና ለልማትና ቢዝነሱ ፋይናንስ ማቅረብ አተኩሮ መንቀሳቀሱን የተናገሩት የባንኩ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ፤ አዳዲስ የባንክ ደንበኞችን ለመሳብና ነባሮቹንም ይበልጥ እንዲቆጥቡ ለማበረታታት በጀመረው የ‹‹ይቆጥቡ ይሸለሙ›› ፕሮግራም፤ የባንኩን ተቀማጭ ሀብት 364 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉንና የባንኩ ደንበኞች ቁጥርም ወደ 16 ሚሊዮን ማደጉን አስታውቀዋል፡፡ የአገር ውስጥ ቅርንጫፎች ቁጥር 1220 መድረሱን የጠቆሙት ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጁ፤ ባንኩ በቀጣይ የሚሰበስበውን ሀብትና የደንበኞች ቁጥር ለማብዛት ሽልማቶቹን በአይነትም ሆነ በብዛት እያሳደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ አገር ገንዘብ በሀዋላ የሚላክላቸው ደንበኞች ብራቸውን ከንግድ ባንክ እንዲወስዱ የማበረታቻ ሽልማት ተዘጋጅቶ፣ ባንኩ በዚህም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አቶ በልሁ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ባንኩ የኤቲኤም አገልግሎቱን በጥራትና በስፋት ለደንበኞቹ ለማቅረብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኔትወርክ ዝርጋታ ግንባር ቀደም ከሆነው ኤንሲአር (NCR) ኮርፖሬሽን ጋር ለመስራት መፈራረሙ ተገልጿል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ የሆነው ንግድ ባንክ የኤቲኤም አገልግሎት መረቡን ለማስፋት የ200 አዲስ የሲኤን አር ሰልፍ ሰርቭ (Selfserve) ኤቲኤሞችን እንዲሁም የባንኩን አጠቃላይ የኔትወርክ ሲስተም መመልከት የሚያስችል የኤቲኤም መቆጣጠሪያ ሲስተም ለመጨመር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡

Read 9233 times