Sunday, 06 August 2017 00:00

የቀድሞው የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፤ በሙስና ተጠርጥረው ታሰሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆም በቁጥጥር ስር ውለዋስ
እስከ ትላንት ድረስ 50 የሙስና ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ዛይድ ወ/ገብርኤል እና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትናንት ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚ/ደኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው መታሰራቸውን  ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ለረጅም ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ስለተጠረጠሩበት የሙስና ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ማግኘት ባይቻልም በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን አዲስ አድማስ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ማረጋገጥ ችሏል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በቀለ ንጉሴም ሰሞኑን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ሌላው ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ ለፓርላማ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀልም  በዝርዝር የተገለፀ ሲሆን ‹‹ፕሮጀክቶች ያለጨረታ በመስጠትና ስራው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቀ በማስመሰል ክፍያ በመፈፀም ለአንድ ድርጅት ውለታ ውለዋል›› የሚል ጥርጣሬ ቀርቦባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ሃላፊው ለዚሁ ስሙ ያልተገለፀ ድርጅት፤ ስምንት ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማስደረጋቸው እንዲሁም 2.2 ሚሊዮን  ዶላር የሚያወጣ ስራን በጥቅም በመተሳሰር ያለጨረታ መስጠታቸው ከጠቅላይ አቃቤ ህግ  ማብራሪያ መረዳት ተችሏል፡፡
ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የግንባታ ቁሳቁሶች ከሚያስገባ አንድ ተቋም ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉርሻ በመቀበል የተጠረጠሩት አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ እንዲሁም ያለ ጨረታ ፕሮጀክት ካሰሩት የአሜሪካ ኩባንያ ማግኘታቸው ለፓርላማ በቀረበው ሪፖርት ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ የአሜሪካ ኩባንያ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር አሜሪካ ለ1 ወር እንዲዝናኑና ልጆቻቸውም እዚያው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል ጥቅም ማግኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡  በምክር ቤቱ የነበሩት ሚኒስቴር ዴኤታው በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ህዝብንና መንግስትን በታማኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ገልፀው፤ ህሊናቸውን የሚቆረቁር ተግባር አለመፈፀማቸውንና በተፈጠረው ነገር በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት እያከናወነ ያለውን የፀረ ሙስና ትግል እደግፋለሁ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ተፈፀመ የተባለው ጉዳይ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢታይ ጥሩ ነበር” ብለዋል፡፡
የመንግስት የተለያዩ መንግስት ሃላፊዎችን በሙስና በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር ማዋል ከጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን እስከ ትላንት የሙስና ተጠርጣሪዎች ቁጥር 50 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 7791 times