Sunday, 06 August 2017 00:00

ለአስራ አንድ ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሳ

Written by 
Rate this item
(34 votes)

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ከ390 ሺ በላይ ሚሊሻዎች ሰልጥነዋል
ከ7ሺ በላይ ተጠርጣሪዎች ክሳቸውን እየተከታተሉ ነው
የሦስት ሚኒስትሮች ሹመት ፀድቋል

ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ11 ወራት በሥራ ላይ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በትላንትናው ዕለት ተነሳ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ያፀደቀ ሲሆን ባካሄደው አንደኛው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሰረት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት መስከረም 28 ጀምሮ በኦሮሚያ 233 ሺ 070፣ በአማራ 143 ሺ 459 እንዲሁም በደቡብ 16 ሺ 475 ሚሊሺያዎች መሰልጠናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በየክልሉ ያሉ የብሔራዊ ተጠባባቂ የሰራዊት አባላትን የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል ተብሏል፡፡
የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን በተመለከተም በሁከትና ብጥብጡ ተሳትፈዋል የተባሉ ከኦሮሚያ ክልል 4136፣ ከአማራ ክልል 1888፣ ከደቡብ ክልል 1166፣ ከአዲስ አበባ 547 በድምሩ 7737 ተጠርጣሪዎች በተለያየ ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ክሳቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ከ21 ሺ በላይ ተጠርጣሪዎችም በሁለት ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደው፣ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። ኮማንድ ፖስቱ የታጠቁ አሸባሪዎችንና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ለመቆጣጠር የተሰሩ ሥራዎች ብሎ ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ በኦሮሚያ 325፣ በአማራ 275፣ በደቡብ 109 በድምሩ 709 ሸማቂዎችና የታጠቁ ኃይሎች፣ ከህዝብና ከመስተዳደር አካላት ጋር በመሆን ለመቆጣጠር እንደተቻለ ጠቁሟል፡፡ ህገወጥ የመሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ከ97 በላይ አዳዲስ ኬላዎችን በማቋቋምና 196 ነባር ኬላዎችን በማጠናከር የተለያዩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም አስታውቋል፡፡ ከነበረው ሁኔታ ልምድ በመውሰድ የጦር መሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑንና አዋጁ በሥራ ላይ ሲውል የዚህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡
በቅርቡ ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር የየክልሉ የፀጥታ አካላት በራሣቸው አቅም መፍታት መቻላቸው፣ የኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊነት ወሣኝ አለመሆኑን አመላክቷል ያለው ሪፖርቱ፤ የፌደራል የፀጥታ አካላትና የክልል የፀጥታ አካላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ያዳበሩትን በጋራ ተቀናጅቶ የመስራት ልምድ በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ሲያከናውን የቆያቸውን ሥራዎች ደረጃ በደረጃ በአካባቢው ላሉ የፀጥታና የሚመለከታቸው አካላት እያስረከበ፣ የቅርብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡
በየቦታው እያጋጠሙ ያሉ ጥቃቅን ክስተቶችና ያልተቋጩ መለስተኛ ሥራዎች ቢኖሩም እነዚህ ሥራዎች በመደበኛ ሁኔታ፣ በየደረጃው ካሉ የፀጥታና የመስተዳድር አካላት አቅም በላይ ሊሆኑ ስለማይችሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳና ቀሪ ሥራዎች በመደበኛው የህግ አግባብ እንዲፈፀሙ ለምክር ቤቱ የውሣኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሣቱ ጉዳይ ላይ ድምፅ መስጠት የሚጠበቅበት ባለመሆኑ፣ የምክር ቤቱ አባላት ድምፅ ሣያስፈልግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከትላንት ሐምሌ 28 ቀን ጀምሮ መነሣቱ ተገልጿል፡፡  
በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ምክር ቤቱ፤ የ3 ሚኒስትሮችን ሹመትም አፅድቋል፡፡ በዚህም መሰረት ባለፈው ህዳር ወር የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ከበደ ጫኔ፤ የፌደራል አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር፣ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ፣ የትምህርት ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን የጉምሩክ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሞገስ ባልቻ፣ በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡  


Read 6243 times