Print this page
Sunday, 06 August 2017 00:00

ለስኬት ክብርን፣ ለብቃት አድናቆትን መስጠት ይተናነቀናል!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(9 votes)

   • የስነምግባር መርሆቻችን የኋሊት የዞሩ፣ በአፍጢማቸው የተደፋ ሆነዋል!
   • ባለብቃት አትሌቶችን ማሸማቀቅ፣ ባለሃብትን ማጣጣል፣ ዘፋኞችን በ‘ቦይኮት’ ማሰናከል
                                      
       ሃብት ፈጠራ፣ የሕይወት ስኬት መሆኑን አለማወቅ ወይስ መካድ?
“አንድ ባለሃብት፣ ለሕዳሴ ግድብ ሚሊዮን ዶላር (ማለትም 24 ሚሊዮን ብር) ቢሰጥ፣ ይሄ... አንዲት ድሃ  ካዋጣችው 200 ብር ይበልጣል ማለት አይደለም” - አሉ ሚኒስቴር ዴኤታው። ይሄ፣ የመንግስት ባለስልጣን ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ነው።
ብቃት የቅድስና ሚዛን መሆኑን መዘንጋት፣ ወይስ ብቃትን መጥላት?
“አንድ አትሌት በአለም ሻምፒዮና ሲያሸንፍ... ሁልጊዜ አገር ይደሰታል ማለት አይደለም። አገር፣ በአትሌቱ ድል የሚያዝነበት ጊዜም ነበር” ብለዋል - ሰባኪው። በአትሌት ድል ማዘን? ለምን? አትሌቱ፣ ሌሎችን ቀድሞ ለማሸነፍ መሮጡ ነው ጥፋቱ። ይሄ፣ እንግዳ አስተሳሰብ አይደለም። ድንገተኛ ስህተትም አይደለም። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደትክክለኛ የሚቆጠር አስተሳሰብ ነው።
“በራሱ ብቃት ተመክቶ፣ ለራሱ ስኬት ቅድሚያ የሚሰጥና ቀዳሚ ለመሆን የሚሮጥ አትሌት”፣... አንወድም? የላቀ ብቃትን ተቀዳጅቶ በእውን ስላሳየን  አናደንቀውም? በዚህም መፈሳችንን ለማደስ ስለቻልን፣ አናመሰግነውም? በጭራሽ! የብዙዎቻችን የስነምግባር መርህ፣ ይህንን አይፈቅድም። በዚህ ባህላዊና ነባር የስነምግባር መርህ አማካኝነት፣... ይህንን አትሌት ስንመዝነው፣ “አሳዛኝ ነውር ሰርቷል” ብለን እንፈርድበታለን። ለምን?
“የወርቅ ሜዳሊያውን ልቀቅልህ፣ አንተ ቅደም” እያለ፣ ሌሎቹን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አልጋበዘም። የራሱን ስኬት፣ ለመስዋዕትነት አላቀረበም።
ይህችኛዋ የኦሎምፒክ ጀግናስ?  ያቺኛዋ ባለሪከርድ፣... ሪከርድ ሰብራ ድንቅ ታሪክ ያስመዘገበች አትሌትስ? ያው፣... አዝነንባታል። ለምን? “ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ አንደኛ እንዲወጡ፣ ቅድሚያ አልሰጠቻቸውም” ብለን ኮንነናታል። “ብቃቷን ተጠቅማ፣ አንደኛ ለመውጣትኮ ነው የተሯሯጠችው!” ብለን እንደነውር እንቆጥርባታለን።
ይሄ ነው፣ የታመመ የስነምግባር መርህ!
ይሄ ነው፣ የኋሊት የዞሩ የስነምግባር መርህ!
ይሄ ነው፣ በአፍጢሙ የተደፋ የስነምግባር መርህ!
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፣ ይሄ የአንድ ሰው ስህተት ወይም የአንድ ባለስልጣን ችግር አይደለም። የአገር ህመም ነው (... ማለትም በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚስተጋባና ተቀባይነት ያገኘ የታመመ የስነምግባር መርህ፣ በአገራችን ውስጥ ስር የሰደደ የዘመናት በሽታ ነው።)
ሚኒስትር ዴኤታው፣ “አንድ ባለሃብት፣ ለሕዳሴ ግድብ ሚሊዮን ዶላር (ማለትም 24 ሚሊዮን ብር) ቢሰጥ፣ አንዲት ድሃ የአቅሟን ያህል ካዋጣችው 200 ብር ይበልጣል ማለት አይደለም” ብለው ሲናገሩ፣ በአነጋገራቸው ግራ የተጋባ ብዙ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። መዋጮ የሚሰበሰበው፣ የግድብ ግንባታውን ለማሳካት ከሆነ፣ ያለምንም ጥርጥር፣ 24 ሚሊዮን ብር፣... ከ200 ብር በጣም በጣም እንደሚበልጥ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን የሚመጥን አድናቆትና ምስጋና ማቅረብ አያስፈልግም? ነውር ነው? እንደነውር የሚቆጥሩት ብዙ ሰዎች ይኖራሉ። እንዲያውም ከዚህ የባሰና እጅግ የታመመ አስተሳሰብ፣ አገራችን ውስጥ ሞልቷል።
ባለሃብትን በጭፍንና በመሰለኝ ማውገዝ፣... የማናውቀውን ባለሃብት፣ “የአንድ ጀንበር ሚልዮነር” ብለን በሌብነት መወንጀል፣ የዘወትር ስራና ሱስ አድርገነዋልኮ። የአንድ ጀንበር ባለሃብትና ሌባ የለም ማለቴ አይደለም። ይኖራል። ግን፣ ልዩነቱን ተመልከቱ። የሕክምና ዶክተሮችን በጭፍን፣ “የአንድ ጀንበር ዶክተር” ብለን በአጭበርባሪነት እንወነጅላለን? ባለሃብት ካልሆኑ በቀር አንወነጅላቸውም። ገና ልማድ አልሆነብንም። የህክምና ዶክተሮቹ ባለሃብት ከሆኑ ግን፣ “ድሃውን ህብረተሰብ የሚዘርፉ ክሊኒኮችና ሐኪሞች” ብለን እናወግዛቸዋለን። (ድሃ፣... ምኑ እንደሚዘረፍ ባይታወቅም!)።
“አንድ አትሌት በአለም ሻምፒዮና ሲያሸንፍ... ሁልጊዜ፣ አገር ይደሰታል ማለት አይደለም። አገር፣ በአትሌቱ ድል የሚያዝነበት ጊዜም አለ” የሚለው አስተሳሰብም፤ ከዓመት ዓመት ለዘብ ብሎ የማያውቅ የአገራችን መለያ ባሕል ነው። አትሌቱን፣ “አዝነንብሃል በስኬትህ!” የምንለው ለምንድነው? ምክንያቱን ታውቃላችሁ። ራሳችሁን ለማታለል ካልፈለጋችሁ በስተቀር፣ ታውቃላችሁ። ልድገመው። ቀዳሚ ለመሆን መሮጡ ነው ጥፋቱ። “የወርቅ ሜዳሊያውን ልቀቅልህ፣ አንተ ቅደም” እያለ ሌሌች አትሌቶችን ካላስቀደመ፣ ለማስቀደም ካልተግደረደረ፣... የራሱን ስኬት ለመስዋዕትነት ካላቀረበ፣... የወራትና የአመታት ጥረቱ መና እንዲቀር በፈቃደኝነት ካልተስማማ፣... የላቀ ብቃቱ ጭዳ ሆኖ አመዱ እንዲቦን በፈቃደኝነት ካልተማገደ ...  አዳሜ ያዝንበታል፤ “ተደፈርን” እንላለን።
ግን ለምን? በእርግጥ አላጭበረበረም። በእርግጥ አላታለለም። አዎ፣ በጭራሽ፣ ሌሎችን አልተተናኮለም፣ አላደናቀፈም። መንገድ ለመዝጋትም ሆነ ለማሰናከል ፈፅሞ አልሞከረም። እንዲያውም፣ የብቃቱን ያህል ለመሮጥ ነው የበረታው። ይህንን ነው፣ “ቅዱስ ተግባር” ብለን ከማድነቅ ይልቅ፣ ሃጥያት የምናደርግበት። አትሌቶች፣ የብቃታቸውን ያህል መጣር የለባቸውም?
የአንዷ አትሌት ብቃት፣ ከጅምር እስከ ፍፃሜ፣ ፍጥነቷን ጠብቃ መሮጥ ነው። የሌላኛዋ አትሌት ደግሞ፣ ገና ከመነሻው ዙሩን የማክረር ብቃቷ የላቀ ይሆናል። ድንገት ፍጥነት ቀይራ፣ በአስደንጋጭ የበረራ ፍጥነት ቀዳሚ መሆን የምትችል፣ ለዚህም ድንቅ ብቃት የተቀዳጀች አትሌትም ትኖራለች። “ንጉሥነት እንጀራዬ ነው” የሚለውን አባባል ለባለብቃት አትሌቶች እንጠቀምበት ካልን፤...
“ብቃት... ስፍራ የማይገድበው ሃሳቤ ነው”፣
“ብቃት፣... የሁልጊዜ አላማዬ ነው”፤
“ብቃት... እንጀራዬ ነው”፣
“ብቃት፣... ሕይወቴ ነው”፤
“ብቃት፣ ... ሁለመናዬ ነው፣... ማንነቴ ነው፣... እኔነቴ ነው”... እንደማለት ይሆናል።
ከብቃት ውጭ፣ ሌላው ነገር በሙሉ... ወይ ብቃትን ለመቀዳጀት የሚያገለግል ነገር ነው። ወይ፣ የብቃት ውጤት ነው። ወይ፣... “ተራ-ተርታ” ነገር ነው።
በሌላ አነገራገር፣ “ተራ-ተርታውን ነገር” እንተወው ካልን፤ ሁሉም ዋጋ ያለው ነገር፣ ከብቃት ጋር የተያያዘ ነገር ነው። ብቃት፣... “የሰው ሕልውና ማጠንጠኛ ነው” ማለት ይቻላል።
ለዚህም ነው፣ ሁሉንም መልካም ባህርያት፣... ሁሉንም የመልካም ምግባር ምንጮች፣... “ብቃት” በሚል ስያሜ ውስጥ መጠቅለል የምንችለው።
ለዚህም ነው፣ “ቅዱስ” የሚለው ቃል፣ በኢትዮጵያ የስልጣኔ ዘመን፣ “ብቃትን የተቀዳጀ” የሚል ትርጉም የነበረው። የዚህ ቃል ትርጉም፣ እንዴት ሁሉንም የመልካም ስነምግባር ባህርያትን እንደሚሸፍን መመልከት ይቻላል - የብቃት አይነቶችን ሁሉ ያጠቃልላል።
ለእውነት የቆመ (ፃዲቅ) እና የእውቀት ወዳጅ ጥበበኛ ሲሆን፣... ብፁዕ ይባላል - “የበቃ ሰው”። ይሄ፣ አንድ የቅድስና ባህርይ ነው። ብፁዕ ማለት፣ የታመነ (ፃድቅ፣ እውነተኛ)፣ ክቡር (በሃብትና በእውቀት የበለፀገ)፣ ምሩቅ (የበቃ)፣ ቡሩክ (ፍሬያማ፣ ስኬታማ)፣... ወጣኒ (ፈርቀዳጅ፣ መሪ)  ፍፁም፣ ቅዱስ ማለት እንደሆነ የደስታ ተክለወልድና የኪዳነወልድ መዝገበቃላት ይገልፃሉ።
“በቃ” ማለት፣... በእውቀትና በሃብት ሠለጠነ፤ በቅድስና ከበረ፣ ፍፁም ሆነ፤ ፀጋ አገኘ ማለት ነው ይላሉ ደስታ ተክለወልድ። ዛሬ ዛሬ ግን፣ የእነዚህ ቃላት ትርጉም በአብዛኛው ተቀይሯል፤ ተገላቢጦሽ ሆኗል።  

የታመመ የስነምግባር መርህ፣ የተምታቱ ቃላት
የቅድስና አንድ ገፅታን ተመልከቱ - የመልካም ስነምግባልና የመልካም ሰብዕና አንድ ገፅታን ይወክላል - “በረከት” የተሰኘው ቃል።  
“ቡሩክ” ማለት፣... እንደ ድሮው ቢሆን ኖሮ፣ ከስኬት ጋር የተሳሰረ ትርጉም ነበረው። ምን ማለት ነው? የበረከተ (ፍሬያማና ስኬታማ)፣ ምሩቅ (ብቃት ላይ የደረሰ)፣... ክቡርና ቅዱስ (በብቃት የላቀና ፍፁም የመጠቀ) እንደማለት ነበር - ቡሩክ ማለት።
ዛሬ ግን፣ “ቡሩክ” ማለት፣... ራሱን ቀና ማድረግና ራሱን ማክበር እንደ ሃጥያት እየተቆጠረ፣ ራሱ ዝቅ አድርጎና አዋርዶ የሚላወስ ማለት መስሏል። አጎንብሶና ተንበርክኮ የሚለማመጥ፣ ጉልበቱን አጣጥፎ የሚኮራመት ወይም መቆም አቅቶት የሚብረከረክ ማለት እየሆነብን ነው - ቡሩክ ማለት።
በአጭሩ፣ “ቡሩክ” እና “ብሩክ”... ትርጉማቸው የተምታታበት ዘመን ላይ ነን።
መበረከት እና መንበርከክ ተቀላቅሎብናል። ራስን መጉዳት... ራስን ለእንብርክክ መዳረግና መብረክረክ፣ ዋነኛ የበጎነት ሚዛን ሆኗል። ከፍሬያማነት ይልቅ መንፈራፈርን ለማየት የምንናፍቅ ሆነናል።
ከስኬታማ ሰው ይልቅ ሚስኪን ሰው... የሚከበርበትና የሚደነቅበት የውድቀት አዘቅት፣ ለኛ እንደ ገነት ሆኖ ይታየናል።
ክቡር፣ የሚለው ቃልም፣ ትርጉሙ እንዲጠፋ እያደረግን ነው። ክቡር ማለት፣ በአእምሮና በሃብት የከበረ ባለጠጋ፣ ከውርደትና ከድህነት የራቀ ማለት ነው ይላሉ ደስታ ተክለወልድ። “ስኬታማ ሰው ነው፣ ክብር የሚገባው” የሚል መልእክትን የያዘ ነው የድሮ ትርጉሙ።
የኪዳነወልድ መዝገበ ቃላትም፣ በዝርዝር ለማስረዳት ይሞክራል።...
“ክብር” የሚለው ቃል፣...
ልዕልና (ወደ ላይ መምጠቅ)፣ ልቂያ (ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ)፣ ብዕል (ባለቤትነትን መቀዳጀት)፣ ብልጫ (በብርታት፣ በሃብት...) ማለት መሆኑን  ይዘረዝራሉ - ኪዳነወልድ።

‘በዓል’ እና ‘ቅዱስ’ ብለን የምናከብረው ማንን ነው?
“ብዕል” የሚለው ቃል፣ “በዓል” ወይም “ክብር” ከሚሉ ቃላት ጋር የተሳሰረ ነው። ትርጉሙም፣ የስኬት ባለቤት መሆን  (የቀዳሚነት፣ የአንደኝነት፣ የሃብት፣ የእድገት፣ የዘመናዊነት ባለቤትና ጌታ መሆን) ማለት ነው።
“ቅዱስ” የሚለው ቃልስ? ትርጉሙ...
ልዩ (ከሌላው የላቀ extraordinary)፣ ቡሩክ (ስኬታማ)፣ የበቃ፣ ንፁህ (እውነተኛና እንከን የለሽ) ማለት መሆኑን በደስታ ተክለወልድ ተዘርዝሯል። ልዩና ምርጥ ማለት መሆኑንም ኪዳነወልድ ይጠቅሳሉ።
ምናለፋችሁ፣... “ብሩክ፣ ብፁዕ፣ ክቡር፣ በዓል፣ ቅዱስ” የሚሉት ቃላት፣ በእውነተኛነትና በእውቀት፣ በክህሎትና በብርታት፣ በስኬትና በሃብት፣... በአጠቃላይ በብቃት የላቀ ደረጃ ላይ ከመድረስ ጋር የተቆራኘ የስልጣኔ ትርጉም ነበራቸው። ዛሬ ግን፣ ይሄ ትርጉማቸው፣ በአብዛኛው ደብዛው ጠፍቷል። በተቃራኒው፣...
ከእውነት ይልቅ አሉባልታና ፕሮፖጋንዳ፣ ከእውቀት ይልቅ ጭፍን እምነትና ‘የአገር በቀል ባህል’ አምልኮና አላዋቂነትን እናራግባለን።
ከክህሎትና ከብርታት ይልቅ ደካማነትና ‘የብሔር ብሔረሰብ ባህል’ የምንላቸው የኋላቀር ልማዶችን እናወድሳለን።
ከስኬትና ከብልፅግና ይልቅ፣ በመስዋእትነት አንዱ ሌላውን እየማገገ መጠፋፋትን፣ እንደ ቅድስና እንቆጥራለን። በዚያ ላይ ደግሞ፣...
ድሃ መሆን ልዩ ሃይል የሚያስገኝ ይመስል፣ ስኬትን እያጥላሉ ባለሃብትን በጭፍን ማውገዝ፣ እንደ ቅዳሴ እናዘወትራለን።
የላቀ ብቃትን... የቅድስና ሚዛን፣ የክብር መለኪያ፣ የአድናቆት ምንጭ፣ የውዳሴ መነሻ እንዲሆን አድርገናል? አላደረግንም። ትርጉማቸውንም ረስተነዋል። በተቃራኒው፣ የብቃት ባለቤቶችን እያሸማቀቅን ሚስኪንነትን እንሰብካለን።
የአለም አትሌቲክ ሻምፒዮናም ሆነ፣ የአገር ውስጥ የእግርኳስ ውድድሮች፣... እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ የብቃት ማሳያ መድረኮች ሁሉ፣... የላቀ ብቃትን በእውን የምንመለከትባቸው ቅዱስ ስፍራዎች እንደሆኑ ዘንግተናል። ጨርሶ አናውቅም። “ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አላቸው” ተብሎ ሲነገር፣ ወይም “ቅዱስ” ከሚል ቃል ጎን ለጎን ሲጠቀሱ መስማት ራሱ፣... ጨርሶ እንግዳ ይሆንብናል።
ምን ይሄ ብቻ!
እነዚሁ መድረኮች፣ “የሰውን ብቃት የማየት ተፈጥሯዊና መንፈሳዊ ፍላጎትን የሚያረኩ” መሆናቸው አለመታወቁ ያነሰ ይመስል፤ ከነአካቴው “የብቃት ፀር” እንዲሆኑ እናደርጋቸዋለን። “የአለም ሪከርድ የሰበረ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትነትን የተቀዳጀ አትሌት ይኖራል፤ ነገር ግን... የአቅሙን ያህል 10ሺ ሜትሩን ሩጫ በ2 ሰዓት ከሚያጠናቅቅ ሚስኪን አትሌት ይበልጣል ማለት አይደለም” በማለት ስኬትን ከማጣጣል የማይመለሱ ብዙ ሰዎች ያሉባት አገር ሆናለች - ኢትዮጵያ።
“ሪከርድ ሰባብራ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አዲስ ድንቅ ሰዓትና አዲስ ግሩም ታሪክ ብታስመዘግብ፣ አይገርመኝም፣... አይደንቀኝም። እንዲያውም፣ አዝነንባታል። የአገርን ድል ከማስቀደም ይልቅ፣ የራሷን ድል ነው ያስቀደመችው። ራሷንና ስኬቷን መስዋእት ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለችም። ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንደኛ እንዲወጡ፣ ቅድሚያ አልሰጠቻቸውም። ብቃቷን ተጠቅማ፣ አንደኛ ለመውጣት ነው የተሯሯጠችው” ብለን ለማውገዝ፣... ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ፣ ባለብቃት ጀግኖችን ለማሸማቀቅ የምንሯሯጥ ሰዎች የበዛንባት ምድር ሆናለች - የድሮዋ የስልጣኔ አገር ኢትዮጵያ፣ የዛሬዋ ኋላቀር ኢትዮጵያ።
ጀግናዋ አትሌት፣ በብቃት እየበለጠቻቸው፣ ግን ቅድሚያ እየሰጠቻቸው፣ ሌሎች አትሌቶች ቢያሸንፉ፣... ያኔ ነው የምንደሰተው?
ከመነሻው፣ የስፖርት ውድድር ዋናው ቁምነገር፣ የላቀ ብቃት በእውን ለስኬት ሲበቃ ለማየት እንደሆነ፣ ሙሉ ለሙሉ ረስተነዋል። ወይም ብቃት ጎልቶ ሲወጣ ከነስኬቱ እያየን፣ መንፈሳችንን ለማደስ አንፈልግም።
በተቃራኒው፤ የላቀ ብቃት ጎልቶ እንዳይወጣ፣ ጎልቶ ከወጣም እንዲወገዝ ነው የምንፈልገው? ይህንንም ለማድረግ ብዙ ሰበብ እንደረድራለን። ግለሰብን ሳይሆን... “ቡድንን ለማስቀደም፣ አገርን ለማስከበር፣ ሕዝብን ለማስደሰት፣”... የሚሉ ሰበቦችን እናዥጎደጉዳለን። በእነዚህ ሰበቦችም አማካኝነት፣ ባለብቃት ጀግኖችን ለማሳቀቅ፣ ብቃታቸው እንዳይታይ ለማደናቀፍ፣ ስኬትን እንዳያጣጥሙ ለማሰናከል፣... የመስዋእት ጥማችንን ለማርካት እንማግዳቸዋለን - ጭዳ ለማድረግ።
ዘፋኞችን ‘ጭዳ’ ለማድረግ፣ በፌስቡክ የሚካሄዱ የ‘ቦይኮት’ ዘመቻዎችም፣ ከዚህ ጋር ይመሳሰላሉ።
በመቧደን እና በማሳደም ላይ የተመሰረቱት የ‘ቦይኮት’ ዘመቻዎች፣ “ለብሔር ብሔረሰብ መብት”፣ “ለሕዝብ ጥቅም”፣ “ለአገር”... በሚሉ ሰበቦች የታጀቡ ናቸው። በቃ፣ እነዚህን ሰበቦች የያዘ የመስዋእትነት አምላኪ፤... ያሻውን አሉቧልታ ቢናገርና ሰዎችን በውሸት ቢወነጅል፣ “ዋሽተሃል” የሚለው ሰው ብዙ እንደማይኖር ያውቃል። “ዋሽተሃል” የሚል ሰው ቢመጣ እንኳ፣ እሱንም በጭፍን ማውገዝና መወንጀል ይችላል። በማጯጯህና በማስተጋባት የሚተባበሩትም ሞልተዋል። “ቢዋሽም”፣ ችግር የለውም። “ወገናችን ነው፣... የቡድናችን አባል ነው” ብለው በቲፎዞነት ይጮሁለታል። በዘረኝነት፣ በቲፎዞነት ወይም በመስዋእትነት አምልኮ ዙሪያ የመቧደን ሱስ፣ ሁሌም በባህርይ ይመሳሰላሉ።
በአንድ በኩል፣ የብቃት ሰዎችን በጭፍን ማውገዝና ስኬታቸውን ለማሰናከል፣ ያለሃፍረት በአደባባይ፣ በግላጭ መዝመት ይቻላል። አንዱ ባለሃብት፣ አንዱ አትሌት፣ አንዱ ዘፋኝ... እንዲህ ጭዳ ሆኖ እንዲቀር ቢዘመትበት፣ በመስዋዕትነት አምልኮ አማካኝነት ተማግዶ ቢከስል... መቃወም አይቻልም። ለምን? ለቡድን፣ ለህዝብ፣ ለአገር መስዋዕት መሆን፣... የቅድስና ሚዛን ነው ብለን ሰብከናላ። “ሃብት መፍጠርና የቢዝነስ ስኬት፣ የአትሌቲክስ ብቃትና በቀዳሚነት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን፣ የኪነጥበብ ፈጠራና የኮንሰርት ስኬት”... የስነምግባር መመዘኛ አይደሉም ብለናልኮ። በተቃራኒው፣ “እነዚህ የብርታትና የስኬት ሰዎች፣ እነዚህ የብቃትና የጀግንነት ሰዎች፣... በሰበብ አስባቡ ሲንቋሸሹና በመስዋእትነት አውድማ ማገዶ ሆነው አመድ ሲሆኑ ማየት”... ዋነኛ የስነምግባር መመዘኛ፣ የቅድስና መለኪያ እንዲሆን አድርገናል። ወይም፣ እንዲህ አይነት ጭፍን የመስዋእትነት አምልኮዎችንን፣ በዝምታ ተቀብለናቸዋል።
ታዲያ፣ ኢትዮጵያ፣... ከድሮው የስልጣኔ ጅምር ጋር ላለመተያየት ተራርቃ፣ ለምዕተ ዓመታት ከኋላቀርነት ጋር ተጣብቃ መቅረቷ ምን ይገርማል?
24 ሚልዮን ብር፣ ከ200 ብር አይበልጥም ለማለት የምንደፍርበት አገር ውስጥ፣... ከሃብት ፈጠራና ከብልፅግና ይልቅ፣ ድህነትና ረሃብ ቢበረክቱ ምን ይገርማል?
ባለብቃት ጀግኖችን የማክበርና የማድነቅ ጤናማ ሰብዕና እየራቀን፣... በአንድ በኩል፣ “በጀግኖቹ ድል ኮራን” በማለት፣ የጀግኖችን የአገር ወይም የብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነትን እየቆጠርን፣ የብቃታቸው ተጋሪ፣ የስኬታቸው ባለቤት ለመሆን እንሯሯጣለን - ያለ አንዳች ብቃትና ጥረት። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጀግኖቹ በራሳቸው ብቃትና ስኬት እንዳይኮሩ፣ በአይነቁራኛ እየተከታተልን እናሳቅቃቸዋለን። እናሰናክላቸዋለን። ታዲያ፣ አገራችን ኢትዮጵያ፣ በስኬታማነትና በብቃት የላቁ ጀግኖች የማይበረክቱባት አገር ብትሆን ምን ይገርማል?

Read 3103 times