Sunday, 06 August 2017 00:00

ሙስና፤ ድሃዋን ኢትዮጵያ የት ያደርሳታል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)


          ሰሞኑን መንግሥት “በሰፊ ጥናት መነሻነት” እየወሰድኩ ነው ባለው እርምጃ፣ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ በማባከን፣አገር ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሎ የጠረጠራቸውን 40 ገደማ የመንግስት ተሿሚዎችና ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ ፍ/ቤት ማቅረብ ጀምሯል፡፡ ለመሆኑ የሀገሪቱ የሙስና ችግር፤ ስፋቱና ጥልቀቱ ምን ያህል ነው? ተጠያቂው ማነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው? የሰሞኑ እርምጃስ ዘላቂ መፍትሄ ነው ወይ? … የአዲስ አድማስ
ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ፖለቲከኞችንና የዩኒቨርሲቲ መምህራንን አነጋግሮ፣ ሀሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

               “ሙስና 40 ሰዎች በማሰር ብቻ አይፈታም”
                    አቶ አዳነ ጥላሁን (ፖለቲከኛ)

       ሙሰኞችን ለማሰር በየጊዜው የሚደረገው የአንድ ሰሞን ዘመቻ፣ እኔ በግሌ አይሞቀኝም አይበርደኝም፡፡ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለውን ሙስና ለተመለከተ ጥቂት ሙሰኞች ተያዙ ሲባል አይደነቅም፡፡ ከትንሿ ቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ በአበል ክፍያ እንኳ የሚመዘበረውና የሚባክነው የሀገር ሀብት ቀላል አይደለም፡፡ በቅርቡ እንኳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኦዲት ሪፖርት ላይ ከ3 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በህገ ወጥ የአበልና ደሞዝ ክፍያ ተመዝብሯል መባሉን እናስታውሳለን፡፡ ያልሰሩበትን እጥፍ አድርጎ የመብላቱ ነገር የተለመደ ሆኗል፡፡
ከእዚህ አንፃር እነዚህ አሁን ተያዙ የተባሉት እጣ ፈንታቸው ሆኖ እንጂ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ማን ንፁህ፣ ማን በሙስና የቆሸሸ ነው የሚለውን ለመለየት አዳጋች ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ አንዲትን በሃጢያተኝነቷ እንድትገደል ህዝቡ የፈረደባትን ሴት አስመልክቶ፣ ለተከታዮቹ ይሄን ብሎ ነበር፡- “እስቲ ሀጥያት የሌለበት ይህቺን ሴት በድንጋይ ይውገራት” አሁንም የተደረገው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ እርግጥ ነው ጅምሩ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ከሚጠበቀው በታች ነው፡፡ እኔ እንደውም 3 ቢሊዮን ብር ጉዳት አደረሱ ሲባል፣ ወደ አዕምሮዬ የመጣው፣ ኢትዮጵያ ቅን መሪ አጥታ ነው እንጂ እጅግ ሀብታም ትሆን እንደነበር ነው፡፡
በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣ በጣት በሚቆጠሩ ተዘርፏል መባሉ እኮ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ አሁን የተጀመረው ምንጣሮ፣ አድማሱን ጥቂት ቢያሰፋ ምን ሊባል ነው? ለጆሮ የሚከብድ ነገር እንሰማለን ማለትኮ ነው፡፡ ሀገርን ማዳን የሚቻለው ዘራፊዎች ከዘረፉ በኋላ ወደ ህግ በማቅረብ ሳይሆን እንዳይዘርፉ በመከላከል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ መጠን ሲዘርፉ እንደመጠየቃቸው፣ በሩን ከፍቶ እንዲዘርፉ ያበረታታቸው ስርአትም ሊጠየቅበት ይገባል፡፡ ህዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቅም ይገባል፡፡
የመንግስቱን ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ፣ ከ1997 ዓ.ም በኋላ፣ ከ5 ሚሊዮን በላይ አባላት ማፍራቱን በኩራት ሲናገር እናደምጠዋለን፡፡ እነዚህ አባላት ለምንድን ነው የኢህአዴግ አባል የሆኑት? የትምህርት እድል ለማግኘት? የስራ እድል ለማግኘት? የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ ለመሆን? አይደለምን? እስቲ ይሄን ቆም ብለን እናስብ፡፡ ታዲያ ይሄ ምንድን ነው ስያሜው? የተለየ ጥቅም ለማግኘት መጣር ምንድን ነው ስያሜው? ማጭበርበር፣ ሙስና አይደለምን? ስለዚህ ጥቂት ሰዎችን በማሰር የሚመጣ ለውጥ እኔ አይታየኝም፡፡
ሀገሪቱም በከፍተኛ የሙስና ማጥ ውስጥ እንዳለች ነው የምገነዘበው፡፡ በጥቅሉ ሙስናን ለመቀነስ ማህበራዊ አብዮት፣ የአስተሳሰብ አብዮት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከ25 ዓመት በላይ የቆየ ሙስና፣ 40 ሰው በማሰር አይፈታም፡፡

-----------------

                  “የሙስናው ደረጃ ለአገሪቱ አስጊ ነው”
                      አቶ አስራት ጣሴ (ፖለቲከኛ)

     ሙስና ዝም ብሎ የስርቆትና የሌብነት ማሳመሪያ ስሙ ነው፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ አርግዞ ወልዶ፣ አፍርቶ ያሳደጉት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው፤ ተገቢውን የዲሞክራሲ አስተዳደር በቦታው አለማስቀመጣችን ነው፡፡ ሌላው፤ የሶስቱ የመንግስት አካላት፡- የህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው አካላት፣ አንዱ ሌላውን የመቆጣጠር አቅም ያለመፈጠሩ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አምባገነንነት ሲነግስ፣ ሙስናም አብሮ ይነግሳል፤ ሌላው ነፃ ፕሬስ ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ በሰለጠነው አለም፣ ነፃ ፕሬስ፣ አራተኛው የመንግስት ዘርፍ ነው የሚባለው፡፡ “መንግስት ከሚኖረን ነፃ ፕሬስ ቢኖረን ይሻላል” ያለውን አሜሪካዊ ሊቅ አባባል መጥቀስ ይችላል፡፡ ማንም ሰው ከህግ በላይ እንዳይሆን የሚታገል ከፍተኛ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ የነፃ ፕሬስ አለመኖር፣ ለሙስና መስፋፋት መልካም እድል የሚፈጥር ነው፡፡ በሀገራችንም ሙስናን የማጋለጥ አቅም ያለው ነፃ ፕሬስ እንዲኖር አለመደረጉ የችግሩ መንስኤ ነው፡፡ የፍትህ እጦት፣ የህግ የበላይነት ሲጓደል ነው ሙስና የሚስፋፋው። የህግ የበላይነት በሌለበት ሙስናን ማጥፋትና መታገል አይቻልም፡፡
አሁን እኮ ሙስና እራሱ ስርአት ሆኗል፡፡ ስለዚህ በዚህ አካሄድ ሙስናን እናጠፋለን ማለት የሚሆን አይደለም፤ ቅዠት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2009፣ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ መውጣቱ ተገልፆ ነበር፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ደግሞ የዓለም ሀገራት ያላቸውን የሙስና ደረጃ በሚያሳየው ሰንጠረዡ፣ ኢትዮጵያን ከ177 ሀገሮች በ113ኛ ደረጃ ነው ያስቀመጣት፡፡ ይህ ማለት ከፍተኛ ሙስና የሚፈፀምባት ሀገር ነች፡፡ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ፣ የሚመሩት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ከፍተኛ ፓናል፣ “ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ይወጣል” ብሎ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ስለ ችግሩ ግዝፈት መረጃ ማጣቀስ ይቻላል፡፡ ይሄ ሁሉ ባለበት ነው እንግዲህ በመካከለኛ የስልጣን ደረጃ ያሉ 30 እና 40 ቴክኖክራቶችን በ“ሙስና ጠርጥረን አስረናል” እየተባለ ያለው፡፡ ይሄ ቀልድ ነው፡፡ ይሄ ህዝብንም አለማክበር ነው፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በመግለጫቸው፣ ከሚኒስትሮች ይልቅ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ አመራሮች ናቸው መዝባሪዎች ብለዋል። ይሄ አባባል በእግሩ የቆመን በጭንቅላቱ እንደ ማቆም ነው፡፡
የአስተዳደር ሀሁ የሚያሣየን፤ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ለሚፈጠር ችግርም ሆነ የሙስና ምዝበራ፣ መሪ ሆኖ የተቀመጠው አናቱ ነው፤ ይሄ ሲባል ታች ያሉት ነፃ ይወጣሉ ማለት አይደለም፡፡ አንድ ሚኒስትር በሚመራው ተቋም ውስጥ ለሚፈጠር ችግር ሁሉ የመጀመሪያ ተጠያቂ መሆን ያለበት ዋናው ሹም ነው፡፡ ህንድ አገር በአንድ ወቅት አንድ የባቡር ሹፌር ላደረሰው አደጋ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ስልጣን የለቀቀበትን አጋጣሚ ስንመለከት፣ በኛ ሃገር ያለው ሁኔታ ያስተዛዝባል፡፡ ከላይ ያልጀመረ የሙስና ማፅዳት፣ ወደ ታች ሊሄድ አይችልም፡፡
ሙስና ካለ ፍትህ የለም፡፡ ሙስና ካለ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መመስረት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የኛ ሃገር የሙስና ደረጃ ለሃገሪቱ ህልውናም አስጊ ነው፡፡ አብዛኛው ህዝብ የድህነት አረንቋ ውስጥ ሆኖ፣ ጥቂቶች ገነት ውስጥ ሲኖሩ፣ ይሄ የሙስና መንሰራፋት ምልክት ነው፡፡
የዜጎች ሃገር ጥሎ መሰደድን ኢኮኖሚያዊ ነው ብለን ስላንቆለጳጰስነው ችግሩ አይለወጥም፤ ያ ዜጋ በሌላ ቋንቋ፣ ተገፍቻለሁ የሚል መልዕክት እያስተላለፈ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ የሚሆነው የዲሞክራሲ ስርአት መፈጠር ነው፡፡ የህዝባዊ መግባባት መድረክ መፍጠርና ስርአቱን በአግባቡ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

--------------

                          “ባለሥልጣናትን በማሰር ብቻ ሙስናን መዋጋት አይቻልም”
                             አብርሃ ደስታ (ፖለቲከኛ)

      ሙስናን ለመቅረፍ የመጀመሪያ እርምጃ፣ የመናገርና የመረጃ ልውውጥ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ባለስልጣናትን ቢያስር፣ መሰረታዊ የአስተሣሠቡ ማስፋፊያና ማጠናከሪያ እስካለ ድረስ ሙስናን በዚህች ሃገር መታገል አይቻልም፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ከብዙ ሌቦች ጥቂቶችን ማደን ነው፡፡ ደካማና  እንዲጠቁ የሚፈለጉትን ነው ማደን የተያዘው፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም ሙሰኞች ይያዙ ቢባል ሥርአቱም ሊኖር አይችልም፡፡ ብዙ ሰዎች የኢህአዴግ አባላት የሚሆኑትም የፖለቲካ ርዕዮቱን አምነውበት ሳይሆን ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ከስርአቱ ተጠቃሚ ለመሆን ነው፡፡ ይሄ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፤ ሙስና ነው፡፡ የሙስና ምንጩ ሥርአቱ እስከሆነ ድረስ አሁን የሚደረገው ጥቂቶችን የማሰር ነገር ብዙም ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
የሙስናው ደረጃው ከሌሎች አንፃር ምን ይመስላል የሚለውን እንኳ የምናውቅበት ግልፅ መንገድ የለም፡፡ አሁን እንደ ኬንያ፣ የሙስና መረጃ፣ የኛን ማግኘት አንችልም፤ ምክንያቱም መረጃ የለንም፡፡ መረጃ የሚሰጥም የለም፡፡ ኬንያ ሚዲያዎቿ በስፋት መረጃ የሚያወጡት በሃገሪቱ በተንሰራፋው የሙስና ጉዳይ ላይ ነው፡፡ እኛ ግን ስለ ሙስና መረጃ መፈልፈል፣ በእሣት መጫወት ነው፡፡ ያንን ማድረግ የሚያስችል የሚዲያ መደላድልም የለንም። እራሱ ስርአቱ እየቆነጠረ የሚነግረንን ይዘን ነው የምናወራው እንጂ ገለልተኛ አካል ያወጣውን መረጃ ይዘን አይደለም፡፡
ስለዚህ የሙስና ደረጃችን ይህ ነው ብለን፣ ከሌሎች ሃገራት ጋር ማነፃፀሩ አይጠቅምም፡፡ መረጃ በታፈነበት አገር ስለ ሙስና ደረጃ ማውራቱ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡
ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው፣ ሙስናን የማያስተናግድ ስርዓት ማበጀት ነው፡፡ አደረጃጀቱ ፖሊሲው መቀየር አለበት፡፡ እንደኔ ስርአቱ ከተቀየረ በኋላም ነፃ የፍትህና የሚዲያ ምህዳር አመቻችቶ፣ ዜጎች ድርጊቱን በነፃነት የሚያጋልጡበትና ከለላ የሚያገኙበት ስርአት መፈጠር አለበት። ባለስልጣናትን በማሰር ብቻ ሙስናን መዋጋት አይቻልም፡፡

---------------------

                             “ሙስና የሚፈጸመው የፖለቲካ ከለላን በመጠቀም ነው”
                                   ሙሼ ሰሙ (የግል ፖለቲከኛ)

     በዚህች ሀገር ሙስናው ከስጋትም በላይ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን የተጠረጠሩት ጥቂት ሰዎችን እንኳ እንደማሳያ ስንወስድ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ባክኗል ነው የተባለው፡፡ እኔ የገረመኝ ይሄ ገንዘብ እንዴት ነው የሚመጣው የሚለው ነው፡፡ ይሄ ሀገር በጣም ደሃ ሀገር ነው፡፡ ዜጎቹ ከአፈር ጋር ታግለው ለዓመት የሚበቃቸውን ፍጆታ ማምረት የማይችሉበት ሀገር ነው፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ህዝቡ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖርበት ሀገር ነው፡፡ በድጎማ፣ በድጋፍ የሚኖር በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያለበት ሀገር ነው፡፡ እስከ 10 ሚሊዮን ህዝብ በየጊዜው የረሃብ ቀጠና ውስጥ የሚገባበት ሀገር ነው፡፡ ታዲያ ከሌቦቹ ውስጥ የተመረጡ ሌቦች፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር አጥፍተዋል ሲባል፣ በየአቅጣጫው በመላ ሀገሪቱ ጉዳዩ  ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ልብ ያለው ልብ ይለዋል፡፡ አሁን የተጠቀሱት 4 መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ላይ ደግሞ ማጣት ቢደረግ ሀገር የማትቋቋመው ውጤት ሊገኝ ይችላል ማለት ነው። ይሄ የሙስና ተጠርጣሪዎችን የማሰር ዘመቻ፣ ኢህአዴግ ሙስናን ለማጥፋት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ አይደለም ያሳየኝ፤ ሀገሩ ምን ያህል በስፋትና በጥልቀት እየተበዘበዘና እየተመዘበረ እንዳለ እንጂ፡፡  ይሄን ከዜጎች ተጨባጭ የኑሮ ደረጃ አንጻር  ስናየው የሚያሳፍርም ነው፡፡
የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በልመና ህይወታቸውን ለማቆየት የሚታገሉ ዜጎች ባሉበት ሀገር ላይ ይሄ ሁሉ ቢሊዮን ብር ባክኗል ማለት አሳፋሪ ነው፡፡ ያየነው ደግሞ ገና ጫፉን ነው። በውጭ ምንዛሬ ጭምር ነው ተመዝብሯል የተባለው፡፡ ይሄ የውጭ ምንዛሬ ደግሞ በአብዛኛው በብድርና በእርዳታ የሚመጣ ነው፡፡ ይሄ ለትውልድ የሚሸጋገር የብድር እዳ፣ እንደዚህ መጫወቻ ሆኖ እንደማየት የሚያስደነግጥ ነገር የለም፡፡ ይሄ መንግስት የት ነበር? የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ የመንግስት የቁጥጥር ስርአት ምን ያህል የላላ፤ የገንዘብ ቁጥጥር ስርአቱ የመጨረሻ የተዝረከረከ እንደሆነ ነው የምንረዳው፡፡
አሁን ለምሳሌ ከአዲስ አበባ መንገዶች ጋር በተያያዘ፣ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሰው እሮሮና እንባ ቀላል አልነበረም፡፡ ይሄን መንግስት አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ነው ያሳለፈው፡፡ ለምንድን ነው መንግስት በወቅቱ እርምጃ ያልወሰደው? ይሄ አሁንም ለኔ ጥያቄ ነው፡፡
ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ጨርቅ የሚያስጥሉ ናቸው፡፡ ሙስና ግለሰቦችን በማሰርና ዘመቻ በመክፈት፣ ለሚዲያ እንዲመች አድርጎ በማቅረብ የሚፈታ ችግር አይደለም። ሙስና የሚፈፀሙት ደግሞ የገዥው ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ አባላቱ ምን ያህል በተሰጣቸው ሃላፊነት ልክ ተጠያቂነት ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ መሆናቸውን የሚያሣይ ነው፡፡
በአጠቃላይ ማህበራዊ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡ እንደ ባህል እየቆጠረው ነው፡፡ ይሄ ቆይቶ የሃገር ቀውስ ነው የሚፈጥረው፡፡ ስለዚህ የባህል ለውጡ ላይ በአንፅኖት መሠራት አለበት። በሌላ በኩል የቁጥጥር ስርአቱ ግልፅ መሆን አለበት፡፡
ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንደፈለጉ የሚሆኑበት ስርአት መቆም አለበት። ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከት ብቻ ለስልጣን ማብቃትና ከፍተኛ ገንዘብ ላይ እንዲወስኑ ማድረግ፣ እንደማይሰራ የተለያዩ ሂደቶች ቢያሳዩም ዛሬም ለመማር ዝግጁ አይደለንም፡፡ ሙያን ለባለሙያ መተው ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ተሿሚው ለህግ የበላይነት ተገዥ አይሆኑም። ማንም አይነካንም የሚል አመለካከት ይኖራቸዋል፡፡
ባለሙያ ብቻ ሲሆን ግን የፖለቲካ ከለላ ስለማይኖር፣ ህግና ስርአትን አክብሮ የመስራት እድሉ ይሰሠፋል፡፡ ብዙ ሙስናዎች የሚፈጸሙሩት የፖለቲካ ከለላን በመጠቀም ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ድርጅት፣ ምን አይነት አባላት ነው በዙሪያዬ የሰበሰብኩት ብሎ ወደ ውስጡ መመልከት አለበት፡፡

--------------------

                         “ዘመቻው ያበጠን ቁስል እንዳይፈነዳ የማከም ነው”
                                ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

      ለኔ ሰሞኑን የሚደረገው ዘመቻ ያበጠ ቁስልን እንዳይፈነዳ የማከም ነገር ነው፤እንጂ መሰረታዊ የሙስና ትግል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሙስናን ለመታገል በቁርጠኝነት ቢፈለግ ኖሮ የሙስና መታገያ ስልቶቹ አሁን ከሚደረጉት የተለዩ ይሆኑ ነበር፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ አይደለም ስል፣ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም መደናበር እንዳለበት በመታዘብ ነው። የፖለቲካ ርዕዮተ አለሙ የጥቅም ፈላጊ አባላት መሰባሰቢያነትን የሚያበረታታ ነው፡፡ ያልተገባ ጥቅም መፈለግ ደግሞ ሙስና ነው፡፡
ሙስን ማጥፋት ከተፈለገ ደግሞ ህዝብ እንደፈለገ ሊጠይቀው የሚችለው ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ነፃ ሚዲያ ነው በሌላው አለም የሙስና መታገያ ቁልፉ፣ነጻ ሚዲያ ነው፡፡ ይሄ በኛ ሀገር አለ? የለም፡፡ ህዝቡ መብትና ግዴታውን፤ የመንግስት ባለስልጣናት የሚያንቀሳቅሱት ሀብት የራሱ መሆኑን እንዲያውቅና የነቃ ክትትል እንዲያደርግ የሚያስተምሩና የሚያበረታቱት የሲቪክ ተቋማት የሉንም፡፡ ይሄ ህዝቡ ጠያቂ እንዳይሆን አድርጎታል። ህዝብ ሲፈልግ ከስልጣኑ በምርጫ ሊያወርደው እንደሚችል አውቆ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር፣ የብዙኃን ፓርቲ ዲሞክራሲ ያስፈልጋል። እነዚህ ሁሉ በሌሉበት ጥቂት ሙሰኞችን አስሮ ሙስናን እየታገልኩ ነው ማለት፣የሚዲያ ሰሞነኛ ርዕሰ ጉዳይ ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡  
አንድ ሰው ወደ ፖለቲካ ስልጣን ሲመጣ፣ ለሃገርና ለህዝብ ጥቅም ከማገልገል ይልቅ ለራሱ ጥቅም መሯሯጥ ተለምዷል፡፡ ሙስናውም በተደራጀ መልክ የሚፈፀም ተቋማት ይዘት ያለው ሆኗል፡፡ ስልጣን ባለውና በሌለው መካከል የሃብት ልዩነቱ ሰፍቷል፡፡
ስለዚህም እያቆጠቆጠ ያለው ነገር በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት ቀጣይ እጣ ፋንታችን አስጊ ይሆናል፡፡ እንደኔ የሙስና ትግል እየተባለ ሰዎች ማሠሩ የትም አያደርሰንም፡፡ መሠረታዊው ጉዳይ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው ስርአት መፍጠሩ ነው፡፡

-------------------

                           “በአመለካከት ደረጃ፣ ሙስና መፈፀም መብት ሆኗል”
                                ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

      የሀገራችንን የሙስና ደረጃ የጠቆመ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት፣ ከ177 ሀገራት ውስጥ 113ኛ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ  ያመለክታል፡፡ ይሄ ሙስና ምን ያህል እንደተንሰራፋ ነው የሚያሳየው፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ደግሞ በአንዴ ሳይሆን በአመታት የዳበረ ልምድ ነው የሚፈጠረው፡፡ ለሙስና ምቹ የሚሆነውን መደላድል መጀመሪያ የሚፈጥረው አመለካከት ነው፡፡ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ መፈጠር አለበት፡፡ ይሄ በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በንግዱ ማህበረሰብ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በሃይማኖት ተቋማትና በሌሎችም የማህበረሰቡ እንቅስቃሴዎች ነው መፈጠር ያለበት፡፡
ህብረተሰቡ እኮ ሁሉም መረጃ አለው፡፡ ለምሳሌ በየከተሞቹ ሙስናን የሚያንፀባርቁ መጠሪያ ያላቸው አካባቢዎችና ህንፃዎች አሉ፡፡ ይሄ ህብረተሰቡ ስርቆትን እንደ ልማድ እየቆጠረውና ለአጠራርም እየቀለለው እንደመጣ ነው የሚያሳየን፡፡ ድሮ ሰው የማይሰርቀው ተይዞ ስለሚቀጣ አይደለም፤ ሌባ መባልና ሙሰኛ መባል ስለሚያሳፍረው ነው፡፡ አሁን ይሄ ተቀይሯል፡፡ ሙስና መስራት መከበሪያ ሆኗል። ይሄ ማህበራዊ ኪሳራችን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ነው ሙስና ማህበረሰቡ ውስጥ የሰረፀው፡፡ አንድ አባት ለልጁ አስተዳደግ እንደሚጠየቀው ሁሉ፣ ለዚህ ማህበራዊ ኪሳራችን ደግሞ ተጠያቂው መንግስት ነው፡፡
ፍፁም ሙስናን የሚጠየፍ መንግስት ቢኖር፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ አመራር ቢኖር፣ ሙስና በዚህ ደረጃ ማህበረሰቡ ውስጥ ለመስረፅ አይችልም ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በሀገሪቱ የተዘረጋው ስርአት በራሱ ሙስናን የሚያበረታታ ነው፡፡ አንድ በሙስና የተጠረጠረን ሰው የስልጣን ቦታ ሲቀየርለት ነው መንግስት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ እንዳልሆነ የታወቀው፡፡ አሁን 30 እና 40 ሰው ላይ እርምጃ መውሰዱ ያን ያህል አስተማሪ አይሆንም፡፡ ትልቁ ነገር የአመለካከት ለውጥ ማምጣቱ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- በስኳር ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር ባክኗል ሲባል መጠየቅ ያለበት አናቱ ነው። በሌላው ዓለም እንዲህ ያለው አመራር ከስልጣኑ ወርዶ በግልፅ በህግ ይጠየቃል፡፡ አናት ላይ ያሉት ሳይጠየቁ ከስር ያሉትን ተጠያቂ ማድረግ ምን ማለት ነው? የአመለካከት ለውጡን መፍጠር የሚቻለውም ትናንሾቹን በማጥቃት አይደለም፡፡ አሁን ያለው እርምጃ “ትናንሾቹን ዓሳ ትላልቆቹ በሏቸው” አይነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው እኮ ፓርማ ላይ “ክልሉን አልነግራችሁም አንድ ክልል የተመደበለትን ብር ባለስልጣናቱ በልተውታል” ብለውን ነበር፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ይሄ ሙስናን ከማበረታታት ምንም አይተናነስም፡፡ ይሄን አድርገዋል ግን እርምጃ አንወስደም እኮ ነው የተባልነው፡፡ ይሄ አመለካከት ነው ሙስናን እዚህ ያደረሰው፡፡   
ከሠሞኑ የመንግስት መግለጫ የምንረዳው፣ ማህበረሰባችን ምን ያህል የማይገባ ጥቅም ፈላጊ እየሆነ እንደመጣ ነው፡፡ የማይገባ ጥቅም ፈላጊ ነጋዴዎችና የማይገባ ጥቅም ፈላጊ ባለስልጣናት ናቸው አሁን የተጣመሩት፡፡ ስለዚህ መፍትሄው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ባለስልጣናት በፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ሳይሆን በሙያ ብቃታቸው ሲሾሙ፣ የመንግስት ጨረታ ግዢና ሽያጭ ጉዳዮች ግልጽነት ባለው ሁኔታ ሲካሄድ፣ ፍ/ቤቶች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሲሰሩ ነው፤ ነገሩ የሚቀየረው እንጂ ሰዎችን በዘመቻ እየለቀሙ አስሮ 20 ዓመት እስራት በመፍረድ አይደለም፡፡
አሁን ያለው አካሄድ የፖለቲካዊ ዘመቻ አካሄድ ነው እንጂ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አይሆንም። በአንድ ወቅት አንድ ባለስልጣን ውለታ ዋልኩለትና በምላሹ፣ ሠበታ ላይ መሬት ልስጥህ አለኝ፡፡ እኔ አይሆንም አልፈልግም አልኩኝ፡፡ ለወዳጆቼ ስነግራቸው፣ “መውሰድ አለብህ፤ ይሄ እኮ የዜግነት መብትህ ነው” አሉኝ፡፡ ይገርማል፤የህዝብ ሃብት መዝረፍ መብት ሆኗል - በአመለካከት ደረጃ፡፡
አሁን ላይ የሃገር መከላከያ፣ የኮንስትራክሽን ኩባንያ አለው፡፡ በወትድርና ሃገር ለመጠበቅ የሠለጠነ አካል እንዴት ነጋዴ ይሆናል? ስራቸው እኮ ሃገር መጠበቅ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ናቸው ስለ ጉዳዩ ስናወራ መፈተሽ ያለባቸው፡፡  

------------------

                     “የፀረ ሙስና ትግል የአስተሳሰብ ትግልን ይጨምራል”
                            አቶ ፋንታው አምባው (የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ)

       የፀረ ሙስና ትግሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ነው።  ወደ ክልሎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሙስና በልማት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ይህን መከላከል የሚቻለው ደግሞ ለዚሁ የወጡትን ህጎች ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ አሁን እየተሰራ ያለው ስራም ህግን የማስከበር ነው፡፡ ያልደከሙበትን ንብረት በመዝረፍ፣ በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ሃይሎችን፤ መንግስት ያለውን መረጃ ተመስርቶ፣ በቁጥጥር ስር የማዋሉን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የፀረ ሙስና ትግሉ በመንግስት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ ሲሳተፍበት ነው የሚሳካው፡፡ ህግ አስፈፃሚው አካል፣ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነትና ስልጣን ተጠቅሞ ህጋዊ እርምጃ ሲወስድ፣ ህብረተሰቡ መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ሙስኞችን በህግ ጥላ ስር የማዋሉ ተግባር በፌደራል ብቻ የሚወሰን አይሆንም፡፡  ግለሠቦችን በህግ ቁጥጥር ከማዋል ባሻገርም ሰርቶ እንጂ ሰርቆ መበልፀግ እንደማይቻል ሰፊ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሠቡም ይህ ተግባር በባህልም ደረጃ አደገኛ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ በጊዜ መፍትሄ ካላገኘም የሃገራችንን ልማት ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ስለዚህ መንግስትና ህብረተሠቡም ተሣስሮ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ዘላቂ ሠላምና ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ የሚቻለው፣ ህግና ህጉን መሠረት አድርጎ ሲኬድ ብቻ ነው፡፡ ህጉ የበላይ ሲሆን ነው፣ እነዚህ ነገሮች ሊረጋገጡ የሚችሉ፡፡
እንደዚህ አይነት የወንጀል ተግባራት በባህሪያቸው አደገኛ ናቸው፡፡ ይሄን ወንጀል ተከትሎ ሊመጣ የሚችል ቀውስ እንዳለም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የፀረ ሙስና ትግል ሲባል የአስተሣሠብ ትግልን ይጨምራል፡፡ የአመለካከትና የአስተሣሠብ ለውጥ ማምጣቱ ነው ዘላቂው መፍትሄ፡፡
ይሄ እርምጃ የተወሠደው የኦዲት ሪፖርቶችንና ሌሎች መዋቅሮችን በመጠቀም በተሰባሰቡ ማስረጃዎች ላይ በመመስረት መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ይሄ መሠሉ እርምጃ ፌደራል ከክልል ሳይለይ፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ ነው የሚቀጥለው፡፡
የወንጀል ህጉ አላማ፣ የሃገሪቱን ህዝቦች ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ ይሄ ህግ ተፈፃሚ ሊሆን የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ ይህ አላማ እንዲሣካ ህጉን የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

Read 4491 times