Sunday, 06 August 2017 00:00

“በስመ ማርያም” ብለን ያመጣነውን እንጀራ፣ ያልደከሙ እየበሉት ነው

Written by 
Rate this item
(15 votes)


         የታወቀ ተረት ይሁን እንጂ አንድ መፅሐፍ ላይ እንደሚከተለው የቀረበ ታሪክ አለ። በአንድ ወቅት አንበሳ፤ የተፈጥሮ ጥላቻውንና ተቀናቃኝነቱን ይብቃኝ ብሎና በሆነ ምክንያት ትቶ፤ ኑሮና ሕይወትን ቀላልና ውጤታማ ለማድረግ ፈለገ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሌሎች እንስሳት ጋር መተባበር አስፈላጊ መሆኑን አመነበት፡፡ ይሄንኑ ለማድረግ ወደ ጅብ፣ ነብርና ተኩላ ሰፈር ሄደ፡፡
ባልተለመደ ትህትናዊ መንገድ የዱሮ ጉልበተኛነቱንና ማስፈራራቱን ሁሉ ትቶ፤ አዲሱን ዕምነቱን ነገራቸው፡፡ ሦስቱም በጣም ተደሰቱ፡፡ ዕምነቱን መጋራታቸውንና ተግባራዊ እንደሚያደርገው ለማረጋገጥ ወደ ጫካ ሄደው፤
የመጀመሪያውን ትብብር በአንድ ታላቅ አደን እናሳይ፤ ተባባሉ፡፡ ሰለባቸውን በመሻት፣ አንድ ላይ ሲጓዙ አርፍደው፤ በመጨረሻ ቋጥኝ የሚያክል ጎሽ አጋጠማቸው፡፡
እርዳ ተራዳ ብለው፤ ተባብረው ጎሽን ግዳይ ጣሉት፡፡
የንብረት ክፍፍሉ ሰዓት ደረሰ፡፡ አንበሳ፤ እንደተለመደው፣ ከውሉና ከስምምነቱ ውጪ፣ የግዳዩ ዋና አዳይና ደልዳይ እኔ ነኝ አለ፡፡ በባህሪያቸው አራቱም የተለያየ የምግብ አወሳሰድ ባህል ስላላቸው፤ አብረው መብላት አይችሉም፡፡ ነገሩን የተረዳው አንበሳ፤ ድርሻ ድርሻችንን መካፈልና መውሰድ አለብን ሲል ወሰነ፡፡ ሶስቱም በጥርጣሬ እያዩት ተስማሙ፣ ይሁን እሺ አሉት፡፡
አንበሳ ሥጋውን በአራት ከፈለውና፤
ይህ የአራዊት ንጉስ በመሆኔ ይገባኛል፤ አለ
ሁለተኛውን መደብ እያሳየ፤ ይሄ ደግሞ፤ በዚህ አደን ትልቁን ሚና ስለተጫወትኩ ዋጋዬ ነው፣ ለእኔ ይገባል
ሦስተኛውን መደብ አቅርቦ፣ ይሄ በእንስሳነቴ የእኔ የግል ድርሻዬ ነው
አራተኛውንና የመጨረሻውን መደብ እያሳያቸው፤ ‹‹ይሄን የሚነካ ወዮለት!›› አለ፡፡
*   *   *
ማንም ቢሆን፤ የባህሪውን፣ የጠባዩን ፈፅሞ አይተውም፡፡ ጅብ ማንከሱን፣ አዞ ማልቀሱን፣ እባብ መላሱን፣ ግስላ ዘራፌነቱን፣ ሰጎን አሸዋ ውስጥ አንገቱዋን መቅበሯን… አይተዉም፡፡ መቼም ቢሆን መቼም፣ የአንበሳውን ድርሻ በእኩልነት የሚካፈል እንስሳ አይፈጠርም፡፡ አንበሳ አንበሳ ነውና፣ የአራዊት ሁሉ ንጉስ መሆኑን ብቻ ነው የሚያምነው!! እንድንቀበለው የሚፈልገውም ይሄንኑ እውነት ነው፡፡ ስለሆነም ሌላው እሱን ለማገልገል እንደተፈጠረ አድርጎ ማየቱና ማስገበሩ ግድ ይመስለዋል፡፡ ሌሎቹ እንስሳት፤ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› የሚለውን ተረት አያውቁትም ብሎ ያስባል፤ ወይም እውነትም አያውቁትም!
ሙስና፤ የሹሞች፣ ከተለመደው አገርን የማገልገል ተግባር ወደ ግል ጥቅም ማፈንገጥ ነው፡፡ ሙስና ያለ ጥርጥር በሁሉም ህብረተሰብ ውስጥ ይኖራል፡፡ ሆኖም ከማህበረሰብ ማህበረሰብ መጠኑ ይለያያል፡፡ ከአንዱ ዘመን አንዱ ዘመን ውስጥ ሊጎላም ይችላል። በስሜታዊ መልኩ የሚታዩ ጭብጦች እንደሚጠቁሙት፤ የሙስና መጠን ከፈጣን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዝመና ጋር ይተሳሰራል፡፡ በአሜሪካ በ18ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የታየው ሙስና፤ ከ19ኛ ምእተ-ዓመትዋ አሜሪካ ሙስና ይልቅ ዝቅ ያለ ነበር የሚል ግምት አለ፡፡ በብሪታኒያም እንደዚሁ፣ በ17ኛው እና በ19ኛው ምእተ-ዓመት መባቻ ላይ የታየው ሙስና፣ በ18ኛው ምእተ ዓመት ከነበረው ያነሰ ነው የሚመስለው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በብሪታኒያ የታየው ሙስና፤ ከኢንዱስትሪው አብዮት፣ አዳዲስ የሀብትና የሥልጣን ምንጮች፣ እንዲሁም መንግስት ላይ አዳዲስ ጥያቄን ይዘው ብቅ ካሉት መደቦች መፈጠር ጋር አብሮ መከሰቱ የአጋጣሚ ነገር ነውን? አይደለም፡፡ ከቡቃያ ሀብታሞች መፈልፈል ጋር አብሮ የፈላ ነው፡፡ የእኛ ግን እንቆቅልሽ ነው! ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከባዩ ፍጥጥ!
እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው በሚል አስተሳሰብ፣ በተቀነበበ ህብረተሰብ ውስጥ መንግስትን ከልብ ማመን ይኖራል ማለት አዳጋች ነው፡፡ በመሰረቱ በኢትዮጵያ የሚከሰተው ለውጥ እስከ ዛሬም ሆነ አሁን፣ ከሥረ መሰረቱ ውል የያዘና ህዝብን በትክክል ያሳተፈ ባለመሆኑ፣ እኔ ምን ተዳዬ ይበዛዋል፡፡ ገዢ ሁሉ አንድ አይነት ነው። ፖለቲካ ሁሉ ወይ አባብሎ ማዘያ፣ ወይ አስፈራርቶ መግዣ፤ ዘዴ እንጂ ማንም የማንንም እንጀራ አብስሎ የሚሰጥበት ሂደት አይደለም፤ የማለት እምነት የተጠናወተው ነው፡፡ በዚህ ማህል አገር፤ ህዝብ፣ ሉአላዊነት፤ ዲፕሎማሲ ወዘተ. ከልብ የሰፈሩና ከልብ የምንታገልላቸው አጀንዳዎች መሆናቸው ይቀርና፣ ሁሉም “እኔን አዳምጡ” የሚባልባቸው ስብከቶች ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ያውጣን!!
ተቃዋሚም ሆነ አጋር ድርጅቶች፤ከአንዱ ገንዘብ እኩል አገኛለሁ ብሎ ገበታው ላይ ዐይኑን ማፍጠጡ፣ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ የፖለቲካውን መድረክ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ያልተጋራ፣ ከኢኮኖሚው አዝመራ ቁና ይደርሰኛል፤ የአገር ሀብት የእኔም ድርሻ አለበት ቢል፤ ‹‹ሞኝ ጎረቤት፤ከልጅህ እኩል አርገኝ አለ” የተባለውን ዓይነት የደካሞች መጃጃል፣ ወደ ፖለቲካው ጎራ ልክተት የማለትን ያህል የሽንፈት መለዮ ማጥለቅ ነው፡፡ አንበሳው ሙሉውን ሳይደክም ወስዶታል፡፡ እውነተኛው ተረት፤ ‹‹በስመ ማሪያም ብለን ያመጣነውን እንጀራ፣ ያልደከሙ እየበሉት ነው›› የሚለው ነው፡፡

Read 5887 times