Sunday, 06 August 2017 00:00

የአንድ አገር ሁለት መሪዎች ፍጥጫ

Written by  ተመስገን ጌታሁን ከበደ (temesgengt@gmail.com)
Rate this item
(3 votes)

      አሁን በተለያየ ክፍለ ዘመናት የነበሩት አፄ ምኒልክና አቶ መለስ ዜናዊ ተገኛኝተው የተፋጠጡበት ዘመን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ የመንግስት ሠራተኛ የነበርኩ ጊዜ ቢፒአር የሚሉት አብዮት መጥቶ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ ያንጊዜ ኢህአዴግ እዚህ ግባ በማይባል ፉክክር፣ በምርጫ አሸንፎ፣ አዲስ አበባን መልሶ ከሁለት ዓመት በኋላ እጁ ያስገባበት ጊዜ ነበር፡፡ አበል የበላንበት የአምስቱ ቀኑ ሰልጠና እንዳለቀ፣ እንደ አዲስ የሠራተኛ ምደባ ተካሄደ፡፡ ኢህአዴግ በሲቪል ሰርቫንቱ ላይ ቂም ይዞ የመጣ ነበር የሚመስለው፡፡
የሚሾሙትን ለመሾም፣ የሚያባርሩትን ለማባረር፣ አዲሶቹ ተሿሚዎች አሪፍ ቀመር ታጥቀው ነበር የመጡት፡፡ ያው የተለመደው ታማኝነት (Patronage) ዋና መስፈሪያ ሆኖ፣ በኢህአዴግ ዓይን ጥርጣሬ ውስጥ የገባ ሲቪል ሰርቫንት አንድም ሳይቀር ተመንጥሯል፡፡
በአንዱ የስልጠና ውሎ የተነሳው ተራ የሚመስል ጥያቄ ነበር ለነገሬ መነሻ የሆነኝ፡፡ አንዲት ተሰብሳቢ፣ የዕለቱ መነጋገሪያ ርዕስ የነበረው፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”፣ምን እንደሆነ አልገባ ሲል እንደ ዋዛ ያነሳችው ጥያቄ፣ አእምሮዬ ውስጥ ተሰንቅሮ ቀረ። ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንም ነገር ባላውቅም መልሱ ተድበስብሶ እንደታለፈም ገብቶኛል፡፡ ፖለቲካ ከሚጠሉ ወይም ከሚሸሹ ሰዎች አንዱ ስለሆንኩ፣ ነገሩን ችላ ብዬ ለማለፍ ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን የሴትዮዋ ጥያቄ ከአእምሮዬ ሊጠፋ አልቻለም ነበርና፣ መልሱን አውቄ መገላገሉን መረጥኩኝ።
አብዛኛዎቻችን በሆነ ምክንያት ፖለቲካ ‘እንጨት እንጨት’ ስለሚለን፣ ጥያቄው “ደባሪ” እንደሆነ ይሰማኛል። ነገር ግን የኢህአዴግ ካድሬዎች፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ምን እንደሆነ በዝርዝር አለማወቃቸው ግር የሚል ነገር አለው፡፡ ምንም አሰብን ምን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የዚችን አገር እጣ ፈንታ እየወሰነ ያለ መሆኑን ግን መካድ አይቻልም። በዚህ ምክንያትም ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማወቅ የሚገባኝን ያህል ማወቅ እንዳለብኝ ራሴን አሳምኜ፣ በጉዳዩ ገፋሁበት፡፡ መጽሐፉን አፈላልጌ ባነብም፣ ጭብጡ ቅርጽ አልይዝ ሲለኝ፣ “እዚያና እዚህ የሚረግጥ፣ ዝርክርክ ያለ ሀሳብ የተሸከመ መጽሐፍ” ነበር የመሰለኝ፡፡ የእኔን ያለመረዳት ድክመት መጽሐፉ ላይ መለጠፍ እንደማያወጣኝ ሲገባኝ ደግሞ የግዴን ደግሜ ደጋግሜ ፈተና እንደደረሰበት ተማሪ አጠናሁት፡፡ በተለይ ከስራ መልስ ምሽት ላይ መጽሐፉን ሳነብ በድካሜ ላይ ድብርት ተጨምሮበት፣ ዐይኔ በእንቅልፍ ብልጭ ድርግም እያለ እቸገር ነበር፡፡ እንቅልፍ ሲያሸንፈኝ መጽሐፉ ከእጄ እያመለጠ ቢወድቅም፣ ከእንቅልፌና ከድብርቴ ጋር እልህ ተያይዤ ሀሳቡን ለመጨበጥ ሞከርኩ፡፡ “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” ብሎ ላደገ ለእንደ እኔ አይነቱ ሰው፤ እንዲህ አይነት መጽሐፍ ማንበብ እጅግ ከፍተኛ ትዕግስት አንደሚጠይቅ ተረድቼአለሁ፡፡
የሆነው ሆኖ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጽሐፍ በመጠኑም ቢሆን የገባኝ ሲመስለኝ ሀሳቡን በመጭመቅ አጠር ያለ ማስታወሻ ያዝኩ፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከፖለቲካ አንጻር ከሌሎች የዲሞክራሲ አይነቶች “እለያለሁ” የሚለው የቡድን መብት (የብሔር ብሔረሰቦች መብት)፣ ከግለሰብ መብቶች በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና መኖሩን እንደ ዋና መነሻ ሀሳብ በመውሰድ፣ ለቡድን መብት ቅድሚያ መሰጠቱ በሰነዱ ተገልጿል። በዚህም ምክንያት አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ የብሔር/ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚያከብር በመሆኑ ከሌሎቹ ይለያል፡፡ ሌላው ልዩነት የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንጂ ብሔራዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ የለም ማለቱ ነው፡፡ በዓለም ላይ በሚገኙ አብዛኛዎቹ የፌዴራል መንግስታት፣ ብሔራዊ ቋንቋ ኖሯቸው፣ ሌሎችም ቋንቋዎች በየትም ስፍራ የስራ ቋንቋ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
የኢኮኖሚውም መርህ በግልጽ እንደሚያሳየው፤ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ጣልቃ ይገባል፡፡ መንግስት ከችርቻሮ ጀምሮ እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ፋብሪካዎች ድረስ ባለቤት ነው። ሆኖም ፍትሀዊ የሀብት ስርጭትን በተመለከት በግልጽ የተጻፈ ነገር የለም፡፡
ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የተለየ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ከማንኛውም ግብር ነጻ ናቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ከ5 እስከ 7 ዓመት ተከታታይ የታክስ እፎይታ ይሰጣል። ሆኖም ከእዚህ ውጭ ያሉ በጥቃቅን ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሳይቀሩ ግብር ስለሚጣልባቸው፣ ፍትሀዊ የሀብት ስርጭት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ነው የወደቀው፡፡ መንግስት ከችርቻሮ እስከ ታላላቅ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እጁን በማስገባቱ፣ የመንግስት ባለስልጣኖች በሙስና ውስጥ ለመዘፈቅ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ራሱ እንደሚነግረን፤ ሙሰኝነት፤ የመልካም አስተዳዳር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮቶች፣ የራሱ የስርአቱ አደጋ ናቸው፡፡
ሆኖም ይህ ችግር አብዮታዊ ዲሞክራሲ የወለደው የኢኮኖሚ ፍልስፍና ችግር መሆኑን ለማመን፣ ለኢህአዴግ የሚታሰብ አይመስልም፡፡ ሌላው ቀርቶ መሀል ከተማ ላይ የተሰሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ድሀው ሕብረተሰብ እንዳይገዛቸው ዋጋቸው የማይቀመሱ ባለብዙ ክፍሎች እንዲሆኑ ዲዛይናቸው መቀየሩ፣ የመንግስት ባለስልጣናትን ለሙስና የሚያጋልጥ ነው፤ በተለይ እንዳይሆኑ፣ ህንጻው ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ፣ በምስጢር ተይዞ፣ ለቤት ባለቤቶች እንደ  ዱብዕዳ ሲነገራቸው፡፡
የሶሻል ዲሞክራሲ ስርአት የሚከተሉ አገሮች፣ ፍትሀዊ የሀብት ስርጭትን በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው ነው የሚሰሩት፡፡ አንዱ የሀብት ማመጣጠኛ ዘዴያቸው የታክስ አስተዳደር ነው፡፡ ብዙ የሚያገኝ ብዙ ታክስ ይከፍላል፡፡ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ማህበረሰብም ለኑሮው የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮች በማሟላት፣ ዜጎቻቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ያደርጋሉ፡፡
አብዛኛዎቹ የአውሮጳ አገራት ይህንን ሞዴል ይከተላሉ፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግን ከእሳትና ከጢስ ጋር የምትታገለውን ጠላ ቸርቻሪ ሴት ሳይቀር ግብር ከማስከፈል ወደ ኋላ አይልም፡፡ የታክስ አስተዳደር፣ አለቆችና ምንዝሮች፣ ከሌላው የመንግስት ሠራተኞች የተለየ ወፍራም ደመወዝ መብላታቸው ሳያንሳቸው፣ ሙስና ብርቃቸው አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ ኢህአዴግ ራሱ ያረጋግጥልናል፡፡ ወህኒ የሚጣሉ የታክስ አስተዳደር አለቆችና ጭፍሮች ቤታቸው ሲፈትሽ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር፤ ዶላርና ዩሮ በየሽርንቁላው አስቀምጠው አጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ይነግረናል። ሕዝቡ ግን ለፖለቲካ ፍጆታ የሚሰራ ትርኢት መሆኑን ማንንም ሳይፈራ ሲናገር  በየዕለቱ ይሰማል። ሕዝብ መንግስትን የቀደመበት አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ናት፡፡ አሁን ያለው የሙስና ሁኔታ፣ ሥጋ የሌለውን አጥንት የመጋጥ ያህል ምህረት የለሽ ጭካኔ  የተሞላበት ሆኗል፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማስመዘገቡን ያህል የኢኮኖሚው ፍሬ ተመጋቢዎች፣ በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሹመኞችና አጃቢዎቻቸው ብቻ በመሆናቸው፣ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ጠብ የሚል ነገር አልታየም፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ቁጥር እያሻቀበ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አንካሳ ሆኖ ለመጓዝ ግድ ሆኖበታል፡፡ የመንግስት ባለሥልጣኖችን የሚያባንን ክፉ ሕልም ምክንያት፣ ይኸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሆኑን ኢህአዴግ ልብ ያለ አይመስለኝም ወይም ልብ ማለት አይፈገልግም ይሆናል፡፡ ማህበራዊ ሕይወትን በተመለከተ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ መሰረቱ ገበሬ ነው ሲል፤ ሶሻል ዲሞክራሲ ሠራተኛው፤ ሊብራል ዲሞክራሲ ባለ ኢንዱስትሪው እንደሆነ ያምናል፡፡ ኢህአዴግ ግን የአገሪቱ  አብዛኛውን ሕዝብ የሆነውን ገበሬ ነው “የእኔ መሰረት” ማለቱ የሚያዋጣ ፍልስፍና ይመስላል። ይሁንና በ1998ቱ ምርጫ ችላ ተብሎ በነበረው በከተሜው ማኅበረሰብ ኢህአዴግ ክፉኛ የፖለቲካ ኪሳራ ደርሶበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ነበር ኢህአዴግ ፊቱን ወደ ከተማ የመለሰው፡፡ በሚሊኒየሙ ዋዜማ ለከተሞች ትኩረት ተሰጥቶ፣ አዳዲስ ፖሊሲዎችን እስከ ማውጣት የተደረሰው በከተሜው የፖለቲካ ጫና ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ነው፣ የቤቶችና ከተሞች ልማት ሚኒስቴር፤ ለከተሞች ልዩ ትኩረት አድርጎ መስራት የጀመረው፡፡ ሆኖም በየዓመቱ ለዜና ፍጆታ የሚሆን የከተሞች ቀን ከማክበር ውጭ ትርጉም ያለው ለውጥ ሲመጣ አላየንም፡፡ ተበታትኖ ከሚኖር ገበሬ ይልቅ ጆሮ ለጆሮ ተጠጋግቶ የሚኖረው ከተሜ ተጽዕኖው ገጠር ድረስ የመሻገር ኃይል እንዳለው ኢህአዴግ በሚገባ ተገንዝቧል ብዬ አስባለሁ፡፡
ምዕራባዊያን አገሮች እንደ ሁኔታው ሶሻል ዲሞክራሲና ሊብራል ዲሞክራሲ እየተከተሉ ዘመናትን ተሻግረውበታል፤ በልጽገውበታልም፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከተረዳን ለርእሴ መነሻ ወደሆነኝ ጉዳይ የአፄ ምኒልክንና አቶ መለስ ዜናዊ የአስተሳሰብ ፍጥጫን እንመልከት፡፡
በታሪክ በቂ ስፍራ ያላት ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፤ በዘመነ መሳፍንት ተዳክማ፣ በየጎጡ ተቆጥረው የማያልቁ ንጉሦች ነበሯት፡፡ ደካማ እንደሆነች ግን አልቀረችም። የጊዜ ሂደቱን ጠብቆ ከወደ ቋራ ባለ ርእዩ መይሳው ካሳ ተነስተው፣ ኢትዮጵያን መልሶ እንደ ጥንቷ ሊገነቧት ዘመነ መሳፍንትን ድባቅ የሚመታ መሠረት ጥለውላት አልፈዋል፡፡ የትግሬው በዝብዝ ካሳ፤ ሕይወታቸውን ሳይሳሱ ሰጥተው፣ ቴዎድሮስ የጀመረውን አጠናክረው አልፈዋል፡፡ በመጨረሻም የሸዋው አቤቶ ምኒልክ፤ ንግሥና ወር ተራው ሲደርስ፣ የአሁኗን ኢትዮጵያን በቅብብሎሽ የመስራቱን የቤት ስራ ለማጠናቀቅ በቅተዋል፡፡ ከአፄ ምኒልክ በኋላ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ ሳይደረግ ንግሥት ዘውዲቱ፤ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ስላሴ፤ ከዚያም የወታደሩ ንጉሥ መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን እየተቀባበሉ ሲገዙ ቆይተው፣ ኢህአዴግ ደርግን አባሮ፣ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ሲገባ ነበር፣ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የፖሊሲ ለውጥ የተደረገው፡፡
አገር የማስተዳደር ወር ተራው የኢህአዴግ ከሆነ 28ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ኢህአዴግ ጫካ ሆኖ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ጽንሰ ሀሳብ አምጦ ከወለደ እነሆ፣ ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን እየተጠጋ ነው፡፡  በኢህአዴግ ዘመን፣ ዳግማዊ ምኒልክ አጀንዳ እየሆኑ በሰፊው የሚቀርቡት ለምንድን ነው? በሕይወት የሌሉት ምኒልክን ማንስ ቢጠላቸው ምን እንዳይሆኑ ነው ኢህአዴግ ምኒልክን የሚያወግዘው? ምርጫ በተቃረበ ቁጥር የምኒልክ ጉዳይ ተደጋጋሚ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል፡፡ አቀራረቡ ምኒልክ፣ የአንድ ኃይለኛና ስልጣን ለመያዝ የሚችል አስጊ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እስኪመስሉን ድረስ፣ ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶበት በአሉታዊ ጎኑ ይቀጠቅጣቸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፤ “እምዬ” ተብለው ሲወደሱና ሲዘመርላቸው፣ አዲሱ ትውልድ ጆሮውንና ልቡን ከፍቶ ያዳምጣል፡፡ አፄ ምኒልክ፤ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ንግሥናቸውን ከአንኮበር ቤተመንግስት ጀምረው፣ የአሁኗ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው፣ መንፈሳቸው አሁንም ድረስ እንደሰፈፈ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ቅኝ ገዥዎችን አንገት አስደፍተዋል፡፡ ይሁንና ይህንን አንጸባራቂ ሰብእና ለማኮሰስ የሚደረገው ጥረት ከምን የተነሣ ነው?
መቼም ምርጫ በደረሰ ቁጥር አገር አቀፍ ስብሰባ እየተደረገ፣ ኢህአዴግ አፄ ምኒልክን አጀንዳ አድርጎ የሚተገትጋቸው፣ መቃብራቸውን አራግፈው ቤተ መንግስት አንዳይገቡ ሰግቶ አንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ከአንድ ምእተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ሰፍፎ የቆየው የምኒልክ አሀዳዊ መንግስት አስተሳሰብና ለጠላቶቿ የማትቆረጠም አገር የፈጠሩበት አስተሳሰብ አሁንም ድረስ ገንኖ የወጣ፣ ሕያው የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢህአዴግ ከጫካ ጀምሮ ላለፉት 40 ዓመታት የሚከተለው የአቶ መለስ ዜናዊ ፌዴራል መንግስት አስተሳሰብና ፖሊሲ አለ፡፡ እነዚህ ጽንፍና ጽንፍ የቆሙ ፖሊሲዎች ናቸው ለአፄ ምኒልክ መንፈስና ለአቶ መለስ ዜናዊ መንፈስ ፍጥጫ ምክንያት የሆኑት። ወንበሩ የኢህአዴግ ስለሆነ ያለ ከልካይ የሚኒልክን የፖለቲካ አስተሳሰብ የማውገዝ ዕድሉ በጣም ከፍ ያለ ቢሆንም የአፄ ምኒልክ አስተሳሰብም መሬት የማይወድቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አፄ ምኒልክ ኢህአዴግ እስካለ ድረስ በአጀንዳነት እየተነሱ  መነታሪኪያ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡
የአፄ ምኒልክንና የአቶ መለስ ዜናዊን አስተሳሰቦች በንጽጽር ስናያቸው፣ በአጼ ሚኒልክ እንደገና ትንሳኤ ያገኘችው ኢትዮጵያ፤ አሀዳዊ መንግስት ነበረች። ብሔራዊ ቋንቋ ነበራት፡፡ በእርሳቸው ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት አንድ መቶ ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በወዳጅነት መንፈስ የተሞላ አልነበረም፡፡ እስከ መንግስቱ ኃይለማርያም መጨረሻ ዘመን ድረስ ኢትዮጵያ በጠላት የተከከበች አገር እንደሆነች ነበር የሚታሰበው፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዳደር አስተሳሰብ፤ ከምኒልክ አስተዳደር አስተሳሰብ በተቃራኒ ነው የቆመው፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ ፊታውራሪነት አሁን ድረስ የሚመራው ኢህአዴግ፤ ኢትዮጵያን ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌዴራል መንግስት አስተዳደር አድርጓታል፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ እንደ አገር የምትቀጥለው ህዝቦቿ ሲፈቃቀዱ ብቻ መሆኑን አስረግጦ በሕገ መንግስቱ ተናግሯል፡፡ ኢህአዴግ የብሔሮችን መብት እስከመገንጠል አከብራለሁ ባይ ነው፡፡ ኢህአዴግ የስራ ቋንቋ እንጂ ብሔራዊ ቋንቋ መኖሩን አይቀበልም፡፡ የኢህአዴግ የውጭ ፖሊሲ፤ ከጎረቤት አገራት ጋር ተባብሮ በሰላም መኖር የሚቻል መሆኑን ያምናል፡፡ ከላይ ባጭሩ ለማየት እንደሞከርነው፤ ከምኒልክ ጀምሮ እስከ መንግስቱ ኃይለማርያም ድረስ የነበረው አንድ ወጥ አስተሳሰብ፣ በአንድ ጎራ የሚፈረጅ ሲሆን የኢህአዴግ አስተሳሰብም በሌላ መንገድ የተቃኘ አስተሳስብ ነው፡፡
ኢህአዴግ ንግስት ዘውዲቱን ሲወቅስ አንሰማም። ኃይለስላሴ ላይም አምርሮ ሲናገር አልሰማንም፡፡ ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ከገባ በኋላ በደርግ ላይ የሚለውን ብሎ ወጥቶለታል። ከማንም በላይ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የነበሩትን ንጉሠ ነገሥት የሚነዘንዛቸው፣ ከመቶ ዓመት በፊት በሚኒልክ የተጠነሰሰው አስተሳሰብ ኢህአዴግን ክፉኛ ስለሚገዳደር ነው፡፡ የእነዚህ ጽንፍ የቆሙ አስተሳሰቦች ፊታውራሪዎች፡- አፄ ምኒልክና አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ፍጥጫው ያለው በሁለቱ መካከል ነው፡፡ ብቃት ያላቸው መሪዎች ከሞቱም በኋላ ቢሆን መፋጠጣቸው የማይቀረው ለዚህ ነው፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወደ ሶስተኛው አስርት ዓመታት ቢቃረብም የሚኒልክ መንፈስ አሁንም በትውልዱ ውስጥ አለ፡፡ በትውልዱ ውስጥ እየገነነ የመጣው የሚኒልክ መንፈስ ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ምኒልክን በነካካ ቁጥር የምኒልክ መንፈስ ከመዳከም ይልቅ በተቃራኒው እየበረታ የሚሄድና በዋዛ እጁን የማይሰጥ ሀሳብ ነው፡፡ ነገሩን በዚህ መንገድ ካየነው፣ የአጼ ምኒልክና የአቶ መለስ ዜናዊ ፍጥጫ የት ላይ እንደሚያበቃለት አላውቅም፡፡
ምናልባት አዲስ ርእይና አዲስ አስተሳሰብ ይዞ የሚነሳ ልበ ሙሉና ብልህ መሪ፣ በአዲሱ ትውልድ ተፈጥሮ እነዚህን ስመ-ጥር ሁለት መሪዎች ያስረሳን ወይም ያስታርቅልን ይሆናል፡፡ ይህ ሊሆን ግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና አልነበረም ብሎ ለማመን የሚያስችል እውነታ የለም፡፡ በኢትዮጵያ፣ የባላባታዊ ስርአት፣ ሁሉንም ዘር ሳይለይ፣ የጎዳውን ያህል በብሄሮችም ላይ የነበረው፣ ጭቆና በቀላሉ የሚድበሰበስ አይደለም፡፡ በሌላ ወገን፣ የብሔርን ጭቆናና ያለፈን ታሪክ በማራገብ፣ አገር ለማፈራረስ መጠቀሚያ መሆን የለበትም’ ብሎ የሚሞግት ትውልድ ተፈጥሯል። በደልና ጭቆና እያሰቡ ባለፈ ነገር መነቋቆር፣ ለማንም አይበጅም’ ብሎ የሚያስብ ትውልድ ቁጥሩ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ “ታሪክ እንጀራ አይሆነንም፤ ያለፈን ዝባዝንኬ መስማት ሰልችቶናል” የሚል አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ በኢህአዴግ ጥላ ስር ያለውም ትውልድ ይህንኑ እያለ ስለሆነ ኢህአዴግ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ድክመትና ክፍተት ቆም ብሎ የሚያስብበት ዘመን አሁን ነው፡፡ ያለጥርጥር ጊዜው አሁን ነው፡፡
የተቃርኖው ዋና ምክንያት፤ “በኢትዮጵያ ቀዳሚው ነገር የቱ መሆን አለበት ወይም እንዴት ሁለቱን ሀሳቦች ማጣጣም ይቻላል?” በሚለው ጉዳይ ላይ የተመሰረተው ነው፡፡ በየጊዜው የሚነሳው ክርክር መነሻ ሀሳቡ፣ በአፄ ምኒልክ አሀዳዊ መንግስት አስተሳሰብና በአቶ መለስ ዜናዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ መሀል በሚነሳው የሀሳብ ግጭት እንደሆነ እርግጡን መናገር ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ምኒልክን አሁን ድረስ አጀንዳ  አድርጎ ያለ እረፍት ለመትገተግ መገደዱን እንረዳለን፡፡ ነገሩን በሰከነ መንፈስ ካየነውና ለጥፋት ካላዋልነው ከሁለቱም ተቃርኖዎች ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሀሳብ ማውጣት የሚያቅተን አይመስልኝም፡፡ ኢትዮጵያ በሰማኒያ ቦታ ቀርቶ በሶስት አራት ቦታ የጎሣ ፖለቲካ ተከፋፍላ የተለያየች አገር ብትሆን በየትኛውም ወገን ለቆመ ሕዝብም ሆነ  መንግስት የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ ይልቁንም በስጋት የምናያቸው ጎረቤት አገሮች የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያ፣ የበለጥ ደካማና ፍርስርሷ የወጣ አገር ለማድረግ የቤት ስራቸውን እራሳችን ሰራልናቸው ማለት ነው፡፡ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከመለያየት የሚገኝ ጥቅም የለም፡፡ ኤርትራን ተመልከቱ። ምን ተጠቀመች? የት ደረሰች? ዜጎቿ በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ስደተኞች ናቸው፡፡ የኢሳያስ አፈወርቂ የአስተዳደር ድክመት፣ ለኤርትራዊያን መሰደድ ዋናውና መሰረታዊ ችግር እንዳልሆነ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡
ዋናው ችግር በአገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት አለመኖሩ ነው፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት ወደ ከፋ ድህነት እየወረዱ ነው፡፡ የኤርትራ መንግስት የትውልዱን ጥያቄ የሚመልስ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር አልቻለም፡፡ ይህ ነገር እስኪለወጥ ስደቱ ይቀጥላል፡፡ የባሕር በሯ ምን ጠቀማት?
ለባዕዳን ጦር ሰፈር ከመሆን የዘለለ ምን ለማበት? አረብ አገራት፤ የተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ የኤርትራ ወጣቶች ምግብ ሳይቀር ወደ አገራቸው ይልካሉ፡፡ ነገር ግን ጠንካራና እንደ እኛ ያልተከፋፈለ ብሔራዊ አንድነት ስለአላቸው፣ በድህነት ምክንያት አገራቸው ላይ ፊታቸውን አላዞሩባትም። ኤርትራ ብዙ ብሔሮችን ያቀፈች ትንሽ አገር ናት፡፡ በብሄራቸው ልዩነት ግን ሲናቆሩ አላየንም። መሪያቸው ኤርትራዊነትን እንደ ሀገር ለመመስረት (Nation building) የተሳካለት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከእነርሱ ልንማር የሚገባን ይህንን ነው፡፡ የእኛ መንግስትና ኢትዮጵያዊያን የሆንን ሁሉ ዘራችንን መናቆሪያ ሳናደርግ ይልቅንም ውበታችን መሆኑን እናጉላው፡፡ ኢትዮጵያን ከፍ ብለን እንዘምርላት- ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄሮች አገር መሆኗን፡፡ የሚያዋጣው ይኼ ነው፡፡
ባለፉት ክፍለ ዘመናት ነገሥታት አስገብረው አገር መፍጠር የመላው ዓለም እውነታ ነውና ምኒልክን ማውገዝ የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ያለፉትን ታሪኮች ተምረንባቸው፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ተሳስበን መኖራችን፣ የጥንካሬአችን ምንጭ መሆኑን ልንዘነጋው የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከ53 አገር በላይ ሆና የምናያት የአሁኗን አፍሪካ፣ ከአገር አገር የሚለየው ድንበሯና ዘመናዊ የአስተዳደር ስርአቷ የተመሰረተው ቅኝ በገዟት ፈረንጆች ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ እንደ አገር ነው የቀጠሉት እንጂ የአፍሪካ ነገሥታት ያፈራረሱት ወይም የነካኩት አገር የለም፡፡ አንዳንዶቹ መነካካት ሲሞክሩ ግን እሳቱ መልሶ ራሳቸውን ሲበላ ነው የተመለከትነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የቅኝ ገዥዎችን ዱላ መክተው፣ ከአፍሪካ ንጉሦች መካከል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑት ምኒልክ ያደረጉት ተጋድሎ ሰብእናቸው በእኛ ቀርቶ በፈረንጅ አገር ጭምር የገዘፈ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካዎች የተነቃቁት በሚኒልክ አሸናፊነት ነው፡፡ ጥቁሮች ከነጮች የማያንሱ መሆናቸውን ለዓለም የሳዩት ምኒልክ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ወራሪዎችን  መመከቷ፣ የማኦን የትግል መንፈስ ያነቃቃ ነበር፡፡
የዳግማዊ ምኒልክን ማንነት ድራሻቸውን ማጥፋት ቢሳካ የዓድዋውን ድል ማንም ትቢያ ሊያለብሰው አይችልም። ዓድዋ በመላው ዓለም የሚገኙ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ናትና፣ ዐድዋን ያለ ምኒልክ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ዓድዋ ላይ ሲቋቋም የምኒልክ ስም የግድ ይነሳል፡፡ በዚህ ምክንያት የእርሳቸውን መንፈስ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ እውነታ፣ የአቶ መለስ ዜናዊም የብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሰፊ ቦታ የያዘ እጅግ ገንኖ የወጣ ትልቅ ሀሳብ ነው፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ከሆነ ወዲህ አንዳንድ ቦታ ከተራገቡ ግጭቶች በቀር ለአገር አደጋ ሆኖ የወጣ መጠነ ሰፊ ግጭት አላየንምና የአቶ መለስ የብሔር ፖለቲካ ፋይዳው ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ እሳቤ ነገሮችን ከተመለከትናቸው፣ የአፄ ምኒልክ መንፈስ አንድ መቶ ዓመት የገዛንን ያህል የአቶ መለስ ዜናዊ መንፈስም ገና ወደፊት የሚገዛን ይሆናል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ የሚወቀሱትን ያህል ተፅእኖአቸውም ገና ወደፊት የመሻገር ኃይል አለው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ የተወደሱትን ያህል በእርሳቸው ዘመን በተሰራ መጥፎ ነገር ከወቀሳ ላያመልጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምርጫ በመጣ ቁጥር የእነዚህ ሁለት ንገሥታት ሀሳብ፣ ትውልድ ተሻጋሪ ሀሳብ ሆኖ በሀሳብ ደረጃ መፋጨቱ አይቀሬ ነው - ሌላ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ካልመጣ በቀር፡፡
በአዲሱ ትውልድ ከምኒልክና ከመለስ ዜናዊ ልቆ በአዲስ አስተሳሰብ የሚነሳ መሪ ሲፈጠር ብቻ ነው፤ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብና የምኒልክ አስተሳሰብ ሊሸነፍ የሚችለው፡፡ ይህ እስኪሆን የሁለቱም ነገሥታቶቻችን ሀሳብ፣ ዥዋዥዌ እየተጫወተ፣ የምዕተ ዓመቱ የታሪክ ሂደት ሆኖ በዚሁ መቀጠሉ አይቀርም። በየስታዲዮሙ ድንጋይ መወራወርና በየድራፍቱ ቤቱ መናቆር ብስጭትንና ጊዜያዊ ድል አድራጊነትን ከማግኘት በቀር ቁርሾው መቀጠሉ አይቀርምና መናቆር ለኢትዮጵያ ልጆች አንዳች የሚፈይደው በጎ ጎን የለውም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊና ዳግማዊ ምኒልክ እኩል እንዲነሱ የሚያደርጋቸው አንድ አጀንዳ አለ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ በሰሎሞን ስርወ መንግስትነታቸው ምክንያት የባሕረ ነጋሽን ነገር የሚደራደሩባት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሆኖም የወቅቱ ሁኔታ አስገድዷቸው የመረብ ወንዝን መሻገር አልቻሉም ነበር፡፡ በእርሳቸው ዘመን ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብጽ ምድር ያሻገረበትን ‘ኤርትራን’፣ ለባሕረ ነጋሽ አዲስ ስም በመስጠት ጣሊያን ኤርትራን ከምኒልክ እጅ መቀማት ችላለች፡፡ የጣሊያን ቅኝ ገዥዎች በቀደዱት ቦይ፣ እንግሊዞች ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ቀብረው ሲሄዱ፣ ለዘመናት ተዋህደው የሚኖሩ ሕዝቦችን አለያይተውን ቀርተዋል። በመለስ ዜናዊ ዘመንም ኤርትራ በውሳኔ ሕዝብ ራሷን የቻለች አገር ሆናለች፡፡ ምኒልክ ጥለዋት የሄዱት ኢትዮጵያና አቶ መለስ ዜናዊ ጥለዋት የሄዱት ኢትዮጵያ፤ መልክአ ምድር ቢያንስም ቢያድገም ተመሳሳይ በመሆኑ፣ እነዚህ መሪዎች በዚህ ነጥብ ይመሳሰላሉ፡፡
ሁለቱም አገራቸውን ወደብ አልባ አገር ያደረጉ መሪዎች ናቸው ብሎ ዳር ቆሞ መውቀስ በጣም ቀላል ነው፡፡ ይሁንና አቶ መለስ ዜናዊ፤ ለወዲ አፈወርቂ ምቹ ሁኔታዎች ቢፈጥሩም ባይፈጥሩም ኢህአዴግ እንዳለፉ መንግሥታት፣ ተመሳሳይ አቋም ኖሮት፣ ከወዲ አፈወርቂ ሠራዊት ጋር ጦርነት ቢቀጥል ኖሮ የኤርትራ ጉዳይ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ አሁንም ድረስ ጦርነት ላይ እንሆን ነበር፡፡ የኢህአዴግ አባላትም ሆኑ ደጋፊዎቹ፣ “ወያኔ ገና መቶ ዓመት ይገዛል” እያሉ በየስታዲየሙ ሳይቀር ቢፎክሩም ባይፎክሩም ኢህአዴግ በምርጫ ቢሸነፍ እንኳን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተጽእኖ በቀላሉ ከፊታችን ዘወር የሚል ጉዳይ አይደለም። ከኢህአዴግ በተቃራኒ የሚቆሙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው ብለን ልንገምት ወይም መረጃው ሊኖረን ይችላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ያሰቡት ተሳክቶላቸው፣ ሥልጣን ለመያዝ የሚያበቃቸው ሁኔታ ተፈጥሮ፣ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ይገባሉ”
ብለን ሕልም የሆነ ሀሳብ ልናስብ እንችላለን፡፡ ኢህአዴግ ክንዱን ሳይንተራስ በምርጫም ቢሆን ሥልጣን እንደማይለቅ የታወቀ ነው፡፡ እንዲያው ኢህአዴግ ድንገት ማጣፊያው አጥሮት ሕልሙ በዚያው ሕልም ሆኖ ባይቀር፣ ለተቃዋሚዎች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስምናን አሸንፎ የሚወጣ ትልቅ ሀሳብ ማግኘት፣ ትልቁ የቤት ስራ ይሆንባቸዋል፡፡
በኢህአዴግ ዘመን አገሪቱ ጭንቅ በጭንቅ ስትሆን፣ አንዲት ቀጭን መልከ መልካም ሴት፤ ሀሳቧም እንደ መልኳ ያማረ፣ የሕግ ባለሙያ፣ ሽማግሌ በሚመክርበት ሸንጎ ተገኝታ፣ ጫፍና ጫፍ አቋም የያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚጋጠሙበት መድረክ፤ ውይይቱን ስትመራ ተመልክቼአለሁ፡፡ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮችም ላይ በሚካሄድ ስብሰባ ተገኝታ የምትሰጠውን መሬት ጠብ የማይል ሀሳብ ጆሮዬን በሰፊው ከፍቼ ነበር የማዳምጣት፡፡ ስሜታዊነትና ግብታዊነት የአዳራሹን ጣራ ነክቶ አገሬው፣ በጎራ ተፈራርጆ ሲጯጯህ፣ እርሷ ተሳስታ ስሜታዊ ሆና ስትናገር ሰምቼአት አላውቅም፡፡ የሰከነ ባለሙያ ማለት እንደ እርሷ ነው፡፡
ኢህአዴግ፤ “እኔ ያልኩት አንድና አንድ ብቻ ካልሆነ” ብሎ “አካኪ ዘራፍ” በሚልበት መድረክ፤ በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ የሀሳብ አመለካከትና የፖለቲካ መርሆ ሳይገደብ፣ ሕዝቡ ይሰማ ዘንድ የወደደውንም እንዲመርጥ፣ በተረጋጋ መንፈስ ስትናገር እሰማታለሁ፡፡ የተለያዩ የዲሞክራሲ አይነት አስተሳሰቦች መንግስት ገደብ ሳያበጅላቸው፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለሕዝቡ እንዲናገሩና ሕዝቡም የሚበጀውን እንዲመርጥ ትመክራለች፡፡ ግራ፤ ግራ ዘመም፤ ቀኝና ቀኝ ዘመም ወይም በሌላ ጠርዝ ያለ ወይም መሀል ላይ የሰፈረ ሀሳብ ሣይቀር፣ ቦታ ተሰጥቶት፣ ሕዝቡ ቢሰማውና ቢመክርበት መልካም እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እንደ እርሷ ያሉ ሴቶች ይብዙልን፡፡  
የአጼ ምኒልክ የስኬት ምስጢር እንደሆነችው፤ የብልሆች ብልህ እንደነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ጣይቱ ማለቴ ነው፡፡ ሴቶች ዓለምን የመለወጥ ኃይል አላቸው፡፡ ነገርግን ሴቶች ያላቸውን እምቅ ኃይል ካላወቁት በቅስቀሳ የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ ለማንኛውም መጽሐፉን ለማንበብ ምክንያት የሆነኝን ጥያቄ መልስ ፍለጋ፣ ከትንሿ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተነስቼ፣ አራት ኪሎ ቤተመንግስት የነበሩት መሪዎች ድረስ ይዞኝ ሄዷል። ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደተናገርኩት፤ በዚያ ስብሰባ ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተሰጠውን የተወለጋገደ መልስ ሳስታውሰው፣ መልስ ለመስጠት የተውተረተሩት የኢህአዴግ አባላትም ሆኑ የመድረኩ መሪ የነበረው ካድሬ ጭምር የድርጅታቸውን ፍልስፍና አያውቁትም ነበር ማለት ነው፡፡ “አባሉ የድርጅቱን ተልዕኮ መፈጸም እስከቻለ ድረስ ዘበኛም ቢሆን ብንሾም ማንም ከልካይ የለብንም” ብሎ የብሽሽቅ መልስ መስጠት የሚያዋጣበት ዘመን ላይ አይደለንምና ኢህአዴግ ወገቡን ታጥቆ አባላቱን በዕውቀት ቢገነባ የሚጎዳው አይመስለኝም። ምንም ሆነ ምን፣ የአሁኑ ትውልድ፣ የነገሩትን እንደ ሶፍትዌር ተጭኖ፣ የሚሸወድ ትውልድ አይደለምና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም፡፡

Read 2857 times