Sunday, 06 August 2017 00:00

የመድብለ - ፓርቲ ስርአት - ጋናና እኛ

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

      የካቲት 30 ቀን 1949 ዓ.ም መላ ጋናውያን ትልቅ ቦታ የሚሰጡት፣ የታሪካቸውን አንድ ወሳኝ ምዕራፍ በደማቅ ቀለም የፃፉበት ቀን ነው፡፡ ጋናውያን ከዛሬ 60 አመት በፊት የእንግሊዝን የቅኝ አገዛዝ ቀንበር በመስበር ነፃነታቸውን ማስመለስ የቻሉት በዚህ ቀን ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ላለፉት 60 ዓመታት ዘመን ተቀይሮ ቀኑ በመጣ ቁጥር በአደባባይ እየተሰበሰቡ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን ለማስመለስ ሲታገሉ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖቻቸውን ውለታ በማስታወስ እለቱን ይዘክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ጋናውያን ከየካቲት 30 ቀን 1949 ዓ.ም ይልቅ ሰኔ 20 ቀን 1984 ዓ.ም በጋና የነፃነት ታሪክ ውስጥ እጅግ የላቀ ቦታ አለው ይላሉ። ሰኔ 20 ቀን 1984 ዓ.ም ጋና በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውን የመድብል ፓርቲ ምርጫ ያካሄደችበት ቀን ነው፡፡
ለዚህ ቀን የተለየ ትኩረት የሚሰጡት ጋናውያን፤ ምነውሳ ሲባሉ የሚሰጡት መልስ ቀላልና ግልጽ ነው፡፡ “በየካቲት 30 ቀን 1949 ዓ.ም ያገኘነው የባንዲራ ነፃነት ብቻ ነው፡፡ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ በኋላ የወደቅነው በአንድ ፓርቲና በወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ላይ ነው፡፡ ለነፃነታችን፣ ለእኩልነትና፣ ለመብታችን መከበር ቁብ የማይሰጠውን ይህን ክፉ አገዛዝ ሳንወድ በግድ ተሸክመን ለ35 ዓመታት ኖረናል፡፡ ከዚህ ክፉ አገዛዝ ተላቀን ወደ መድብለ ፓርቲ ስርአት የተሸጋገርነውና ስርአት መሰረቱ የተጣለው ሰኔ 20 ቀን 1984 ዓ.ም ነው በማለት ይመልሳሉ፡፡
ለአለማችን ጥንታውያን ከሚባሉት ጥቂት ሀገራት አንዱ ተደርጎ በሚቆጠረው የሀገራችን የሉአላዊ መንግስትነት የታሪክ መዝገብ ውስጥ ጉልህ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ክንውን ከተካሄደባቸው እጅግ በርካታ ታሪካዊ ቀኖች አንዱ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ነው፡፡
በዘር ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ የአስተዳደር ስርአትና በዋናነት ዘርን መሰረት ያደረገ የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምህዳር የተዘረጋው ከዚህ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ለዜጎች ነፃነትና እኩልነት እውቅና የሚሰጥ፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያው መብቶቻቸው መከበርም ዋስትናና ጥበቃ የሚያጎናጽፍ፣ ህገመንግስት ፀድቆ፣ በስራ ላይ እንዲውል የተደረገው ግንቦት 20ን ተከትሎ ነው፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፣ ቀኑ በብሄራዊ በአልነት ተመዝግቦ እንዲከበር በወሰነው መሰረት፣ ላለፉ 26 ዓመታት ግንቦት 20 ቀን በመጣ ቁጥር ደግሱ የተባሉትን ድግስ እየጣሉ፣ አድርጉ የተባሉን እያደረጉና ‹‹ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!›› የሚል መፈክር እያሰሙ አክብረውታል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ለኢትዮጰያውያንም ሆነ ለጋናውያን ትልቁ ጉዳይ ግንቦት 20ንና ሰኔ 20 ቀንን ዳስ ጥለው፣ ቅጠል ጎዝጉዘው ማክበራቸው አይደለም። ይልቁንስ በየአመቱ የሚዘክሯቸው ቀኖች በፖለቲካ ስርአታቸው ውስጥ ለህዝቡ የሚበጅ ምን ሰናይ ትሩፋት አመጡላቸው? በተለይም የዛሬ 25 አመት በሰኔ 20 እና ግንቦት 20 የጀመሩት የመድብል ፓርቲ ስርአት ዛሬ የት ላይ ደርሷል የሚለው ነው፡፡
ጋናውያን የመድብለ ፓርቲ ስርአታቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩት ስልጣን የጨበጠ ፓርቲ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ጉልበት የተሰማው ቀን እንደፈለገ ከፍ ዝቅ፤ ሰፋ ጠበብ የማያደርገውና ሁሉንም የፖለቲካ ቡድን እኩል ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ በመገንባት ነው፡፡
የእስልምና የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ 75 ብሄርና ብሄረሰቦች የሚኖሩባት ጋና፤ ዜጎቿ በፖለቲካ የተነሳ በዘርና በሀይማኖት ተከፋፍለው ብሄራዊ አንድነቷ እንዳይላላ፣ እርስ በርሳቸውም እንዳይጫረሱ ሁነኛ የህግ መላ መፈለግ ቀጣዩ የቤት ስራዋ ነበር፡፡
እናም በ2000 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ቁጥር 574ን አወጀች፡፡ የዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 ቁጥር 1 ሀ፤ በዘር፣ በጾታ፣ በሀይማኖት፣ በአካባቢና በሙያ ዘርፍ ተደራጅቶ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በዚህ የተነሳ በታህሳስ ወር 1984 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ የመድብለ ፓርቲ ብሄራዊ የምርጫ ውድድር ለመካፈል፣ በአወዳዳሪው የጋና ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የቀረቡት 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሂደት በጋና የፖለቲካ መድረክ ላይ ጎልተው የወጡትና የጋናን የምርጫ ፖለቲካ መቆጣጠር የቻሉት ግን የሊበራል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ነው የሚባለው ኒው ፓትሪዮቲክ ፓርቲ (NPP) እና የግራ መሀል (center - left) ርዕዮተ ዓለም የሚያራምደው የብሄራዊ ዲሞክራቲክ ኮንግረስ (NDC) ናቸው፡፡ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በጋና የተካሄዱትን ብሄራዊ ምርጫዎች በማሸነፍ የስልጣን ወንበሩን የተፈራረቁበት እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ለዚህ የበቁት የስልጣን መንበሩን ሲቆጣጠሩ ተፎካካሪያቸውን በማዋከብ እያዳከሙ፤ ወይም መሪዎቻቸውን በሰበብ አስባቡ እስር ቤት በማጎር እያፈረሱ ከቶውንም አይደለም፡፡ ይህን ለማድረግ ቢፈልጉም እንኳ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው የጋና የፍትህ ስርአትና የዲሞክራሲ ተቋማት እድልም ቀዳዳም የሚሰጡ አይደሉም፡፡
እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በጋና የመድብለ ፓርቲ ስርአት ውስጥ ይህን የመሰለ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉት የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ከፍተኛ የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ችሎታ ያለው ንቁ አመራር ባለቤቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ጋናውያን ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ አባል በሆኑበት ወይም በሚደግፉት የፖለቲካ ፓርቲ የተነሳ አንዳች አይነት ችግር ይገጥመኛል ብለው መጨነቅ አቁመዋል፡፡ የጋና የፖለቲካ ፓርቲዎችም የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ ኪራይ ጉዳይ ጨርሶ የሚጨነቁበትና እንደ ቁምነገር የሚያዩት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ መላ ጋናውያን በሀገራቸው የፖለቲካ መድረክ በነፃነትና በሙሉ ፍላጎት ተካፋይ እንዲሆኑ ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
በጋና የፖለቲካ መድረክ ስልጣን የጨበጠ ፓርቲ፤ የፓርቲውንና የመንግስቱን ስራና ኃላፊነት ማደበላለቅና ማምታታት፣ በመንግስት ሀብትና ገንዘብ የፓርቲውን ስራ ማከናወን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን እንዳይጠቀሙ መከልከል እንዲሁም ሌሎች ህጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን እንዳያካሂዱ መከልከል ወይም ማደናቀፍ አይችልም፡፡
ከሁሉ በላይ በምርጫ ወቅት ኮረጆ መገልበጥ፣ የትኛውም በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ደፍሮ የሚፈጽመው ነገር አይደለም፡፡ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማቱ፣ ይህ እንዲሆን ክፍተት የሚፈጥሩ አይደሉም። ስለዚህ የፈለገው አይነት ገዢ ፓርቲ፣ በምርጫ 99% ድምጽ አግኝቶ ማሸነፍ መቸም ቢሆን አይችልም። ለምሳሌ በ1984 በተካሄደው ምርጫ የNDC እጩ ጀሪ ሮውንግስ ተቀባይነት ጣራ ነክቶ ለተፎካካሪያቸው አንድም ሰው ድምጽ አይሰጣቸውም ተብሎ በሰፊው በተገመተበት ወቅት፣ ጀሪ ሮውንግስ ማግኘት የቻሉት 55% ድምፅ ብቻ ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ጋናውያን በምርጫ ጊዜ የሚሰጡት ድምጽ ትልቅ ዋጋ እንዳለውና በማንም እንደማይሰረቅ በሙሉ ልብ እንዲተማመኑ አስችሏቸዋል፡፡
ከሁሉም በእጅጉ የላቀው የመድብለ ፓርቲ ስርአታቸው ትሩፋት ጋናውያን ያስፈለጉትን መንግስት አመፅ ማስነሳት ሳያስፈልጋቸው በድምፃቸው ብቻ ማስወገድና የሚፈልጉትን ወደ ስልጣን ማምጣት መቻላቸው ነው፡፡ አምና በታህሳስ ወር የተካሄደውና በስልጣን ላይ የነበረው NDC ፓርቲና ፕሬዚዳንቱ ጆን ማሀማ ከስልጣን የተወገዱበት ምርጫ፣ ለዚህ ማለፊያ ምሳሌ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ጆን ማሀማና ፓርቲያቸው NDC ማሽቆልቆል የጀመረውን የጋናን የኢኮኖሚ እድገትና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የወጣት ስራ አጥነት በአፋጣኝ መላ እንዲፈለጉለት ህዝቡ ላደረገው ጉትጎታ የሰጡት መልስ ቸልታ ነበር፡፡
በታህሳስ 2008 ዓ.ም ህዝቡን በድጋሚ በፕሬዚዳንትነት እንዲመርጣቸው አይናቸውን በጨው አጥበው ሲጠይቁት ያገኙት መልስም እንዲሁ ቸልታ ነበር፡፡፡ የህዝቡ ቸልታ ውጤትም፣ በተቀናቃኛቸው የአዲስ አርበኞች ፓርቲ እጩ ናና አኩርፎ አዶ፣ በአስተማማኝ የድምጽ ልዩነት ተሸንፎ ከፕሬዚዳንታዊው የጋና ቤተመንግስት መባረር ሆነ፡፡
ለመሆኑ የእኛ የመድብል ፓርቲ ስርአትስ ከየት ተጀምሮ ዛሬ ከምን ላይ ደረሰ? የሳምንት ሰው ይበለን፡፡

Read 3575 times