Saturday, 05 August 2017 11:39

ካሴቱ

Written by  በሚኪያስ ጥ.
Rate this item
(0 votes)

 …ጸጉሩን ያፍተለትላል፤በቀኝ እጁ የያዘዉን የጎርኪይን ‹‹እናት›› መጽሃፍ ወደ አልጋዉ ወረወረዉ። በርካታ ቀናትን፣ ከዚህ ትልቅ መጽሃፍ’ጋ አሳልፏል፤ ታሪኩን ለመረዳት ሞክሯል። አልሆነለትም እንጂ እንደ ‹‹ዳሰሳ›› ያለ፣ መጠነኛ ጽሁፍ ለመጻፍ፣ ሲንቆራጠጠጥ  ቆይቷል፡፡ በዚህም፣በዚያም ቢል አልተሳካለትም፡፡
‹‹ቀሽም ጸሃፊ!››
በጡጫ ግንባሩን መታ፡፡ ህመሙ አልዘለቀዉም መሰል- ደጋግሞ ግንባሩን ደቃ፡፡
‹‹ቀሽም ‹ጋዜጠኛ› ተብዬ!››
ትንሽ የጎደለለትን ጠጅ፣ ፊት ለፊት ከተዘረጋዉ ጠረጴዛ ላይ አንስቶ፣ አንደቀደቀና እነበረበት ቦታ መልሶ፣ አስቀመጠዉ፡፡ ጠጁ የልቡን ሰርጣ-ሰርጦች አልፎ፣ ሆድቃዉን ዳብሶ፣ ወደ ታች ቁልቁል ሲወርድ፣ ታወቀዉ፤ በዉጥረት የተጨማተረ ገጹ ሲፍታታ ተሰማዉ፡፡
የበፊት ትዝታዎቹን ለማስታወስ ሞከረ፡፡ የፍቅር ጊዜያቱ ምን ያህል በሸፍጥ እንደተሞሉ፣ ከፍቅሩ በፊት የነበረዉ-የልጅነት ህይወቱ ምን ያህል ቀፋፊ እንደነበር፣ በተለይ ደግሞ የጋዜጠኝነት (እርሱ- በአብዛኛዉ -ራሱን ሲያስተዋዉቅ፣ ‹‹ጸሃፊ ነኝ!›› እያለ ነዉ፡፡) ዘመኑ ምን ያህል አስጨናቂና አዋካቢ እንደነበር፤ በትዝታ ፈረስ ጋልቦ፣ ቀናቱን አስታወሰ፡፡
‹‹ከንቱ ዘመናት! አይረቤ ጊዜያት!››
ከተቀመጠበት ተነሳና፣ ጠባቧን የቤቱን ሳሎን ይዞራት ገባ፡፡
አልጋዉ ሰፊ ቦታ በመያዙ ምክንያት፣ቤቲቱ ጠባብ ትመስላለች፡፡ የያዘችዉ እቃ ግን ለጉድ ነዉ፡፡ ቁም ሳጥኑን፣ ማቀዝቀዣዉን…ምንትሱን-ምናምንትሱን አንቀርቅባ አዝላለች፡፡
አንድ አይኑን ጨፍኖ፣ በገላጣ አይኑ ቤቱን ይማትራል፡፡
በድንገት፣ቁም ሳጥኑ’ጋ ሄደና ታች ያለዉን መሳቢያ ሳበ፡፡ ወረቀቶችን፣ የመጽሃፍ ነድዎችን መዘክዘክ ጀመረ፡፡ ወዲያ-ወዲህ አመሰቃቅሎ፣ቤቱን በመዝረክረክ ደረመን አቆፋፈደዉ፡፡ እጁ ላይ አንዲት ካሴት ስትገባ፣ረጋ አለ፡፡ ደመነፍሱ፣‹‹ፈልግ!›› ብላ ያዘዘችዉን አስፈላጊና ወሳኝ እቃ፣ይህቺዉ ካሴት ነበረች፡፡ ከካሴቲቱ በታች የተጻፈዉን ደቃቅ ጽሁፍ ለማንበብ ዓይኑን እንደገና አጨናቆረ፡፡
‹‹ከባለቅኔዉ ጋር የተደረገ ቆይታ-ክፍል ፩››
ደነገጠ፡፡
‹‹ከባለቅኔዉ ጋር መቼ ነዉ ያወጋነዉ? እንዴ!... ሰዉዬዉ የሞቱት’ኮ የዛሬ 11 ዓመት ነዉ፡፡ እና፣ በምን ተዓምር አግኝቼ ላወራቸዉ የቻልኩት? እንዴት?!››
በጥያቄ ክበብ ዉስጥ ተንዘባነነ፤ ካሴቱን ቴፕ ሬከርደሩ ዉስጥ ወሸቀና፣ የማስጀመሪያ ቁልፉን ተጫነ፡፡
‹‹መጀመሪያ በቀጠሯችን ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል›› ጎርናናዉ የራሱ ድምጽ፡፡
‹‹እኔም- እንዳ’ንተ- ሎጋ፣ ሸንቃጣ ጋዜጠኛ ስለሚጠይቀኝ፣ ደስተኛ ነኝ!›› ለስላሴዉ የባለቅኔዉ ድምጽ፡፡
‹‹መጀመሪያ ስለተወለዱበት ቦታ… ቢነግሩኝ?››
‹‹በመጀመሪያ፣ እኔ የተወለድኩበት ቦታ ለአንባቢዉም ሆነ ለሰሚዉ አይረባም፤ የተወለድኩበት ዓመተ-ምህረትም አይረባም። ስለዚህ ስለ ጠቃሚዉና ስለሚረባዉ ጉዳይ ላዉራ፤እናዉራ፡፡ አይመስልህም - ሎጋዉ?››
ካሴቱ ላይ የራሱ ድምጽ ሲጠፋበት ተሸበረ፤ ‹‹ምን ሆኜ ነበር? ምን እያደረግሁ ነበር?›› ሲል ራሱን ጠየቀ፡፡ ምላሽ ከአንጎሉ ጓዳ ስላልመጣለት ከማሰብ ተቆጠበ፡፡
‹‹…አንዳንድዬ፣ ይህ ዘመን ‹የእስራት ዘመን› ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሰዉ በአስተሳሰብ ዝቅጠት እመቀ-መቃት ወርዷል፡፡ እንዳያስብ ‹ቴክኖሎጂ› የሚሉት፣ አንድ መቅሰፍት መጥቷል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ቢጠቅም፣ምንኛ መልካም በነበረ! ግን እንኳን ሊጠቅምንና ሊያጠፋን የሰይጣን ማጭዱን ስሎ መጥቶብናል፡፡
በእጀ-ሙቅና በእግረ-ሙቅ፣ እግረ-ልቦናችንንና እጀ-ልቦናችንን ቴክኖሎጂ ተብትቦብን፣ አዉተብትቦብን፣ መና አድርጎናል፡፡
እኔም፣ አንተም፣ ሁላችንም እስራቱን መስበር አለብን፤ በቴክኖሎጂ ዶማ ጭንቅላታችንን እየፈለጡ ለመግዛት የመጡትን ካሮት - መሳይና ንጫጭባዎችን ‹ወግዱልን› ማለት ያሻል፡፡ አለበለዚያ ተያይዘን ወደማንወጣበት ጉድጓድ እንገባለን!!››
ዝምታዉ ነገሰ-ቴፕ ሬከርደሩ ታምቡር ዉስጥ። ጸሃፊዉም በዝምታ ተዉጧል፤ ከቴፑ የሚለየዉ ዝምታዉ ላይ ትዝታ ተጨምሮበታል፡፡
‹‹ሁሌ ‹ትቀኛለህ፤ ትገጥማለህ!› ይሉኛል-ብዙ ሰዎች፡፡ እኔ ግን-‹መቀኘቱስ› ይሁንልኝና-‹ትገጥማለህ› የሚሉኝ ነገር፣ምኑም አይገባኝም። ምንድነዉ የምገጥመዉ? ቃልና ቃልን-እርስ በርስ ማፋልመዉ ምን ፖለቲካዊ ትርፍ ላገኝ ነዉ? እዉነቱን ልንገርህ! ‹ትገጥማለህ› ከሚሉኝ፣ ‹ቅኔ ትቀኛለህ› ቢሉኝ ደስ ይለኛል፤ ኑሮ-ራሷ-ቅኔ ናትና። ከኑሮ እየቀዳሁ ወደ ወረቀት እገለብጣለሁ፤ በቀለም እከትባለሁ፡፡ የኔ ስራ ይሄዉ ነዉ››
ዝምታዉ አሁንም ገባ፡፡ ጸሃፊዉ እንደሆነ ከትዝታዉም፣ ከዝምታዉም መንኖ ሄዷል፤ አሁን የለም-በመንፈስ፡፡
‹‹ይህቺ-ፊትለፊቴ ያለችዉ የሻይ ብርጭቆ፣ ሳያት ምን ትመስለኛለች? ...የሰዉ ልጅ የምኞት ድንበር! ሁሌም ቢሆን፣ በብርጭቆ ዉስጥ የምንጨምረዉ ዉሃም ይሁን ሻይ በልኩ ነዉ የሚሰፈረዉ፡፡ ከዛ በላይ ከሆነ ግን ይደፋል ፤ያገኘዉን ጨርቅ ሁሉ ያረጥባል፡፡ ምኞት ከገደቡ ሲያልፍ፣ በዙሪያችን ካሉት ሰዎች ጋር ያቃቅረናል፤ በነገር እርጥበት ያጣላናል፡፡ ምኞታችንን ስንገራዉ፣ የሰዉነታችን ሰዉነት ህልዉ ይሆናል››
የአፍታ ዝምታ!
‹‹ግጥሜን ታዉቀዋለህ?›› ጠየቁ-ጸሃፊዉን፡፡
‹‹የትኛዉን፣ ጋሼ?›› ጸሃፊዉ አንደበቱ ተፈትቶለት ተናገረ፡፡
‹‹ይኸኛዉን...!››
አሁንም ዝምታ አረበበ፡፡
‹‹እስቲ አንብበዉ!›› አዘዙት ጸሃፊዉን፡፡
‹‹የማይነጋ ህልም ሳልም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የማይድን በሽታ ሳክም
የሰዉ ህይወት ስከረክም
እኔ ለእኔ ኖሬ አላዉቅም፡፡›› እያንዳንዱን ስንኝ አንብቦ ጨረሰ፡፡
‹‹አየህ! የኔ ህይወት ያለፈዉ በዚህ መንገድ ነበር፤ በየቦታዉ የበቀለዉን ሳይ ሃሳብ ሳርም፣ ስኮተኩት፣ ስከረክም ብዙ ዘመን አስቆጥሪያለሁ፡፡ እና…እንዲህ መጨረሻዬ አግጥጦ ሲመጣ፣ አለመቀበል አልችልም!››
‹‹ጋሼ!..››
አቋረጡት፡፡
‹‹…የሚበቃኝን ያህል ሰርቼያለሁ፡፡ ፍልስፍናዬን በየመጽሃፍቱ፣ በየመጽሄቱ እንደ ዛር ቆሎ በትኛለሁ። የሚቀረኝ ለራሴ ‹ደስታ› ስል እየጻፍኩ መኖር ነዉ፡፡ ሌላ ምርጫ የለኝም፡፡››
ካሴቱ ቆመ፤ ጸሃፊዉ ከሃሳቡ ነቃ፡፡ ለካስ የተቀዳዉን ድምጽ፣ ቴፕ ሬከርደሩ አጫዉቶ ጨርሷል፡፡ ወደ ሌላኛዉ አቅጣጫ አዙሮ አስገባዉ፤ የማጫወቻ ቁልፉን ተጫነ፡፡
ድምጽ የለም፡፡
‹‹ይህንን ብቻ ነበር ያወራነዉ?!›› በቁጭት ከንፈሩን ነከሰ፡፡
ሁለተኛዉን ክፍል ካሴት ለማግኘት ብዙ እቃዎችን ፈላለሰ፡፡ ግን የለም፡፡
‹‹የት ገባ?››
አሁንም አተራመሰ፡፡
ተፈላጊዉ ካሴት የለም፡፡
‹‹ፈልግ›› ያለችዉን ደመነፍስ እየተራገመ፣ ካሴቱን ፍለጋ ከቤቱ ወጣ…

Read 1335 times