Sunday, 06 August 2017 00:00

“ደህና ሁኑ ልጆች…!” የአባባ ተስፋዬ ስንብት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በህዳር ወር 1957 ዓ.ም ላይ ነበር እስከዛሬም ድረስ መለያቸው የሆነውን “ጤና ይስጥልኝ ልጆች… የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች…” የሚለውን ሰላምታቸውን አስቀድመው፣ በዘመኑ ብርቅዬ በነበረው ባለጥቁርና ነጭ ቀለሙ ቴሌቪዥን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያሉት። እንዲህ እንደ ዛሬው ቴሌቪዥን በየሰው ቤት ሣይገባ የዘመኑ ልጆች የአበባ ተስፋዬን ተረትና ቀልዶች ለመስማት ቴሌቪዥን ላላቸው ጎረቤቶቻቸው የጉልበት ዋጋ ይከፍሉ ነበር፡፡ ግቢ ማፅዳት…አትክልት መኮትኮት…ቆሻሻ መድፋት.. እና የመሳሰሉት ሥራዎች የወቅቱ ልጆች ለአባባ ተስፋዬ ተረትና ጨዋታ የሚከፍሏቸው ዋጋዎች ነበሩ፡፡
ሰኔ 20 ቀን 1915 ዓ.ም በባሌ ክፍለ አገር ከዱ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተወለዱት አባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሳህሉ)፤ የልጅነት ህይወታቸው ያለፈው በከፍተኛ ችግርና እንግልት ነበር፡፡ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስለነበር ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአንድ መምህር ቤት ነበር። ግፈኛው የጣሊያን ወራሪ እኚህን አሣዳጊያቸውንም በስቅላት ገድሎባቸዋል፡፡ ይህንን መከራና ሐዘን መቋቋም ያቃታቸው አባባ ተስፋዬ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ታመሙና ሚኒሊክ ሆስፒታል ገቡ። በሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን ሕክምና አጠናቀው ሲጨርሱም መሄጃና መጠጊያ ስለአልነበራቸው በወቅቱ ሆስፒታሉን የሚያስተዳድረው ጣሊያናዊ በሆስፒታሉ ውስጥ በአቅማቸው እንዲያገለግሉ ፈቀደላቸውና ሥራ ጀመሩ። መርፌ ከመቀቀል፣እስከ ቁስል ማሸግና የፈንጣጣ ክትባትን መከተብ እንዲሁም የአበላዘር በሽታዎችን እስከ ማከም  ድረስ ይሰሩ ነበር፡፡
ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት 11 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቆርጦላቸው ሥራ ጀመሩ፡፡ ሴት ተዋንያን በሌሉበት ዘመን ፀጉራቸው ላይ ሻሽ በማሰርና ፂማቸውን ሙልጭ አድርገው በመላጨት፣ እንደ ሴት ሆነው ለአራት ዓመታት ተውነዋል፡፡ የመጀመሪያ የመድረክ ቲያትራቸውም “የአርበኛው ሚስት” የሚል ሲሆን በዚህ ቲያትር ላይ የሴት ገፀባህርይን ወክለው ነበር የተወኑት፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በሙያቸው አገራቸውንና ወገኖቻቸውን ሲያገለግሉ የኖሩት አባባ ተስፋዬ፤ በመድረክ ላይ ከተጫወቷቸው ቲያትሮች መካከል አፋጀሺኝ፣ የደም ድምፅ፣ ጎንደሬው ገ/ማርያም መቀነቷን ትፍታ፣ አርበኞችና ኢትዮጵያ የተባሉት ይገኙበታል፡፡
በ1944 ዓ.ም በጀነራል መንግስቱ ንዋይ ተመርጠው፣ ወደ ኮሪያ ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ጋር አብረው ዘመቱ፡፡ በዚህም የሃምሣ አለቃ ማዕረግ ተሰጥቶአቸዋል፡፡ በኮሪያ ቆይታቸውም ከእውቁ ኮሚዲያን ቻርሊ ቻፕሊንና ከፊልም ተዋናይ ማርል ቦሮ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሞአቸዋል፡፡
አበባ ተስፋዬ፣ የልጆች ፕሮግራምን በቴሌቪዥን ማቅረብ በጀመሩበት ወቅት ደመወዛቸው በፕሮግራም 175 ብር ነበር፡፡ በወቅቱ ሥራውን የሚቆጣጠረው አንድ እንግሊዛዊ ስለነበር  ክፍያቸው ጥሩ ነበር - “እንደ ፈረንጅ ነበር የሚከፈለኝ” ይሉ ነበር - በወቅቱ ስለነበረው ደመወዛቸው ሲናገሩ፡፡ እንግሊዛዊው ሥራውን አስረክቦ ሲሄድ ደመወዛቸው ቁልቁል ወርዶ፣ 70 ብር ሲደረግ ቅሬታ አላቀረቡም፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት ሥራቸውን ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ ደርግ ስልጣን ያዘ፡፡ ያኔ ደግሞ የአባባ ተስፋዬ ደመወዝ ወደ አምሳ ብር፣ ቀጥሎም ወደ 25 ብር እንዲያሽቆለቁል ተደረገ፡፡ ሁኔታው እጅግ የሚያበሳጭ ቢሆንም አባባ ተስፋዬ ስራቸውን ያለምንም ቅሬታ ቀጠሉ፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸውና እያበረከቱት ያሉት አስተዋፅኦን ከግምት ውስጥ ያስገባው የወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያው አስተዳደር፤ ለአባባ ተስፋዬ 750 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ይገባዎታል ብሎ ቆረጠላቸው፡፡
ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ አገራቸውንና ወገኖቻቸውን በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩት የትውልድ ድልድዩ አባባ ተስፋዬ፤ የብዙ ሙያዎች ባለቤት ነበሩ። ተዋናይ፣ ደራሲ፣ ድምፃዊ፣ ሐኪም፣ የሆቴል ቤት አስተናጋጅ፣ የምትሃት ትርኢት አቅራቢ፣ ኮሜዲያን፣ መድረክ መሪ፣ ወታደር፣ ገበሬ እና የሞራል መምህር ሆነው የሚወዱትን ህዝብና አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ እኚህን የበርካታ ሙያዎች ባለቤትና የሞራል መምህር፣ አገር በአንድ ድምፅ “አባባ” የሚል ማዕረግ ደርቦ፣ አክብሮአቸው ለዓመታት ኖረዋል፡፡ ከ42 ዓመታት በላይ የህፃናት መካሪ፣ አስተማሪና አጫዋች በመሆን ያገለገሉትን እኚህን ባለሙያ፤የማታ ማታ፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሁለት መስመር ደብዳቤ፣የሥራ ውላቸው መቋረጡን ነግሮ ነው ያሰናበታቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንዲት የ3 ዓመት ህፃን ባወራችው ቀልድ ላይ የብሔረሰቦችን ክብር የሚነካ ነገር ተናግራለች የሚል ነበር፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ሆነው የስንብት ደብዳቤው እስከተሰጣቸው መስከረም 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናትን በስነ ምግባር ኮትኩተው አሳድገዋል፡፡
እኚህን ታላቅ የሞራል መምህርና የአገር ባለውለታ የቴሌቪዥን ጣቢያው በዚህ መልኩ ያሰናብታቸው እንጂ ለአገራቸውና ለወገኖቻቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚዘክርና ክብራቸውን የሚገልፅ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በተለያዩ ጊዜያት በአክባሪዎቻቸውና በመንፈስ ልጆቻቸው ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ከዚህም መካከል ህዳር 28 ቀን 2000 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተከናውኖ የነበረው ልዩ የምስጋና ምሽት ተጠቃሽ ነው። በወቅቱም ለክብራቸውና ለውለታቸው መታሰቢያነት የተዘጋጀላቸውን የወርቅ ሜዳልያ ከደጃዝማች ዶ/ር ዘውዴ ገ/ሥላሴ እጅ ተቀብለዋል፡፡
በትወና ችሎታቸው ከቀድሞው ንጉስ አፄ ኃይለ ሥላሴ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በሽልማት ያገኙት አባባ ተስፋዬ፤ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ከእነዚህ ሽልማቶችም መካከል የኢትዮጵያ የስነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት፣ በ1991 ዓ.ም ያዘጋጀውና በቴአትር ዘርፍ በተዋናይነት የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑበት ዋንኛው ነው፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ እኚህን ታላቅ የአገር ሀብት ከዓመታት በኋላ አስታውሶ፣ በዘንድሮው ዓመት፣ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶአቸዋል፡፡

የአባባ ተስፋዬ እውነታዎች
ወላጅ አባታቸው ኤጀርሣ በዳኔ ይባላሉ፡፡ የሚጠሩበት ሣህሉ የአሳዳጊያቸው ስም ነው፡፡
አዲስ አበባ የገቡት በ10 ዓመታቸው ነበር፡፡
የተማሩት ተፈሪ መኮንን፣ አሁን ኮከበ ፅባህ በተባለው ት/ቤት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ነው መጀመሪያ የተቀጠሩት፡፡
ደመወዛቸው 11 ብር ነበር፡፡
በ1947 ዓ.ም አግብተው በትዳር ለ48 አመት ኖረው፣ ባለቤታቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡
ስልክ ማናገር አይወዱም ነበር፡፡
ቃጫ በጥቁር ቀለም ነክሮ፣ እንደ ዊግ መጠቀም የጀመሩት እሳቸው ናቸው፡፡
በሐረር ራስ ሆቴል፣ ከአስተናጋጅነት እስከ ኃላፊነት ደረጃ ሰርተዋል፡፡
በ1938 ማዘጋጃ ቤት ሲቀጠሩ፣ የሴት ተዋናይ ባለመኖሩ ለአራት ዓመታት እንደሴት በመሆን ተውነዋል፡፡
በአንድ ቲያትር ላይ 3 ገፀ ባህርያትን ወክለው ተውነዋል፡፡
በሚሰሩት የምትሀት ትርኢት ሳቢያ፣ ከሰው ተገልለው ነበር፡፡  
የፃፏቸውን የተረት መፃህፍት ከገበያ እየገዙ፣ በየቦታው እያዞሩ ይሸጡ ነበር፡፡
አፋጀሺኝ የተሰኘው ቲያትር ላይ፣ የንግስቲቱን ገፀባህርይ በመወከል ተውነዋል፡፡

Read 1272 times