Sunday, 06 August 2017 00:00

ኮከብ ቆጣሪው

Written by  ድርሰት - ራሲፑራም ክሪሽናስዋሚ ናራያን ትርጉም - ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

      ልክ እኩለ ሲሆን፤ ጓዙን ፈትቶ፤ የስራ ማከናወኛ ኮልኮሌዎቹን አወጣ፡፡ አስራ ሁለት የቀንዳውጣ ዛጎሎችን ደረደረ፡፡ በምትሀት ጽሑፍና የተጠማዘዙ ሀረጋት ስእል ንድፍ የተዥጎረጎረ፣ ሰፊ ጠልሰም መሀረብ አነጠፈ፡፡ የእጅ መዳፍ ረቂቅ ምስጢር መፍቻ ጥቅልሉን ዘረጋ፡፡ ከዛፍ ቅርፊት በተላጉ ገጾች ተጽፎ የተደጎሰ የማስተርጎሚያ ጥራዙን ገለጠ። ግንባሩ ላይ የተቀባው ፍም መሳይ ቀይ የሜርኩሪ ቬሚሊየን፣ የአስማት አመድ፣ ጎልቶ ያንጸባርቃል። ያለመታከት ደንበኛ ፍለጋ ናፍቀው ከሚንተገተጉ አይኖቹ የሚወረወሩት፣ በጉጉት የጦዙ ጨረሮች ጤናማ ብርሀን አይረጩም፡፡ ያም ሆኖ፤ እጅ የሚነሱት ምስኪን ደጅ ጠኚ ደንበኞቹ፣ እርሱን በመሳለማቸው ሀሴት ያደርጋሉ፤ የትንቢት ካፊያው ጠል ይርከፈከፍባቸዋልና፡፡ ስለዬህም፤ ሰርሳሪ አይኖቹ እንደ ማንም ሰው በቀለም ባጌጠው ግንባሩና አገጩ ድረስ እየተጥመለመለ በሚወርደው መላ ፊቱን በሸፈነው ከርዳዳ ጢሙ መሀል የተቀመጡ ቢሆንም፤ ምሉእነት ለሚጎድለው ጠንቋይነቱ አንዳች ግርማ ሞገስ ለመጨመር ይንቦገቦጋሉ። ንግሥናውን እንዲያግዘውም ደማቅ ቡርቱካናማ ጥብጣብ፣ በአናቱ ዙሪያ እንደ ዘውድ ጠምጥሟል፡፡ ይኸውም የሴራ ቋጠሮው የአላማው ማሳኪያ በመሆን ባግባቡ ያገለግለዋል፡፡ ልክ ንቦች ወደ አበባና ጣፋጭ እንደሚተምሙት ሁሉ ደንበኞቹን እያግተለተለ ያመጣለታል፡፡
በአንድ ቅርንጫፎቹ በተንዠረገጉ ትልቅ ዛፍ ስር ለመቀመጥ ሲመርጥም፤ ዛፉ ወደ ሀል ፓርክ ከተማ በሚወስደው ጎዳና መሀል ፊት ለፊት በሚታይ ቦታ ላይ ያለ መሆኑን አገናዝቦ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ መሆኑም ብዙ ጥቅም አለው፤ በጠባቡ መንገድ ላይ የህዝብ ማእበል፤ ከንጋት እስከ ምሽት፣ ላይ ታች ይርመሰመስበታል፡፡ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የስራ ግንኙነትች የሚካሄዱትም በዚሁ መንገድ ላይ ነው፡፡ መድኃኒት ሻጮች፣ የተሰረቁ ቁሳቁሶች፣ ያገለገሉ አሮጌ እቃዎችና ቅራቅንቦዎችን ሁሉ ገዢና ሻጮች የሚገበያዩበት፤ ምትሀተኞች የሚዘዋወሩበት፤ ከሁሉም በላይ ደሞ ሰልባጅ  ነጋዴዎች  ልብስ በርካሽ ከምረው የሚያቀርቡበትና የከተማዋን ዙሪያ ነዋሪዎች ገበያ ለመሳብ ተፍ ተፍ እሚሉበት አማካይ መንገድ ነው። ከሱ ራቅ ብሎ ምድጃውን እያራገበ ለውዝ እየቆላ የሚሸጠው ነጋዴ፤ ከለውዙ ሌላ በየቀኑ ልዩ ልዩ እቃዎችን እየለዋወጠ እያመጣ፤ የተንቆለጳጰሰ ስም እየሰጠ፣ ጮክ ባለ ድምጽ፣ ገዢዎችን ይጣራል፤ አንድ ቀን ‹‹ይኼውላችሁ ምርጡ የቦምቤ ከረሜላ!››፤ በማግስቱ ‹‹ጉደኛው የደልሂ ስኳር ድንች!››፤ በሶስተኛው ቀን ‹‹ጣመን ድገመን የሚያሰኘው ጣፋጩ የራጃን ብስኩት!›› እናም በቀጣዩ ቀን ሌላ፤ አሁንም ሲነጋ ሌላ፤ አድሮም ሌላ . . . በዚህም የተነሳ ገበያተኞች እንደ ጉድ ይንጋጉለታል፡፡ ከዚሁም ጋጋታ መሀል ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ሰዎች ኮከብ ቆጣሪው ዘንድ ጎራ ይላሉ፡፡
ኮከብ ቆጣሪው በምሽት ጊዜ ስራውን የሚያከናውነውም፤ በዚሁ የለውዝ ነጋዴ ጎረቤቱ አዋኪ ጩኸት ታጅቦ፤ በእርሱው የምድጃ እሳት ወጋገንና ጢስ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ የአካባቢውን ገጽታ የራሱ የሆነ ማራኪ ውበት የሚያላብሰው መልኩም። በከተማዋ አስተዳደር ካልተቸረው የመብራት አገልግሎት ንፍገት የተገኘ ነው፤ በዙሪያ ካሉ ነጋዴዎች በሚንፀባረቁ ጭላንጭል ፍንጣቂዎች ብቻ እየታገዘ ተዳፍኖ መኖሩ፡፡ አንድ ሁለቱ በላምባ የሚበሩ ኩራዞች አሏቸው፤ አንዳንዱም በቋሚ ምሰሶዎቻቸው ላይ የሚያንጠለጥሏቸው ፋኖሶች፤ ሌሎቹ ደግሞ ከአሮጌ ብስክሌቶች ላይ የተነቀሉ አምፖሎች፤ እንደ ኮከብ ቆጣሪው ያሉት ምንም አይነት የራሳቸው የሆነ የብርሀን ምንጭ የሌላቸውም፤ በነዚሁ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተሽሎኩልከው በሚፈነጥቁ አልፎ ሂያጅና የተዘበራረቁ ጨረሮች ድባብ ስር እየተንከላወሱ ያመሻሉ፡፡ ይህም ለኮከብ ቆጣሪው ተመችቶታል፤ ለምን ቢሉ፣ በኮከብ ቆጣሪነት ለመሰማራት ሲነሳ፣ በሞያው ባለቤቶች ዝርዝር ውስጥ ስሙ የለምና ነው፤ እናም የሌሎችን እጣ ፈንታ ማወቅ ቀርቶ በእርሱ በራሱም ላይ በቀጣይዋ ደቂቃ ሊሆን የሚችለውን አንዳችም ጉዳይ አለማወቁም፡፡ ደንበኞቹን ፍፁም የማያውቃቸውን ያህልም እርሱም ከአውደ ከዋክብት እውቀት ፈፅሞ የፀዳ ነው፡፡ ለደንበኞቹ የሚሰነዝራቸው መልካም ገድ ሁላቸውንም በደስታ የሚያስፈነጥዙ ትንበያዎቹም፤ በማንነታቸው ዙሪያ ከሚነግሩት በመነሳት የሚያመነጫቸው፣ በልምምድ ያዳበረው ተናግሮ የማሳመን ጮሌነቱ ነው፡፡ እናም ሌሎች ጥረው ግረውና ላባቸውን ጠብ አርገው፣ በታማኝነት በገበሩት ጉልበታቸው፣ የእለት መቁንናቸውን ቋጥረው ወደየቤታቸው እንደሚሄዱት ሁሉ፤ እርሱም በዚህ መልኩ፣ በየቀኑ የሚያስገባውን ገቢ ደረቱን ነፍቶ ይቆጥራል፡፡
ከቀድሞ መኖሪያ መንደሩ የተሰደደው ድንገት በተከሰተ አጋጣሚ ተገፍቶ ነው፤ ከቶም ባልተዘጋጀበት ሁኔታ፡፡ በርግጥ በዚያው በመንደሩ መኖር ቢቀጥል ኖሮ፣ የእርሱም እድል ከዚያው ከአያት ቅድማያቶቹ ያልተለየ በሆነ ነበር፡፡ ማረስ፣ መዝራት፣ በገጠር ኑሮ መባዘን፣ ትዳር መያዝ፣ የበቆሎ እሸቱ ‹አጎነቆለ አሊያስ አረም ውጦት - ዋግ አጠናፍሮት ከረረ› እያለ፣ እንደነዚያው ቅማያቶቹ እየተብሰከሰከ፣: የዝናብ መና አንጋጥጦ እየጠበቀ፣ በዚያው በምንጅላቶቹ ታዛ እድሜውን መፍጀት። ግን ያም ይሆን ዘንድ ቢሻ እንኳ አሁን ሊሆን አይቻለውም፡፡ ለማንም ትንፍሽ ሳይል የግዱን ከቀዬው ሹልክ ብሎ ወጥቶ መንጎድ ነበረበት። የሁለት ቀን መንገድ ተጉዞ፣ ሀገር አቋርጦ ወዲህ ባይመጣ ኖሮ፣ ነፃነቱን አያገኝም ነበራ፡፡ ስለዬህ ከሸሸው ጉዳይ ጋር ሲነፃፀር ዛሬ የሚኖረው ኑሮ፣ ለእሱ ቢጤ የገጠር ነዋሪ ትልቅ እድል የሚባል ነው - በአዱኛ ባህር የመጠመቅ ያህል፡፡
እንደ ትዳር፣የሀብት እጦት ጉዳይና በእለት ተዕለት የማህበራዊ ኑሮ ትስስሮሽ  በሚፈጠሩ ውስብስብ ጣጣዎች ላይ ትንታኔ የመስጠትን ተግባር ነው የሚያቀላጥፈው፡፡ የስራ ልምዱ በጨመረ ቁጥርም በዚያው መጠን የግንዛቤ ደረጃውም የሰላ ሆኖለታል። በአምስት ደቂቃ ቆይታ ብቻ ከደንበኛው ጀርባ ያለውን የምኞት ጥማትና የኑሮ ስብራት ይደርስበታል። ለአንድ ‹ምልጃ› አስር ብር የሚያስከፍል ሲሆን፤ ደንበኛው በችግሩ ዙሪያ ቢያንስ የአስር ደቂቃ ማብራሪያ እስኪሰጥ ድረስ፤ እርሱ በዝምታ ተሸብቦ በአንክሮ ያደምጣል። ይህም ቀጥሎ ለደንበኛው ለሚቸረው ደርዘን ሙሉ የመፍትኄ ምላሽ፡ ማጽናኛ ምክርና የተስፋ ስንቅ  በቂ ይረዳዋል፡፡ የደንበኞቹን የእጅ መዳፍ ትኩር ብሎ እያየ...‹‹ትለፋለህ! ትግራለህ! ግና ምን ዋጋ አለው፡ አመዳፋሽ ነህ! ዋ! የዘሩትን ያለማጨድ ገዳፋ!!!›› ይላቸዋል፡፡ ከአስሩ ሰዎች ዘጠኙ ያለማንገራገር እጅ ይሰጣሉ፡፡ እርሱ የጠያቂነቱን ተራ ሲወስድ ደግሞ...‹‹አንዲት ሴት ትታየኛለች፡ ቤተኛ ወይም የቅርብ ዘመድ የሆነች፣ በቤተሰባችሁ ላይ የምታንጎራጉረው የሆዷ እማይታወቅ?!››ይላል፤ ወይም የባህሪ ትንታኔዎችን ይደረድራል... ‹‹ይኼ የመወለድ ቀን  ያመጣው ሳንካ፣ እትብት ሲቀበር ያልተቀበረ፣ እንደ ጥላ ተጣብቶ የሚኖር መዘዝ ነው! ታዲያ እንግዲህ ገውዝ እሳት ለቤት ቀጋ ለውጪ አልጋ ከሆነው ከአመል እሳት ጋ፣ በምን ተአምር አብሮ ሊዘልቅ ይቻለዋል፤ሦስት ጉልቻውም አጉል ቅዠት ነው! አንድ መላ ካልተበጀለት በቀር፣ እሳትና ጭድ ሆኖ ሲቃጠሉ፡ ሲያርሩ፡ ሲደብኑ መኖር ብቻ !!!›› ይህን ሲላቸው በቃ ባንዳፍታ በደንበኞቹ ልብ ውስጥ ገብቶ ይጎዘጎዛል፡፡ በፍፁም አንወናበድም እምንል ብንሆንም እንኳ፤እንደ ‹‹የውጪ አልጋ የቤት ቀጋ›› አይነት ድፍንፍን ያሉ ገለፃዎች፣ ሳይታወቀን ልቦናችንን ሰቅዞ የሚይዝ፣ አንዳች ጥርጣሬ እንዲያድርብን ያመቻቹናል - ሰው ነን እኮ፡፡
ምሽቱ ለአይን መያዝ ሲጀምር ለውዝ ነጋዴው ወደ ቤቱ ለመሄድ መዘገጃጀት ጀመረ፡፡ ኮከብ ቆጣሪውም ጓዙን መጠቅለሉ ግድ መሆኑ ነው። ከምድጃው እሳት ወላፈን ጭላንጭል ብርሀኑን የሚቸረው ጎረቤቱ ሄደ ማለት፤ ቦታው: ከርቀት፣ ከማይታወቅ አቅጣጫ ተወርውሮ፣ እርሱን ተሻግሮ ፊት ለፊቱ መሬት ላይ የሚያረብበው ድንግዝግዝ አረንጓዴ የብርሀን ፍንጣቂ ብቻ ቀርቶ በጨለማ ይዋጣል፡፡ ጥምልምል ዛጎሎቹንና መገልገያ ቅራቅንቦዎቹን ለመሸከፍ ሲሰናዳ፤ ደብዛዛው አረንጓዴ ብርሀን ድንገት ተጋረደ፡፡ ቀና ሲል አንድ ሰው ጀርባውን ሰጥቶት ወዲያ ወዲህ ያማትራል። እንደ ማንኛውም ደንበኛ ቆጥሮት፣ ማጥመጃ መረቡን ለመጣል ያህል፣ ‹‹ስትቅበዘበዝ አይሀለሁ፤ ምናልባት ላፍታ አረፍ ብለህ ብናወጋ፣ እረፍት ታገኝ ይመስለኛል!›› አለው፡፡ ሰውየው በበኩሉ፤ ግልፅ ያልሆነ የማይሰማ ንግግር አልጎመጎመ፡፡ ኮከብ ቆጠሪውም የግብዣ ጉትጎታውን ቀጠለ፡፡ ይህኔ ሰውየው መዳፉን ዘርግቶ፣ ኮከብ ቆጣሪው አፍንጫ ስር ሰተረለትና፤ ‹‹ጥሩ፡ አዋቂ ነኝ ካልክ ይኸው እንይህ!›› አለው፡፡ ኮከብ ቆጣሪው፤ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ፤ የሰውየውን መዳፍ ወደዚያችው አረንጓዴ የብርሀን ሰበዝ ከፍ አድርጎ እያየ፤ ‹‹ያንተ ክፉ እጣ ከዘር ማንዘርህ...›› ማለት ሲጀምር፤ ‹‹ኤይ! ዝባዝንኬ ሀተታ አልፈልግም እሺ! ዙሪያ ጥምጥሙን ተወውና እቅጯን ብቻ ተናገር!›› አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ወዳጃችን ቅያሜ አጠላበት፡፡ ‹‹ለያንዳንዱ ጉዳይ አስር አስር ብር ነው እማስከፍለው፤ ገንዘብክን ይጭነቀው እንጂ ያሻህን ጉዳይ...››፣ አሁንም ሰውየው አቋረጠውና የዘረጋውን እጁን መልሶ ኪሱ ከትቶ፣ ድፍን ሀምሳ ብር አወጣና ኮከብ ቆጣሪው አገጭ ስር ወርውሮለት፤ ‹‹ይኸው እንካ፤ እናም ጥያቄዎችን አቀርብልሀለው፤ ምላሽህ ትክክል ከሆነ የሰጠውህን ብር ሁሉንም ትወስደዋለህ፤ ካልመለስክ ግን የሰጠውህን ገንዘብ እጥፍ አድርገህ ትመልሳለህ፤ ትስማማለህ?!››
‹‹አንተስ፡ ምላሼ ትክክል ሆኖ ስታገኘው፤ አሁን የሰጠኸኝን እጥፍ አድርገህ ትከፍለኛለህ?!››
‹‹ለምን ብዬ?!››
‹‹እሺ ግማሹን ትጨምርልኛለህ?››
‹‹ጥሩ ይሁንልህ! አንተ ከፎረሽክ ግን እጥፍ አድርገህ መመለስህን እንዳትዘነጋ! ልብ በል!››
በውርርዱ ላይ ጥቂት ከተከራከሩ በኋላ ተስማሙ።
ሰውየው ሲጋራ አውጥቶ ሲለኩስ፤ ኮከብ ቆጣሪው የ‹አውጣኝ› ጸሎቱን ለፈጣሪው እያደረሰ ነበር፡፡ ድንገት! በተጫረው የክብሪት ብርሀን ውስጥ የሰውየውን ፊት አየው፡፡ በዚች ቅጽበት በሰፈነው ዘላለማዊ ፀጥታ ውስጥ፡ በአውራ ጎዳናው ላይ የሚያቋርጡ ሰረገላ ነጂዎች፣ ፈረሳቸውን ሸንቁጠው ‹‹ቼ!›› ብለው ሲጮሁና ሲሸመጥጡ፤ አብሮም ድፍን ጨለማ የዋጠውን መንገድ እየተደናበሩ የሚያቋርጡት እግረኞች፣ መንገድ ስለተዘጋባቸው፣ በተቃውሞ ያሰሙት የደቦ ጉርምሩምታ ጎልቶ ተሰማ፡፡ ሰውየው አረፍ ብሎ ሲጋራውን እያቦነነ መቁነጥነጥ ያዘ፡፡ ኮከብ ቆጣሪው፤ ድንገተኛ አጋጣሚው እንደ መርግ ከብዶት ውጥረት ነገሰበት፡፡ ‹‹በል በል በል ገንዘብህን ወዲያ ውሰድልኝ፤ ላንተ ጉዳይ መላ መምታት እንደማልችል ትከሻዬ ነገረኝ፡፡
በዚያ ላይ በጣም ስለመሸብኝ ባይሆን ነገ ብቅ በልና አይልሀለው እንጂ ዛሬስ...›› ሲል፤ ሰውየው  እጁን ለቀም አርጎ ይዞ፣ ‹‹አሁንማ አንዴ አስጀምረኸኛል፤ ማቋረጥ አትችልም! ከመንገዴ አናጥበህ ግብዣ ያቀረብክልኝ አንተው መስለኸኝ!›› ብሎ አፋጠጠው። ኮከብ ቆጣሪው፣ ክንዱን እንደተያዘ፣ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠና ድምጹ በፍርሀት እየተርገበገበ፣ ‹‹የዛሬን ተወኝ አልኩህኮ ወንድሜ፤ ነገ እንደሚሆን እንደሚሆን እናደርገዋለን፤ እባክህን እጄን ልቀቀኝ?!›› በመለማመጥ ተማፀነ፡፡
ሰውየው ግን አሁንም ኮከብ ቆጣሪው አይኖች ስር መዳፉን እንደዘረጋ፤ ‹‹ወዴት ወዴት መሸሽ ባክህ! ውርርድ ውርርድ ነው፤ በል ቀጥል አሁን!›› ሲል አምባረቀ፡፡ ኮከብ ቆጣሪው ጉሮሮው ደርቆበት፤ በሚያሳዝን ቅላፄ ‹‹አንዲት ሴት ትታየኛለች...›› ማለት ሲጀምር ገና፤ ሰውየው ‹‹ኦኦኦ! ያንተን እንቶ ፈንቶ መስማት አልፈልግም አልኩህኮ! የጀመርኩት ፍለጋ ይሳካልኛል ወይስ አይሳካልኝም? በቃ! ለዚህ ጥያቄ አንዲት አጭር ምላሽህን ብቻ ዱቅ አርገህልኝ ጥርግ ልትል ትችላለህ! አይ ካልክ ግን፤ ወይ በውርርዱ መረታትህን አምነህ ገንዘቤን እጥፍ አፍርገህ ካልመለስክ፤ ሺ ጊዜ መሽቶ ቢነጋ እንደማልለቅህ ቁርጥህን እወቅ!›› ብሎ አስጠነቀቀው፡፡
ኮከብ ቆጣሪው፤ በለሆሳስ ካጉተመተመ በኋላ፣ ‹‹ይሁን፤ መልካም እነግርሀለው፡፡ ግን እኔ ቢመሽብኝ ይምሽብኝ ብዬ ያንተን ጥያቄ መለስኩልህ እንበል፤ እናም ትክክል ሆኖ አገኘኸው፤በተራህ ያስያዝከውን ገንዘብ እጥፍ ታደርግልኛለህ ወይ?! አይ ካልክ እኔም አንዲት ቃል ትንፍሽ እንደማልል አንተም ቁርጡን እወቀው! እናም ማድረግ ያሻህን ልታደርግ ትችላለህ!›› አሁንም እንደገና  በውርርዱ ላይ ንትርክ ያዙና ተስማሙ፡፡
‹‹ሞተሀል ብለው ጥለውህ ሄደው፣ ሬሳህ ነፍስ ዘርቶ የተነሳህ ሰው ነህ፤ እሺ ተሳሳትኩ?!›› ሲል ጠየቀ ኮከብ ቆጣሪው፡፡
‹‹ቀጥል! ቀጥል!›› አለ ሰውየው፡፡
‹‹በገጀራ ስለት ነበር ስጋህን የመተሩት!›› ቀጠለ፤ ኮከብ ቆጣሪው፡፡
‹‹ይኸው ነው ገበያው!  እየው...›› አለና ሰውየው ጠባሳውን ገልጦ አሳየው፡፡ ‹‹እሺ ሌላስ? ዝለቅ...!
‹‹ሞቷል ብለው ገደል ውስጥ ጥለውህ ሄዱ፡፡ አንተም ራስክን ስተህ፣ ትንፋሽክን አጥተህ፣እንዴ! በቃ ሞተህ ነበረኮ!››
‹‹እንክት! እውነት ነው! ትረፍ ቢለኝ፤ በዚያ በኩል የሚያልፍ አንድ መንገደኛ ባጋጣሚ አይቶኝ ባይደርስልኝና ባያነሳኝ ኖሮ አብቅቶልኝ፤ ሞቼ ነበር! ... ትክክል!” ሰውየው በመደነቅ፣የተነገረው ሀቅ መሆኑን እየመሰከረና፤ በል በል እሚለው እልህ እየገነፈለበት፤ ‹‹እና መቼ ነው ገዳዬን ማንቁርቱን እማንቀው?!›› ሲል ጠየቀ፤ ቡጢ እየጨበጠ፡፡ ‹‹ከሞት በኋላ! በሰማይ ቤት!›› ብሎ መለሰ፣ ኮከብ ቆጣሪው፡፡ ‹‹መንፈቅ አለፈው... በአንዲት ራቅ  ባለች መንደር ውስጥ ሞቶ ተቀብሯል፡፡...ስለዬህ፣ :ከእንግዲህ ፈፅሞ በአይነ ስጋ አታየውም!›› ሰውየው ይህን ሲሰማ አቃሰተ፡፡
‹‹ጉሩ ናያክ!››
‹‹እንዴ! ስሜንም አወቅከውና!›› አለ ሰውየው ደንግጦ፡፡
‹‹ማንኛዋም ጉዳይ እንደማትጠፋኝ ሁሉ - አዎን! ...እና ጉሩ ናያክ፤ እምልህን በጥሞና አድምጥ፤ ከመኖሪያ መንደርህ የሁለት ቀን መንገድ ተጉዘህ ወዲህ እንደመጣኸው፤ አሁኑኑ የሚቀጥለውን ባቡር ተሳፍረህ ከዚህ ከተማ ሹልክ ብለህ ሂድ! እናም፤ ከእንግዲህ በኋላም ቢሆን፤ ከመንደርህ ወጥተህ ወዴትም ውልፍት ያልክ እንደሁ፤ በላይህ ላይ የሚያንዣብብ አጉል!... ንግርት!... ጋሬጣ! ጠልፎ! ሲጥልህ! ውልል! ብሎ ይታየኛል!!!›› አለውና፤ አመድ ቆንጥሮ መዳፉ ላይ እያኖረለት፣ ‹‹በዚህ አስማተ መሰውር ግንባርህን ፈትገህ! ግራ ቀኝ ሳታይ፣ ወደ መጣህበት መሰስ በል - አሁኑኑ! ምክሬን ሰምተህ፣አደብህን ገዝተህ፣ ዳግመኛ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዲች ብለህ እግርህን እማታላውስ የሆነ እንደሁ ግን ፤ እስከ መቶ አመት ድረስም ረዥም እድሜን ትኖራለህ!!!››
‹‹ኧረ ምን ቆርጦኝ! ምናባቴ ሲያቀብጠኝ ዳግመኛ ከመንደሬ እወጣለሁ?!›› አለ ሰውየው ሽምቅቅ ብሎ። ‹‹አሁንም ላንዴው ከሀገሬ መውጣቴ፤ ባላጋራዬን እምጥ ስምጥ ገብቼ አግኝቼ፤ ባፍጢሙ ደፍቼ ነፍሱን ላወድማት ነበረ እንጂ!›› እያለና ጭንቅላቱን እየነቀነቀ፣ ‹‹እንግዲህማ ከእጄ አምልጧል፤ ያም ሆኖ እንደተመኘሁት የሚገባውን የሞት ጽዋ ተጎንጭቷታል!››
‹‹አበቃ!›› አለ ኮከብ ቆጣሪውም፤ ‹‹ተሳፍሮበት የነበረው ሰረገላ ተገልብጦ ነው የሞተው!›› ሲለውማ፤ ሰውየው በተነገረው የመርዶ ብስራት ጮቤ ረገጠ፡፡
ከተማው ጭር ብሎ በረሀ ሲመስል፤ ኮከብ ቆጣሪው ግሳንግሶቹን ወደ ቦርሳው ከተተ፡፡ አሁን አረንጓዴው ደብዛዛ ብርሀንም ድርግም ብሎ ጠፍቶ፤ አካባቢው በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ፣ ፀጥ እረጭ ብሏል፡፡ እንግዳው ሰውየም፤ ለኮከብ ቆጣሪው እጥፍ ክፍያውን አስጨብጦት፣ ባቡሩን ተሳፍሮ ወደ መጣበት እብስ ብሏል፡፡
ኮከብ ቆጣሪው መኖሪያ ቤቱ ሲደርስ፤ እኩለ ሌት አልፎ ነበር፡፡ በር ላይ ቆማ እምትጠባበቀው ሚስቱ፤ የቆየበትን ምክንያት ለማወቅ አቆብቁባለች፡፡ ያገኘውን ገንዘብ እላይዋ ላይ በትኖላት፤ ‹‹ቁጠሪው! ይህን ሁሉ ከአንድ ዘንካታ ነው ያገኘሁት!›› አላት፡፡
‹‹ይኼን ሁሉ?!›› አለች ገንዘቡን ቆጥራ ስትጨርስ፣ እጅግ በጣም እየተደሰተች፡፡ ‹‹ነገ ማለዳ ተነስቼ አስቤዛ እሸምታለሁ፤ ስኳር ድንችና ዘይት፣ ቅቤም ትንሽ እገዛለሁ፡፡ ልጃችን ስኳር ድንች ግዢልኝ ብሎ ሲወተውተኝ ነው የሰነበተው፤ ዛሬምንኳ ጠይቆኛል። ነገ ምሳ እማዘጋጀውን ብቻ ነግቶ እስካሳይህ ቸኩያለሁ!!!››
‹‹ያንን አሳማ ግን ከዚህም በላይ ላስከፍለው እችል ነበር! የጠየቅኩትን ከመስጠት አያመነታም ነበራ!›› አለ ኮከብ ቆጣሪው፡፡ ሚስትየዋ ትክ ብላ እያየችው፤ ‹‹የተጨነቅክ ትመስላለህ ልበል? ምነው ምን አገኘህ?›› ብላ ጠየቀችው፡፡
‹‹ምንም!›› አላት፡፡
ራት ከበሉ በኋላ ፤ ሰፊው መኝታ መደብ ላይ ቁጭ ብለው ሁሉንም ነገር ነገራት፡፡ ‹‹የዛሬዋ ቀን ለኔ በህይወቴ ልዩ ቀን ናት፤ ጫንቃዬ ላይ ተሸክሜው የኖርኩትን ቋጥኝ ያራጋፍኩባት እለት መሆኗን ብነግርሽስ!...በእጄ ላይ የሰው ደም ነበረ፤ ሌት ተቀን ሲያብሰከስከኝ ነው የኖርኩት! ለዚያም ነበረ እትብቴ ከተቀበረበት መንደር እርቄ ወደዚች ከተማ ለመሰደድ የተገደድኩት፡፡ እናም አንቺን አግብቼ መኖር የጀመርኩት፡፡ ሰውየው ለካ በህይወት አለ!››
ሚስትየዋ ትቃትት ጀመር፡፡ ‹‹ሰውን ለመግደል ሞክረህ ነበር ማለት ነው?!››
‹‹እህን!...በመንደራችን ውስጥ፤ አፍላ ጎረምሳ ሳለሁ፤ አንድ ቀን፤ ከአብሮ አደጎቼ ጋ መጠጥ ስንጋት ውለን፤ ጥምብዝ ብለን ሰክረን፤ ቁማር ስንቆምር ሳለን፤ ድንገት! በመካከላችን የጦፈ አምባጓሮ ተነሳ። ... ግን አሁን ለምንድነው ያን ክፉ አጋጣሚ ደግሜ እማስታውሰው?! ይልቅ ብንተኛ ይሻላል›› አለና እያፋሸከ መደቡ ላይ ፈንደስ አለ፡፡

Read 1185 times