Sunday, 06 August 2017 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን ወርቁ
Rate this item
(5 votes)

 “… እንዲሁ ባለም ላይ ብዙ ነገር፣ በዚህ ቢሉት በዚያ መሆኑ የማይቀር፡፡”
ሰውየው ዕቃ ሊገዛ ወደ ሱቅ ሲገባ መስታወት ውስጥ ሞቱን አየ፡፡ ዞር ብሎ ወደ ኋላው ሲመለከት ምንም አልነበረም፡፡ ሽንቱን መቆጣጠር እየሞከረ ሩጫውን ለቀቀ፡፡ አንድ ቡና ቤት ዘው አለና ወደ መፀደጃ ቤቱ አቀና፡፡ እንዳጋጣሚ እዛም መስታወት ነበርና ከኋላው ቆሞ ተመለከተ፡፡ …ዞር ሲል ግን የለም፡፡ እየተጣደፈ ወደ ቤቱ እምነቱ ሄዶ፣ ቀጥታ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡ ግድግዳው ላይ ወደ ተሰቀለው ምስል እያማተበ ሲጠጋ፣ ውልብ ያለ ነገር ያየ መሰለው፡፡ አትኩሮ ሲመለከት እሱ ነው፡፡…ጮኾ በፍጥነት ወደ ኋላው ዞሮ ፈረጠጠ፡፡
መንገድ አቆራረጠና ከሰፈሩ ደረሰ፡፡ ደከመው፤ ውሃም ጠማው፡፡ ቢራ የሚጠጣበት ግቢ ገብቶ እንደ መተንፈስ አለ፡፡
አስተናጋጁ “ጋሼ ምን ይምጣ?” ሲለው፣
“ቢራ” አለ
ይዞለት መጣና ሲከፍትለት ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ።…እሱው ነው፡፡ በጀርባው ተፈነገለ፡፡
ወዳጄ ሆይ፤ ሞት በዚህ ቢሉት በዚያ የሚቀር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከፈራኸው ደግሞ ተስፋህን፣ ምኞትህን፣ ትግልህን ያደናቅፍብሃል፡፡ ራስህን ለማዳን ብለህ፣ በሌላው ላይ በሀሰት ብትመሰክር ያመለጥከው እንዳይመስልህ፡፡ ወንድምህ በትግል ሜዳ ሲወድቅ አይተህ ብትሸሽ ያመለጥከው እንዳይመስልህ፡፡ ካንተ ቀድሞ ዞሮ ይጠብቅሀል፡፡ ባልጠረጠረክበት ሰዓት፣ ባልጠረጠርክበት ቦታ መንገድህ ላይ ይደነቀራል፡፡
መኝታ ቤትህ በምትሞቀው ከሰል፣ ወይ ስትስቅና ስትጫወት፣ በትንታህ ውስጥ ሊደበቅ ይችላል፡፡ መኪናህን ሊገለብጥ ወይ ሌላ መኪና ጎማ ስር ሊገፈትርህ ይችላል፡፡ ታመህ በምትተኛበት ጊዜ እንዳስታማሚህ፤ እንደ ወዳጁ ገባ ወጣ እያለ ያይሃል፡፡ “አለሁ እዚሁ አካባቢ ነኝ” የሚልህ ይመስልህና፣ ጥርስህን ስትነክስበት ወገቡን ይዞ ይስቃል፡፡ ሌሎች አያዩትም፣ አይሰሙትም፡፡…ያንተ ሞት ያንተ ብቻ ነው፡፡ (You live together, you die alone) እንደሚሉት፡፡
ወዳጄ፤ ንጉሥ ወይ ለማኝ፤ ዘፋኝ ወይ አትሌት፤ ወታደር ወይ መምህር፣ ቄስ ወይ ሼህ፤ ቅን የህዝብ አገልጋይ ወይ ወሮበላ ባለስልጣን ልትሆን ትችላለህ፡፡ ዕድሜህ ላይ መቶ ዓመት ተጨምሮልህ አሁን ባለህበት ሁኔታ እዚሁ ምድር ላይ መኖርህን ብትቀጥል ይሻልሃል? ወይስ በዚች ደቂቃ ብትሞትና መንግሥተ ሰማያት ገብተህ ለዘለዓለም ብትኖር ትወዳለህ? ብዬ ብጠይቅህ፣ መልስህ ምንድነው፣ የትኛውን ትመርጣለህ?
እውነት፣ እውነት እልሃለሁ፡፡  በጣም ጥቂት ‹የበቁ› (the perfect ones) ወይም በከፋ ህመም የሚሰቃዩ ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር፣ ሌላው ሁሉ ‹እዚሁ ይሻለኛል› እንደሚል አትጠራጠር፡፡ ምክንያቱም ሞትን ስለሚፈራ!!
አንድ ነገር ልጨምርልህ፡፡ ይኸ መኖር ወይም ዕድሜ የምንለው፣ ‹ህይወት› በገንዘብ የሚገዛ ቢሆን፣ አንተ ደግሞ ንዋይ የበዛልህ ግን ጤና የጎደለብህ ብትሆን፣ ከሌሎች ምስኪኖች ዕድሜ ለመግዛት ታንገራግራለህ? ለመልሱ አትጨነቅ፡፡… ግን፣ ግን ድህነት ሽሽት፤ እንጀራ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲሉ በወሮበሎች እየታነቁ፣ ሰውነታቸው እንደ ከብት እየተዘነጠለ፣ ልባቸው፤ ኩላሊታቸውና ሌሎች የሰውነት አካላቸው እየተወሰደ፣ በየበረሃውና በ‹ገዳይ ሆስፒታሎች› የቀሩት ወገኖች ጉዳይ ‹ዕድሜን ለመግዛት እንጂ ከቶ ምን ሊሆን ይችላል?
“If life is a thing that money can buy, the poor wouldn’t live and the rich would not die”
“ህይወት እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ሲሸመት፤
ድሃ አይኖርም ነበር ባለፀጋም አይሞት…”
ተብሎ የተፃፈውና በጊዜው ድንቅ የነበረ አባባል በዚህ ዘመን እየደበዘዘ ነው፡፡ ለጊዜው ክፋት ዋናው ምክንያት ሲመረመር ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡….. ሞትን መፍራት!!
እርግጥ ሞት የሚያስፈራ ክፉ መንፈስ ነው? አይመስለኝም፡፡ አንደኛ ሞት ተላላኪ፤ ጉዳይ ፈፃሚ ነገር እንጂ በራሱ መጨረሻ አይደለም፡፡ ትኬት ከሌላ ቦታ ተልኮልህ ተሳፍረህ እንደምት ሄድበት አውቶብስ ወይ አውሮፕላን እንደ ማለት፡፡ ሁለተኛ፡- ሞት ከህይወታችን ጋር የተሳሰረ፤ ከልደት እስከ መቃብር Womb to Tomb አቅፈነው የምንዞር የኑሮአችን አካል ነው፡፡ አንድ ደቂቃ እድሜህ ላይ ጨመርክ ማለት፣ አንድ ደቂቃ ወደ ሞትህ ቀረብክ ማለት ነው፡፡ “ሞት ከሌለ ህይወት የለም” እንደሚባለው፡፡ ሶስተኛ፡- የህይወት እሽክርክሮሽ ወይም ለውጥ የምንለው የማይለወጠው ነገር (change is the on changing reality)፤ የማይሻገር የተፈጥሮ ሕግ በመሆኑ ሰዎች በሞት ጎዳና ቢመላለሱም ህይወት ይቀጥላል፡፡ “ሰዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል” (Men come and go but man goes on forever) ይለናል አርስቶትል፡፡ አራተኛ፡- ሰው የሚፈራው ሞትን ሳይሆን ‹ሞት› የሚለውን ቃል ነው። ዐዋቂዎች ሞትን ‹ሞት› ብለው አይጠሩትም፡፡ ወደ ‹ነበርንበት መመለስ› ነው የሚሉት፡፡ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” (ashes to ashes, dust to dust) የሚባለው ለዚህ ነው።
ስለዚህ ወዳጄ፤ እውነተኛው ሞት፣ ሳትቸገር ወይ ሳትገደድ የዋሸህ ወይ የሰረቀህ ጊዜ ነው፡፡ ዕውነተኛው ሞት፤ በልብህ የምትጠላውን ባፍህ ‹እወደዋለሁ› ያልክ ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛው ሞት ባመንክበት መፅናት ሲያቅትህ ወይ ጓደኛህን ስትከዳ ነው፡፡ እውነተኛ ሞት እያለህ፣ እንደሌለህ ስታስመስል ወይ ስስታም ስትሆን ነው፡፡ ዕውነተኛ ሞት በዘር፤ በሃይማኖት፣ በቀለም ልዩነት ሰክረህ መቃዝት ስትጀምር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈሪ ስትሆን ነው፡፡
ወዳጄ፤ ጎበዝና ደፋር ከሆንክ ‹ሞት› በመከራህ ጊዜ እንኳን አይጠጋህም፡፡… ትንፋሽህን እስከትጨርስ ይጠብቅሃል፡፡
አቡነ ጴጥሮስ በጥይት ሲደበደቡ፣ ራቅ ብሎ ነበር የቆመው፡፡ ሶቅራጥስ ሲቀልድበት ተደብቆ ነበር የሚያየው፡፡ ቼ ጉቬራ ገዳዩን ‹ተኩስ!› ሲለው የሚገባበት ነበር የጨነቀው፡፡ አንተም አትፍራ፡፡ የልብህን ተናገርና ሙት፡፡ “Say your words and break in pieces” ይልሃል፤ ፍሬዴሪክ ኒሼ፡፡
በነገራችን ላይ ሞትን ሟቹ ብቻ አይደለም የሚያየው። ቡድሂስቶች-ኒርቫና (nirvana) ሂንዱ-ሙክቲ (mukti) እንደሚሉት፣ ከፍተኛ ብቃት ላይ የደረሱ (the highest level of consciousnese) ሰዎች ካሉ ያዩታል፡፡ ካርሎስ ካስቴናዳ Journy to Ixalan (The teachings of Don Juan book (1) በሚለው መጽሃፍ፤ ሞቴን አየሁት ብሏል፡፡

Read 1032 times