Saturday, 05 August 2017 11:50

የ‹‹ለዛ›› ፕሮግራም አድማጮች ሽልማት ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም በውድድሩ ተካትቷል

       በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬዲዮ ላይ የሚተላለፈው የ‹‹ለዛ›› ፕሮግራም አድማጮች የሽልማት ስነ - ስርዓት 7ኛ ዙር ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ፡፡ በዘንድሮው ውድድር ላይ የተካፈሉት ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የወጡ የፊልምና የሙዚቃ ስራዎች ሲሆኑ የሽልማት ሂደቱ ከወትሮው በተለየ ምርጥ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም የሚል አዲስ ዘርፍ ማካተቱን የለዛ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅና የሽልማቱ ፈጣሪ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ አዲሱ ምድብ የሽልማት ዘርፎቹን ዘጠኝ ያደርሳቸዋል የተባለ ሲሆን ምርጥ አልበም፣ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ተዋናይ፣ ምርጥ አዲስ ድምፃዊና ድምፃዊት፣ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮና የህይወት ዘመን ተሸላሚ በሚሉ ዘርፎች ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡
የሙዚቃ ቪዲዮ ምድብ ተሳታፊዎች  በአልበምነት በተጠቀሰው ዓመት የቀረቡና የሙዚቃ ቪዲዮ የተሰራላቸው መሆን አለባቸው ያሉት አዘጋጆቹ፤ ይህም የተደረገው የአልበም ስራዎችን ለማበረታታት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዘንድሮውም የድምፅ አሰጣጥ የመጀመሪያ ዙር በwwwshgerfm.com የሚከናወን ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ምርጥ አምስቱ ከተለዩ በኋላ ኮድ ተሰጥቷቸው በ8101 በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ተጨማሪ የድምፅ ማሰባሰብ ስራ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡ የሙዚቃ ድምፅ አሰጣጡ መቶ በመቶ ለአድማጭ የተሰጠ ሲሆን የውድድሩን ሂደትና የድምፅ ቆጠራውን ለመቆጣጠር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ማህበራትና ተቋማትን ለማሳተፍ እንደታቀደ አዘጋጆቹ  ተናግረዋል፡፡ በፊልም ስራው ውድድር 60 በመቶ በዳኞች፣ ቀሪው 40 በመቶ በተመልካች የሚዳኝ ሲሆን በዚህ የምርጫ ሂደት ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግና ሽልማት የሚገባቸውን የኪነ - ጥበብ ሰዎች ለመሸለም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲደርግ የሽልማቱ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ጥሪ አድርጓል፡፡  

Read 1042 times