Saturday, 05 August 2017 12:04

የአንጋፋው ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ የስንብት ኮንሰርት ነገ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  የአንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ የክብር የስንብት ኮንሰርት፤ ነገ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ይካሄዳል፡፡
ድምፃዊው ከዚህ ኮንሰርት በኋላ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የግብዣ መድረኮች ላይ ካልሆነ በስተቀር እንደወትሮው እንደማይዘፍን በቅርቡ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ በክብር ለማሰናበት በተዘጋጀው በዚህ ኮንሰርት ላይ፣ አንጋፋዎቹ ድምፃዊያን ግርማ በየነ፣ ግርማ ነጋሽ፣ ባህታ ገብረ ህይወት፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ወንድሙ ጅራ፣ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ አስገኘሁ አሸኮ፣ አስቴር ከበደና ሌሎች ድምፃዊያን ለክብሩ እንደሚያቀነቅኑ የኮንሰርቱ አዘጋጅ ኢኢጂ ኤቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ እሸቱ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡  አንጋፋው ድምፃዊ በክብር በሚሸኝበት ኮንሰርት ላይ ለክብሩ ለመዝፈን በርካታ ድምፃዊያን እየጠየቁ መሆኑን የገለፁት አቶ ኢሳያስ፤ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ቀመር የሱፍና ታደለ ሮባ በአጋጣሚ ውጭ ቢሆኑም ከደረሱ ተገኝተው እንደሚዘፍኑ ቃል መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ኮንሰርት ላይ ሀበሻ ባንድ እና ኩል ባንድ ድምፃዊያኑን ያጅባሉ ተብሏል፡፡ የኢንተርኮንትኔንታል በሮች ነገ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት የሚሆኑ ሲሆን ኮንሰርቱ እስከ ሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ይዘልቃል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ የመግቢያ ዋጋው 500 ብር እንደሆነና ጠቅላላ ገቢው ለጋሽ አለማየሁ እሸቴ  እንደሚውል ገልፀዋል፡፡ ድምፃዊያኑ በጠቅላላ ያለምንም ክፍያ በነፃ ለክብሩ ብቻ እንደሚያቀነቅኑ የገለፁት አቶ ኢሳያስ፤ ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ክላስፕላስ ኤቨንት ስፖንሰር ማድረጋቸውንና ሆቴሉም በቅናሽ ዋጋ አዳራሹን በመፍቀዱ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ ከ25 ሺ እስከ 35ሺ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አዘጋጁ ገልፀዋል፡

Read 1401 times