Saturday, 05 August 2017 12:00

(Uterine Prolapse) የማጸን ተፈጥሯዊ ቦታ መዛባት/ መንሸራተት

Written by  በአዲሱ ደረሰ (ኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

በእንግሊዘኛው አጠራር (Uterine Prolapse) የምንለው የማህጸን የተፈጥሮ ቦታውን መልቀቅ እና ወደታች መንሸራተትን ለመግለጽ ያገለግላል፡፡ ይህ የማህጸን የተፈጥሮ ይዘት መዛባት ባስ ካለም በሴቷ ብልት በኩል ወደውጪ እስከመውጣት ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲፈጠርም ማህጸኑ ብቻውን ብቻ ሳይሆን የሴቷን ብልትና የሽንት መቋጠሪያ ከረጢት እና አካባቢው ላይ የሚገኙ አካላትን ይዞ የመውጣት እድል ሊኖረው ይችላል፡፡
ይህ አይነቱ መዛባት በምን ያህል ሴቶች ላይ እንደሚከሰት በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአሜሪካን አገር ውሜንስ ኸልዝ ኢኒሺዬቲቭ በተባለና የሴቶች ጤና ላይ አተኩሮ ከ27 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት፤ ከተሳታፊዎቹ መካከል ችግሩ በ14% በሚሆኑት ላይ እንደታየ ተገልጾአል። በዚያው በአሜሪካን አገር ከ149 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በተደረገ ክትትል ደግሞ፤ ከሴቶቹ መካከል 11% የሚሆኑት መዛባቱን ለማስወገድ የሚደረገውን ቀዶ ህክምና በህይወታቸው አጋጣሚ ማድረጋቸው እንደማይቀር ተተንብዮአል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም በኦክስፎርድ የቤተሰብ እቅድ ማህበር ከ17/ ሺህ በላይ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በተደረገው ክትትል ደግሞ፤ እድሜያቸው ከ25-39/ ከሚሆኑት ሴቶች መካከል በተመሳሳይ ምክንያት ወደሆስፒታል የሚሄዱት ሴቶች ቁጥር ከ100 ሺዎች 21.4/ እንደሚደርስ ይገልጻል፡፡
የማህጸን መንሸራተት የመፈጠር እድሉ ከ100/ ሺህ ሴቶች 16.2/ ይደርሳል ይላል ይኸው ጥናት፡፡ የማህጸን መንሸራተት የሚፈጠርበትን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መመዝገብ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የማህጸን መንሸራተትን ከሌሎች  የመራቢያ አካላት ጋር በትክክል ለይቶ መረዳት አለመቻል ነው ይላል ጽሁፉ፡፡
ችግሩ በኢትዮጲያም እንዳለ ያሳያል አንድ ጅማ ዩንቨርስቲ ላይ መሰረት አድርጎ የተሰራ ጽሁፍ፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ ጥናቱ በተሰራበት 2012 ዓ/ም ከተደረጉ እና ከስነተዋልዶ ጤና ጋር ከተገኛኙ የቀዶ ህክምናዎች መካከል 40% የሚሆኑት ከማህጸን እና የመራቢያ አካላት መንሸራተት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡
ይህ ጥናት በማጠቃለያው በገጠር በሚኖሩ፤ እድሚያቸው በገፋ እና ከዚህ በፊት ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ያለህክምና ባለሞያ እርዳታ የወለዱ ሴቶች ላይ ችግሩ ይበረታል፡፡ ጥናቱ በተጨማሪም ችግሩ ከጥንካሬ ከእድሜ እና ሴቶች ከሚሰሩት ስራ ጋር ይገናኛል ይላል፡፡
የማጸን መንሸራተት ችግር ደረጃዎች አሉት፡- ከደረጃ አንድ እስከ አራት፡፡ ደረጃ አንድ የምንለው የማህጸን መንሸራተት ደረጃ ችግሩ የለም የሚባልበት ሲሆን ደረጃ አራት የምንለው ደግሞ ማህጸን ቦታውን ስቶ ከብልት ውጪ የሚወጣበት ደረጃ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ውሜንስ ኸልዝ ኢኒሺየቲቭ የማህጸን መንሸራተትን የደረጃ እድገት ለማጥናት በ112/ ሴቶች ላይ ክትትል አድርጎ ነበር፡፡ በዚሁ ጥናት መሰረት በተለይ የደረጃ አንድ የማህጸን መንሸራተት ሊሻሻልበት የሚችልበት እድል ከፍተኛ እንደሆነ እና የመባባስ እና ደረጃው የማደጉ እድል ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል። ይህም የማህጸን መንሸራተት ሁል ጊዜ ደረጃው እያደገ እና እየተባባሰ ይሄዳል የሚለውን መላምት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡  
የማህጸን የተፈጥሮ ቦታ መዛባት የሚፈጠርበት ምክንያት አሻሚ ሊሆን ይችላል፡፡ የሴት ልጅ የመራቢያ አካላት እርስ በእርሳቸው የተያያዙና የተደጋገፉ በመሆናቸው መንሸራተቱ የቱ ጋር እንደተፈጠረ በትክክል መገመት የሚያዳግትበት ብዙ አጋጣሚ አለ፡፡ ሆኖም የሴት ልጅ ብልት ደጋፊ አካላትን በቅርበት ማጥናት ምክኒያቱን ለማወቅ ይረዳል፡፡
ለማህጸን የተፈጥሮ ቦታውን መሳት ተጋላጭ የምንሆንባቸው ምክኒያቶች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ብዙ ምክኒያቶች አንድኛው እድሜ ሊሆን ይችላል፡፡ የሴት ልጅ እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተጋላጭነቷም እንዲሁ ይጨምራል፡፡ እያንዳንዱ አስርተ አመታት ሴት ልጅ ለችግሩ ያላትን ተጋላጭነት በእጥፍ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል፡፡
ሌላኛው ምክኒያት ደግሞ በተፈጥሮ ማለትም በምጥ ምክንያት የሚወልዱ ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ችግሩ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ብዙ ልጅ መውለድ ወይንም የተራዘሙ ምጦች የገጠማት ሴት ከአኑዋኑዋሩዋም ባህርይ የተነሳ ለእራስዋ እንክብካቤ የማታደርግ ከሆነች በብልት አካባቢ በደረሰ ጉዳት የተነሳ የማህጸን መንሸራተት ሊገጥማት ይችላል፡፡ በዚህ መልክ ሁለት እና ከዚያ በላይ የወለዱ ሴቶች ልጅ ካልወለዱ ወይም አንድ ብቻ ከወለዱ ሴቶች ጋር ሲነጻጸር ለማህጸን መንሸራተት ያላቸው ተጋላጭነት በ8.4% ጨምሮ እንደተገኘ አንድ ጥናት ያሳያል፡፡
ምንም እኳን በብልት በኩል በምጥ የተደረገ ወሊድ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጥናቶች ቢያሳዩም ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችም አብረው ሊታዩ እንደሚገባ ጥናቱ ያሳስባል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች መካከል ከላይ እንደተገለጸው የተራዘመ ምጥ እና ቤተሰብ ከችግሩ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ወፍራም ሴቶች ወይም የውፍረት-ቁመት ቀመራቸው ከ25-30/ የሚሆኑ ሴቶች ወይም ደግሞ በጣም ወፍራም ሴቶች የውፍረት-ቁመት ቀመራቸው ከ30/ በላይ የሆኑ ሴቶች ላይ የማህጸን መንሸራተት የመፈጠር እድሉ እንደሚጨምር የጠቆመ ጥናት አለ፡፡ ከዘር ጋር በተገናኘም የማህጸን መንሸራተት ያለባቸው ቤተሰቦች ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ እድላቸው እንደሚጨምር ተጠቁሟል፡፡ አንድ ጥናት እንዳሳየው ደግሞ እናታቸው እና እህቶቻቸው ላይ የማህጸን መንሸራተት የታየባቸው ሰዎች ላይ ችግሩ ጨምሮ እንደታየ ገልጾአል፡፡
ማረጥ እና ኤስትሮጅን የተባለውን በሴቷ የሚመነጨውን ሆርሞን ማመንጨት ማቆም ከመራቢያ አካላት መንሸራተት ጋር እንደሚገናኝ የጠቆሙ ብዙ ጥናቶች አሉ፡፡ ሆኖም የውሜንስ ኸልዝ በ270/ ሴቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ከማህጸን መንሸራተት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
የማህጸን መንሸራተት ምልክቶቹ እጅግ አሻሚዎች ናቸው፡፡ አንድ በግልጽ ከማህጸን መንሸራተት ጋር የተገናኘው ምልክት ግን የሴት ልጅ ብልት ከውስጥ ወደ ውጪ የመግፋት አይነት ስሜት መሰማት ነው፡፡ የማህጸን መንሸራተት የለም ከሚባልበት ደረጃ ማህጸን ከብልት ወጥቶ እስከሚታይበት ደረጃ ድረስ ባለው የችግሩ እድገት ምልክቶቹም እንዲሁ እየተወሳሰቡ እንደሚመጡ ምንጭ ያደረግነው ጽሁፍ ያስረዳል፡፡
የማህጸን የተፈጥሮ ቦታ መዛባት ምልክት የሚታይባቸው ሴቶች በቅድሚያ ወደመጀመሪያ ደረጃ የጤና ጣቢያዎች ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በዚያ የሚገኙ ባለሞያዎች አስፈላጊውን ምርመራ ካካሄዱ በኋላ እንደችግሩ ደረጃ ታማሚዎችን ወደ ከፍተኛ ሆስፒታል መላክ ይኖርባቸዋል፡፡
የሚደረገው ምርመራ የማህጸን መንሸራተቱን ደረጃ ለመወሰን እና በዚህም ምክኒያት ተጽዕኖ የደረሰበትን የሴቷን ብልት አካል ቦታ ለመለየት ይረዳል፡፡ በሽተኛዋ በምርመራ ወቅት እረፍት ማድረግ የሚጠበቅባት ሲሆን በምርመራው ወቅትም የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠንንም መለካት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡
ብዙ ጊዜ የማህጸን መንሸራተት ደረጃው እና ምልክቶቹ አብረው ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ ምልክቶቹን በቅርበትና በንቃት መከታተል የመንሸራተቱ ደረጃ  አንድ ከሆነ ሊመከር ይችላል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ደግሞ የማህጸን መንሸራተቱ ደረጃ ምንም ያህል ይሁን ከህክምናው ይልቅ ምልክቶቹን በቅርበት መከታተልን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በየተወሰነው ጊዜ ወደሆስፒታል አየሄዱ ከሃኪሞቻቸው ጋር መማከርን ሊዘነጉት አይገባም፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ወቅት ሲጸዳዱ የተለዩ ምልክቶችን የሚያስተውሉ ሴቶች የሃኪሞቻቸውን ምክር ማገኘታቸው የግድ ይሆናል፡፡
የማህጸን ተሸካሚ አጥንትን ለማጠንከር የሚደረግ የሰውነት እንቅስቃሴ እንደ አንዱ የህክምና አይነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የሽንት መሽናት መዛባትን ስለማስተካከሉ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም የማህጸን መንሸራተትን ለመከላከል ያለው ሚና ግን አሻሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በሁሉም የጽንስና ማህጸን ሃኪሞች ማለት ይቻላል ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው መንገድ ግን በእንግሊዘኛው አጠራር- ፓሳሪ የተባለው የህክምና አይነት ነው፡፡ ይህ የህክምና አይነት በሴቷ ብልት በኩል የሚገባ እና ችግሩን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚለጠጥ ወይም ጠንካራ የሆነ ፕላስቲክ በመክተት ማህጸንን ደግፎ እንዲይዝ ማድረግ ነው፡፡
ሌላኛው የህክምና መንገድ ቀዶ ጥገና ነው፡፡ የቀዶ ሕክምና በማድረግ ሕመምተኛዋን ማከም በብዙ አገሮች የሚመረጥ ነው፡፡ ነገር ግን  የዚህ መንገድ ብቸኛው ችግር የቀዶ ህክምና ከተሰራ በኋላ ተከትሎ የሚመጣው የብልት ግድግዳ መንሸራተት ስለሆነ በዚህ ረገድ የህክምና ባለሙያዎችም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ታካሚዎችም በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር በጥንቃቄ መተግበር ገባቸዋል፡፡ 

Read 1764 times