Saturday, 07 April 2012 08:12

ፖለቲካችን በአንድ ዲጂትም አላድግ ብሎናል!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

የአዳራሽ ምህዳርም እየጠበበ ነው!

የዛሬ ፖለቲካዊ ጨዋታችንን አሃዱ የምንለው በሩሲያ ሥሪት ቀልድ ነው፡፡ ምነው… ልማታዊ መንግስታችን እኮ ወዳጅነቱ ከቻይና እንጂ ከሩሲያ አይደለም፡፡ በርግጥ ሩሲያም ብትሆን የቀድሞ ፍሬንዳችን ነበረች! (ጥሎብን ፍሬንዶቻችን ኮሙኒስቶች ናቸው!) አሁን ነገር መቆስቆሱን ትተን በቀጥታ ወደ ቀልዳችን፡፡ በወህኒ ቤት ውስጥ ሁለት የእስር ጓደኛሞች ተመክሮአቸውን ይጋራሉ - እዚያው ሩሲያ ውስጥ፡፡ አንደኛው ታሳሪ ሌላኛውን “በምን ምክንያት አሰሩህ? ፖለቲካዊ ነው ተራ ወንጀል?” ይጠይቀዋል፡፡ “ፖለቲካዊ ነው እንጂ!” ይልና በኩራት ማብራራት ይጀምራል፡፡ “አየህ እኔ የቧንቧ ሠራተኛ ነኝ፡፡ አንድ ቀን የግዛቱ የፓርቲ ኮሚቴ የፍሳሽ መውረጃ ቱቦውን እንድጠግንላቸው ጠሩኝ፡፡ እኔም ሁሉ ነገሩን ከተመለከትኩኝ በኋላ፤ “መላ ሲስተሙ ከላይ እስከ ታች በአዲስ መተካት አለበት” ብዬ ነገርኳቸው፡፡ እነሱም ወዲያ ወዲህ ሳይሉ 7 ዓመት እስር አከናነቡኝ” እሱም እኮ አበዛው! (በሩስያኛ ቅኔ እየተናገረ እኮ ነው)

አንድ ሌላ ቀልድ ብደግማችሁ ምን ይላችኋል? በሳይንስ ባይረጋገጥም ቀልድ ጤናዊ ጠቀሜታዎች ሊኖረው እንደሚችል መገመት ሃጢአት አይደለም (ደሞ እኮ የሩሲያ ስሪት ነው ብለናል) እንግዲህ የሩሲያ ኮሙኒስት ፓርቲ የአባልነት ማመልከቻ ሲቀርብ አመልካቹ ከሚጠየቃቸው ጥያቄዎች አንዱ “ለሶቭየት ባለሥልጣናት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?” የሚል ነው፡፡ አንዱ አመልካች “ልክ እንደሚስቴ ነው የማያቸው!” ሲል መለሰ፡፡ “እስቲ አብራራው!” ተብሎ ተጠየቀ (ጉድ ፈላ!) “በመጀመሪያ ደረጃ - አፈቅራታለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ - እፈራታለሁ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ - ሌላ ሚስት ቢኖረኝ ብዬ እመኛለሁ”

መቼም … ይሄን የተናገረ ሰውዬ በሩሲያ ምድር በህይወት እንደማይኖር እወራረዳለሁ! እኔ የምለው ግን… እዚህ ጦቢያ አንድ ዜጋ የኢህአዴግ አባል ለመሆን ሲያመለክት ምን ዓይነት ጥያቄዎች ነው የሚቀርብለት? “ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ያለህ አመለካከት ምን ይመስላል?” ይባል ይሆን? (ድንገት አባልነት ከነሸጠኝ ብዬ እኮ ነው!) ምስጢር እናውቃለን የምትሉ ወሮታውን ስለምከፍል ሹክ በሉኛ! (ለመረጃ እኮ ነው!)

እንግዲህ የሰው አገር ሁልጊዜዋ የሰው ነውና ከሩሲያ ውልቅ ብለን እንውጣና ወደ ጦቢያችን የፖለቲካ “የጨረባ ተስካር” እንግባ!

አንዳንዴ ግራ ግብት የሚለኝ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ኢኮኖሚው በ3 ዲጂት ለማደግ እያኮበኮበ …ለምንድነው ፖለቲካችን በአንድ ዲጂት እንኳን አላድግ ያለው? (ፈጣሪና ኢህአዴግ ይወቁት!)

እኔ የምለው…ከሳምንቱ አብይ ክስተቶች ትኩረቴን የሳበው የትኛው እንደሆነ ታውቃላችሁ? የባለሥልጣናትና የአርቲስቶች ቡድን ባለፈው እሁድ በአ.አ ስቴዲየም ያደረጉት ግጥምያ ነው፡፡ (የምርጫ ግጥምያ አልወጣኝም! የእግር ኳስ ነው!) የምርጫ ግጥሚያ ቢሆንማ የኢህአዴግ ቡድኖች በከባድ ግምገማ ታምሶ ነበር (3ለ0 ማለት እኮ በዝረራ ነው!) ይሄኛው ግን ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ግንባታ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተከናወነ ግጥምያ ስለሆነ ዋናው ጉዳይ ውጤቱ አይደለም - ሂደቱ እንጂ!

አንዲት ዋዘኛ የአዲሳቤ ልጅ የዛኑ ዕለት ምን አለች መሰላችሁ? ኢህአዴግ አመሻሽ ላይ (3 ሰዓት ግድም ማለቷ ነው) መግለጫ መስጠቱ አይቀርም አለችን፡፡ ምን ዓይነት መግለጫ ስንላት “አርቲስቶች አሸነፉ ቢባልም በአጠቃላይ ውጤት ግን የባለስልጣናት ቡድን አቸንፏል!” የሚል አለችን፡፡ (ልብ አድርጉ “አቸንፏል” ነው!)

ልጅቷ ከሁሉም ያስደነቀችኝ በምን መሰላችሁ? የኢህአዴግን የክት ቃል ማወቋ ነው (ቡዳም አያውቀውም እኮ!) የክት ቃሏን አወቃችኋት አይደል … “አቸንፏል!” የምትለዋን ማለቴ ነው፡፡ አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት ኢህአዴግ “አቸንፈናል!” የሚል ቃል ከአንደበቱ ከወጣ በአንድ ነገር ክፉኛ በግኗል ማለት ነው፡፡ (የ97ቱ ናዳ ዓይነት!) አንዳንድ ኳስ ሳይሆን ፖለቲካ ላይ የሙጥኝ ያሉ የመዲናችን አራዶች ደግሞ የባለስልጣናቱን ሽንፈት የብቃት ማነስ ነው ብለው ነገርዬውን አከረሩት፡፡ በዚህ ቢበቃቸው ደግሞ ጥሩ ነበር፡፡ ባለስልጣናቱ በኳስ ያስመዘገቡት ውጤት የመንግስት ኃላፊነታቸው ነፀብራቅ ነው ብለው ደመደሙት! (ማን ሊሰማቸው!)

የአዲሳቤዋ ልጅ ስለባለስልጣናቱ ቡድን ያለችውን ተናግሬ አልጨረስኩም እኮ … “በዜና ላይ በሱፍ የሰለቹንንን፣ በቁምጣ በኳስ አመጡብን!” አትል መሰላችሁ! (መቼም ሌላ ነገር ለማለት ፈልጋ መሆን አለበት!) በዚህ አባባል እንኳን እኔ አልስማማም፡፡ ለለውጥም ቢሆን (ለእኛም ለእነሱም) አንዳንዴ በቁምጣ ብናያቸው አይከፋም እኮ!

ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ኢንተርቪው የተደረጉት የ”አንጋፋው” ኢዴፓ ሊ/መንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፤ ለኢህአዴግ ልክ ልኩን ነገሩት አይደል! (ያውም Loyal party እየተባሉ!) በሌላ ነገር እንዳይመስላችሁ በሥልጣን ጉዳይ ነው!! ኢህአዴግ 40 ዓመት መግዛት እፈልጋለሁ ቢል ችግር የለውም ያሉት አቶ ሙሼ፤ ችግር የሚመጣው 40 ዓመት እገዛለሁ ብሎ የደመደመ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ (ደመደመ እንዴ?) አያችሁ… 40 ዓመት መግዛት እፈልጋለሁ ማለት ምኞት ስለሆነ ችግር የለውም - ሊ/መንበሩ እንዳሉት! ደግሞም ህገመንግስታዊ መብቱ ነው! (ግን ስለምኞት ህገመንግስቱ ላይ ተፅፏል እንዴ?) የኢዴፓው ሊ/መንበር ሲቀጥሉ፤ ኢህአዴግ 40 ዓመት እገዛለሁ ሲል ግን አምባገነንነት ነው! በማለት አስረድተዋል፡፡ አያችሁልኝ….የ”እፈልጋለሁ” እና የ”እገዛለሁ” ልዩነትን!

ወዳጆቼ፡- የስብሰባ አዳራሽን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ወጣ እንዴ? … ለምንድነው ታዲያ አንዳንድ ሆቴሎችና አዳራሽ አለን የሚሉ ኢንተርፕራይዞች ገንዘብ ተቀብለው አዳራሽ ካከራዩ በኋላ “ገንዘባችሁን ውሰዱ!” የሚሉት?

በመሰብሰቢያ አዳራሾች ላይ የወጣ አዋጅም ካለ እኮ ለውይይት መቅረብ ነበረበት (እንደሊዙ አዋጅ!) ጠ/ሚኒስትሩ ከፓርላማው ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ከአቶ ግርማ ሰይፉ ስለ አዳራሽ ችግር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምን ነበር ያሉት?

“የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ ልንነጋገርበት እንችላለን..እኛ ግን አዳራሽ አናከራይም” ያሉ መሰለኝ እኔ የምለው … የእሁዱ የባለስልጣናትና የአርቲስቶች ግጥምያ ላይ የአትሌት ሃይሌ ዳኝነት እንዴት ነበር? አንዳንዶች ግን ሲተርቡት ሰምቻለሁ፡፡ ተመቸኝ ብሎ ቀይ ካርድ ሲስብ ነው የዋለው … ምናምን በሚል፡፡ (ሥራ አይደለም እንዴ!) እኔ ግን ምን ተመኘሁ መሰላችሁ? ኃይሌ የምር ዳኛ ቢሆን አልኩ! (የሥልጣን ዳኛ ማለቴ እኮ ነው!) በስመዓብ! የጠ/ሚኒስትሩን አላውቅም እንጂ አንድም የመንግስት ባለስልጣን አይተርፈውም ነበር! የአፈፃፀም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብንም ሲሉ - ቀይ ካርድ! የአቅም ችግር አለባቸው ለተባሉት - ቀይ ካርድ! በሙስና ለተነካኩት - ቀይ ካርድ! ቢፒ አር ኢላማውን ስቷል ሲሉ - ቀይ ካርድ ያሽርልኝና አንጀቴ ቅቤ ይጠጣ ነበር፡፡ ያን ጊዜ መንግስት የሚያሳትመው ብር ሳይሆን ቀይ ካርድ ይሆን ነበር፡፡

እኔ የምላችሁ…ይሄ የአዳራሽ ጉዳይ መድረክን በጠበጠው አይደለም እንዴ? አሁን እኮ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል ብቻ ሳይሆን የአዳራሹ ምህዳርም ጠቧል ለማለት እየተገደድን ነው (ይሄን እንኳን “መድረክ” ቢናገረው ይሻላል!) እውነቴን እኮ ነው የስብሰባ ፈቃድ የሚሰጠው አካል ፈቃድ ከሰጠ በኋላ የምን አዳራሽ መከልከል ነው! ምናልባት ግን የገዢው ፓርቲ ጨቅላ ካድሬዎች የሞኝ ሥራ እንዳይሆንና “ልማታዊ መንግስታችንን” ለአጓጉል ትችት እንዳይዳርጉብን!! ወይም እኮ ለተቃዋሚ ፓርቲ አዳራሽ አናከራይም ቢሉ የአባት ነው! መድረክም ቁርጡን አውቆ የመሰብሰቢያ ቦታ በሊዝ ይገዛ ነበር (ለሊዝ አዋጅ ስብሰባ ማለት ነው)በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ህዳሴው ግድብ ከዜጐች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የነበሩ “ብዥታዎች”ን ስላጠሩልን ምስጋና ይገባቸዋል (ሥራቸው ቢሆንም) በዚሁ መሰረት የህዳሴውን ግድብ መቃወም መብት ነው ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ (ዲሞክራሲ ለዘላለም ይኑር!) ለህዳሴው ግድብ ዜጐችን በግድ አዋጡ ማለት ወንጀል ነውም ብለዋል፡፡ (ከዚህ በኋላ ማጭበርበር የለም!)

ትንሽ ቅር የሚያሰኘው ግን ምን መሰላችሁ? ይሄንን ለማወቅ አንድ ዓመት መጠበቃችን ብቻ ሳይሆን ለዚህም ጠ/ሚኒስትሩ መጠበቃቸው ነው! (እቺም ቁም ነገር ሆና!) እንዴ እሳቸው የኑሮ ውድነቱ የሚቃለልበትን መንገድ እንዲያስቡ ለምን ፋታ አንሰጣቸውም?! ስለ ሊዝ አዋጅ ማብራሪያ ለመስጠት - ጠ/ሚኒስትሩ! ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ለመናገር - ጠ/ሚኒስትሩ! (ኧረ ሁሉም ሥራውን ይስራ!)

የፖለቲካ ጨዋታችንን ከመቋጨታችን በፊት በፈጣን ጀት እንደገና ወደ ሩሲያ እንበርና አንድ ሁለት ቀልዶችን ላፍ አድርገን እንመለሳለን፡፡ የሶቭየት ህብረት ኮሙኒስት ፓርቲ አንደኛ ፀሐፊ የነበሩት ጓድ ክሩስቼቭ የዓሳማ ማርቢያ ሥፍራን ሲጐበኙ ጋዜጠኛ ፎቶግራፍ ያነሳቸዋል፡፡ በጋዜጣው ቢሮ ውስጥ ታዲያ ከፎቶግራፉ ሥር በሚፃፈው መግለጫ (Caption) ዙሪያ ሞቅ ያለ ውይይት ሲካሄድ ቆየና የተለያዩ ሃሳቦች ቀረቡ፡፡

“ጓድ ክሩስቼቭ በዓሳማዎች መሃል”፣ “ጓድ ክሩስቼቭ እና አሳማዎች”፣ “ዓሳማዎች በጓድ ክሩስቼቭ ዙሪያ” ሁሉም ውድቅ ተደረጉ - እንዴት ክሩስቼቭን ከዓሳማ ጋር ደምረን እንጠራለን በሚል፡፡ በመጨረሻ ኤዲተሩ የራሱን ካፕሽን ጻፈ:- “በስተግራ በኩል ሦስተኛው - ጓድ ክሩስቼቭ” በማለት፡፡

ሩሲያ ድረስ ወስጃችሁ በእነ ሌኒን ላይ የተኮመከ ነገር ሳትሰሙማ አትመለሱም፡፡

ስታሊን ወደ ሌኒን ቢሮ ጐራ ይልና፤ “ቭላድሚር ኢሊች፤ አንድ ደርዘን ኮሙኒስቶች እንዲገደሉ ትፈቅድልኛለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡

“ለፓርቲው የሚጠቅም ከሆነ እንዴታ?!” በማለት ሌኒን መለሰ፡፡

“ቭላድሚር ኢሊች፤ አስፈላጊ ከሆነ አንድ መቶ ኮሙኒስቶችን ብንገድልስ?”

“አስፈላጊ ከሆነ ጥርጥር የለውም!”

“ቭላድሚር ኢሊች፤ አስፈላጊ ከሆነ አንድ ሺ የፓርቲ አባላትን ብንገድልስ?”

“የግድ ከሆነ አዎ!”

“ቭላድሚር ኢሊች፤ ሁኔታዎች የሚያስገድዱን ከሆነ አንድ ሚሊዮን የፓርቲ አባላትን እንግደል?”

“አሁን ትናንሽ ነገሮችን እያካበድክ ነው ብለን በጓዳዊነት ልንገመግምህ እንችላለን” አለው ሌኒን ስታሊንን፡፡

ከዚህ በላይ ቆይታ አድርገን የሩሲያ ቀልዶችን የበለጠ ብናጣጥም ትንሽ ዘና እንደምንል ጥርጣሬ የለንም፡፡ የፍላይት ሰዓት በመድረሱ ግን ይብቃን!! የሳምንት ሰው ይበለን!!

 

 

 

Read 3247 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:24