Sunday, 06 August 2017 00:00

ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግምት በተሰጠበት የዓለም ሻምፒዮና

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   • 7.3 ሚ ዶላር የሽልማት ገንዘብ ተዘጋጅቷል፡፡
         • ከ660 ሺ በላይ ትኬቶች ተሸጠው ሪከርድ ተመዝግቧል፡፡
         • ብሬንዳን ፎስተርና ፖል ቴርጋት ልዩ የክብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
         • ቦልት፤ ሞ ፋራህ እና ጥሩነሽ የመጨረሻ ተሳትፏቸውን ያደርጋሉ፡፡
         • ጥሩነሽ 6ኛዋን የወርቅ ሜዳልያ በ10ሺ ሜ እንደምታገኝ ብዙ ሲገመት፤ ለኢትዮጵያ ሌላ የወርቅ ሜዳልያ የተጠበቀው በወንዶች ማራቶን ብቻ ነው፡፡
         • ገንዘቤ በ1500 ሜትር ፤ አልማዝ አያና በ5 ሺ ሜ፣ እንዲሁም ማሬ ዲባባ በማራቶን የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ፡፡ የአትሌቲክስ    ዊክሊእና የትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያዎች
     16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን ከተማ በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታድዬም ትናንት ተጀምሯል። 205 አገራትን የሚወክሉ 2000 አትሌቶች ለ10 ቀናት በሚካፈሉበት ሻምፒዮናው 7.3 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ተዘጋጅቷል፡፡ በሽልማቱ ዝርዝር አከፋፈል መሰረት ለወርቅ ሜዳልያ 60ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ ዶላር እንዲሁም ለነሐስ ሜዳልያ 20ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆን ለአራተኛ ደረጃ 15ሺ ዶላር፤ ለአምስተኛ ደረጃ 10ሺ ዶላር፤ ለስድስተኛ ደረጃ 6ሺ ዶላር፤ ለሰባተኛ ደረጃ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለስምንተኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚበረከት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በሻምፒዮናው ላይ አዲስ የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች የውድድሩ አብይ ስፖንሰሮች ቲዲኬ 100ሺ ዶላር እንዲሁም በተጨማሪ ቶዮታ 100ሺ ዶላር እንደሚሰጡ ታውቋል። ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደውና የዌስትሃም ክለብ ሜዳ የሆነው የኦሎምፒክ ስታድዬም በ563 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ነው፡፡
ለ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  1.04 ሚሊዮን ስታድዬም የመግቢያ ትኬቶች ለገበያ ቀርበው ከ660 ሺ በላይ የተሸጡ ሲሆን ይህም በ2009 እኤአ ላይ በበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ417, 156 የተመዘገበውን የትኬቶች ሽያጭ ክብረወሰን ያሻሻለ ሆኗል፡፡
በሻምፒዮናው ዋዜማ ላይ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር 51ኛው የኮንግረስ ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን ከ200 በላይ አገራት ተሳትፈውበታል፡፡ በዚሁ ጉባኤ ላይ ለታዋቂው እንግሊዛዊ የረጅም ርቀት ሯጭ እና፤ የታላቁ ሩጫ ኩባንያ በእንግሊዝ መስራች ብሬንዳን ፎስተር የአይኤኤኤፍ ‹‹ጎልደን ኦርደር ኦፍ ሜሪት›› ፤ ለኬንያዊው የረጅምር ርቀት ሯጭ ፤ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ፖል ቴርጋት ደግሞ የአይኤኤኤኤፍ ‹‹ፕላግ ኦርደር ኦፍ ሜሪት›› ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡
በዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመጨረሻ ግዜ በመሳተፍ ልዩ  ትኩረት ከሳቡት መካከል ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት፤ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ፤ እና ኢትዮጰያዊቷ ጥሩነሽ ዲባባ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኩ 11 የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰበው ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ከለንደን የዓለም ሻምፒዮና የመጨረሻ ተሳትፎው በኋላ ጡረታ ለመውጣት መወሰኑ ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡
ቦልት በዓለም ሻምፒዮናው ለመጨረሻ ጊዜ በ100 ሜትር እና በ4 በ100 ሜትር ውድድሮች በመሳተፍ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ማግኘት ከቻለ በሻምፒዮናው ታሪክ በአጭር ርቀት 13 የወርቅ ሜዳልያዎች በመጎናፀፍ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን የሚያስመዘግብ ይሆናል፡፡ ዩሴያን ቦልት በሩጫ ዘመኑ  60 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ያካበተ ሲሆን በውድድር ያገኛቸው ሽልማቶች እስከ 2.24 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ዘ ቴሌግራፍ በሰራው ትንታኔ ዩሴያን ቦልት አብዛኛውን ገቢ የሚያገኘው ከስፖንሰሮቹ ሲሆን በተለይ እስከ 2025 እኤአ ከፑማ ኩባንያ ጋር በፈፀመው ውል በየዓመቱ የሚከፈለው 3.1 ሚሊዮን ዶላር ትልቁ ገቢው ነው። ጋቶርዴ፤ ሁብቦልት፤  ቨርጂን ሚዲያ፤ ቪዛ ካርድ እና ኒሳን ሞተርስ ሌሎች የአትሌቱ ስፖንሰሮች ናቸው። የዩሲያን ቦልትን የአትሌቲክስ ገቢ ቴሌግራፍ ሲያሰላ በዓለም ሻምፒዮና 728ሺ ዶላር እንዲሁም 23 ጊዜ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን በማሸነፍ 210ሺ ዶላር ማግኘቱን ጠቅሶ በ2009 እኤአ በርሊን ባስተናገደችው 11ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 2 የዓለም ሪከርዶችን በ100 ሜትር 9.58 ሰከንዶች እንዲሁም በ200 ሜትር 19.19 ሰኮንዶች ሲያስመዘግብ የወሰደው 200ሺ ዶላር የሪከርድ ቦነስ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል የ34 ዓመቱ እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጨረሻውን ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን በሶስት ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ በታሪክ የመጀመርያው አትሌት ለመሆን አነጣጥሯል፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ለስድስተኛ ጊዜ የምትሳተፈው ጥሩነሽ ዲባባ 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ10ሺ ሜትር በመሳተፍ ማስመዝገቧ አዲስ የታሪክ ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በታዋቂዎቹ የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፆች ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ እና አትሌቲክስ ዊኪሊ ድረገፆች ለ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተዘጋጅተው  የወጡ የሜዳልያ ትንበያዎች ለኢትዮጵያ ዝቅ ያለ ግምት ሰጥተዋል፡
ከ1 ሳምንት በፊት ተሻሽሎ የተሰራጨው የትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ እንዲሁም የአትሌቲክስ ዊክሊ  የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች ዝርዝር ግምት እንዲሁም ያለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የውጤት ታሪክ፤ የውድድር ፕሮግራሞች እና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
በ800 ሜትር
ለኢትዮጵያ የተሰጠ የሜዳልያ ግምት የለም
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች (1 የወርቅ ሜዳልያ በወንዶች)
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች ሐብታም አለሙ፤ ኮሬ ቶላ ፤ ማህሌት ሙሉጌታ(በሴቶች) እንዲሁም  መሃመድ አማን (በወንዶች) ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ብቸኛው ውጤት በወንዶች የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ድል በ2013 እኤአ ላይ በሞስኮ ያስመዘገበው መሃመድ አማን ነው፡፡ አትሌቲክስ ዊኪሊ በሰራው ትንብያ በወንዶች ምድብ የወርቅ ሜዳልያው ለኬንያዊው ኢማኑዌል ኮሪር፤ የብር ሜዳልያው ለቦትስዋናው ኒጄል አሞስ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለኬንያው ኪፕዮጌ ቤት የተገመተ ሲሆን በሴቶች ምድስብ ደግሞ የወርቅ ሜዳልያው ለደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያ፤ የብር ሜዳልያው ለብሩንዲዋ ፍራንኪሶ ኒኮሻ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለአሜሪካዋ አጄ ዊልሰን ተሰጥቷል፡፡
ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለሴቶች የሰራው ትንበያ ከአትሌቲክስ ዊክሊ ጋር የተመሳሰለ ሲሆን በወንዶች ግን የወርቅ ሜዳልያው ለቦትስዋናው ኒጄል አሞስ፤ የብር ሜዳልያው ለኢማኑዌል ኮሪር እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለኬንያው ኪፕዮጌ ቤት ነው የተገመተው፡፡
በ1500 ሜትር
የዓለም ሻምፒዮንና የዓለም ሪከርድ ባለቤት ገንዘቤ የነሐስ ሜዳልያ ተገምቶላታል
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች በሴቶች 1 የወርቅ ሜዳልያ ፤ በወንዶች 1 የብር ሜዳልያ
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች በሴቶች ገንዘቤ ዲባባ (ሻምፒዮን)፤ ጉዳፍ ፀጋዬ፤ በሱ ሳዶና  ፋንቱ ወርቁ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ አማን  ወጤ፤  ሳሙኤል ተፈራና ተሬሳ ቶሎሳ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ2015 እኤአ በቤጂንግ ያስመዘገበችው በሴቶች ገንዘቤ ዲባባ ናት፡፡ በወንዶች ደግሞ ብቸኛውን ውጤት በ2009 እኤአ በርሊን ላይ ደረሰ መኮንን በብር ሜዳልያ አስመዝግቦታል፡፡ አትሌቲክስ ዊኪሊና ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በሰሩት ትንበያ የሜዳልያ ውጤቶቹን በወንዶች ምድብ ለኬንያውያን ሙሉለሙሉ ሰጥተዋል። በሴቶች ደግሞ የወርቅ ሜዳልያውን ለኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዮጌ፤ የብር ሜዳልያውን ለባህሬኗ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሲፋን ሃሰን እንዲሁምየነሐስ ሜዳልያውን ለገንዘቤ ዲባባ አትሌቲክስ ዊክሊ ሲገምት ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ደግሞ የወርቅ ሜዳልያውን ለባህሬኗ ሲፋን ሃሰን ሰጥቶ የብር ሜዳልያውን ለኬንያው ፌዝ ኪፕዮጌ በመገመት ገንዘቤ ዲባባን ለነሐስ ሜዳልያ ጠብቋታል፡፡
በ3ሺ ሜ. መሰናክል
ለኢትዮጵያ የተሰጠ የሜዳልያ ግምት የለም
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች በሴቶች 1 የብር 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች በሴቶች ሶፍያ አሰፋ፤  እቴነሽ ዲሮና ብርቱካን ፈንቴ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ ጌትነት ዋሴ፤ ታፈሰ ሰቦቃና ተስፋዬ ድሪባ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3ሺ ሜትር መሰናክል በሁለቱም ፆታዎች  የወርቅ የሜዳልያ ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም፡፡ በ2013 እኤአ  በሞስኮ ሲካሄድ በሴቶች የብር እና የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ አትሌቲክስ ዊክሊና ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በሁለቱም ፆታዎች የሜዳልያ ግምቱን ለኬንያውያን ሰጥተዋል፡፡
በ5ሺ ሜትር
በሴቶች ሪከርድ ሊሰበር እንደሚችል፤ የወርቅ ሜዳልያው በኬንያ እንደሚነጠቅ ቢገመትም፤ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከ1 እስከ 3 ተጠብቋል፡፡
በወንዶች ትልቁ ግምት ለሙክታር ኢድሪስ የተሰጠው የብር ሜዳልያ ነው፡፡
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች  በሴቶች  5 የወርቅ ፤ 1 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎች በወንዶች 1 የወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች በሴቶች ሻምፒዮናነቷን ለማጠበቅ የምትሰለፈው አልማዝ አያና፤ ገንዘቤ ዲባባ፤  ሰንበሬ ተፈሪና  ለተሰንበት ግደይ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ ሙክታር እድሪስ፤  ሰለሞን ባረጋ፤ ዮሚፍ ቀጄልቻና በዳይመንድ ሊግ አሸናፊነቱ በቀጥታ መሳተፍ የሚችለው ሃጎስ ገ/ህይወት ናቸው፡፡ በዚህ ርቀት 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አዲስ የዓለም ሪከርድ ሊመዘገብ እንደሚችል በርካታ ዘገባዎች ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያኑ ሴት አትሌቶች ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና ከመሳተፋቸው ጋር ተያይዞ ነው፡፡  በ5ሺ ሜትር ሴቶች ፍፁም የበላይነት ያላት ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳልያዎችን መውሰድ የቻለች ሲሆን በተሳትፎ ታሪኳ ከወንዶች እጅግ የላቀ ውጤት አላት፡፡ በ15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በሴቶች  5 የወርቅ ፤ 1 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች። በ1999 እና በ2001 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለት ተከታታይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አየለች ወርቁ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በማግኘት ፈርቀዳጅ ነበረች፡፡ ከዚያም በ2003 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ መሰረት ደፋር የብር እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር የወርቅ፤ በ2009 እና በ2011 እኤአ መሰረት ደፋር ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በ2013 እኤአ ላይ  መሰረት ደፋር የወርቅ እንዲሁም አልማዝ አያና የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በ2015 እኤአ ደግሞ አልማዝ አያና የወርቅ ሰንበሬ ተፈሪ የነሐስ ሜዳልያዎችን ማግኘት ችለዋል።  በወንዶች 5ሺ ሜትር በሻምፒዮናው ታሪክ ከአንድ ጊዜ በላይ የወርቅ ሜዳልያው ለማግኘት ለኢትዮጵያ ለማግኘት ሳይቻል  ቆይቷል፡፡ የመጀመርያው የሜዳልያ ውጤት የተመዘገበው በ1991 እኤአ ላይ በፊጣ ባይሳ በተገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በ1993 እኤአ ላይ ሃይሌ ገብረስላሴ የብርና ፊጣ ባይሳ የነሐስ፤ በ2001 እኤአ ላይ ሚሊዮን ወልዴ የብር፤ በ2003 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ደጀን ገብረመስቀል እንዲሁም በ2013 እኤአ ደጀን ገብረመስቀል  የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በ2015 እኤአ ደግሞ ሐጎስ ገብረህይወት የብር ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ወንዶች ለኢትዮጵያ ያስመዘገቡት በወንዶች 1 የወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች ብቻ ናቸው፡፡
አትሌቲክስ ዊከሊና ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በሰሯቸው የሜዳልያ ትንበያዎች በሁለቱም ፆታዎች ተመሳሳይ ሆነዋል፡፡ በሴቶች የወርቅ ሜዳልያውን ኬንያዊቷ ሄለን ኦቡሪ እንደምትወስድ ገምቶ የብር ሜዳልያውን ለገንዘቤ ዲባባ የነኘስ ሜዳልያውን ደግሞ ለአልማዝ አያና ሲሰጥ፤ በወንዶች ደግሞ የወርቅ ሜዳልያው ለሞ ፋራህ፤ የብር ሜልያው ለሙክታር ኢድሪስ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያ ለአሜሪካው ፖል ቼሌሞ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
በ10ሺ ሜትር
የአልማዝና የጥሩነሽ ፍጥጫ እንዲሁም ብቸኛው የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ በሴቶች ተጠብቋል፡፡
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች በሴቶች 6 የወርቅ፣ 6 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች በወንዶች 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች በሴቶች የዓለም ሪከርድ የያዘችውና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ አልማዝ አያና፤ የምንግዜም የረጅም ርቀት ምርጥ ሯጭ ጥሩነሽ ዲባባ እና  ደራ ዲዳ ሲሆኑ በወንዶች አባዲ ሃዲስ፤ ጀማል ይመርና  አንዱአምላክ በልሁ ናቸው፡፡
በርግጥ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዋንኛው የኢትዮጵያ የበላይነት   በ10ሺ ሜትር እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱ 15 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ ሜዳልያ በወንዶች እንዲሁም 5 የወርቅ ሜዳልያ በሴቶች በማግኘት ተሳክቶላታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1993 እኤአ በኃይሌ ገብረስላሴ በተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1995፣ በ1997 እና በ1999 እኤአ ላይ ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ የተጎናፀፈውም ራሱ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ ተጨማሪ የብር ሜዳልያ ወስዷል፡፡ በ2001 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ የብርና ኃይሌ ገብረስላሴ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ የብርና ስለሺ ስህን የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እና ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ቀነኒሳ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ኢብራሂም ጄይላን የወርቅ እና ኢማና መርጋ የነሐስ ሜዳልያዎችን እንዲሁም በ2013 እኤአ ኢማና መርጋ የነሐስ ሜዳልያ በመሰብሰብ የኢትዮጵያን የበላይነት ለረጅም ጊዜ አስጠብቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር በወንዶች 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች ማለት ነው፡፡ በ2013 እኤአ እና በ2015 እኤአ በሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳልያዎቹን ከኢትዮጵያ የነጠቀው ሞፋራህ ነው፡፡ በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር ሴቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1995 እኤአ ደራርቱ ቱሉ በተጎናፀፈችው የብር ሜዳልያ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ ጌጤ ዋሚ የወርቅ፤ በ2001 እኤአ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ብርሃኔ አደሬ የወርቅ እና ወርቅነሽ ኪዳኔ የብር፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2009እኤአ መሰለች መልካሙ የብርና ዉዴ አያሌው የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር ከ4 አመት በፊት ምንም አይነት የሜዳልያ ውጤት ባይኖራትም በ2013 እኤአ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ክብሩን መልሳለች፡፡ በላይነሕ ኦልጅራ ደግሞ ነሐስ ወስዳ ነበር፡፡ ይሁንና በ2015 እኤአ ኬንያ የወርቅ ሜዳልያ ነጥቃለች፡፡የብር ሜዳልያ የወሰደችው ደግሚ ገለቴ ቡርቃ ነበረች፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 15 የዓለም ሻምፒዮናዎች በሴቶች 10ሺ ሜትር 6 የወርቅ፣ 6 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝታለች፡፡
አትሌቲክስ ዊክሊ በሰራው ትንበያ በወንዶች የወርቅ ሜዳልያ ለሞ ፋራህ፤ የብር ሜዳልያው ለጄፍሪ ኪዋሪር እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለአባዲ ሃዲስ ሲገመት በሴቶች የወርቅ ሜዳልያው ለጥሩነሽ ዲባባ፤ የብር ሜዳልያው ለአልማዝ አያና እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለማትሰለፈው ገለቴ ቡርቃ ተጠብቋል፡፡ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በበኩሉ በወንዶች የወርቅ ሜዳልያውን በተመሳሳይ ለሞ ፋራህ ሰጥቶ የብር ሜዳልያውን ለአባዲ ሃዲስ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያውን ለኬንያው ቤዳን ሙቹሪ ሲጠብቅ በሴቶች ደግሞ የወርቅና የብር ሜዳልያውን ጥሩነሽ ዲባባ እና አልማዝ አያና እንደሚያሸንፉ በመገመት የነሐስ ሜዳልያውን ለኬንያዋ አሊስ ንዋንዋ ሰጥቷታል፡፡
በማራቶን
በሴቶች ለኢትዮጵያ ከወርቅ ውጭ፤ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ
ለታምራት ቶላ የወርቅ ሜዳሊያ ድል ብዙ ግምት አለ
ባለፉት 15 ሻምፒዮናዎች በሴቶች 1 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች በወንዶች 1 የወርቅ 2 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች
በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች በሴቶች ማሬ ዲባባ (ሻምፒዮን)፤ ብርሃኔ ዲባባ፤ ሹሬ ደምሴና  አሰለፈች መርጋ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ ታምራት ቶላ፤  ፀጋዬ  መኮንንና  የማነ ፀጋዬ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ብቻ አስመዝግባለች፡፡ በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ የመጀመርያ የሜዳልያ ድሏን በመጀመርያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1983 እኤአ ላይ ያገኘችው ከበደ ባልቻ ባስመዘገበው የብር ሜዳልያ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2001 እኤአ ላይ ገዛሐኝ አበራ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል አስመዘግቧል። በ2009 እኤአ በፀጋዬ ከበደ ፤በ2011 እኤአ በፈይሳ ሌሊሳ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች፤  በ2013 እኤአ ሌሊሳ ዴሲሳ የብር ሜዳልያ እንዲሁም በ2015 በየማነ ፀጋዬ የነሐስ ሜዳልያ ተገኝቷል ፡፡በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው የመጀመርያ የሜዳልያ ድል በ2009 እኤአ ላይ አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው የነሐስ ሜዳልያ ሲሆን በ2015 እኤአ ላይ ማሬ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያ ወስዳለች፡፡
 አትሌቲክስ ዊክሊ  በሰራው ትንበያ በወንዶች ማራቶን የኬንያ ዋንጂሩ የወርቅ ሜዳልያውን እንደሚወስድ ተገምቶ ታምራት ቶላ የብር ሜዳልያ እንዲሁም ፀጋዬ መኮንን የነሐስ ሜዳልያዎች እንደሚያገኙ የተጠበቀ ሲሆን በሴቶች ኤድና ኪፕላጋት ከኬንያ የወርቅ ሜዳልያውን እንደምታሸንፍ እንዲሁም ብርሃኔ ዲባባ እና ማሬ ዲባባ የብርና የነሐስሜዳልያዎች ተገምቶላቸዋል። በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያ ደግሞ በሴቶች ምድብ ለባህሬኗ ዩሪስ ጅፕኪሪዊ የወርቅ ሜዳልያ፤ ለኢትዮጵየዊቷ ማሬ ዲባባ የብር ሜዳልያ እንዲሁል ለኬንያዋ ኤድና ኪፕላጋት የነሐስ ሜዳልያ ሲሰጥ በወንዶች ምድብ የወርቅ ሜዳልያው ለታምራት ቶላ፤ የብር ሜዳልያው ለዳንኤል ዋንጂሩ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያው ለፀጋዬ መኮንን ተገምተዋል፡፡  

Read 3434 times