Saturday, 07 April 2012 08:12

በቀን ለ16 ሰዓት የሚሰሩ አዛውንት!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“ኑሮው ዕለት ተዕለት እየከበደ ነው”

ራስዎትን ለአንባቢያን ያስተዋውቁ….

ሳህሌ ጨማሪ እባላለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ካፈሯቸው 8 ልጆች አንዱ ነኝ፡፡ ትውልዴ በቀድሞ ጨቦና ጉራጌ አውራጃ ቸሀ ወረዳ ዳጉና ቀበሌ ሲሆን አሁን የ51 ዓመት ሰው ነኝ፡፡ ወንድምና እህቶቼ አባትና እናቴን ጨምሮ ሁሉም ቤተሰቦቼ በሞት ተለይተውኛል፡፡

የትምህርት ታሪክዎ ምን ይመስላል?

በዳቁና መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 6 ከተማርኩ በኋላ 7ኛ ክፍልን በእንድብር ተምሬያለሁ፡፡ ከዚያ በላይ አልቀጠልኩም፡፡ በ1970 ዓ.ም ትምህርቴን አቋርጬ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ወደዚህ ይዘውኝ የመጡት የአባቴ ዘመድ ናቸው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር አብሬ ኖሬያለሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ እንድመጣ ያነሳሳኝ፣ ከከተማ ወደ ገጠር በበዓል ወቅት የሚመጡ ሰዎች አለባበሳቸውና ነገረ ሥራቸው ስለሳበኝ ነበር፡፡

ከዚያስ … በምን መስክ ሥራ ጀመሩ?

ለሥራ አዲስ አይደለሁም፡፡ ገጠርም እያለሁ አባቴን በእርሻና ቤተሰቤን በተለያየ ሥራ እረዳ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ጫማ የማሳመር ሥራ መርካቶ ውስጥ ጀመርኩ፡፡ በሊስትሮነት ለሁለት ዓመት ከሰራሁ በኋላ በ1972 ዓ.ም ውትድርና ተቀጠርኩ፡፡ በታጠቅ ጦር ሠፈር የተሰጠንን ስልጠና ስናጠናቅቅ፣ ኤርትራ ተመድቤ ደርግ እስከወደቀ ድረስ በውትድርና አገልግያለሁ፡፡

ማዕረግ አግኝተዋል?

አላገኘሁም፡፡ በመጀመሪያ በመሐንዲስነት ነበር የማገለግለው፡፡ በኋላ በሻለቃ ፀሐፊነት ተመድቤ እያገለገልኩ እያለ ለውጡ መጣ፡፡ ሠራዊቱ ሲበተን ከአሥመራ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡

ቀጣይ ታሪክዎ…

እዚህ ማንም ስላልነበረኝ በቀጥታ ወደ ቤተሰቦቼ ጋ ገጠር ሄድኩ፡፡ ገጠር በገባሁ በ2ኛው ወር አባቴ በሞት ተለየን፡፡ ቤተሰቡን ለማገዝና ለመርዳት በገጠር እንድቆይ የሚያደርግ ነገር ተፈጠረ፡፡ ለ7 ዓመት ያህል ገጠር በቆየሁበት አጋጣሚ ትዳር መሠረትኩ፡፡ ቤተሰቤን ለማስተዳደር የገጠሩ ሕይወት ስለከበደብኝ፣ በ1990 ዓ.ም ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ እንደመጣሁ ጋዜጣ አዙሮ በመሸጥ ሥራ ላይ ተሰማራሁ፡፡ ይኸው በዚህ ሥራ እስካሁን ድረስ አለሁ፡፡

ሥራዎትን ለመቀየር ወይም ለማሳደግ አልሞከሩም?

ከጋዜጣና መጽሔት ንግድ ጐን ለጐን ሎተሪ፣ ካልሲ፣ መጽሐፍ ለመሸጥ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁን ዋነኛው ሥራዬ ግን  የጋዜጣውና መጽሔቱ ንግድ ነው፡፡

ሥራውን በምን ያህል ካፒታል ጀመሩ?

ከባዶ ነው የተነሳሁት፡፡ በዱቤ ጋዜጣ በመውሰድ ነበር ሥራውን የጀመርኩት፡፡ በዚህ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ የግለሰብ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ገጠር ያለችው ባለቤቴንና አራት ልጆቼንም የምረዳው በዚሁ ገቢ ነው፡፡ እኔ በቀን ለ16 ሰዓት ነው የምሰራው፡፡ ከጠዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ጋዜጣ እነግዳለሁ፡፡ ከ12 እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ደግሞ አውቶቢስ ተራ ጐዳና ላይ የተለያዩ መፃሕፍትና መጽሔቶችን በመዘርጋት እሸጣለሁ፡፡ በቅርቡ ግን በድንገተኛ የእሳት አደጋ ሦስት ማዳበሪያ ሙሉ መፃሕፍት፣ መጽሔትና ጋዜጦች ተቃጥሎብኝ ካፒታሌ ወድሟል፡፡

አደጋው መቼና የት ነው የተከሰተው? የተቃጠለብዎት ንብረት በገንዘብ ቢተመን ስንት ይሆናል?

የሥራ አድራሻዬ መርካቶ አምባሰል ሙዚቃ ቤት ፊትለፊት ነው፡፡ በአዲስ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ቤትና በዳንኤል ሆቴል አጥር ዙሪያ በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ የተሰሩ የላሜራ ሱቆች አሉ፡፡ ጋዜጦቼን፣ መፃሕፍቴንና መጽሔቶችን የማሳድረው በዚህ ስፍራ ሰዎቹ ትብብር እያደረጉልኝ ነበር፡፡

መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት በአካባቢው የእሳት አደጋ ተከስቶ ከወደመው ንብረት አንዱ የእኔ ሆኗል፡፡ በዚህ ቃጠሎ ከ12-15 ሺህ ብር የሚሆን ንብረት ነው የተቃጠለብኝ፡፡ ጠዋት እንደተለመደው ማልጄ ለሥራ ስደርስ ነበር ቃጠሎ መድረሱን ያየሁት፡፡ በጣም የሚገርመው ቃጠሎው የተከሰተ ዕለት፣ ማምሻውን 3 ሰዓት ላይ 20 መጽሐፍ በ400 ብር ገዝቼ በማሳድርበት ቦታ አስቀምጬ ነበር ወደ ቤቴ የሄድኩት፡፡ ጥፋ ያለው ገንዘብ ማለት ይህ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በተለያዩ ዘመን የታተሙ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚመጡ ታይምስና ኮስሞ የመሳሰሉ ብዙ ስብስብ ነው በእሳት አመድ የሆነብኝ፡፡

አሁንም በጋዜጣ ንግድ ላይ ነው ያገኘሁዎት፡፡ ከቃጠሎው በኋላ ያገዝዎት አለ?

ችግሩ መከሰቱን የሰሙና የሚያውቁኝ ሰዎች አይዞህ በማለትና አቅማቸው የፈቀደውን በመስጠት እያበረታቱኝ ነው፡፡ ገጠሩ ያሉ ቤተሰቦቼን ሕይወት የመለወጥ ጠንካራ ፍላጐት ስለነበረኝ ነው ከጠዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት በትጋት እሰራ የነበረው፡፡ ግን ባልጠበኩት አደጋ የዓመታት ድካሜን እሳት በላው፡፡

ገጠር የሚታረስ መሬት የሰዎትም?

አለኝ፡፡ ግን አንደኛ መሬቱ አነስተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ በየዓመቱ ባሳርሰውም ቤተሰቤን ዓመቱን ሙሉ ሊያኖር የሚያስችል ነገር አያስገኝልኝም፡፡ ስለዚህ እኔ ከተማ ላይ ሠርቼ ቤተሰቤን መደጐም አለብኝ፡፡ ለሥራ የደረሱ ልጆች የሉኝም፡፡

መንግሥት በአነስተኛና ጥቃቅን በሚያደራጀው ዕድል ለመጠቀም አልሞከርኩም?

በአንድ ወቅት በአውቶቢስ ተራ አካባቢ የምንገኝ የጐዳና ነጋዴዎችን የማደራጀት ነገር ተሞክሮ ነበር፡፡ እኔም ተመዝግቤ ነበር፡፡ ከምን እንዳደረሱት አላውቅም፡፡

የጋዜጣ ንግድ እንዴት ነው?

በጣም እየቀነሰ ነው የመጣው፡፡ በፊት በቀን እስከ 50 ብር ትርፍ የምናገኝበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን እየሸጥን ብቻ ሳይሆን ጋዜጣና መጽሔት እያከራየንም ቢሆን ገቢው ጠብ የሚል አይደለም፡፡ እኔ መጽሐፍና መጽሔቶችን ስለምሸጥ ነው እንጂ ሰኞና ሐሙስ ምንም አንሰራም፡፡ ትንሽ እንቅስቃሴ አለ ከተባለም ከዐርብ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት ነው፡፡

ቀጣይ የሕይወት ዓላማዎት ምንድነው?

የራሴንና የቤተሰቤን ኑሮ ማሻሻል ነው የእኔ ዋነኛ ዓላማ፡፡ ለቤተሰቦቼ የቆርቆሮ ቤት ብሰራላቸው የሚል ትልቅ ምኞት አለኝ፡፡ እንደምታየው ግን ኑሮው ዕለት ተዕለት በጣም እየከበደ ነው የመጣው፡፡ ይህንን የሕዝብ ችግር መንግሥት ቢረዳልን የሚል ምኞት አለኝ፡፡

 

 

Read 1963 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:40